የዛሬ አመት ባለፈው ሳምንት፤ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ታሪክ ይቅር የማይለው ክህደት ተፈጸመባቸው። ኢትዮጵያ ክህደት ተፈጸመባት። አገራዊ ለውጡን በመቃወም በትግራይ ክልል በመሸገው ክልሉን ያስተዳድር በነበረው የሕወሓት ቡድን የአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ ክህደት ተፈጸመበት፤ በገዛ ወገኑ ከጀርባው ተወጋ።
ሰሜን ዕዝ በትግራይ ክልል 20 አመታትን የቆየ አገሩን ከወራሪዎች ጠብቆ ታሪክ ያስመዘገበ ሠራዊት ነው። የሚከበርና በእሳት የተፈተኑ ጀግኖችን ያፈራ። ሠራዊቱ የአገርን ሉዓላዊነት ብቻ የሚጠብቅ አልነበረም። ከትግራይ ክልል ሕዝብ ጎን ሆኖ አያሌ ልማታዊ ሥራዎችን በማከናወንም ይታወቃል። ትምህርት ቤቶችን፣ ጤና ተቋማትን፣ መንገዶችንና የመሳሰሉትን መሠረተ ልማቶች ገንብቷል። የአርሶ አደሩን ሰብል ከአረም ታድጓል፤ የደረሰ አዝመራውን ከዝናብና ከአንበጣ የጠበቀም ነው። ይህ እንደ አይን ብሌን ሊጠበቅ የሚገባው ሠራዊት ነው እንግዲህ በገዛ ወገኑ በተኛበት የፈሪዎች ብትር ያረፈበት።
በሠራዊቱ ላይ ክህደት በተፈጸመበት በዚያን ምሽት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለመላ ኢትዮጵያውያን የተፈጸመውን የክህደት ተግባር አስታወቁ። በመልእክታቸውም ‹‹ከሃዲ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያን ወግተዋታል፣ ያጎረሰ እጇ፣ ያጠባ ጡቷ ተነክሷል … ከሃያ ዓመታት በላይ በኖረበት አካባቢ ከሃዲዎች ባደራጁት ኃይል ከጀርባው በመሆን በመወጋት፣ በአገሪቱ ታሪክ ከተከሰቱት መሰል ጥቃቶች አጅግ አስነዋሪ ድርጊት ፈጽመዋል፤›› በማለት ዕኩይ ድርጊቱን አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ሉዓላዊነትና ሕገ መንግሥት ላይ የተቃጣው ጥቃትና የተፈጠረውን ክስተት በማይደገምበት ሁኔታ እንዲቀለበስ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት የሕግ ማስከበር ሥራ እንዲያከናውን ትዕዛዝ መሰጠቱንም ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልእክት በመገናኛ ብዙሃን ሌሊቱን ብቻ ሳይሆን በማግስቱም ሲተላለፍ ዋለ። ድርጊቱ መላ ኢትዮጵያውያን በእጅጉ አስቆጣ። የመከላከያ ሠራዊቱ ይበልጥ ወኔ ሰንቆ እንዲነሳ አደረገ።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ውድቅት ሌሊት ላይ ሲሆን፣ ከሀዲዎቹ የሰሜን ዕዝ መምሪያ ም/ኃላፊ የነበሩትን ብ/ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴን ጭምሮ በርካታ የጦር መሪዎችን አፍነው ወሰዱ። በትግራይ ክልል በሚገኙት የሰሜን ዕዝ የተለያዩ ክፍሎች በሙሉ ጥቃቱ ተፈጸመባቸው። ከሀዲዎቹ የሠራዊቱን የሬዲዮ መገናኛ በማቋረጣቸው ሠራዊቱ ከግንኙነት ውጭ ተደረገ። ሬዲዮውን ያቋረጡት አሁን በቁጥጥር ስር የሚገኙት ሜጀር ጄኔራል ገብረመድህን ፈቃዱ (ወዲ ነጮ) መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። የአገር መከላከያ ሠራዊትን 60 በመቶ የሰው ኃይልና ትጥቅ አቅም እንደሆነ በሚነገርለት በዚህ እዝ ላይ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው። ግዙፍ እዝ።
እነዚህ የአገር ባለውለታዎች በተለይም የትግራይ ሕዝብ ባለውለታዎች ከትግራይ ሕዝብ አብራክ በወጡ ከሀዲዎች ታሪክ ይቅር የማይለው ጥቃት ተፈጸመባቸው። ሠራዊቱ ጥቃቱ የተፈጸመ ዕለት ቀን ላይ ሁሌም በአዝመራ ወቅት እንደሚያደርገው የአርሶ አደሩን ሰብል ሲሰበስብ ነው የዋለው። ያን እለት ምሽት ላይ ደግሞ ዘና የሚልበት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ነበር። ሠራዊት በቀኑ ስራም በምሽቱ መርሀ ግብርም ደካክሞ በተኛበት ነው ያ ሁሉ ጥቃት የወረደበት።
