በሴካፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ውድድር ቻምፒዮን የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አቀባበል ተደረገለት፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለቡድኑ የገንዘብ ሽልማትም አበርክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ከ20ዓመት በታች ሴቶች ቡድን ከጥቅምት 20 እስከ ጥቅምት 30/2014ዓ.ም በዩጋንዳ ሲካሄድ በቆየው ከ20ዓመት በታች የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት ዋንጫ (ሴካፋ) ውድድር አዘጋጇ ዩጋንዳን በመርታት የዋንጫ ባለቤት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቡድኑ ከትናንት በስቲያ ወደ አገሩ ሲመለስ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን፤ የእራት ግብዣ እና የምስጋና መርሃ ግብርም በፌዴሬሽኑ በኩል ተደርጎለታል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፣ የስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኪነጥበብ፣ ስነጥበብ እና የፈጠራ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሃዲ እንዲሁም የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል፡፡
የሴካፋ ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ በመርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹በሴካፋ የመጨረሻው ቀን ጨዋታ የነበረው ሁኔታ እንዴት ግብ ይቆጠርብናል በሚል ባለመረጋጋት ስሜት በሁለት የተከፈለ ተቃራኒ መስመር ላይ የነበረ ስሜት ነበረ፡፡ያንን ወደ አንድ አምጥተው ያላቸውን አቅም አውጥተው ለዚህ ደረጃ እንድንበቃ ያደረገው ሰው ብቻም ሳይሆን ፈጣሪም ተጨምሮበት ስለሆነ እናመሰግነዋለን፡፡ ይህንን ድል ያስመዘገቡትን የብሄራዊ ቡድን አባላት በሙሉ ከልብ እናመሰግናለን›› ብለዋል፡፡
ፌዴሬሽኑም ለቡድኑ አባላት የገንዘብ ሽልማት ያበረከተ ሲሆን፤ ለቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የመቶ ሺ ብር እንዲሁም ለእያንዳንዱ ተጫዋች ስልሳ ሺ ብር ሽልማት ተበርክቷል፡፡ የቡድን መሪው ሰባ ሺ፣ የቴክኒክ ባለሙያ ሰባ አምስት ሺ፣ ለህክምና ባለሙያዎች 50 ሺ እንዲሁም ለሌሎች የቡድኑ አባላት በጥቅሉ አንድ ሚሊየን ስምንት መቶ ስልሳ ሺ ብር ወጪ ተደርጓል፡፡
በሴቶች ብሔራዊ ቡድን በየትኛውም ደረጃ የመጀመሪያ ዋንጫ ያስመዘገቡት የሉሲዎቹ ተተኪዎች በዘንድሮው የሴካፋ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ቢሳተፉም በአምስት ጨዋታዎች አንድም ሳይሸነፉ ለቻምፒዮንነት ክብር በቅተዋል፡፡ በውድድሩም በአጠቃላይ አስራ ስምንት ግቦችን አስቆጥረው ሦስት ግብ ብቻ አስተናግደዋል፡፡ ይህም ብሔራዊ ቡድኑን በቀጣይ ወር በደቡብ አፍሪካ ለሚካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ተሳታፊ አድርጎታል፡፡
የሉሲዎቹ ተተኪዎች በአምስት ጨዋታ ከፍተኛውን ነጥብ የሰበሰበው ቡድን አሸናፊ በሚሆንበት ውድድር ዋንጫ ማንሳት የቻሉት ጅቡቲን ሰባት ለ ዜሮ፣ ኤርትራን አምስት ለ ዜሮ፣ ታንዛኒያን ሁለት ለአንድ፣ ቡሩንዲን አንድ ለዜሮና ዩጋንዳን ሦስት ለሁለት በሆነ ውጤት አሸንፈው መሆኑ ይታወሳል፡፡ በአምስቱ ጨዋታዎች ለኢትዮጵያ ስምንት የተለያዩ ተጫዋቾች ግቦችን ያስቆጠሩ ሲሆን ረድኤት አስረሳኸኝ ስድስት ግቦችን በማስቆጠር ቀዳሚ ናት፡፡
ቱሪስት ለማ በውድድሩ አራት ግቦችን ያስቆጠረች ተጫዋች ስትሆን መሳይ ተመስገንና አሪያት ኦዶንግ ሁለት ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችለዋል፡፡ እፀገነት ግርማ፣ ቤተልሔም በቀለ፣ብዙአየሁ ታደሰና ንቦኝ የን አንዳንድ ግቦችን በማስቆጠር ኢትዮጵያ የሴካፋውን ዋንጫ እንድታነሳ ትልቅ ሚና ነበራቸው፡፡
በዘንድሮው የሴካፋ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ውድድር አዘጋጇ ዩጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ኤርትራ፣ጅቡቲና ቡሩንዲ የተሳተፉ ስድስት አገራት ናቸው፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3 /2014