ድምጻዊ፣ የዜማ እና ግጥም ደራሲ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ባለፈው ሳምንት አንድ ነጠላ ዜማ ለሕዝብ አድርሷል። ይህ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየ የአርቲስቱ ሥራ ገና እንደወጣ ነበር የማህበራዊ ገጾችን ያጥለቀለቀው።
ዘፈኑ ለምን በጉጉት ተጠበቀ?
የቴዲ አፍሮ ነጠላ ዜማ ሊወጣ ነው መባሉ ለምን ያን ያህል እንዳጥለቀለቀ ጥናት የሚያስፈልገው አይደለም። ሁለት ነገሮች ተገማች ናቸው። አንደኛ፤ አርቲስቱ ቴዲ አፍሮ ነው፤ ሁሌም በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ያለ። ቴዲ ከእረኛ እስከ ፖለቲከኛ፣ ከህዳጣን እስከ ባለሥልጣን፣ ከጎዳና ተዳዳሪ እስከ ከፍተኛ ባለሀብት የሚታወቅ ዘፋኝ ነው። ወደ ማምለክ የሚጠጉ አድናቂዎች እንዳሉት ሁሉ፣ ‹‹የአጼው ሥርዓት አወዳሽ›› የሚሉ ብዙ ወቃሾችም አሉት። ቴዲ ግን በዚያም አለ በዚህ፣ በአድናቂዎቹም በወቃሾቹም ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ታዋቂ ነው።
ዘፈኑ በጉጉት የተጠበቀበት ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ፤ ይለቀቃል የተባለበት ዕለት ነው። ማክሰኞ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ከሰዓት በራሱ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ‹‹ነገ ይወጣል›› ሲል ድንገተኛ ዜና ተናገረ። ዕለቱ ደግሞ የጥቅምት 24 ዋዜማ ነው፤ ዘፈኑ ይወጣል የተባለው ጥቅምት 24 ነው። ጥቅምት 24 ደግሞ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ ባደረሰው የክህደት ጭፍጨፋ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ቀን ነው።
እንግዲህ አርቲስቱ ለምን ይሄን ቀን እንደመረጠ የገለጸው ነገር ባይኖርም ያለምክንያት ነው የመረጠው ብሎ ማሰብ አይቻልም፤ ቀኑን አስቦበት የመረጠው ለመሆኑ ደግሞ የዘፈኑ ስንኞች ጠቋሚዎች ናቸው። ይዘታቸውን ወደ ግጥሙ ስንገባ እናያቸዋለን።
የአርቲስቱ ታዋቂ መሆን፣ ከዚህ በፊት በነበሩት ሥራዎች ፖለቲካን መነካካቱ (በተለይም ኢህአዴግን) ፣ ቀኑ ጥቅምት 24 መሆኑ ተደማምረው፤ ዘፈኑ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ አድማጭ ተመልካች አገኘ።
የተለቀቀበት ሰዓት ወደ ሌሊት የተጠጋ ምሽት ነበር፤ እንግዲህ እስከሚነጋ ድረስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰው አይቶታል ማለት ነው። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ በዚያ ሰዓት የኢንተርኔት ተደራሽነት ያለው ሰው ጥቂት ነው፤ ያም ሆኖ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ እና ከአርቲስቱ ቀደምት ሥራዎች አንፃር ይህን ያህል በጉጉት ተጠብቆ ነበር ማለት ነው። ከዚያ በኋላ የቱንም ያህል ተመልካች ቢኖረው አይደንቅም።
በነገራችን ላይ የቴዲ አፍሮ ዘፈኖች ተመልካች የመበታተን ችግር ያጋጥማቸዋል። ምክንያቱም ዘፈኖቹ በብዙ የ‹‹ዩ ትዩብ›› ቻናሎች መጫናቸው ይመስለኛል። ሰዎች የሚያዩት ከአንድ ቦታ ብቻ ስላልሆነ የተመልካቹ ቁጥር ይበታተናል። አንድ ላይ ቢደማመር ብዙ ሚሊዮን ይሆናል ማለት ነው።
የዘፈኑ ይዘት ምንድን ይሆን ?