የአገሪቱ በእሳት የተፈተኑ ጀግኖች በከሀዲዎች በግፍ ተጨፈጨፉ። ከሀዲዎቹ ሬሳቸው የትም ወድቆ እንዲቀር አረጉ፤ የሬሳ ወግ ነፈጉት። አንዳንዶችን ልብሳቸውን አውልቀው ራቁታቸውን እንዲሄዱ አደረጓቸው። የተወሰኑትንም በሕይወት እያሉ መሬት ላይ አጋድመው መኪና እየነዱባቸው የገደሉዋቸው ስለመኖራቸው ድርጊቱ የተፈጸመባቸውና ለወሬ ነጋሪ የተረፉ የሠራዊቱ አባላትም ይህንኑ መስክረዋል። የዓይን እማኞችም እያነቡ ለመገናኛ ብዙሃን የሰጡት መረጃዎችም ይህንኑ ያመለክታሉ። በዚህ ጥቃት ከሃያ ዓመታት በላይ በክልሉ የቆዩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ተገድለዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ታፍነው ተወስደዋል።
የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታ ማዦር ሹም ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ ዕኩይ ድርጊቱን አስመልክተው በገለጹት ዜጎች በእጅጉ አዝነዋል። ከሀዲዎቹ «የሠራዊቱን አባላት ገድለው ልብሳቸውን አውልቀው ሬሳቸውን አንድ ላይ ከምረው ሌሊቱን ሙሉ ሲጨፍሩ አደሩ» በማለት ሌ/ ጄኔራል ባጫ ደበሌ ገልፀውታል። ከሀዲዎቹ የሠራዊቱን አባላት መግደላቸውና መጨፈራቸው ሳያንስ ልብሳቸውን አውልቀው አስከሬናቸውን በአውላላ ሜዳ ላይ አስጥተው ብርድና ፀሀይ እንዲፈራረቅበት አድርገው እንደነበር በወቅቱ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
አገር በድርጊቱ የሀዘን ማቅ በለበሰችበት በዚያ ወቅት የሕወሓት መሪዎች በደስታው ውስጥ ሆነው መግለጫዎችን ይሰጡ ነበር። ቡድኑ የእዙን መሳሪያዎች ሁሉ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ ርእስ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን አስታወቀዋል። አሁን ከአገሪቱ የጦር ኃይል አቅም 80 በመቶውን በእጃችን አስገብተናል ሲሉም የማስጠንቀቂያ አይነት መልእክት አስተላለፉ።
ቡድኑ የዘረፋቸውን የጦር መሣሪያዎች ላደራጃቸው ልዩ ኃይሎች እና ሚሊሻዎች መስጠቱን በወቅቱ የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የሕወሓቱ አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው በሰሜን እዝ ላይ 45 ደቂቃ ብቻ የወሰደ መብረቃዊ ጥቃት በመፈጸም በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉን በአንድ መድረክ ላይ አስታውቀዋል።
ሕወሓት ይህን የክህደት ተግባሩን ለመፈጸም ሁለት አመታትን የዘለቀ ዝግጅት አድርጓል። ራሱን ሲያደራጅ ቆይቷል፤ በዚህም 11 ብርጌድ ልዩ ኃይል እንዲሁም 14 ብርጌድ በዞን ደረጃ ኃይል እንደነበረው በወቅቱ የጦር አዛዦች የሰጡት መረጃ ያስረዳል።
ፊትም የሰሜን እዝን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ይከታተል ነበር። ሠራዊቱ ለተለያዩ ግዳጆችና ተግባሮች እንዳይንቀሳቀስ ጭምር ያደርገው እንደነበር ሲገለጽ ቆይቷል፤ ሠራዊቱ ያለበትን አካባቢ ነዋሪዎች ‹‹ትታችሁን አትሂዱ፤ ለጥቃት እንጋለጣለን›› እንዲሉ እያረገና ሠራዊቱ በሚጓዝበት ጎዳና ላይ እንዲተኙ በማድረግ እንቅስቃሴውን ያስተጓጉል ነበር። ያን ያደረግ የነበረው የሚፈልገው ጥቃት የሚፈጽምበት ቀን እስኪደርስ ብሎ እንጂ ለሠራዊቱ ክብር ሲል አልነበረም።
ጥቅምት 18 ቀን 2013 ዓ.ም መንግሥት ሜጀር ጄኔራል በላይ ስዩም የሰሜን ዕዝን እንዲመሩ ቢሾምም ሕወሓት ወደ ክልሉ መግባት እንደማይችሉ ሲያሳውቅ፤ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ ደግሞ የሕወሓትን እርምጃ ተከትሎ መሰል ድርጊቶችን እንደማይታገስ አስጠነቀቀ።
በዚህ ሁሉ መካከል ቡድኑ በመላ ኢትዮጵያ በተላላኪዎቹ በኩል ግጭት እንዲጫር ጥቃት እንዲፈጸም እያደረገ ንጹኃን ዜጎችን ያስጨፈጭፍ ነበር፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ተፈናቃይ ኢትዮጵያን አጋጥሟት ስሟም በውስጥ ተፈናቃይ ብዛት ከእነ ሶርያ ተርታ እንድትሰለፍ የሆነችው በዚሁ ወቅት ነበር።
ይህ ሁኔታ ያሳሰበው መንግሥት በበኩሉ መከላከያ ሠራዊትን ግጭት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች እያሰማራ፣ ኮማንድ ፖስት እያቋቋመ ችግሩን ለመፍታትና ሕዝቡን ለመጠበቅ ተንቀሳቅሷል። ቡድኑ ግን ግጭት እየቀሰቀሰና ሕዝብ እየጨረሰና እያፈናቀለ መንግሥት አገር ማስተዳደር አልቻለም እያለ ይከስ ነበር።
