ኢትዮጵያ ስትፈራርስ ለማየት የተመኙ የውስጥ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ካወጁ ሰነባብተዋል።የሶርያና ሊቢያን ታሪክ በኢትዮጵያም እንደግማለን ብለው ተማምለዋል።ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የሚፈልጉ የውጭ ኃይሎችም በግልጽ ድጋፍም ግፊትም እያደረጉላቸው ናቸው።
ዓላማና ክፋታችሁ እንጂ ‹‹ኢትዮጵያማ አትፈርስም›› ያሉ አገር ወዳዶች ደግሞ በሌላ ጎራ ፍልሚያ ላይ ይገኛሉ።የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ጸጥታ ኃይሎችና ሚሊሻዎች የአገር ህልውናን በማስከበር ኢትዮጵያን ለማዳን በሚደረገው እንቅስቃሴ ዘመቻ ላይ ናቸው።
ሕወሓትንና ሸኔን ለመደምሰስ ኢትዮጵያውያን በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ እየደገፉ ይገኛሉ።ወጣቶች አሸባሪዎቹን ለመደምሰስ በከፍተኛ ወኔና በአሸናፊነት መንፈስ ተሰልፈዋል።
መከላከያን መደገፍ ማለት፤ ሰላምን ማስፈንና የጠላቶችን አንገት ማስደፋት እንደመሆኑ መከላከያ ሠራዊትን መደገፍ ቀዳሚ አጀንዳዬ ነው ያሉ በርካቶች ናቸው።
‹‹ለመዝመት አቅምህ አይፈቅድም ከተባልኩ በምችለው አቅም መከላከያን መደገፍ አለብኝ›› ካሉ ኢትዮጵያውያን መካከል ሐጂ መሐመድጀማል አብዱልሰቡር ይጠቀሳሉ።
ለመከላከያ ሰራዊት ‹‹ጭኮ›› በመባል የሚታወቀውን ባህላዊ ምግብ በማዘጋጀት ከሰንጋ ጋር ማቅረባቸው ለሠራዊቱ ትልቅ እውቅና እና ክብር መስጠታቸውን ያመለክታል።ተግባራቸው አጋርነታቸውን ይመሰክራል፡፡
የድሬ ሼክ ሁሴን ተወላጅ ናቸው።‹‹ድሬ ሼክ ሁሴን ሁሉንም እኩል የማየትና የመያዝ ልምድ አላቸው እኔም የወረስኩት ያንን ነው›› ሲሉም ይመሰክራሉ።
ከሶማሊያ ጋር በተካሄደው ጦርነት መዝመታቸውን፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትም በደጀንነት ተሰልፈው አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ።
ባይዘምቱም በስንቅ ማቀበል መሳተፋቸውን፣ አሸባሪው ሕወሓትን ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት ከጎን መሰለፋቸውን ይናገራሉ።
አሸባሪው ሕወሓት ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልሙን ለማሳካት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝን ከኋላ በመምታት አሳፋሪና አስነዋሪ ድርጊት መፈጸሙን ያስታውሳሉ።
መከላከያ ሠራዊት ወገኔ ብሎ በሚያስበው፣ ባመነው አካል ሲጠቃ በጣም ነው ያዘንኩት የሚሉት ሐጂ መሐመድጀማል፤ ሀብቴን ንብረቴን ያለኝን ሁሉ እለግሳለሁ ሠራዊቱ በድል እስከሚመለስ እኔ ከጎኑ ነኝ ብዬ ወሰንኩ ባይ ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በቅን አመለካከቱ የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ ነገሮች እንዲረጋጉ፣ አርሶ አደሩ ወደ እርሻው እንዲገባ አድርጎ እንደነበር ይጠቁማሉ።አሸባሪው ሕወሓት ግን ይህንን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአሰቃቂ መንገድ ተመልሶ ማኅበረሰብን መጨፍጨፍ መጀመሩን ነው የሚናገሩት።