በመጀመሪያ አንድ ነገር ልብ በሉልኝ። ስለዘፈኑ ከዜማ አንፃር ምንም አልልም፤ ምክንያቱም ዜማ ራሱን የቻለ ረቂቅ ሳይንስ ነው። ዜማ አዋቂን ይፈልጋል። ከፍታው ዝቅታው እያለ ማብራራት የሚችለው የዜማ ባለሙያ ነው። በዜማው ውስጥ ለብዙዎቻችን ግልጽ የሆነው ነገር የብሶት እንጉርጉሮ ያለበት መሆኑ ነው፤ ከጭፈራ ይልቅ ለትካዜ የሚጋብዝ መሆኑ።
በዘፈን ውስጥ የጋራ ስሜት ማግኘት ከባድ መሆኑም ይሰመርበት። በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነውን ጥላሁን ገሠሠን ‹‹ኤጭ! ሲያስጠላኝ›› የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፤ እዚህ ግባ የማይባል ነው በሚባል ሙዚቃ ክንፍ የሚል ሰው ሊኖር ይችላል። ይህንንም ታሳቢ አድርገን እንቀጥል።
የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹አርማሽ (ቀና በል)›› አዲሱ ነጠላ ዜማ ርዕሱ ሁለት ነው። ‹‹አርማሽ›› የሚለው እና በቅንፍ ውስጥ የተቀመጠው ‹‹ቀና በል›› የሚለው።
የዘፈኑ ጥቅል መልዕክት የጠፋችበትን ኢትዮጵያ መፈለግ ነው። ትመጣለች ብሎ የሚጠብቃት ኢትዮጵያ አለች፤ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚመኛት ኢትዮጵያ ልትመጣ ነው ብሎ ተስፋ አድርጎ ያደረገ ይመስላል። አሁን በውስጡ ያለው ስሜት ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ያቺ የተስፋይቱ ምድር ኢትዮጵያ መምጣቷ ስለማይቀር ቶሎ ትምጣልኝ የሚል ናፍቆት ነው።
የግጥም አተረጓጎም ከሰው ሰው ስለሚለያይ ግጥሞችን እያየን እንሄዳለን። በነገራችን ላይ ዜማ የራሱ ባለሙያ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ግጥምም የራሱ ባለሙያ ያስፈልገዋል፤ ቢሆንም ግን ይለያያል። ግጥም ሀሳብ ነው። ከቅርጽ እና ከቋንቋ አንፃር ባለሙያዎች የሚሉት ቢኖራቸውም፣ ይዘቱን ግን ማንም መረዳትና የተረዳውን ያህል መግለጽ ይችላል። በአጭሩ በሰዎች ሀሳብ (ስሜት) ላይ አስተያየት መስጠት ማለት ነው። ወደ ዘፈኑ ግጥሞች!
አርማሽ ይውለብለብ ከደጄ
ልቤ ናፍቆሻል ወዳጄ
እኔስ እስካይሽ ጨነቀኝ
አገሬ መምጫሽ ናፈቀኝ
ድምጻዊው ትመጣለች ብሎ የሚጠብቃት ኢትዮጵያ አለች ማለት ነው። የሚጠብቃት ኢትዮጵያ እስከምትመጣ ድረስ ያለው ሁኔታ ግን አስጨንቆታል።
….
ቀን እየሄደ ቀን መጣ
ልቤ ከሀሳብ ሳይወጣ
መጥታ ታብሰው እንባዬን
አገሬን ጥሯት አርማዬ
…
ከዛሬ ነገ ይስተካከላል እያለ ተስፋ ያደረገበት ነገር ቶሎ አልመጣለትም ማለት ነው። ምናልባትም ባለፉት ሦስት የለውጥ ዓመታት የተስፋይቱ ምድር ኢትዮጵያን አያለሁ ብሎ ተስፋ አርጎ ይሆናል፤ ወይም በአገሩ ላይ ያሳደረው ተስፋ ምን ያህል ትልቅ እንደሆነም ያመለክታል፤ ምክንያቱ ደግሞ መጥታ እንባውን እንድታብስ መፈለጉ ነው። በሀገሪቱ የተፈጠሩት አስጨናቂና አሰቃቂ ነገሮች ግን ከዛሬ ነገ ይስተካከላሉ ብሎ ቢጠብቅም የራቁበት ይመስላል። ‹‹ኢትዮጵያ እንድትመጪ ስንት ቀን ይበቃል?›› በማለትም ጠይቋል።
