ዓሳ ከውሃ ውጭ ሊኖር እንደማይቻለው ሁሉ አገርም ያለሕብረተሰብ አገር ተብላ ልትጠራ አትችልም። አንድ ሕብረተሰብን ለመፍጠር መሠረቱ ቤተሰብ ነው። እያንዳንዱ ቤተሰብ ደግሞ ትውልድ እየተካ አገር እንዲቀጥል ጉልህ አስተዋጽኦ አለው።
“መልካም ትዳር መልካም ፍሬን ያፈራል” እንደሚባለው ሁሉ ልጆች ከቤተሰቦቻቸው የሚያገኙትን ማንነት ይዘው ወደ ማህበረሰቡ ይቀላቀላሉ። ይህም ማለት ልጆች ቤተሰቦቻቸውን በማየት የጠለቀ እውነትን በቀጥታ ይማራሉ።
የተማሩትንም ወደ ተግባር ይቀይራሉ። ‹‹ልጆች ነጭ ወረቀት ናቸው›› የሚባለውም ለዚሁ ነው። ታዲያ በሥነ-ምግባርና በዕውቀት ታንጾ ያደገ ልጅ ከራሱና ከቤተሰቡ አልፎ ለማህበረሰቡ ብሎም ለአገር ይተርፋል። በተቃራኒው ደግሞ ምግባረ ብልሹ ትውልድ አገር ያፈርሳል።
ይህን ሀሳብ ያነሳሁት ታዲያ አገር እያፈረሰ ስላለው አሸባሪው የትህነግ ቡድን ለማተት ፈልጌ አይደለም። ይልቁንም ቤተሰብን በማየትና በጥልቀት በመረዳት ከእነርሱ የቀሰመችውን ዕውቀት በሥራ ላይ በማዋል ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ መሆን የቻለች ባለሙያ እንግዳ አድርጌ በማቅረቤ ነው። እንግዳዬ መሠረቷ ከተገነባበት ቤተሰቧ ተነሥታለች። ማንኛውንም ነገር መሞከርና ለመሥራት ዝግጁ ሆኖ በፍላጎት መሥራት ውጤታማ ያደርጋል የሚል ጠንካራ ዕምነትም አላት።
‹‹የሥራ ክቡርነትንና በዚያ ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባለፈ ውስጣዊ እርካታ ከሁሉ የሚበልጥ መሆኑን ጭምር ከቤተሰቦቼ በተግባር ተረድቻለሁ›› የምትለው የዕለቱ የስኬት እንግዳችን በፋሽን ዲዛይን፣ በእጅ ሥራና በከተማ ግብርና ተሰማርታ እየተጋች ያለች ባለሙያ ናት። የተለያዩ የእጅ ሥራ ሙያዎችን ከወላጅ እናቷ የግብርና ሥራውን ደግሞ ታታሪና ሥራ ወዳድ ከነበሩት ወላጅ አባቷ የወረሰችው ስለመሆኑ የምትናገረው ዲዛይነር ቅድስት አበራ፤ ከወላጆቿ ባገኘችው ዕውቀት ምክንያት ሥራ ጠባቂ ካለመሆኗም በላይ በደስታ የምትሠራው ሥራ እንደሆነ ትናገራለች።
ዲዛይነር ቅድስት፤ ማህበረሰቡን ለመፍጠር መሠረት ከሆነው ቤተሰብ ያገኘችውን እምቅ ችሎታ በመጠቀም ወደ ተግባር ቀይራዋለች። እኛም የገጹ እንግዳ ልናደርጋት ማሰባችን ያለምክንያት አይደለም። እያንዳንዱ ቤተሰብ ለልጆቹ ከቀለም ትምህርት ባለፈ ምን እያስተማራቸው እንደሆነ ቢያስብና የተለያዩ አገር በቀል የሆኑ ሙያዎችን መቅሰም የሚችሉበትን አጋጣሚ መፍጠር ቢችል አገር ከዘርፉ ብዙ ማትረፍ እንደምትችል ለማሳየት ጭምር ነው።
በምዕራብ ሸዋ ባኮ ትቤ ወረዳ ተወልዳ ያደገችው ዲዛይነር ቅድስት፤ የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን ተምራ ያጠናቀቀቸውም በዚሁ በትውልድ ሥፍራዋ ነው። ከልጅነት ዕድሜዋ ጀምራ በውስጧ ያከማቸችውን ሙያ በፋሽን ዲዛይን፣ በእጅ ሥራና በከተማ ግብርና ሥራ ላይ አውላለች። የስኬት ደረጃው የተለያየ ነውና ሰዎች በውስጣቸው ያላቸውን ዕውቀትና ችሎታ አውጥተው መጠቀም ከቻሉ ውጤታማ መሆን የሚያስችላቸውና ይህ በራሱ ስኬት እንደሆነም አምናለሁ ትላለች።