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ አሸባሪ ቡድኑ በንጹሃን ዜጎች ላይ አረመኔያዊ በሆነ መንገድ የሚፈጽማቸው የወንጀል ድርጊቶች በዓለም ታሪክ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም።የሰይጣንን ስልጣን የያዘ፣ የንጹሃን ሰው ደም የሚያምረው፣ ሕጻንና ሽማግሌን የማይለይ ነው።ርህራሄ ያልፈጠረበት ነው።
ይህንን አስከፊ ውንብድና በማየቴ የመከላከያ ሠራዊት ለድል አስስኪበቃ ድጋፌን እቀጥላለሁ በማለት የሚጠቁሙት ሐጂ መሐመድጀማል፤ አሁን ለሰራዊቱ በድጋፍ መልክ አሰርቼ ያቀረብኩት የስንቅ ድጋፍ ጭኮ የሚባል ሲሆን፤ በየብሔሩ የሚታወቅ ምግብ ነው በማለት ነው የሚገልጹት።
በጥንቃቄ የሚሰራ፣ ከቅቤ በስተቀር ምንም ነገር የማይገባበት፣ በማማሰያ ከማዋሃድና በማንኪያ ወደ ማሸጊያ ላስቲክ ጨምሮ ከማሸግ ውጪ የእጅ ንክኪ የማይፈልግ ለየት ባለ መልኩ እንደሚዘጋጅም ይጠቁማሉ።
ይህንን ምግብ ያዘጋጀሁት ሠራዊቱ በቀላሉ በኪሱ ይዞ ምሽግ ቢገባ ላያያዝ የሚያመቸው መሆኑን ግምት በመውሰድ ነው። ምሽግ ውስጥ ሆኖ ወር ቢቀመጥ በምግብነት ያገለግለዋል። ከፍተኛ የቅቤ መጠን ስላለው ለአካል ጠቃሚ ነው። ለሰውነትም ገንቢ ነው።የሠራዊቱን ልቦናውን ይቀሰቅሳል፣ ወኔም ይሰጠዋል፡፡
ለታላላቅ ሰዎች፣ ለክቡር እንግዶች፣ ለሚኒስትሮች፣ ለታላላቅ እና ውድ እንግዶች የሚሰራ ምግብ ነው።ለህልውናችን፣ ለዋልታችንና የአገር ዋስትናችን ለሆነው የጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን በፍቃዴ አዘጋጅቼ አቅርቤያለሁ። ይሄ ለሌሎች ምሳሌና ተነሳሽነት እንደሚፈጥር አስባለሁ።
ደረቅ በሶ፣ ዳቦ ቆሎና ሌሎች የተለመዱ ስንቆችን መላክ ጥሩ ነው። ከእዛ ባሻገር ግን ውድ ከሆነው የአገራችን ተወዳጅ ምግብ መካከል እንደ ጭኮና ሌሎችንም ለመላክ እንዲነሳሱ ምሳሌ ለመሆን በማሰብ ያደረግኩት ነው ይላሉ፡፡
ስንቁን ለማዘጋጀት የፈጀው አንድ ሳምንት ያህል ነው። ለማዘጋጀት በርካታ የሰው ኃይል ይፈልጋል።በቀጣይነትም የመከላከያ ሠራዊት በድል እስኪመለስ፣ የብስራት ዜና እስኪያደርሰን፣ ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ ተውለብልቦ፣ ሠራዊቱ በድል ተመልሶ እስኪገባ ድረስ አቅሜ በፈቀደ ሁሉ ድጋፍ ማድረጌን እቀጥላለሁ።
የሙያና የአገልግሎት አሰጣጥ ዘርፍ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በሪል እስቴት መሰማራታቸውን በመጠቆምም፤ ለአገሬና ለወገኔ ዳር ድንበር መከበር የሀብቴን ጠብታ ሳላስቀር ድጋፍ በማድረግ ላይ የምገኝ ኢትዮጵያዊ ነኝ ሲሉም ይናገራሉ፡፡
“እስካሁን አስር ሰንጋ፣ አንድ ሚሊዮን ብር አስገብቻለሁ፤ በምኖርበት አካባቢም ለመከላከያ ድጋፍ ሲደረግ 60 ሺህ ብር አዋጥቻለሁ፣ በመከላከያ ሠራዊት የባንክ ሂሳብ በየወሩ 10 ሺህ ብር አስገባለሁ” ብለዋል።
ይህንን የማደርገው ከእኔ የበለጠ አቅም ላላቸው አርኣያ ለመሆን ነው፣ አገር ህልውናችን ነው፣ አለኝታችንም ነው። ኢትዮጵያ አገራችን በዚህ ትውልድ መከበር አለባት።