ግጭቱ ከመከሰቱ በፊት የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ እናቶች እርቅ ለመፍጠር ጥረት አደረጉ፤ በጁንታው ትዕቢትና ዕብሪት ምክንያት ተቀባይነት አላገኘም። መንግሥት አምባሳደሮችን ጭምር በመላክ ቡድኑ ሰላም እንዲያወርድ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካም።
ሕወሓት ግን ቀን ቀን መንግሥት መስሎ ክልል እየመራ በአስፈላጊ ሰዓት ከፌዴራል መንግሥት ጋራ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች በስብሰባ እያወራ ለጦርነቱ ሴራውን ሲያደራና ሥራውን ሲሠራ ቆይቷል። ልዩ ኃይል ማሰልጠን መመረቁ፣ ወታደራዊ ትርኢት ማሳየቱ ተጠናክሮ ቀጠለ። በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የመከላከያ አባላት በዝውውርና በመሳሰሉት ወደ ሰሜን እዝ እንዲሰበሰቡ ይደረግ እንደነበርም ይነገራል።
አስቀድሞም የቀድሞ ኤታማዦር ሹም ፃድቃን ገ/ ትንሳይ ከመቀሌ ተጠርተው ሄዱ፤ ሌሎችም በመከላከያ ጦር ውስጥ የነበሩ በጥቃቱ ዙሪያ የሚዶልቱም እንዲሁ። የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሠራዊት ጡረተኞችም ጥሪ ተደርጎላቸዋል። ቱባ ቱባ የሕወሓት አባላትም ወደ መቀሌ ተመዋል። የሕወሓት አባላት የሆኑ የፓርላማ አባላትም ወንበሩን ለቃችሁ ወደ መቀሌ ኑ ተብለው ሄዱ።
እነዚህ ማስረጃዎች ሕወሓት ነገር እየወረወረ ጦር ለመወርወር እየተውተረተረ የነበረ ስለመሆኑ ያመለክታሉ። ሕዝቡ የሕግ የበላይነት ይከበር እያለ ሲጠይቅ መንግሥት በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያረገ ከእነሰንኮፉ እንቅላለሁ እያለ መልስ ይሰጥ ነበር።
በሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመውን ክህደት ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በመወያየት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጣ። መንግሥት ሠራዊቱን በአጭር ጊዜ አሳባስቦ ግንኙነትን ወደ ቀድሞው መልሶ በትግራይ ክልል ሕግ የማስከበር ዘመቻውን አጠናክሮ ቀጠለ። ይህ ኃላፊነት የማይሰማው ቡድን በእጁ በገቡ ከባድ መሳሪያዎች እንዳይጠቀም በሚል መሳሪያዎቹ በአየር ኃይል እንዲወድሙ ተደረገ።
የቡድኑ አመራሮች እና ታጣቂዎቻቸው እጃቸውን በሠላም እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ተጠየቁ፤ አሻፈረን ብለው በክህደቱ ቀጠሉ። ሦስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የፌዴራል መንግሥት ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ የተለያዩ የትግራይ ክልል ከተሞች በቁጥጥር ስር ዋሉ። መቀሌም በቁጥጥር ስር ውላ አሸባሪው ትህነግ ወደ ዋሻ ተመለሰ። ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው፤ የኢትዮጵያን የመከላከያ አቅም 80 በመቶ በቁጥጥር ስር አውለናል እያሉ ሲያስጠነቅቁን የነበሩት ውሃ በላቸው። የትግራይ ክልል አዲስ ጊዜያዊ አስተዳደር ተመሰረተላት። በተከታታይ በተወሰዱ ሕግ የማስከበር ተግባሮች በርካታ የቡድኑ አመራሮች ተገደሉ።
በሰሜን እዝ ላይ 45 ደቂቃ ብቻ የፈጀ መብረቃዊ ጥቃት ፈጸምንበት ያለው ሴኩቱሬ ጌታቸውን ጨምሮ በርካታ ቱባ ቱባ የከሀዲው ቡድን አመራሮች ተገደሉ። በርካቶችም በቁጥጥር ስር ዋሉ። አሸባሪው ያናፋውን ያህል ለወራት ዋሻ ውስጥ ተቀመጠ።
በሰሜን ዕዝ ላይ የተካሄደውን አስነዋሪ ድርጊት ለማስታወስ ዜጎች ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ በያለቡት በመቆም፣ ቀኝ እጃቸውን ደረታቸው ላይ በማድረግ ‹‹አልረሳውም ፤ እኔም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ›› በሚል መሪ ቃል ቀኑ አስበውታል።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2014