ከፊታችን ሁለት ኩነቶች ይጠብቁናል። ሕወሓትን የማሰናበትና ግብአተ መሬቱን የማጣደፍ፤ የኢትዮጵያን የከፍታ ዘመን እውን ማድረግ። በነዚህ ሁለት ኩነቶች ውስጥ ሕወሓት ላይመለስ ጠፍቶ፣ ኢትዮጵያዊነት ላይደርቅ ይለመልማል፤ ሀሰተኛው ይዋረዳል፤ እውነተኛው በኩራት ይቆማል። ከፊታችን ያሉት ወሳኝ ወቅቶች ለሕወሓት ሰሞነ ኑዛዜ ናቸው። ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ደግሞ የተስፋ ብስራቶች ናቸው።
ሕወሓትና ኢትዮጵያ የብርሃንና የጨለማን ያህል ይራራቃሉ። በአንዱ ውስጥ ሰውነት ምንም ነው፤ በአንዱ ውስጥ ደግሞ ሰው መሆን ቅኔና የክብር ጥግ ነው። ኢትዮጵያዊነት ገናና እውነት ነው። ሕወሓት ደግሞ በዚህ ገናና እውነት ውስጥ የተገኘ እንክርዳድ። ኢትዮጵያዊነት በእውነትና በፍትሕ በብርሃንም የተከበበ ጸዐዳ መልክ ነው፤ ሕወሓትነት ደግሞ ይሄን ውብ የሕዝቦች መልክ ያጎሳቆለ የስግብግብነት መገለጫ አዳፋ ገጽታ ነው።
ኢትዮጵያ ለሕወሓት ኳስ ነበረች፤ ወደፈለገበት ቦታ እንደፈለገ የሚጠልዛት፤ መጫወቻው። ለሀያ ሰባት አመታት ጠላዟታል፤ ለሀያ ሰባት አመታት ጠልዞናል። ለሀያ ሰባት አመታት በትውልዱ ላይ እቃቃ ተጫውቷል። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በዚህ ከሀዲ ቡድን በእነዚህ አመታት ክፉኛ ጠልሽተዋል፤ በጣም የሚገርመው ደግሞ ቡድኑ ገለል ተደርጎም ከሀገራዊው ለውጥ በኋላ እሰከ አሁንም ድረስ በዚህ ራስ ወዳድ ቡድን ክፉኛ ማደፋቸው ነው።
እጅግ ደስ የሚለው ግን ይህን ቡድን ከጫንቃችን ልናወርደው መቃረባችን መሆኑ ነው። ብዙ ዋጋ ቢያስከፍልም የሕወሓት የስንብት ቀን ተቃርቧል። በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን፣ በአገር ወዳድ ዜጎቻችን እልህ አስጨራሽ ትግል ይሄን ከሀዲ ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልንሰናበተው ከጫፍ ደርሰናል። አሁን ሁሉም ነገር ተቀይሯል፤ በተባበሩ ክንዶች፣ ሠላም በተራቡ ነፍሶች የኢትዮጵያ ጠላቶች እያፈሩ የመጡበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
አዎን፤ የቡድኑ አሳፋሪ ድርጊት በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር እየተጋለጠ ነው። እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንደሚባለው ኢትዮጵያን በሀሰት ሲያብጠለጥሉ የቆዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ምእራባውያንን እያፈሩ ያለበት ሁኔታም ይህን ያመለክታል። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሰሞኑን ይፋ ያደረጉት በጋራ ያካሄዱት ጥናት ሀሰተኞች ይዘገያል እንጂ እንደሚጋለጡ አረጋግጧል። ኢትዮጵያን በሰብዓዊ መብት ጥስት በመወንጀል ባልዋለችበት ሊያውሉ የሞከሩት ትህነግ እና አጨብጫቢዎቹ ቅሌታቸውን ተከናንበዋል።
