በጎጥ በረት ውስጥ የተፈለፈለውና የጎሳ ጡጦ ጠብቶ ያደገው አሸባሪው የህወሓት ቡድን የማእከላዊ መንግሥቱን ስልጣን በተቆጣጠረበት ሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ አረመኔና ጨካኝ መሆኑን የሚያስመሰክሩ በርካታ ጥፋቶችን ፈፅሟል።እንደመዥገር ተለጥፎ የኢትዮጵያን ደም በመምጠጥ በሃብት ላይ ሃብት አግበስብሷል።
በጎሰኝነትና ጎጠኝነት አስተሳሰብ በጠበበ ፖለቲካ የተካኑት የአሸባሪው ህወሓት አባላትና ጋሻጃግሬዎቻቸው የሃብት ምንጭም ከታታሪነት እና ከፈጠራ ጋር ምንም ዝምድና የለውም። የናጠጡ ባለሃብት የሆኑት በሌብነት ነው። ቡድኑ በየፈርጁ የሚፈጽመው ሌብነት በድብቅ የሚከወን አይደለም።ይልቁንም በጠራራ ፀሐይ ‹‹ህግን›› ተገን ያደረገ ነው።ከዋና ዋና የሌብነት መሠረቶቹ መካከል ደግሞ እርዳታ፣ ፕራይቬታይዜሽን፣ የመንግሥት ጨረታ፣ ተፈፃሚ የማይሆኑ ፕሮጀክቶች፣ የባንክ ብድር ይጠቀሳሉ።
አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሃብት ከዘረፈባቸው በርካታ መንገዶች አንዱ እርዳታ አንዱ ነው።እርዳታ ለአሸባሪው ህወሓት መክበሪያው ነው። ወያኔ ከበረሃ ወጥታ አዲስ አበባ እንድትገባና በእግሯ እንድትቆም ያደረጋት በድርቅ ለተጎዳ ሕዝብ የመጣ እርዳታ ነው።
ወያኔ ለህዝብ የመጣን እርዳታ እህል ሳይቀር የሚዘርፍ ሌባ፣ዘራፊና በቅጥፈት የተሞላ የማፊያ ድርጅት ስለመሆኑ ዋነኛ ማሳያ ደግሞ እ.ኤ.አ በ1984 የተከሰተውና በወቅቱ የቢቢሲው ጋዜጠኛ ሚካኤል ቡርክ ‹‹በመሬት ላይ ለሲኦል የቀረበ ‹‹the closest thing to hell on Earth›› ሲል የገለፀው ረሃብ ዋነኛ ማሳያ ነው።
በወቅቱ የወያኔ አባላት በዚህ ደረጃ አሰቃቂ ሆኖ የተገለፀውን ረሃብና የረኃብ ሰለባዎች ወደ ጎን በመተው ለነብስ ማዳኛ የመጣውን የሰብአዊ እርዳታ እህል ከታለመለት ዓላማ ውጭ ከዓለም አቀፍ ለጋሾችና አበዳሪ ድርጅቶች ጋር በመሞዳሞድ ለጦር መሳሪያ ግዥና ለግል ጥቅም አውለውታል።
ይህንንም የቀድሞ የማእከላዊ አባላቱ ሳይቀር በተደጋጋሚ በግልፅ በአደባባይ መስክረዋል።ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውትም የዘረፋ ቅሌቱን ለዓለም አጋልጦታል።ፕሮፌሰር ሀሰን ሰይድ ‹‹መንግሥታዊ ጥቃት በኢትዮጵያ፣ ሰብአዊ እርዳታ እና ሙስና›› በሚል ርዕስ ባሰናዱት መጽሐፍ በጥልቀት አትተውታል።
ቡድኑ ጫካ በነበረበት ጊዜ የጀመረው የዓለም አቀፍ የእርዳታ ስርቆት፣ ዘረፋና ሙስና የማይላቀቀው መናጢ አመል ሆኖበት በስልጣን በቆየባቸው ሃያ ሰባት ዓመታት ለምግብ፣ለመጠጥ ውሃ፣ ለመድኃኒትና ለትምህርት እየተባለ ወደ ኢትዮጵያ የሚፈሰውን እርዳታ ቅርጥፍ አድርጎ በልቷል።
አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሃብት ከዘረፈባቸው በርካታ መንገዶች ሌላኛው ፕራይቬታይዜሽን ነው።በመሰረቱ የፕራይቬታይዜሽን ዓላማ በመንግሥት ይዞታነት የተያዙ የማምረቻና የንግድ ተቋማትን ይበልጥ ውጤታማ ነው ተብሎ ወደሚታሰበው የግል ኢኮኖሚ ዘርፍ በማዛወር የገበያ ውድድር እንዲበዛና ምርታማነት እንዲያድግ ማድረግ ነው። በወያኔ ዘመን ግን በኢትዮጵያ የነበረው ሃቅ የዚህ ተቃራኒ ነው።
