ኢትዮጵያ በታሪኳ ብዙ ፈተናዎች ገጥመዋት ሁሉንም እንደየአመጣጣቸው በመቀበል በድል አጠናቃለች:: በዚህም ዘመናትን ተሻግራለች:: ዛሬም ይህ እውነት የህያው ታሪካችን አካል ነው። እኛም የከዳተኞችን የእናት ጡት ነካሾችን ቅስም ሰብረን አገራችንን ወደአዲስ ምዕራፍ ለማሻገር በምንችልበት ታሪካዊ ምዕራፍ ላይ ነን::
ወቅቱ የከዳተኞች ጀንበር ጠልቃ እውነት ደምቃና ፈክታ የድል ጮራ በመላው አገሪቱ እስከሚወጣ ድረስ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሁሉ እንደ አንድ ልብ መካሪ፤ በአንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን አሸባሪውንና ወራሪውን የጁንታ ቡድን ለመዋጋት ወገባችንን ጠበቅ የምናደርግበትም ነው::
በተለይም በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ሕወሓት ከሽንፈቱ የተነሳ በረዘመው ምላሱ የሚረጨውን ፕሮፖጋንዳ እና በበሉበት የሚጮሁት የምዕራቡ ዓለም ውሾችን የጣር ድምጽ ወደጎን በማለትም ሕዝብ እንደ ሕዝብ ተባብሮና ተፈቃቅሮ በአንድነት በመቆም ለመከላከያ ሰራዊቱ ደጀንነቱን ማረጋገጥ አለበት ። ጤና ያለው እድሜው የሚፈቅድለት ሁሉ ወደጦር ግንባር በመሄድ ለአገሩ ያለውን ፍቅር በተጨባጭ ማሳየት ይጠበቅበታል ::
የአሸባሪው ቡድን የሽብር ተግባራት መላው ኢትዮጵያውያንን ያስደነገጠ፣ ያሳዘነ በጠቅላላው ጉድ ያሰኘ የክህደት ጥግ የታየበት ነው:: ይህ የብዙዎችን ልብ የሰበረ እኩይ ተግባር ደግሞ ስጋ ለብሶ ነፍስ ዘርቶ እንዲንፈራገጥ ካደረጉት አካላት መካከል ዋነኛዎቹ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራትና ተቋማቶቻቸው እንደሆኑ ግልጽ ነው:: ቡድኑ ተወልዶ ያደገበት የውሸት ወሬው ያላደረገውን አደረኩ ባይ መሆኑና ጥቂት ደጋፊዎቹን በዚህ መልኩ መቃኘቱ ለሐሰት ትርክቱ አግዞታል:: ይህንን ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን ልንረዳውና ቀድመን ልንነቃ ይገባል::
“ታሪክ ሰሪዎቿን ትመስላለች “ እንደሚባለው ሁሉ መልካም ነገር ያደረጉ ሰዎች በመልካምነታቸው ታሪክ እንደማይዘነጋቸው ሁሉ፤ እቡያንና እኩያንም በዛው በምግባራቸው ልክ ታሪክ ሲያስታውሳቸውና ሲወቅሳቸው መኖሩ አይቀሬ ነው:: ለእውነት የቆሙና ከግል ጥቅማቸው ይልቅ አገርን ያስቀደሙት ደግሞ በዛው ልክ ታሪክም ሕዝብም ሲያመሰግናቸው፤ አገርም በሰሩላት ሥራ አድጋና በልጽጋ ሰላሟ በዝቶ እያስታወሰቻቸው ትኖራለች::