‹‹ዕውቀት ሌባ የማይሰርቀው ሀብት ነው›› እንደሚባለው ለቤተሰቡ አራተኛና የመጨረሻ ልጅ የሆነችው ዲዛይነር ቅድስት፤ ካደጉበት ቤታቸው የሴት ወጉ ሆኖ ወደ ትዳር ዓለም በመቀላቀል የወላጆቿን ቤት በመተው ነገር ግን የቀሰሙትን ዕውቀትና ችሎታ በውስጧ ይዛ ወደ አዲስ አበባ ተጉዛ ኑሮን ጀመረች። በትዳር ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ከተማ ገብታ አራት ልጆች አፍርታለች። ልጅ ወልዶ በማሳደግ ሥራ ሴቶች ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዙ በመሆናቸው ረዘም ያለውን ጊዜ በቤታቸው ያሳልፋሉ። በመሆኑም ሰፊ ጊዜዋን በቤት ውስጥ በምታሳልፍበት ጊዜ ሁሉ ከወላጅ እናቷ የቀሰመችውን የእጅ ሥራ ዕውቀት በመጠቀም በርካታ ሥራዎችን መሥራት ጀመረች።
ዲዛይነር ቅድስት፤ ከወላጅ እናቷ ከወረሰችው አገር በቀል ከሆነ ዕውቀትና ሙያ የሚበልጥ ምን ሥራ አለ በማለት ይመስላል አገር በቀል የሆነውን ዕውቀት በዘመናዊ ስልጠና አጠናክራለች። ወደ ሥልጠና ማዕከል በመግባትም በፋሽን ዲዛይን ትምህርት እንዲሁም በከተማ ግብርና የከብት እርባታ ሥልጠና በመውስድ የምስክር ወረቀት አግኝታለች። ለእጅ ሥራው ግን ወላጅ እናቷ ካወረሷት በላይ ልዩ ሥልጠና አላስፈለጋትም። ይሁንና የእጅ ሥራ የሚፈልገውንና ከውስጥ ፍላጎት የሚመነጭ የፈጠራ ሥራ በማከል በርካታ የዕጅ ሥራዎችን መሥራት ጀመረች።
ወላጅ እናታቸው ክርና ኪሮሽ አገናኝተው ይሰሩ ከነበረው የአንገት ልብስ፣ ሹራብ፣ የአልጋ ልብስና ሌሎችም አልባሳት በተጨማሪ በአሁን ወቅት ዲዛይነር ቅድስት፤ የተለያዩ የክር ጫማዎችን በመጨመር በርካታ አልባሳትን በመሥራት ለገበያ ታቀርባለች።
በመኖሪያ ቤት በርከት ያሉና የተለዩ የእጅ ሥራዎችን በማምረት የምትታወቀው ዲዛይነር ቅድስት፤ ሞያውን በፍቅር ወዳው የምትሰራው ከመሆኑ የተነሳ በየጊዜው አዳዲስና ለየት ያሉ የፈጠራ ጥበቦችን ትጠቀማለች። ጥራት ያላቸውን ምርቶች በእጅ ብቻ በመሥራት ብዙዎችን አልብሳለች። ምንም እንኳን የመሸጫና የማምረቻ ቦታ እጥረት ያለባት ቢሆንም በመኖሪያ ቤቷ ውስጥ በማምረት በኦን ላይን ገበያ ትሸጣለች። ለኦን ላይን ሽያጩም የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ የሆኑትን ቴሌግራምና ፌስቡክን ትጠቀማለች። ከዚህ በተጨማሪም ሥራዋን የሚያውቁ ደንበኞች ቤት ድረስ ሄደው በትዕዛዝ ያሰሯታል።
ሥራው አዋጭና በተለይም በአሁን ወቅት ተመራጭ መሆኑን ዲዛይነር ቅድስት አንስታ ነገር ግን ሙያውን የሚያውቅና ሊሰራ የሚችል ሰው ባለመኖሩ ካለው ፍላጎት በታች እያመረተች መሆኑን ትናገራለች። በዋናነት ሥራው በእጅ የሚሠራ እንደመሆኑ ጊዜ የሚወስድ ነው። በተጨማሪ በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል እንደልብ የሚገኝበት ባለመሆኑ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የምትቀጥረው ባለሙያ ያጣች መሆኑን ታስታውሳለች። በዚህ ምክንያትም በትውልድ ቦታቸው በምዕራብ ሸዋ ባኮ ትቤ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ስድስት እናቶች በማሠልጠን ማምረት እንዲችሉና የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጋለች። ሥልጠናውን ያገኙት እናቶችም የክር ጫማዎችን እያመረቱ ይልኩላታል።
የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው እናቶች ከግል ሥራቸው በሚተርፋቸው ጊዜ የሚሰሩ ሲሆን ባመረቱት የምርት መጠን ይከፈላቸዋል። የሚፈለገውን ምርት ለማግኘት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብም እንዲሰሩ ታደርጋለች። ሙያው ያላቸው ሰዎችን በአቅራቢያዋ ማግኘት ያልቻለችው ዲዛይነር ቅድስት፤ በሥራ ከፍተኛ መዘግየት የሚፈጠር መሆኑን በቁጭት ትናገራለች። ችግሩን ለመፍታትም በዘርፉ ትምህርት ቤት ከፍታ ሥልጠና ለመሥጠት ጥረት ያደረገች ቢሆንም ሊሳካ እንዳልቻለና አሁንም ወደፊትም ፍላጎቷ መሆኑንም አንስታለች።
ከእጅ ሥራው በተጨማሪ በፋሽን ዲዛይን ሥራዋ የራሷን ዲዛይን በመፍጠር ከባህላዊ አልባሳት ጋር ቀላቅላ ትሠራለች። የተለያዩ የእጅ ሥራዎችን በኪሮሽ ሠርታም በብትን ጨርቅና በአገር ባህል አልባሳት ላይ ትቀላቅላለች። መጋረጃዎችና የአልጋ ልብሶችንም እንዲሁ በባህላዊ አሠራር ትሠራለች።
በየአካባቢው ሥራ አጥ ሆነው የተቀመጡ በርካታ እናቶችና አካል ጉዳተኞች ስለመኖራቸው ያነሳችው ዲዛይነር ቅድስት፤ እነዚህን ሰዎች በቀላሉ አሰልጥኖ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚቻልም ትናገራለች። የእጅ ሥራ የትምህርት ደረጃም ሆነ ምንም አይነት መስፈርት የሚጠይቅ ባለመሆኑና በመኖሪያ ቤታቸውም ሆነ በየትኛውም ቦታ ሆኖ መሥራት የሚቻል ሥራ በመሆኑ ፍላጎት ያላቸው ሰዎችን አሰልጥኖ የሥራ ዕድል የመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎትና ዝግጁነት አላት።
ዲዛይነር ቅድስት፤ ለምታመርታቸው የክር አልባሳትና የተለያዩ ጫማዎች ከምትጠቀመው ኪሮሽና የሹራብ መስሪያ ሽቦ በተጨማሪ የአንገት ልብስ ለመስራት ክንዶቿን ትጠቀማለች። በተጨማሪም ጣቶቿን በመጠቀም የተለያዩ ሥራዎችን ትሰራለች። የሚሰሩት አልባሳትና ጫማዎች ከክር እንደመሆኑ ክር በስፋትና በጥራት ማግኘት ያስፈልጋል። ነገር ግን የክሮቹ አይነት የተለያየ የጥራት ደረጃ ያላቸው በመሆኑ ጥራት ያለውን የክር አይነት እንደልብ ማግኘት የሚቸግር ስለመሆኑም ጠቁማለች።
የእጅ ሥራ ሲባል መጠሪያው እንደሚነግረን በእጅ ብቻ የሚሰራ ሲሆን ሰፊ ጊዜን ከመውሰዱም ባለፈ አይን ያፈዛል፤ ወገብ ያጎብጣል። በመሆኑም በእጅ የሚሰሩ የእጅ ሥራ አልባሳት ዋጋቸው ውድ ነው ይባላል ትላለች። ሆኖም ግን ዋጋው የሚባለውን ያህል አዋጭና አትራፊ እንዳልሆነና በሙያው ፍቅርና ይለመድ በሚል እየሰራች መሆኑንም አክላለች።