እናም ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ካለበሷት ትቢያ ውስጥ እየወጣች ነው። ሕወሓት እስከወዲያኛው ሲደመሰስ ደግሞ ይህ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ወደ ከፍታ ዘመናቸው መጓዛቸውን ይቀጥላሉ። በሕወሓት አለመኖር ውስጥ የምትፈጠረዋን ኢትዮጵያ አስባችኋታል? በሕወሓት መክሰም ውስጥ የሚጎመራውን ኢትዮጵያዊነት ገምታችሁታል? ከዚህ ከሀዲ ቡድን በኋላ የሚመጣውን ትውልድስ? የምንታገለው በምክንያት ነውና እርግጠኛ ነኝ ታውቁታላችሁ።
ኢትዮጵያ … ኢትዮጵያ የምንለው በምክንያት ነው። ከሕወሓት ወዲያ ማዶና ከሕወሓት ወዲህ ማዶ ያለችው ኢትዮጵያ የአንድነት ኢትዮጵያ ናት። ከሕወሓት ወዲያ ማዶ ያለችው ኢትዮጵያ የአባቶቻችን ኢትዮጵያ ነበረች፤ በእውነት፣ በፍትሕ፣ በአንድነትና በፍቅር ያጌጠች። በዚች ኢትዮጵያ ውስጥ እኔነት አልነበረም። እንደ ሕወሓት ያሉ ከአብራክ ወጥተው ጡት ነካሽ ትውልዶች አልተፈጠሩባትም ነበራ።
ከሕወሓት ወዲህ ማዶ ያለችው ኢትዮጵያ ደግሞ በሕወሓት እኔነት ውስጥ በእጅጉ የተጎዳች ኢትዮጵያ ናት። ይህችን የእኔና የእናንተ የህልማችን ኢትዮጵያን ከሕወሓት የእኔነት ክፉ መዳፍ ውስጥ ለማውጣት እየታገልን ነው።
አሁን የምንታገልላት ኢትዮጵያ እንደ አባቶቻችን ኢትዮጵያ የአንድነትና የእውነት ኢትዮጵያ ናት። ዛሬ ላይ ነፍሳችንን አሲዘን ከሕወሓትና ከመሰል ጠላቶቻችን ጋር የምንታገለው ስለዚች ኢትዮጵያ ነው። ይህቺኛዋ ኢትዮጵያ በሁላችንም ልብ ውስጥ ቆይታለች፤ ከሕወሓት ግብአተ መሬት በኋላ ደግሞ ይበልጥ ጎልታ በመውጣት የቀደመ ስፍራዋን ትይዛለች።
የከሀዲውን ቡድን ግብአተ መሬት አፋጥነን፣ የምንናፍቃትን ይህቺን አገር ለመፍጠር ጊዜው አሁን ነው። እየከፈልን ባለነው መስዋእትነት ሕወሓት ከመቃብሩ አፋፍ ላይ ደርሷል። ጥቂት የክፋት ወዳጆቹን እየተሰናበተ ይገኛል። ትግላችን ፍሬያማ እንዲሆን እስከ ግብአተ መሬቱ እስከሚፈጸም ድረስ ልንፋለመው ይገባል።
ቡድኑ ውሸትና ማስመሰል ጥርሱን የነቀለበት ነው። በሞቱ የመጨረሻ ሰዓት ላይ አሁንም የመረጠው ይሄንኑ ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨቱን ነው። እየሞተ ከሚነግረን ውሸት፣ እየወደቀ ከሚነዛልን የማስመሰል ወሬ ራሳችንን ጠብቀን በጀመርነው የትግል እርምጃ ተጉዘን ግብአተ መሬቱን እናፋጥን፤ ብረትን እንደጋለ ይባላል፤ ለነገ ብለን የምናሳድረው ሥራ ሊኖር አይገባም። በዚህ ወሳኝ ወቅት የተጀመረውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ይበልጥ አቀጣጥለን በመረጠው የትግል ስልት ልንደመስሰው ይገባል።
የመጨረሻዎቹ ቀናት ጥንቃቄ ይሻሉ፤ በአስተውሎት ካልተጓዝናቸው ዋጋ ያስከፍላሉ። የአሁኑ የሕወሓት እርምጃ ከሞትኩ አይቀር የሚል አይነት ነው። በታላቅ ተስፋ መቁረጥ በውሸት ወሬ ህዝብ ማደናገርን በከፍተኛ ሁኔታ ተያይዞታል።
ሰሞኑን በጦር ግንባር ድል እየተደረገ መሆኑን ሲረዳ ወደ ለመደው የሐሰት ፕሮፓጋንዳው ተመልሷል። በግብረአበሮቹ በኩል ሀሰተኛ መረጃ ማሰራጨቱን ቀጥሏል። በሞት አፋፍ ላይ ሆኖም ፣ በሀሰተኛ መረጃ ሕዝብ ማወናበዱን ተያይዞታል።