ያለፈው ዘመን እንደሚያሳየን በተለይም እንደ ጁንታው ያሉ እቡያንና እኩያን ከዚህ ቀደምም ባለው ታሪካቸው አገራቸውን ከድተዋል ፤ለግል ጥቅማቸው ብለው ባንዳ ሆነዋል ፤አገራቸውን ወግተዋል፤ የትጥቅ ትግል ብለው በጀመሩት ጦርነትም ሕዝባቸውን አስይዘው ጦር መሳሪያ ሸምተዋል፣ ረሃብን እንደ አንድ የጦር ስልት አድርገው ደጋፊ ሰብስበዋል፤ በዚህም ያልተገባቸውን አሸናፊነት አግኝተው አገርን ላለፉት 30 ዓመታት የኋሊት እንድትጓዝ ሕዝብ በአገሩ እንዲማረር አድርገው ቆይተዋል :: ይህ ሁሉ ነገር ሳይበቃቸው ዛሬም የእናታቸውን ጡት ነክሰው ፤ ሕዝብን አስጨርሰዋል፣ አሳዝነዋል፣ አስለቅሰዋል፤ እርስ በእርስ እንዲነካከስ ለማድረግ ሞክረዋል ::
ዛሬም በለመዱት የውንብድናና የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እዚህ ደረስን እዚያ ገባን በማለት ምላሳቸውን እያረዘሙ እየፎከሩ ነው ፤ እውነታው ግን ይህ አይደለም፤ እኛም እንደ ሕዝብ ልንረዳው የሚገባው የሚወራውና የሚሆነው “ዱባና ቅል ለየቅል” ይሉት አይነት ነገር መሆኑን ነው::
እነዚህ የወሬ ማማዎች ድሮም በወሬና በሽብር የተካኑ መሆናቸውን መቼም ከ 30 ዓመታት የአብሮነት ቆይታችን ጠንቅቀን የምናውቀው ይመስለኛል፤ ዛሬ ላይም ትንሽ እድል ሲያገኙ የሚይዙት የሚጨብጡት በማጣት በራሳቸውም ሆነ በግብር በሚመስሏቸው የጥቅም ተጋሪ የውጭ ሚዲያዎች አማካይነት ከጣሪያ በላይ ይጮሃሉ :: ለነገሩ ትንሽ ሲጎሸሙም እርዱን ብሎ ለመጮህ የሚቀድማቸው የለም ::
ታዲያ እነሱ አሉ ብሎ ማን ይሸበራል? ማንም? ይልቁንም ለወሬ የለንም ጊዜ ብለን እስከ ወዲያኛው የሚቀበሩበትን መንገድ እንደ ሕዝብና አገር መሥራቱ ያዋጣል:: የእነሱን ጩኸት በበሉት ልክ እየመዘኑ የሚያላዝኑ የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ተብዬም ጆሮ መስጠት አሁን ወቅቱ አይደለም:: ወቅቱ አይደለም ያልኩበት ዋና ምክንያቴ ደግሞ እውነታው አዘናጊ በመሆኑ ነው::
ወገኖቼ እነዚህ የወሬ ማማዎች በተለይም የውጭ ሚዲያዎቹ እኮ የአሸባሪውን ቡድን ሥራ ለኢትዮጵያ መንግሥት በመስጠት ባለፈው አንድ ዓመት ያላሉት ነገር አልነበረም። የኢትዮጵያ መንግሥት ግጭቱን ጀመረ፣ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያ እየተጠቀመ ነው፣የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጸመ፤ ኧረ ምኑ ቅጡ፤ ያልሰማነው ነገር አለ እንዴ? ታዲያ አሁንስ እነዚህ የተባሉት ነገሮች ሁሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት በሰሩት ጥናትና ባወጡት መግለጫ አልተረጋገጡም ? ተረጋግጠዋል::