መቼም ከዚህ ምድር ላይ ሄዶ ነው ሁሉም ቀሪ
አገር ናት ቋሚ ሰንደቅ ለዘላለም ኗሪ
ከያኒው ለምንም ይጠቀመው ለምን፤ ይህ ግጥም ግን ትልቅ ወቅታዊ መልዕክት አለው። ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ መሪዎች ይመጣሉ ይሄዳሉ፤ ሥርዓት ይመጣል ይሄዳል፤ ይለወጣል። ኢትዮጵያ ግን ያው ኢትዮጵያ ናት። ለምሳሌ አሁን ያለው አገራዊ ጥሪ ያለውን መንግስት የማዳን ሳይሆን ኢትዮጵያን የማዳን ነው።
እኔማ ላይሽ በቶሎ ምኞት ነበረኝ
ግን ባባሁ ናፈኩሽ እና ዕምባ ቀደመኝ
እኔማ አለሁ እስካሁን ተስፋ ሰንቄ
በወንዜ ባገሬ እያለሁ አገር ናፍቄ
ወጥተሽ በምሥራቅ አንቺ ያለም ጀምበር
አንድ አርጊንና ጠላትሽ ይፈር
‹‹እኔማ አለሁ እስካሁን ተስፋ ሰንቄ›› በማለት በአገሩ ተስፋ ያልቆረጠ መሆኑን ይነግረናል። የተስፋይቱ ምድር ኢትዮጵያን የማየት ተስፋ ተጀምሮ እንደገና ያሰጋው ይመስላል። በአገሩ ውስጥ ሆኖ አገሩን ይናፍቃል። ይህን ስንመለከትም በአገሩ የሚፈልገውን መሆን ስላልቻለ ትውልድም ለማመልከት የገጠመው ነው ።
ኢትዮጵያ የዓለም የሥልጣኔ ጀማሪ መሆኗን በመጠቆም፤ አንድ እንሁንና የተነሱብን ጠላቶቻችንን እናሳፍራቸው የሚል መልዕክትም አስተላልፏል።
የቦረቅኩበት በልጅነቴ
የያኔው መልክሽ ብቅ ሲል ፊቴ
እየመለሰኝ ወደ ትላንቱ
ናፍቆኝ በብርቱ ትዝ አለኝ የጥንቱ
ቴዲ ስለቀደመችው ኢትዮጵያ ግን ብዙ የሚለው ያለው ስለመሆኑ በቀደሙት ሥራዎቹ አይተናል። በኢህአደጎቹ ሳቢያ በኢህአዴግ ጊዜ የነበረችውን ኢትዮጵያ ላይናፍቅ ይችላል፤ በአሁኑ ዘፉኙ የበፊቷን ኢትዮጵያ ናፍቋል የሚያሰኙን ስንኞችን አይተናል። የአያት ቅድመ አያቶቻችን ሥልጣኔ ያረፈባትን፣ የሕዝብ አንድነት የነበረባትን፣ እንደ ዓድዋ አይነት በዓለም በደማቁ የሚጻፍ ታሪክ የሚጻፍባት ኢትዮጵያ ናፍቃው ይሆናል።
አገር ለክብሩ ሲጣራ
ከፍ ያደረግነው ባንዲራ
ዘመም ሳይል ቀን ጎሎ
ባክሽ ኢትዮጵያ ነይ ቶሎ
ብዙነሽ አንቺ አገሬ የሞላሽ ታምራት
ምኩራብሽ የተፈራ የነጻነት ቤት
የአርበኞች የድል ችቦ ለትውልድ እንዳበራ
መኖር ላገር ሲሆን ሞትም አያስፈራ
‹‹አገር ለክብሩ ሲጣራ›› አሁን ላለው አገራዊ ጥሪም ይመስላል። አገር እንድትከበር እንድትጠበቅ ሲባል መስዋዕትነት መክፈል ምንም እንደማያስፈራ ያስገነዝባል። የአርበኞች የተጋድሎ ታሪክ ሁሌም በትውልዶች እየታወሰ መሆኑን በማስገንዘብ፣ ይህም ትውልድ ለአገሩ ሲል መሞቱን ሊፈራው እንደማይገባም ያመለክታል።
ዘር ያበቀለው ታጭዷል መከራው
የኢትዮጵያዊነት አሁን ነው ተራው
እነዚህ ስንኞች፤ ቴዲ በዚህኛው ሥርዓት ተስፋ እንዳደረገ ያሳያሉ። የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬትን በተቀበለበት ወቅት ከተናገረው ጋር ስንደምረው የኢህአዴግ መጥፋት ኢትዮጵያን በዘር ላይ ከተመሰረተ አስተዳደር ያወጣታል ብሎ ያምናል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ ‹‹ኢትዮጵያን ለቀውስ የዳረጋት የጎሳ ፖለቲካ ሀሳብ ተወልዶ፣ አድጎ፣ አርጅቶና በስብሶ ተፈጥሯዊ ሞቱን ሞቷል›› ብሏል። ስለዚህ ከዚያኛው ሥርዓት ይልቅ በዚህኛው ሥርዓት ተስፋ አድርጓል ማለት ነው። የዘር ፖለቲካ ያተረፈን መከራ መሆኑንም በመጥቀስ ቀጣዩ ተራ ኢትዮጵያዊነት መሆኑንም ይጠቁማል።