አሸባሪው ቡድን ፕራይቬታይዜሽንን ለሁለት ዋነኛ ዓላማዎች ተጠቅሞበታል።አንደኛ የተመረጡ ሃብታሞችን ይበልጥ ሃብታም ለማድረግ፤ ሁለተኛ ደግሞ ከብድር ስርዓት ጋር በማቀናጀት ቀድሞ የረባ ንብረት ያልነበራቸው የሥርዓቱ ደጋፊዎችን በፍጥነት ሃብታም እንዲሆኑ ለማስቻል።
የወያኔ አገዛዝ ፕራይቬታይዜሽንን ተጠቅሞ ዘረፋና ሕገወጥ የሃብት ክፍፍል ስለማድረጉ ለመረዳትም በወቅቱ ከመንግሥት ወደ ግል ይዞታነት ከተሸጋገሩት መካከል አብዛኞቹ የተዘዋወሩት ለጥቂት ግለሰቦች መሆኑንም ማስታወስ በቂ ነው።
አሸባሪው ህወሓት በዘራቸው የሚመርጣቸው የሥርዓቱ ተጠቃሚዎችም በፕራይቬታይዜሽን ሰበብ በቢሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያን ሃብት መጠዋል።በዚህ ገንዘብም በአዲስ አበባ ሌሎች ከተሞች እጅግ ዘመናዊ ህንፃዎችን ገንብተዋል።ህንፃ በመደርደርም ኢትዮጵያ በእርግጥም ያለፈላት እንዲመስል አስመስለዋል።
ከሃያ ዓመታት በፊት ያልነበራቸውን ሃብት አካብተዋል።እነዚህ ጥቂት ግለሰቦች በሃብት ላይ ሃብት ሲያካብቱ በርካታ ድሆች ይበልጥ ደህይተዋል። ከይዞታቸው ተፈናቅለው በራሳቸው መሬት ላይ ለሚገነባ ህንፃ የቀን ሠራተኛ ሆነዋል።ልመና ውስጥ ገብተዋል።
ለሌላኛው የወያኔ ሰዎች የሃብት ምንጭ ጨረታ ነው።ለወያኔዎች ጨረታ የሃብት ማካበቻ መሳሪያ ነው።መብያ ነው።መበልፀጊያም ማጥፊያም ነው። ትላልቅ የመንግሥት ጨረታዎች ለውጭ አገር ኩባንያዎች ሲሰጥ በርከት ያለ ኮሚሽን ለወያኔ ባለሥልጣኖች የሚሰጥ መሆኑ ሃሜት ሳይሆን ራሳቸውም በተጣሉ ጊዜ የሚናገሩት ነው። ግድብ፣ መንገድ፣ ድልድይ፣ ኮንዶሚኒየም፣ ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ ወይም ሌላ ግንባታ በተሰራ ቁጥር ወያኔዎች ኪሳቸውን ያደልባሉ። አጫፋሪዎቻቸው ወደ ሰማይ ይመነጠቃሉ።
የባንክ ብድር በመውሰድና የውጭ ምንዛሪን በመሸሽና በማስቀረትም ኢትዮጵያን ክፉኛ አቁስለዋል።በዘመድ አዝማድ በመቧደን በንግድ ሽፋን አስመጪም ላኪም በመሆን ለአንድ ታዳጊ አገር እጅግ ወሳኝ ምርኩዝና የኢኮኖሚ ዋልታ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ መዝብረዋል።
በኢትዮጵያ ዙሪያ ገባ የድንበር ከተሞች ላይ በከፍተኛ የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ተሰማርተው፣ ያለምንም ቀረጥና ታክስ ወደ ውጭ አገር ምርቶችን በመላክ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ወደ አገር ቤት ከማምጣት ይልቅ በተለያዩ የአውሮፓና የኢሲያ አገራት ባንኮች አከማችተዋል።
ተፈፃሚ የማይሆኑ ፕሮጀክቶች ማዘጋጀት አሸባሪው ህወሓት በስልጣን በቆየባቸው ሃያ ሰባት ዓመታት ለዝርፊያ እንዲመቸው ከሚጠቀምባቸው ዋነኛ የዝርፊያ ታክቲኮች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነው።ለዚህ ደግሞ ሜቴክ ወይንም ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሚል ተቋም በማደራጀት የፈፀሙትን ዘግናኝ ዘረፋ ማስታወሱ በቂ ነው።
