ለ2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ የአፍሪካ አገራት ማጣሪያ ጨዋታ በምድብ ሰባት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካና ዚምባቡዌ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) በአራት የማጣሪያ ጨዋታዎች ሶስቱን ተሸንፎ አንዱን ብቻ በማሸነፍ በጊዜ ከዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ፉክክሩ መውጣቱ ይታወቃል። ቀሪ ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎችንም ለመርሃግብር ማሟያ የሚጫወት ይሆናል።
ዋልያዎቹ ከወር በፊት በባህርዳር ስቴድየም በደቡብ አፍሪካ 3ለ1 ከተሸነፉበት ጨዋታ በኋላ የኢትዮጵያ ስቴድየሞች ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያስተናግዱ በካፍ መታገዳቸውን ተከትሎ ዋልያዎቹ ዛሬ አምስተኛ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ከጋና አቻቸው ጋር በገለልተኛ ሜዳ ደቡብ አፍሪካ ላይ ለማድረግ ተገደዋል።
የጨዋታው ውጤት ለዋልያዎቹ ከክብር በዘለለ ትርጉም የሌለው ቢሆንም ተጋጣሚያቸው ጋና ጨዋታው ከሚካሄድባት ደቡብ አፍሪካ ጋር በተመሳሳይ ምድብ በአንድ ነጥብ ልዩነት እየተፎካከረች የምትገኝ አገር በመሆኗ ጨዋታው በባፋና ባፋናዎቹ ሜዳ መካሄዱ ተገቢ እንዳልሆነ ለካፍ ቅሬታ መቅረቡ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ጥቁር ከዋክብቱ ቅሬታቸው ተቀባይነት ሳያገኝ በዘጠኝ ነጥብ ከደቡብ አፍሪካ በአንድ ነጥብ አንሰው የዓለም ዋንጫ ተስፋቸውን የሚወስን ጨዋታ ዛሬ ከዋልያዎቹ ጋር ያደርጋሉ።
ዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ተስፋቸው በጊዜ ቢከስምም በመጪው ጥር በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ መሆናቸውን ቀደም ብሎ ማረጋገጣቸውን ተከትሎ ዛሬ ከጥቁር ከዋክብቱ ጋር እንዲሁም በቀጣይ ከዚምባቡዌ ጋር የሚያደርጉት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ከመርሃግብር ማሟያ በዘለለ ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድን እንደ አቋም መፈተሻ ጨዋታ ይጠቅማል ተብሎ ይጠበቃል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ወደ ጆሃንስበርግ ቡድናቸውን ይዘው ከማቅናታቸው አስቀድሞ ከደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ቡድን ጋር የነበሩትን የደርሶ መልስ ጨዋታዎችና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ‹‹የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድባችን የነበሩት ዚምባቡዌ፣ ጋናና ደቡብ አፍሪካ ከኛ የተሻሉ ቢሆንም ከነሱ የተሻለ ሆኖ ለመገኘት ጥረናል፣ ያ ባለመሳካቱ ፊታችንን ወደ አፍሪካ ዋንጫ መዘጋጂያ አድርገን እየሰራን ነው፣ በነጥብ ደረጃ የምንፈልገውን ባለማግኘታችን ውስጣችን ቅር ተሰኝቷል፣ በቀሪ ሁለት ጨዋታ ላይ የተሻለ ለመሆን እንሰራለን›› ሲሉ ተናግረዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ‹‹ንግድ ባንክ ሜዳ ላይ በቀን አንዴ ልምምዳችንን ስንሰራ ቆይተናል፣ 5 ተጫዋቾች በተለያየ ምክንያት ከቡድኑ ተለይተዋል፣ ካሉን ቀሪ ተጫዋቾች ጋር የምንችለውን እናደርጋለን ቀጣይ ሁለቱ ጨዋታዎች ግን ለኛ ለውጥ ባይኖራቸውም ማንንም ሳንጎዳ ማንንም ሳንጠቅም በጨዋነት ግጥሚያዎችን ለማድረግ እንጥራለን›› ሲሉም ገልጸዋል።
‹‹ከኒጀሩ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ጀምሮ ለውጥ ያየንበት ሂደት አለ፣ ባለፉት 7 ጨዋታዎች ያለውን ሂደት ስንገመገም በአማካይ 556 የኳስ ቅብብሎች አድርገን 520 የተሳካ ኳስ መኖሩ የቡድናችን አጨዋወቱ ምን እንደሚመስል ያሳየን ነው›› በማለት አሰልጣኙ ቡድናቸው ላይ ስላለው ለውጥ አስረድተዋል።
በሐዋሳ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘውን የፕሪሚየርሊግ ጨዋታን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ አሰልጣኙ ምላሽ ሲሰጡም ‹‹የሐዋሳው ሜዳ ኳስ መቀባበል የማይቻልበት ሜዳ ነው፣ በዚህ ሜዳ ማጫወትም ራሱ በደል ነው፣ ተጫዋቾቹ ሲወድቁ ጠርሙስ ላይ እንደወደቀ እግራቸው ተቆራርጦ የሚነሱበት መሆኑ ያሳዝናል፣ በቀጣይ ሌሎች ሜዳዎች ከሐዋሳ ትምህርት ሊያገኙ ይገባል›› በማለት የመጫወቻ ሜዳው ምቹ አለመሆኑን ተናግረዋል።
አሰልጣኙ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት አስተያየትም ‹‹አሁን ኢትዮጵያ ካላችበት አገራዊ ችግር አንጻር ጉዳዩ በቀጥታ ይመለከተናል፣ ሁላችንም ከዚህ ቤተሰብ ነው የወጣነው፣ ይሄ አይመለከተኝም የሚል የለም፣ ነገር ግን ፈተናውን ለማለፍና አገራችንን በወከልንበት መድረክ የተሻለ ተፋላሚ ለመሆን እንጥራለን›› በማለት አስረድተዋል።
ዋልያዎቹ ከጋና አቻቸው ጋር ዛሬ የሚያደርጉትን ጨዋታ እንደቋጩ ወደ ኢትዮጵያ ሳይመለሱ በዚያው ወደ ሌላኛዋ ደቡብ አፍሪካዊት አገር ዚምባቡዌ በማቅናት የመጨረሻውን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ያደርጋሉ። በዚህ ምድብ ከአፍሪካ አስሩ ምርጥ ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ ሆኖ ወደ መጨረሻው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ለማለፍ በሚደረገው ፉክክር ጋና በዛሬው የዋልያዎቹ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ካልቻለችና ደቡብ አፍሪካ ዚምቡዋቤን በሜዳዋ ካሸነፈች ጥቁር ከዋክብቱ ወደ ኳታሩ የዓለም ዋንጫ የማቅናታቸው ተስፋ ህልም ሆኖ ይቀራል።
በአንድ ነጥብ ልዩነት እየተፎካከሩ የሚገኙት ሁለቱ አገራት ዛሬ ተጋጣሚዎቻቸውን ማሸነፍ ከቻሉ ግን የመጨረሻው የእርስበርስ ግንኙነታቸው ጨዋታ እጅግ ወሳኝና በጉጉት የሚጠበቅ ይሆናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሕዳር 2/2014