በቡድኑ ሀሰተኛ መረጃ በተደጋጋሚ ተጠቅተናል፤ አሁን መንቃት ይኖርብናል። ሕወሓት በመጨረሻ ቀኑ ላይ ነው። ወደፊትም ሆነ ወደኋላ የሚልበት አቅም የለውም። ይሄን ሀቅ በሚገባ በመረዳት ከመንግሥት ጎን መቆም ይኖርብናል። በቡድኑ የመጨረሻዎቹ ሰዓታት የፈጠራ ወሬዎች ሳንደናበር ከእሱ ውሸት ይልቅ የእኛ እውነት ዋጋ እንዳለው ልናሳየው ይገባል።
ትግላችን ከእኔነት ወይም ግለኝነት ነጻ የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር ነው፤ ከማንነትና ከምንነት የበረታች አገር መገንባት ነው። እየሞትን ያለነው የሁላችንንም የጋራ አገር ለመጠበቅ እንደሆነ እሙን ነው። የሕወሓት መሰናበትና ግብአተ መሬቱ መፈጸም ለኢትዮጵያ ትንሳኤ ነው። የሕወሓት አለመኖር ለኢትዮጵያውያን ትንሳኤ ነው።
እንደ አገርም ሆነ እንደ ዜጋ እንዲሁም እንደ ግለሰብ የዚህ ቡድን አለመኖር ዋጋው የላቀ ነው። በኢትዮጵያውያን ትግል፣ ለውጥ በናፈቃቸው እጆች፣ ብርሃን በናፈቃቸው አይኖች ሕወሓት የዶግ አመድ ሊሆን ተቃርቧል። አሁን ጊዜው የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ነው። በቃ ባለጊዜዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። አገራችን ኢትዮጵያ የተስፋ ችቦዋን ለኩሳለች። ሕዝብ ከሕወሓት የክፋት እጆች ነጻ ወጥቶ የድል ብስራቱን ሊያሰማ ነው። ትውልዱ ወደ ምሥራቅ እያየ ነው።
የውሸትን ኃይል ለማወቅ ሕወሓትን ማየቱ ብቻ በቂ ነው። ከሕወሓት ውሸት ራሳችሁን አርቁ፤ ጆሮአችሁን አሽሹ። ደጋግሜ አሳስባለሁ፤ አሁንም ሕወሓት ባልሆነና በማይሆን ውሸት እየመጣ ነው። ድላችሁ በውሸት እንዳይታጠፍ፣ ግስጋሴአችን በውሸት እንዳይደናቀፍ ከዚያ ወገን የሚለቀቁትን ሁሉ አትመኑ።
በአሁኑ ሰዓት ሁላችንንም የሚያግባቡት ሁለት እውነቶች የሕወሓት የውድቀት ዜናና የኢትዮጵያ ትንሳኤ ናቸው። ሕወሓት በጣዕረ ሞት ውስጥ ሆኖ እየተንከላወሰ ነው። አዎን፤ ቡድኑ በግፍ የጨፈጨፋቸው ንጹሃን ደም፣ ያሰቃያቸው ንጹሐን እንባ ጣዕረ ሞቱን አርዝመውት እንጂ አለ የሚባል አይደለም።
በተቃራኒው ደግሞ ኢትዮጵያዊነት እየለመለመ ነው። ብዙዎቻችን ይሄን ቀን በጉጉት ስንጠብቅ ቆይተናል። አሁንም ቢሆን በጣዕረ ሞት ውስጥ ሆኖ በሚፈጥራቸው የውሸት ዜናዎቹ ሳንደናገጥ እስትንፋሱ እስከምትወጣ ድረስ ልንታገለው ይገባል።
የሕወሓትን ውድቀትና የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማየት የናፈቁ አይኖች ብዙ ናቸው። ትንሳኤያችንን ለማወጅ በመጨረሻዋ ሰዓት ላይ ነን። ከፍ ብዬ እንደጠቅስኩት ሕወሓት ሲሰናበት መወራጨቱ አይቀርም። በረቀቀና እውነት በሚመስል ውሸት የተሞላ መረጃ አያሰራጭም ተብሎ አይጠበቅም። የሰሞኑን ሽንፈቱን ተከትሎ የፈጠራ ወሬዎችን እየተለቀቀ ነው፤ እነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች ሞቱን ይፋ የሚያደርጉ ቢሆኑም፣ የእኛንም ጥንቃቄ የሚሹ ናቸውና እንጠንቀቅ እላለሁ አበቃሁ። ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 29/2014