ኢትዮጵያውያን የህልውናውን ትግል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት አንድ ክንድ፣ አንድ አፍና ልብ ሆነን ተነስተናል። የአሜሪካንና የምእራባውያኑ መቅበዝበዝ ግን እንደቀጠለ ነው። አሸባሪው ትህነግ ታርዶ ሳህን እንደተደፋበት ዶሮ እየተንደፋደፈ ይገኛል።
አቅሉን ስቶ የሚወራጭ ነገር በእርግጥ ጉዳት ማድረሱ የማይቀር ነው። ሳያውቅ በገባበት ቀለበት ውስጥ የሚገኙ ንፁሃንን በግፍ እየረሸነ መሆኑን ሰምተናል። ቡድኑ ግብሩ ከፍጥረቱ ጀምሮ ይሄ ነው። ምንም አዲስ ነገር የለውም።
በጅምላ መግደል፣ ህዝብን ማናከስና በዚያ ላይ ተረማምዶ የስልጣንና የዘረፋ ጥሙን ማርካት። አሁንም ይሄንኑ ለመፈፀም ነው አቅሉን ስቶ እንደ እብድ ውሻ ያገኘውን የሚነክሰው። በእርግጥ የአሁን መንፈራገጡ ካለፉት ዘመናት የተለየ ነው። ኢትዮጵያውያን አንቅረን ተፍተነዋል።
ከጫንቃችን ላይ አውርደን ላይመለስ ልንቀብረው በአንድነት ቃል ገብተናል። አሸባሪው ትህነግ የቫምፓዬር ጥርሱን አሹሎ የአማራን ህዝብ ለመበቀል ሲመጣ በንፁሃን ገበሬው ምድር ላይ እራሱ ትቢያ ሆኖ እንደሚቀር አላወቀውም ነበር።
የጦር ግንባር እውነታው የሚያሳየን ይህንኑ ነው። በየደረሰበት ጠላት እያፈራ የቀደመ ታሪኩን በደንብ የማያውቁትን ንፁሃን “ስጥንናውን” እያሳየ መውጫውን እያጠበበ ይገኛል።ሸዋ፣ ጎንደር ጎጃምና ወሎ ተቆጥተዋል። አፋር ጥርሱን ነክሷል። መላው ኢትዮጵያዊ በፕሮፓጋንዳ የሚነዛውን ወሬ “አባ ከና ሳይል” ወደ ጦር ግንባር እየገሰገሰ ነው። በየአቅጣጫው እየተመመ ነው።
ላይጨርሰው የነካካው ህዝብ ሞቱን ሊያፈጥንለት ተማምሏል። ኢትዮጵያ ሳትሆን የቡድኑ እኩይ አላማ አስፈፃሚዎች ግንባር እንደሚፈራርስ ግልፅ ነው።“ላያዛልቅ ፀሎት ለቅስፈት” እንደሚባለው የአገራችን ብሂል “በአንድ ሰሃን ካልበላን” ያሉት አሸባሪዎቹ ሸኔና ትህነግ መሬት ላይ ሳይሆን በነጮቹ ልብና በማህበራዊ ድረ ገፅ ላይ ብቻ እየተተራመሱ ህዝብን ለማሸበር ሙከራ እያደረጉ ይገኛሉ። ግንባር ላይ ያለው እውነት ግን ለየቅል ነው።
አሸባሪው ትህነግ ማጣፊያው አጥሮታል። ምን እነሱ ብቻ። አለቆቻቸውም ደንግጠዋል። ለዚያ ነው የሳይበርና የፕሮፓጋንዳ ጦርነቱን በማህበራዊ ሚዲያና በሚዘውሯቸው የመገናኛ ብዙሃን ዘንድ ያደረጉት።
ከሰሞኑ ጥምር የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ያወጣው ሪፖርት እነ ፊልትማንን አስደንግጧል። ከአሸባሪው ትህነግ ውጪ በኢትዮጵያውያን ላይ የግፍ በትሩን ያነሳ ኃይል እንደሌለ ተረጋግጧል። ቀድሞውኑም ልባቸው የነገራቸው እውነት ሌላ ቢሆንም እንደፈረስ የሚጋልቡትን ትህነግ ቤተመንግሥት ድረስ አዝለው ለማስገባት ቆርጠው ስለተነሱ እንጂ እውነቱ ተሰውሮባቸው አይደለም።
ለዚህም ነው የቻሉትን ሁሉ ነገር ተጠቅመው ህዝቡን ማወናበድና ማሸበራቸውን የቀጠሉበት። የመገናኛ ብዙሃኖቻቸው መንግሥትን የሚያሳጣ መስሎ ከታያቸው “ከአሸዋ ውስጥ” መርፌ ፈልገው ያገኛሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ “እኛ ስንገፋ በስልክ ጥሪ ያጨናንቁናል እነሱ ሲገፉ አንድ እንኳን ጠያቂ የለም” የሚለውን የሰሞኑ የግርምት ንግግር የዚሁ እውነታ አካል ነው ።
