የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) አቻ ቡድኖችን በአገራቸው ማስተናገድ አለመቻላቸውን ተከትሎ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ከትናንት በስቲያ በደቡብ አፍሪካ አካሂደዋል፡፡ ይህ ውድድር በኢትዮጵያ ሜዳ የሚደረግ ቢሆንም በገለልተኛ ሜዳ ማካሄዳቸው የግድ የሆነው ኢትዮጵያ በካፍ ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ጨዋታ እንዳታካሂድ በመታገዷ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህም ቡድኑ በኪራይ ለሚጫወትበት ስታዲየም፣ ለመጓጓዣ፣ ለሆቴል እንዲሁም ሌሎች ወጪዎች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለማውጣት አስገዳጅ ሆኗል፡፡
በርካታ ስታዲየሞችን በየክልሉ እያስገነባች እንደምትገኘው ኢትዮጵያም በዚህ ምክንያት መጎዳቷ አይቀርም፡፡ ከብቸኛው ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች አስተናጋጅ የነበረው የባህር ዳር ስታዲየም የካፍ እገዳ ጋር ተያይዞም በግንባታ ላይ የሚገኙት ስታዲየሞች ጥራትና በመሠረታዊነት ሊሟሉ በሚገባቸው መስፈርቶች ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ምክንያት ይሆናል፡፡ ይህም በእነዚህና በቀጣይ በተቀመጡ የመፍትሄ ሐሳቦች ዙርያ መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጓል፡፡
በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ አስመራ ግዛው ካፍ ባለሙያዎቹን ልኮ በኢትዮጵያ ስታዲየሞች ላይ ቅኝት ማድረግ የጀመረው ከሶስት ዓመታት ወዲህ መሆኑን ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ተናግረዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፣ ኢትዮጵያ በወቅቱ የቻን ውድድር አዘጋጅ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ በተለይ የአዲስ አበባ፣ ባህርዳር፣ ሃዋሳ እና ብሔራዊ ስታዲየሞች ላይ ምልከታ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በወቅቱ ውድድሩን የማስተናገድ አቅም ያለው ስታዲየም እንደሌለ ሲገለጽም የባህርዳር ስታዲየም በማስጠንቀቂያ ውድድሮችን እንዲያስተናግድ ፈቃድ ሊያገኝ ችሏል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም እንዲሻሻሉ አስተያየትና ምክረሐሳብ በተሰጠባቸው ጉዳዮች ላይ ሲሰራም ቆይቷል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም ግልጽ ሊሆን የሚገባው አስተያየት ስታዲየሞቹ መስፈርት አላሟሉም ማለት የጥራት ችግር አለባቸው ማለት አለመሆኑን ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። የስታዲየሞቹ ዲዛይንም ሆነ ግንባታቸው የካፍንም ሆነ የፊፋን መስፈርት ባሟላ መልክ ነው የሚገነቡት፡፡ ነገር ግን ለማጠናቀቅ የበጀት ችግር ማነቆ ሆኖባቸዋል፡፡ ክልሎች አስፈላጊ የግንባታ መስፈርቶችን ሁሉ በማሟላት ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ በአቅም ማነስ ምክንያት ባሉበት ሁኔታ ይቆማሉ፡፡ የካፍን መስፈርት አለመሟላት የሚለው ጉዳይ የሚከሰተውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ለአብነት ያህል በመልበሻ ክፍል ሊሟሉ የሚገባቸው ቁሳቁስ ዝርዝር ውስጥ የቁጥርም ሆነ የዕቃ ጉድለት ቢኖር መስፈርቱ እንዳልተሟላ ይታሰባል፡፡ ከዚያ ውጪ በባህርዳር ስታዲየም ያልተሟሉ በሚል የሚገለጹ ጉዳዮች ግን ከግንባታ ጋር የሚመለሱ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነው በማታ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ እንዲቻል በስታዲየሙ መብራት መኖር አለበት የሚለው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከስታዲየሙ ዲዛይን ጋር ተያይዞ መብራት ሊገጠም የሚችለው ከጣራ ሥራው ጋር ነው፡፡ ይህም ሆነ የወንበር ገጠማን በሚመለከት ለተሰጠው አስተያየት ምላሽ ለመስጠት በዋነኛነት ችግር የሆነው በጀት ነው፡፡
በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ውድድሮችን እንዳታካሂድ መታገዱ ጉዳት ቢሆንም መልካም ዕድልን ሊፈጥር ይችላል የሚል ምልከታም አላቸው ዳይሬክተሩ፡፡ ይኸውም በማስጠንቀቂያ ብቻ ለረጅም ጊዜ መቆየት መዘናጋትን የሚፈጥር ሲሆን፤ የእገዳ ዜናው ግን ሁሉንም ሊያነቃና መፍትሔ ለመስጠት እንዲረባረብ ያደርጋል፡፡ በአገሪቷ የተለያዩ ክልሎች 12 የሚሆኑ ደረጃ አንድ ስታዲየሞች መዋቅራቸው ብቻ ተሰርቶ ቆመዋል፡፡ ይህ ሲሆን ግን የጎደላቸውን ወደ ማሟላት ይገባሉ፤ ስለዚህም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ከማስተናገድ መታገድ የራሱ ጉዳት እንዳለው ሁሉ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥርበት እድል እንዳለ መመልከት አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በሰጠው መግለጫ በራሱ አቅም ሊሟሉ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ጥረት እንደሚያደርግ፤ ከአቅም በላይ በሆነው ላይ ደግሞ የፌዴራል መንግስት እገዛ እንዲያደርግለት መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም ላይ ዳሬክተሩ ስታዲየሞች በየክልሉ ይገንቡ እንጂ የአገር ሀብት እንደመሆናቸው ሁሉም ተረባርቦ ይሰራቸው ዘንድ እንደሚጠበቅ ይገልፃሉ። በሚኒስቴሩ በኩልም የቴክኒክ ቡድን በማቋቋም ሊጠናቀቁ የተቃረቡ አምስት ስታዲየሞችን በመለየት ጥልቅ ጥናት አካሂዷል፡፡ በዚህም የአዲስ አበባ ስታዲየም በፌዴራል ስር የሚገኝ በመሆኑ በተሰጠው ግብረመልስ ላይ የተመሰረተ እድሳት እየተደረገለት ይገኛል፡፡ የሃዋሳ እና የባህርዳር ስታዲየሞች ደግሞ በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እንዲደረግላቸው አስፈላጊውን በጀት ጭምር በማመላከት ለስፖርት ምክር ቤት ሰብሳቢው የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ቀርቧል፡፡ ነገር ግን ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጠም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/2014