በጦር ሜዳ የተሰለፉ ወገኖች ደማቸውን እያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን እየከሰከሱ የሕይወት ዋጋ እየከፈሉ ይገኛሉ። ወደ ጦር ሜዳ ያልሄድነው ደግሞ አቅማችን በፈቀደ ሁሉ ድጋፍ በማድረግ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መቆም ይኖርብናል።የጀመርኩትን ድጋፍ እቀጥላለሁ።
በመከላከያ ሠራዊት የቀድሞ የሀብት ማሰባሰብ የክልሎች አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ተመስጌን ቡርቃ፤ የሐጂ መሐመድጀማል ድጋፍ የተለየ የሚያደርጋቸው መገለጫዎች አሏቸው ይላሉ። በድሬ ሼክ ሑሴን ረጅም ታሪክ እንዳላቸው ይጠቁማሉ።
በኢትዮጵያ የአገር ህልውና ጦርነት ውስጥ እንደሶማሌ ጦርነት ተሳታፊ ሰው በመሆን ታሪክ በማስመዝገብ የአደገ የአገር ፍቅር እንዳላቸው ያመለክታሉ።ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ በየወሩ የሚያስገቡት ሂሳብ መኖሩንም ይጠቁማሉ።
ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይም ድጋፍ አድርገዋል። በቅርቡ 12 ሰንጋዎችን በድጋፍ አስገብተዋል።ከ290 ሺህ ብር በላይ ቅቤ የፈጀ ጭኮና አንድ ሰንጋ ለሠራዊቱ ድጋፍ ማስገባታቸውን ነው የሚናገሩት።
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ በአገር ውስጥ ሀብት ጠፍቶ አይደለም። ሠራዊቱን ለመደገፍ የሚያስፈልገው አመለካከት፣ ወኔና አርበኝነት ነው።እንጂ ኢትዮጵያ ሀብታም አገር ናት። የጀግኖችም አገር ናት። በመሆኑም እንደ ሐጂ መሐመድጀማል አይነት በርካታ ድጋፍ የሚያደርጉ ሰዎች መፈጠር አለባቸው።
ሐጅ መሐመድጀማል በግላቸው ተነሳስተው፣ ልጆቻቸውን ማነሳሳት ችለዋል። ልጆቻቸው የአርበኝነት ውርስን ከአባታቸው በመቀበል ባደረጉት ተግባር ለአገር ፍቅርና ለመከላከያ ሠራዊትም ያላቸውን ክብር ያመለክታል። ሌሎችም የእርሳቸውን አይነት ምሳሌ ማንጸባረቅ ቢችሉ መልካም ነው፡፡
የመከላከያ ሠራዊት አባል ኮሎኔል ተስፋዬ በቀለ፤ ሐጂ መሐመድጀማል ምሳሌ ናቸው፣ ለሠራዊቱ ድጋፍ እያደረጉ ናቸው። ጭኮ ባህላዊ ምግብ ከመሆኑም ባሻገር ታዋቂና ታላላቅ ለሚባሉ ሰዎች የሚቀርብ ነው።ለበርካታ ጊዜ ቆይቶ ለምግብነት ማገልገል ይችላል።
እርሳቸው ጭኮ በማዘጋጀት ከሰንጋ ጋር አድርገው ማምጣታቸው ለሠራዊቱ ትልቅ እውቅና እና ክብር መስጠታቸውን ያመለክታል። ተግባራቸው የልማትና የሠራዊቱ አጋር የሆኑ ሰው መሆናቸውን ይመሰክራል። የእርሳቸውን ፈለግ በመከተል በቀጣይ ሌሎችም ተግባራዊ ያደርጋሉ ብዬ እገምታለሁ ነው ኮሎኔል ተስፋዬ የሚሉት።
እንደ ኮሎኔል ተስፋዬ ማብራሪያ፤ የጭኮ ስንቅ ሠራዊቱ በቀላሉ ለመያዝ ያስችለዋል። አስቸጋሪ ቦታ ሲገባ ያገለግለዋል። ምግቡ እስከ ስድስት ዓመታት መቆየት ይችላል። ከንጹህ ቅቤና ከገብስ እህል ያለንክኪ የተሰራ በመሆኑ ይበላሻል የሚል ስጋት ውስጥ የሚያስገባ አይደለም። ሰራዊቱ አስቸጋሪ ግዳጅ ላይ በኪሱ ይዞ ለረጅም ጊዜ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡
እንዲህ አይነት ድጋፍ ለሠራዊቱ ከፍተኛ ተነሳሽነትን ይፈጥራል። ሐጂ መሐመድጀማል አሁንም ከሰራዊቱ ጎን ቆሜ እዋጋለሁ ሲሉ መስማት እንደአባል የሚፈጥረው ተነሳሽነት ከፍተኛ ነው።