ዘመን አድሰሽ በፍቅር ቀለም
ብቅ በይ ኢትዮጵያ ሆነሽ መስከረም
መስከረም የአዲስ ዓመት መግቢያ ወር ነው፤ የተስፋ ወር። ብዙ ነገሮች እንደ አዲስ የሚጀመሩበት ወር፣በተፈጥሮም ምድሩ አረንጓዴ የሚለብስበት፣ ጋራ ሸንተረሩ በአበባ የሚንቆጠቆጥበት ደማቅ ወር ነው። የኢትዮጵያ ዘመን በፍቅር ቀለም መታደስ አንዳለበት ቴዲ ጠቅሶ፤ ልክ እንደ መስከረም ተስፋና ፍካት ይዛ የምትመጣ ኢትዮጵያን ይጠብቃል።
ቀን አለ በሉ
ቀን አለ ገና
ለኢትዮጵያዊነት ቀን አለው ገና
ስምሽን በክፉ ያነሳሽ ጠፍቶ
አርማሽ ከፍ ሲል ሰማይ ላይ ወጥቶ
እኛ ልጆችሽ ልናይ ቆመናል
አንድ ቀን መጥቶ አንድ ያደርገናል
‹‹ቀን አለ ገና›› አሁን እያስጨነቀው ያለው ነገር ያልፋል ብሎ ተስፋ አድርጓል። የኢትዮጵያ ልጆች ያንን ተስፋ ለማየት በአንድነት መቆማቸውን አስተውሏል። በክፉ ያነሱዋት ጠፍተው አርማዋ ክፍ ብሎ እንደሚውለብለብ በግጥሙ አመልክቷል። አንድ የሚያደርገን አንድ ቀን ይመጣል ብሎም ተስፋ አርጓል።
የጀግኖቹ ልጅ አንተ ነህና
ካገር ወዲያ ሞት ሞት የለምና
ዝም ያለ መስሎ ኢትዮጵያዊነት
ማንም አይገታው የተነሳለት
‹‹ካገር ወዲያ ሞት ሞት የለምና›› ሲል አገሩን የገደለበት አካል እንዳለ ጠቋሚ ነው። ኢትዮጵያዊነት ዝም ያለ መስሎ ሊሆን አንደሚችል ጠቅሶ፣ በኢትዮጵያዊነት ላይ ዝምታ እንደሌለም ያመለክታል። በአንድነት ሆኖ ኢትዮጵያን ማዳን እንደሚገባም ይጠቁማል።
ቴዲ በዚህኛው መንግሥት
ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በኢህአዴግ ጊዜ ግልጽ ዘመቻ ይደረግበት ነበር። ትልልቅ ባለሥልጣናት ዘፈኑን የሚከፍቱ ሰዎችን ያስፈራሩ ነበር። በ2009 ዓ.ም አዲስ አልበም ሲያወጣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ ከተደረገ በኋላ እንዳይተላለፍ መታገዱም ይታወሳል። ኢህአዴግ ባልሰራው ወንጀል ወንጀለኛ ብሎ አንገላቶታል፤ የተበቀለው መስሎት። ቃሊቲ እስር ቤት እንዲታሽም አድርጎታል። ቴዲ አፍሮም በዘፈኖቹ ሥርዓቱን አምርሮ ሲሞግት ቆይቷል።
ቴዲ ለብልጽግና ፓርቲ ድጋፍ ይኑረው ተቃውሞ እስከ አሁን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም። ሥርዓቱን የሚተነኩስ ዘፈን ግን አላወጣም። ከለውጡ ወዲህ ሁለት ነጠላ ዜማዎችን አውጥቷል። አንደኛው ‹‹ደግሞ በአባይ›› የሚለው ሲሆን፣ ይዘቱም ስለአባይ ወንዝ ነው። ሁለተኛው የአሁኑ ‹‹አርማሽ (ቀና በል)›› ነው። ሁለቱም ዜማዎች በመንግሥትም በግልም መገናኛ ብዙኃን በስፋት ተደምጠዋል።
ቴዲ ለመገናኛ ብዙኃን ቁጥብ ነው፤ ስለዚህ የዘፈኖቹን መልዕክት ማንም በተረዳው መንገድ መተርጎም ይችላል፤ ይህ ደግሞ የግጥም ባህሪ ነው። ጥበበኛው ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የጥበብ ልቦናውን አይለውጠው እንላለን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሕዳር 2/2014