ጥቅምት 24፤2013 የጎደፈ ታሪክ
ይህ ባንወደውም ፈፅሞ መርሳት የማንችለው እውነት፤ ባንፈልገውም በታሪካች ላይ በጥቁር ቀለም የተከተበ ሀቅ ነው።የኢትዮጵያ ጠላቶች እኩይ ምግባር የሚያሳይ ታሪክ።ተገልጦ ሲታይ ያደፈ፤ ሲነገር አሳፋሪ የሆነ ታሪክ እዚያ ልክ በዚህ ቀን ሆነ።አዎ ኢትዮጵያን በከዱ ግፈኞች ይህቺን ቅድስት አገር ባረከሱ ሴረኞች የተፈፀመ ጥቁር ታሪክ።
በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሆኖ በማያውቅ መልኩ በእናት ጡት ነካሽ ከሀዲያን እኩይነት ተግባር በእውን ታየ።በወጠኑት ድብቅ ሴራ በአገር መከታዎች ላይ የተፈፀመ ግፍ፤ በሕዝብ ላይ የተደረገ ደባ በሰው ልጆች የማይፈፀም አረመኔያዊ ተግባር ሆኖ በታሪክ እንዳይረሳ ሆኖ ተቀመጠ።
ይህ የጎደፈ ታሪክ በዚህች ቅድስት በሆነች አገር በግፈኞች እኩይ ተግባር ጥቅምት 2013 ዓ.ም ተመዘገበ።ለአገሩ ቀርቶ ለጎረቤት አገሮች መከታ የሆነ ሰላማዊ ሰራዊት፣ በሄደበት ሁሉ ጠላትን በማሳፈር ለአገሩ ድል የሚያበስረው መከላከያ በስሩ በተሰገሰጉ ክፉዓን ለዚሁ ሴራ ባዘጋጁዋቸው በዳዮች ባልጠበቀውና ለመገመት በሚከብድ ክህደት በግፍ ተረሸነ።
አብሮት የበላ ጓዱን ለአገሩ ክብር አብሮት የተሰለፈው ወገኑን እንዴት ሊጠረጥር ይቻለዋል።ለእነሱ አገር ማለት ምንም፤ ወገን ማለት ጠባብና እኩይ ምልከታ የሚለካበት መንደርተኝነት ሆነና ለነፃነታቸው የተዋደቀው ጦር ላይ እጃቸውን አነሱ።
ለዓመታት ከሌለው ላይ ቆጥቦ ትምህርት ቤት የሰራ ከሚጎርሰው ላይ ቀንሶ መሰረተ ልማት የገነባው እራሱን አሳልፎ እየሰጠ ከጠላት የተከላከለውን የሰሜን እዝ ውለታ በጭካኔ በክህደት ደመደሙት።አገሩን ከጠላት ሊጠብቅ ዱር ቤቴ ያለ፤ ለአገሩ ክብርና ነፃነት እራሱን ለመስጠት ዝግጁ በሆነው ጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደት በሴረኞች ተፈፀመ።
ሰራዊቱ በዚያው ቀን ላይ
ሲነገር የሚከብድ ግፍ የተፈፀመበት ሰራዊት አገር በጠላት እንዳትወረር ሲጠብቅ፣ የህዝብና የአገር ሉዓላዊነት እንዳይደፈር ሲከላከል ሁለት አስርት ዓመታት እዚያ አካባቢ ቆይቷል።እራሱን ለአገር ክብርና ፍቅር ከመስጠት ባለፈ በሰላሙ ጊዜ ደጀን የሆነውን ህዝብ ጉልበቱና ጊዜውን ሳይሰስት እንካችሁ እያለም ኃላፊነቱን በሚገባ ተወጥቷል።