ወያኔዎች በዚህ ተቋም አማካኝነት በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ጠቅልሎ በመያዝ፣ ተፈፃሚነት የሌላቸውን እቅዶች በማወጣትና በከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖቹ በመቆጣጠር የህዝብን ሃብት ያለተቀናቃኝ መዝብረዋል። ከውጭ ሀገር ለሚገቡ ማሽነሪዎች ግዢዎች እንዲሁም ለህንጻዎችና ሆቴሎች ለቢሮና ለእንግዳ ማረፊያ በሚል የኪራይ ስም በቢሊዮን ብር ወጪ አድርገዋል።
በተቋም ውስጥ የኃላፊነት ቦታዎችን የተቆጣጠሩት ግለሰቦች በዘር የተመዳደቡ የህወሓት አባላት መሆናቸው ደግሞ በተቋሙ የኦዲት ሥራ ለመስራትና የንብረት ቁጥጥር ለማድረግ አስቸጋሪ እንዲሆን ምክንያት ነበር።ይህ እንደመሆኑም ኢትዮጵያ በወያኔ መዥገሮች ብዙ ተመጣለች።
የአሸባሪውን ቡድን ሌቦች ልዩ የሚያደርጋቸው ደግሞ በዝምታ ውስጥ የሚሰማ የህዝብ ጩኸት ሲሰሙና ስርዓቱን የማይደግፍ ሲመለከቱም የሀገር ጠላት በማስመሰልና በተለመደው ፍረጃቸው የድሮ ስርዓት ናፋቂ፣ ነፍጠኛና ልማት አደናቃፊ የሚል ቅጽል ስም ማውጣታቸው፤ አለፍ ሲልም እስር ቤት መወርወራቸው ነው።
የቡድኑ አባላት የፖለቲካው ትኩሳት ከፍ ብሎ ሲሰማቸውም የፀረ ሙስና ተረት-ተረት ሲደሰኩሩ መሰማታቸውም ሌላ መገለጫቸው ነው።ሌቦቹ ስለ ሙስና አስከፊነት የመናገሩን ሞራል ከየት እንዳመጡት በሚያስገርም፣ በሚያስደነግጥና በሚያስተዛዝብ መልኩ ዓይናቸውን በጨው አጥበው ኢትዮጵያ እንዴት በሙስና እንደተከበበች ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣሉ።
‹‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ! እንዲሉ ከሳሽም፣ ተከሳሽም ሆነ ዳኛው አንድ አካል ነው። በዚህ የተነሳ ሌቦቹን በአደባባይ ከመንጎማለል ያስቀራቸው አልነበረም።ጸረ-ሙስና በሚሉት ድርጅታቸውም አፈንጋጮችን ለመምቻ ሲገለገሉበት አሳይተውናል።
የቡድኑ ዓይን ያወጣ አፀያፊ ተግባርም አምባገነኑ ሥርዓት በኢኮኖሚ እንዳይዳከም የጀርባ አጥንት ሆኖለታል።ኢትዮጵያዊ የሆነውን ሀገር ወዳድነታችንን፣ መተሳሰባችንንና መከባበራችንን ሳይቀር ሲፈትነው ቆይቷል።ከዚህ ፍትሃዊነት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ግጭቶችና ግለኝነት መንስኤ ሆኖ ታይቷል።
በኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ስልጣኑን ከተነጠቀ በኋላም የስልጣን አባዜ የሚያመጣው እብደት ከእኛ በላይ ላሳር በሚል ትእቢት ተወጥሮ እኩይ ምግባሩን ሲያስቀጥል ቆይቷል።በተለይም ኢትዮጵያን መምራት የምችለው ብቸኛ ድርጅት ‹‹እኔ ነኝ›› በሚል መረጃ እያምታታና በሚዲያ የበላይነት ራሱን የተሻለ አድርጎ ሲያቀርብም ቆይቷል።
የሽብር ቡድኑ ከዚህ የባንዳ ተግባሩ ባሻገር ኢትዮጵያን የሚፈልጋት እርሱ እስከገዛትና የትግራይ ብሄርተኝነት የበላይነትን ይዞ እስከቀጠለ ብቻ በመሆኑ ለ20 አመታት ነፍሳቸውን ሰጥተው ሲጠብቁት የነበሩ የሰሜን እዝ አባላትን አስከፊ በሆነ መልኩ በመጨፍጨፍ እና በማዋረድ በኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ላይ ጥቃት በመሰንዘር ግልፅ ጦርነት ከፍቷል።