በክር የሚሰራ ጫማ ምን ያህል አገልግሎት ይሰጥ ይሆን የሚል ጥያቄ አጭሮብዎት ከሆነ ጠንካራ ስለመሆኑ ምስክርነት ሰጥታለች። ከጥንካሬው በተጨማሪም በቀላሉ ለማጽዳት የሚመችና ሶሉ ቢያልቅ እንኳን ሌላ ሶል ቀይሮ መገልገል ይቻላል። በዚህም ተቀባይነቱ የጎላ ነው። አልባሳቶቹም እንዲሁ ውበትን ከጥራት ጋር የያዙ ስለመሆናቸው ያስረዳችው ዲዛይነር ቅድስት፤ በተለይም የእጅ ሥራውን ከአገር ባህል ጋር ቀላቅላ ለመሥራት በቅድሚያ ለግሏ የሠራችውን ልብስም ለብሳ ፎቶ በመነሳት በማህበራዊ ሚዲያ ለዕይታ ታበቃለች። ሰዎችም የወደዱትን መርጠው ያዛሉ። በዚህ መንገድ ከበርካታ ሰዎች ጋር መድረስ ችላለች።
የግብርና ሥራ እጅግ አድካሚ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን ከውጣ ውረዱና ከድካሙ ይበልጥ በመሥራት የሚገኘውን ደስታና ውስጣዊ እርካታ በማስበለጥ ዲዛይነር ቅድስት፤ በከተማ ግብርና ተሰማርታ ከብት ታረባለች። የከብት እርባታውን ደከመኝ ሰለቸኝ ከማይሉት ወላጅ አባቷ ያገኘች ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ ሰሚት አካባቢ በማህበር በመደራጀት ከወረዳው ባገኙት ቦታ ላይ ከብቶችን በማርባት ወተት ለሕጻናት ታቀርባለች። በዋናነት ወደ ከብት እርባታው የገባችውም ሕጻናት ንጹሕ ወተት ማግኘት አለባቸው በሚል ሀሳብ ነው።
ሁለት ላሞችን በብድር በመግዛት በከተማ ግብርና ከብት እርባታውን የጀመረችው ዲዛይነር ቅድስት፤ በአሁን ወቅት ጊደሮችን ጨምሮ አሥር ላሞች አሏት። ወተት ከሚሰጡት ላሞችም በቀን በአማካኝ 50 ሊትር ወተት ይገኛል። ወተቱንም በአካባቢያቸው ለሚገኙ ሕጻናት የሚቀርብ ሲሆን ሰዎች በመኖሪያ ቤቷ እየመጡ ይገዛሉ። ከፍተኛ የሆነ የወተት ፍላጎት መኖሩን ያነሳችው ዲዛይነር ቅድስት፤ በቀጣይም ዘርፉን አጠናክሮ በመቀጠል የወተት አቅርቦቱን ካለው ፍላጎት ጋር ለማጣጣም ፍላጎት አላት።
በከብት እርባታ እንዲሁም በፋሽን ዲዛነርነትና በእጅ ሥራ ሙያ የምትተጋው ዲዛይነር ቅድስት፤ ዛሬ ላይ ለደረሰችበት ደረጃ የባለቤቷና የወንድሟ እገዛ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን ትናገራለች። ለሥራዋ ከፍተኛ እገዛ ከሚያደርጉላት ባለቤቷና ወንድሟ በተጨማሪ በከብት እርባታው ለሁለት ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረች ሲሆን በእጅ ሥራው ደግሞ ስድስት በድምሩ ስምንት ሰዎች በሥሯ እንዲሰሩ ማድረግ ችላለች።
የዘርፈ ብዙ ሙያ ባለቤት የሆነችው ዲዛይነር ቅድስት ያለመሰልቸት በሥራ የምትተጋና ጠንካራ ሴት ነች። በቀጣይም የእጅ ሥራውን በስፋት ለማምረትና ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል እሷን የመሳሰሉ በርካታ ባለሙያዎች መፍጠር እንዳለባቸው ታምናለች። በመሆኑ ትምህርት ቤት ከፍታ የእጅ ሥራ ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች፣ እናቶችና አካል ጉዳተኞችን የማሰልጠን ፍላጎት አላት።
ከዚሁ ጎን ለጎንም በእጅ ሥራው ዘርፍ አገርን የማስተዋወቅ ተስፋ ሰንቃለች። በተለያዩ አገራት የአገር ባህል አልባሳት የሚተዋወቀውን ያህል የእጅ ሥራዎቿን በማስተዋወቅ አገርን የሚጠቅም ሥራ የመሥራት ራዕይ አላት። እኛም ዕቅዷ እንዲሳካ በመመኘትና ጥረቷን በማድነቅ አበቃን!
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2014