ብርጋዴል ጄነራል አስረስ አያሌው በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ ሕዝቡ ካለው የነፈገው ነገር የለም። በገንዘብ፣ በሰው ኃይል፣ በስንቅ፣ በደም ልገሳ እና በሞራል አለኝታነቱን እያሳየ ነው። ኢትዮጵያዊነቱንና አገር ወዳድነቱን በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡
በግለሰብ ደረጃ ሐጂ መሐመድጀማል አብዱልሰቡር በግላቸው የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ ነው። መነገድ፣ መውጣትም ሆነ መግባት የሚቻለው አገር ሲኖር ነው በማለት ከሁሉም ነገር አስቀድመው አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
እስካሁን ሰንጋና ስንቅ መለገሳቸው አገር ወዳድነታቸውን፣ ኢትዮጵያዊነታቸውን የሚያሳይና የበለጠ የሚያስመሰግናቸው ነው።ከእዚህ በፊትም በሶማሊያ ወረራ ወዶ ዘማች ሆነው ወራሪውን የዚያድ ባሬን ጦር በመመከትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው።
አሸባሪ፣ ዘራፊና ወራሪ የትህነግ ቡድን በወረራ ሲነሳ ለ47 ዓመታት ኢትዮጵያን በማዳከም ከፍተኛ ሥራ ሰርቷል፡፡በቀላሉ ኢትዮጵያን እበትናታለሁ፣አማራና ኦሮሞ ተቋስሏል፣አፋርና ሱማሌ ክልሎች ተቀያይመዋል፣ ኦሮሞና ሱማሌም ተቋስለዋል። ስለዚህ በቀላሉ ኢትዮጵያን በታትኜ በኢትዮጵያ መቃብር ላይም ታላቋን ትግራይን እመሰርታለሁ ብሎ ተነስቷል፡፡
ከአማራ፣ ከአፋር ከቻለም ከሌሎች ጎረቤት አገሮች የሚፈልገውን መሬት በመውሰድ ታላቋን ትግራይን ለመመስረት ኢትዮጵያን ድምጥማጧን ለማጥፋት እየሰራ ይገኛል። ሆኖም ግን ሁሉም ሕዝብ፤ ብሔር፣ ብሔረሰብ እንደ አንድ ሆኖ ኢትዮጵያዊነቱንና አገር ወዳድነቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ ያጠናከረበት ጊዜ አሁን ነው።
በእዚህ ሕብረት ምክንያትም የአሸባሪው ሃሳብ ሙሉ ለሙሉ ከሽፏል። አማራው ከኦሮሞው፣ ኦሮሞው ከሱማሌው፣ ሶማሌው ከአፋሩ ጋር በመሰለፍ አስደናቂ ጀብድ እየፈጸመ ይገኛል። በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ ክልሎች የሚደረግ ጀብድና አገር ወዳድነት በታሪክ ተመዝግቧል።
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም፣ ሉዓላዊነትና አንድነት ቅንጣት ታህል ተቆርቋሪነት የሌለውን አፍራሽ ቡድን ለመመከት ሕዝቡ ተነስቷል።
የሕልውናና ኢትዮጵያን የማዳን ዘመቻው ሙሉ ለሙሉ አልተጠናቀቀም፣ አሁንም አሸባሪ የትህነግ ቡድን አልተደመሰሰም፣ ግብአተ መሬቱም አልተፈጸመም። በሚተነኩሰው ትንኮሳ የሕዝብ መፈናቀል፣ የኢንቨስትመንት ውድመትና ልማት ሙሉ ለሙሉ አውድሟል። የሚፈልገውንም ከየአካባቢው ጭኗል።
ይህንን በመገንዘብ መላው ሕዝብ ሰራዊቱን የማጠናከር ተግባርና የተፈናቀለውን ሕዝብ ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ብርቱ ድጋፍ ይጠይቃል። መላው ሕዝብ ለመከላከያ ሠራዊት እያደረገ ያለውን ሞራልና ድጋፍ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ነው ብርጋዴል ጀነራል አስረስ የሚሉት።
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ኅዳር 3 /2014