የሽብር ቡድኑ የአገርን ሉዓላዊነት ከመድፈር ባሻገር የህዝብ ሃብት እና ንብረት የሆኑ ትላልቅ ሀገራዊ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን አድርሷል።ኢትዮጵያም በቡድኑ እብሪትና ጥቃት ምክንያት ሳትፈልግ ጦርነት ውስጥ ለመግባት ተገዳለች።በልዩ የሰላም ማስከበር ኦፕሬሽን እና በመከላከያ ሰራዊታችን አስደናቂ ብቃት አማካኝነት የሽብር ቡድኑን ወደ በረሃ በማስገባት ትግራይን በቁጥጥር ስር ማድረግም ችላለች።
ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ህዝብ በማዘንና የጥሞና ጊዜ ለመስጠት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ውሳኔ ቢያስተላልፍም የሽብር ቡድኑ በአንፃሩ የተኩስ ማቆም ፍላጎት እንደሌለው በተግባር በማሳየት፣ በጦርነቱ ገፍቶበታል።በአዲስ መልክ ሂሳብ አወራርዳለሁ ብሎ መጥቷል።
ጦርነቱን ወደ አፋርና ወደ አማራው ክልል በመግፋት ለበርካቶች እልቂት ምክንያት ሆናል።ወጣት፣ ሴቶች፤ ህጻናትና አዛውንቶችን ጨፍጭፏል። ደፍሯል።ቅርሶችን ሰርቋል።በድሃ ህዝብ የተሰሩ ክሊኒኮች፤ ሆስፒታሎች ዘርፏል።አቃጥሏል። አውድማል።በርካቶችን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ብሎም ሰው ሰራሽ ርሃብ እንዲከሰት አድርጓል።
ትላንት ለእርዳታ እህል እጁ ያልተሰበሰበ ቡድን ዛሬ ደግሞ አብሲት እየሰረቀ ይገኛል።የሌብነት ልክፍት – ከእርዳታ እህል እስከ ሊጥ ቀጥሏል።ቡድኑ በወረራቸው አካባቢችም እንስሳትን እየገደለና እየሰረቀ ይገኛል።በድርቅ ለተጎዳ ሕዝብ የመጣ እርዳታን ለእኩይ አላማው እየተጠቀመ፣ ሌላው ቀርቶ ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች የደረሰ አዝመራ ሳይቀር አጭዶ ሲሰርቅ ታይቷል።የእርዳታ መኪኖችን እየዘረፈ፣ ወታደር ማመላለሻ እያደረገ ነው።
የአሸባሪው ቡድን አባላት የሌብነት ተግባር ቡድኑ ለኢትዮጵያ ምን ያህል ስር የሰደደ ሰይጣናዊ ጥላቻ እንዳለውና በትእቢት የተሞላ እንደሆነ የሚመሰክር ነው።ይሁንና ኢትዮጵያውያንም ይህንን ቡድን ከትላንት በተሻለ ዛሬ ይበልጥ አውቀውታል።ፍላጎቱ ምን እንደሆነ አብጠርጥረው ተረድተውታል።
‹‹በማንኛውም ግዳጅ ወይም ተግባር የላቀ ውጤት›› በሚል እሴት የተገነባው፣በየትኛውም ሁኔታ በማንኛውም የአየር ፀባይ ማንኛውም ግዳጅ በውጤት የማጠናቀቅ አንፀባራቂ ድል የማስመዝገብ አቋምና አቅም ያለው የኢትዮጵያ ሰራዊትም የሽብር ቡድኑን እያንኮታኮተው ይገኛል።
የኢትዮጵያ ህዝብም ዳር እስከ ዳር በአገር ፍቅር ስሜት የአሸባሪውን ቡድን ግብአተ መሬት በማፋጠን ሂደት ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጎንና ከሰንደቅ ዓላማ አጠገብ ቆሟል።ለዜግነትና ለአገር ክብር በኢትዮጵያዊነት ስሜት አንድ ላይ እየታገለ ይገኛል።ኢትዮጵያም አሸናፊ ሆና መውጣቷ እርግጥ ነው።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014