ይህም ሆኖ ዛሬም ቢሆን አሜሪካና ጥቂት ሽርከኞቿ የጀመሩትን የጥላቻ መንዛት ዘመቻ አላቆሙም ። የሚያቆሙም አይመስልም። የኢትዮጵያ መንግሥት ተገዶ ሰራዊቱ ተጨፍጭፎበት የገባበትን የህግ ማስከበር እንቅስቃሴ ሲያወግዙ የነበሩት አካላት ዛሬ ዓይን ላወጣው የወያኔ ወረራ አፋቸውን ለጉመው ተቀምጠዋል። ምክንያቱም የእነዚህ አገራት አሜሪካን ጨምሮ ዓላማቸው ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት የሚል ለፈስፋሳ መንግሥት ማስቀመጥ እንጂ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አልያም የትግራይ ሕዝብ ሰቆቃ አይደለም። ዓላማቸው የሕዝብ እልቂትን መፈናቀልና የንብረት ውድመትን መታደግ ቢሆን በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ተፈጥረው ለነበሩት ግጭቶችም እንደአሁኑ ደግመው ደጋግመው ድምጻቸውን ባሰሙ ነበር።
ኧረ ሁሉም ይቅር እንደ ፈረስ ሊጋልቡ ካስቀመጡት ትህነግ ደህንነት ውጪ የትግራይ ሕዝብ ጉዳይ የሚያሳስባቸው ቢሆን የላኩት የእርዳታ እህል ሲዘረፍ ዘራፍ ባሉ ነበር። ያልተዋጋ ወንድ ቀሚስ ይልበስ እኛን ያልደገፈ ይወገድ እያሉ በራሳቸው ሕዝብ ላይ ሲዘምቱ ባስጠነቀቁም ነበር። ግን መነሻቸውም መድረሻቸውም ተላላኪ መንግስት መፍጠር በመሆኑ እነዚህን ጉዳዮች አይነኳቸውም።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ልብ እንዲባል የምፈልገው ነገር የጁንታው ቡድን አፈቀላጤዎች የሆኑት የውጭ ሚዲያዎች ብሎም በአገር ውስጥ ቁጭ ብለው የሚቀለቡ ከሃዲያን የሚነዙትን የሽብር ወሬ ወደጎን ብለን እንደ ሕዝብ መተባበር አለብን የሚለውን ነው::
እንደ ሕዝብ የመተባበራችን ቀዳሚው ፋይዳ በትናንሽ እሳቤዎች የውጪ ኃይሎችን ፍላጎት ለማሟላት የሚንቀሳቀሱትን እንዳያንሰራሩ አድርገን ለማጥፋት ያስችለናል። ይህን ካደረግን ደግሞ እነ አሜሪካ በውስጥ ጉዳያችን ሾልከው እንዲገቡ የሚያስችላቸው ቀዳዳ ይደፈናል ማለት ነው።
በእርግጥ ይህንን ለማድረግ የምንጓዝበት መንገድ ማዕቀብ መጣል ስንዴ መከልከል የመሳሰሉትን መሰናክሎች ያሉበት ነው። ዋናው ቁም ነገር ግን ሕብረታችንን ይዘን እንንቀሳቀስ እንጂ ሁሉም ቀላል ነው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ ሩቅ ሳንሄድ ከወራት በፊት በራሳችን ጉዳይ የታላቁን ህዳሴ ግድብ በተመለከተ በተመሳሳይ መንገድ ተጉዘናል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቃል በቃል ግብጽ ግድቡን ልታፈርሰው እንደምትችል ነግረውን ነበር።
የነገሩን ግን ግብጽ ደፍራ ያንን ታደርጋለች ብለው ሳይሆን እነሱ ፈርተው ያቆማሉ በሚል ተልካሻ እሳቤ መሆኑን ቃላችንን ጠብቀን ሙሌቱን በማከናወን በተግባር አይተናል። ባጭሩ በአሁኑ ወቅት ያለው የጁንታው ማስፈራሪያና ዛቻም ይኸው ነው። የሚሉንን የሐሰት ጥርቅምቅም ሰምተን ከፈራንና ከተደናበርን የፈለጉትን ያሳካሉ ከጸናንና ከታገልናቸው ዋጋቸውን እንሰጣቸዋለን። በመሆኑም የትህነግን ድንፋታ ትተን የሚጠበቅብንን እንወጣ መልእክቴ ነው።
በዕምነት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 30/2014