አሜሪካ አይኗን በጨው አጥባ ከአሸባሪው ትህነግ ጎን ከኢትዮጵያውያን በተቃራኒ ቆማለች። ከሰሞኑ ለእጅ መጠምዣነት የምትጠቀምበት ዳረጎት ከሆነው “አጎአ” ኢትዮጵያን መሰረዟን አሳውቃለች። የጦር መሳሪያ ግዢ እገዳውንም እንደዛው። ማእቀብ መሆኑ ነው። እጅ መጠምዘዣ። እኛ ኢትዮጵያውያን ምእራባውያኑ ከሚሰፍሩልን ዳረጎት በላይ የአሸባሪዎቹ ግፍ ከአንገታችን ድረስ ሞልቶ እንደፈሰሰ ግን የተገነዘቡት አይመስለኝም።
ሁሉም ዜጋ በአንድነት “በቃኝ” ብሏል። ሰይጣንን የሚያስቀናው “ትህነግ” ለመደምሰስ መውዜሩን እያዘጋጀ ነው። ይህን ግን ነጮቹ የተረዱት አይመስልም።መሬት ላይ ያለውን እውነት እኩይ ዓላማ ይዘው ከሚንቀሳቀሱ የመረጃ ቀበኛ አክቲቪስቶች እኩል እያዛቡ ሽብር በመፍጠር ላይ ይገኛሉ።
የሰሞኑ የአሜሪካ ኢምባሲ ለዜጎቹ ያስተላለፈው የስጋት መልእክት ይሄንኑ የሚያሳይ ነው። መላው ዜጋ ግን ምእራባውያኑ፣ አሜሪካም ሆኑ የትህነግ የማህበራዊ ድረ ገፅ ፕሮፓጋንዲስቶች “ነጭ ውሸትን” በሚገባ ተረድቶታል። በአይን ጥቅሻ ሳይቀር ይግባባል። እጃቸውን እንደማይሰበስቡም እናውቃለን። ለዚያ ነው በቀላሉ ለሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ፊት አንስጥ እያልን በተደጋጋሚ የምንጮኸው።የኢትዮጵያ ሰራዊት ግንባር ላይ እየተዋደቀ ነው። ይዘግይ እንጂ ድሉ ከእውነት ጋር ለተሰለፈው ኢትዮጵያዊ ነው።
የአሸባሪው ትህነግ ተቅበዝባዢ ሠራዊት ሰተት ብሎ ወጥመድ ውስጥ ገብቷል። ደጀኔ ከሚለው አካባቢ በብዙ እርቀት ላይ ነው የሚገኘው። ይሄ ለኛ ድል ነው። ሊበቀለን አሰፍስፎ የመጣን ጠላት በግንባሩ እሳት መልቀቅ ከሕሊናችን ጋር የሚጋጭ አይደለም። የሞራል ልዕልናው እኛ ጋር ነው። በእርግጥ ጠላት በህዝባችን ላይ ያላሰብነው ግፍና መከራን አውርዶበታል። ይህ ቀን ግን መልሶ ላይመጣ ዳግመኛ ያበቃል። የመጨረሻዋን መከራ ብንቀበልም የመጨረሻው ድል ግን የኛ ነው።
የጥንቃቄ መልእክት ነጮቹ አለቆቻቸውም ሆነ የትህነግ አክቲቪስቶች ተናበዋል። በጦር ግንባር ያጡትን ድል በፕሮፓጋንዳው ለማካካስ፣ ህዝብን አሸብሮ በሠራዊቱ ላይ አመኔታ እንዲያጣ እየሰሩ ነው። እውነታውን ለማወቅ የቅርብ ጊዜውን ማስረጃ ማየት ብቻ በቂ ነው።
የዓለም አቀፉ ጥምር የሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን በማይካድራ እንዲሁም በተለያዩ ስፍራዎች በአማራ ህዝብ ላይ “የዘር ማፅዳት” ጭፍጨፋ የፈፀመው ትህነግ መሆኑን ይፋ ቢያደርገም ማእቀብ የጣሉት፣ በመገናኛ ብዙሃን ላይ እጃቸውን የሚጠቁሙት ግን እኛ ኢትዮጵያውያን ላይ ነው።
ከሰሞኑ የአሜሪካው ልዩ ልኡክ ጄፍሪ ፊልትማን “እና በ1983 ትህነግን ኢትዮጵያን እንዲቆጣጠር አላገዝንም” የሚል አስቂኝ ኑዛዜውን ነግሮናል። ቅኔውን ስንፈታው እንዲህ የሚል ነው። “አሁንም እንደ ፈረስ የምንጋልባቸው ባንዳዎች ኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ እንዲወጡ የማንፈነቅለው ድንጋይ የለም” የሚል ነው ። እኛ ደግሞ ይሄን እንላለል “ህዝብ በተዛባ መረጃ እንዳይሸበር።
ግንባር ላይ ያለው እውነታ የአሸባሪው ትህነግና የቡድኑ አባላትን መቃብር የሚያፋጥን ድል እንጂ በማህበራዊ ድረ ገፅ እንደሚነዛው ሽብር አይደለም” ዜጎች ይሄን ካደረጉ ጦርነቱ ካሰብነው ጊዜ በፈጠነ በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት ይደመደማል። ጠላቶቻችንም አፍረው “ጭድ ያክላሉ” ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2014