በአዝመራ ወቅት አጭዶ በእርሻ ወቅት አይዞኝ ወገኔ ማለትና መርዳት አብዝቶ የለመደው ተግባሩ ነበርና በዚያ ቀን ይህ ተገበረ።የአካባቢው ገበሬ በምስራቅ አፍሪካ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ሰብሉን እንዳያወድምበት ስጋት ገብቶት ነበርና ህዝባዊ የሆነው ሰራዊት ጠመንጃውን አስቀምጦ ሰብል ሲሰበስብ ዋለ።
ይህን ማድረግ ለሰራዊቱ የቀለለው ተግባሩ ነበር።ምክንያቱም እርሱ ህይወቱን ለአገሬ እንኩ ያለ ከራሴ ይልቅ ለወገንና ለህዝቤ ያለውን ለመስጠት የማይታክተው ሰራዊት ነውና።ህዝባዊነቱንም በተግባር እያረጋገጠ የቆየም ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአገሩን ነፃነት ለማስከበር በቆራጥነት የቆመ፤ የህዝቡን ደህንነት ማረጋገጥ የዘወትር ተግባሩ ያደረገ ድል አብሳሪና ህዝባዊ ሰራዊት መሆኑ በብዙ መልኩም አሳይቷል።ከራሱ በላይ አገሩን ብሎ ኑሮው በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ያደረገው ለዘመናት ለአገሩ ዳር ድንበር መከበር መስዋዕት የሆነ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ዘብ የሆነ ሰራዊት ወገኑን በሰብል ስብሰባ በማገዝና አዝመራውን በመሰብሰብ ውሎውን አደረገ።
የግፈኞቹ ሴራ
ሰራዊቱ ህዝባዊ ባህሪ የተላበሰ ነበርና ወገኔ ብሎ መስክ ላይ አርሷአደሩን ለመርዳት ሳይሰስት ሲለፋ መዋሉ ግድ አልሰጣቸውምና ደክሞት አረፍ ሲል ለመውጋት አሴሩ።አገሬን ብሎ ለዓመታት ድንበር
በመጠበቅ መስዋዕት የሆነውን ለማጥፋት የክፋት መንገድ መዘርጋት ላይ ተጠመዱ።ይሄኛው ለወገን መከራ ለማራቅ ሲጥር እነዚያ ደግሞ ክፋት ውስጥ ውስጡን ሲጠነስሱ ለሴራቸውም የሚሆን መሰናዶ ሲያደርጉ ዋሉ።
የሰራዊቱን ትጥቆች ለመቀማትና የአገር መከላከያ ሰራዊቱን ለማፍረስ በማለም የአገር ክህደት ተግባራቸውን በስውር ወጠኑ።መገናኛዎች ቀድሞ ማሰናከል፤አንድነትና ግንኙነቱን ማፍረስ ጥቃት ሲከፍቱም አንዱ ከሌላው ጋር ፈፅሞ ግንኙነት እንዳያደርግ በዚህም እኩይ አላማቸው ይሰምርላቸውና የወጠኑት ሴራ ከግብ ይደርስላቸው ዘንድ አጥብቀው አሴሩ።ሊያደርጉ ያሰቡት ክፋት መተግበሪያ ቀን ለተንኮላቸው ፍፃሜ የሚሆን ምሽት ይህ እንዲሆን መርጠውት ነበርና መርዘኛ ሀሳባቸው በአገር ጠባቂው በወገን አኩሪው ሰራዊት ላይ ሊተገብሩ ተዘጋጅተው መጠበቅ ያዙ።
የከሀዲያን የክፋት ጥግ፤ ምሽት
ሰራዊቱ በእህል ስብሰባ ጉልበቱ ዝሎ ወገኖቹን ሲደግፍ ውሎ ለማረፍ ወደ ካምፑ ተመልሶ ጎኑን አሳረፈ።ይህ ጊዜ ነበር የክህደት መጨረሻ የጭካኔ ጥግ ላይ የደረሰ ስውር ሴራቸው መተግበር የጀመሩት።ጓዴ ብሎ ይጠብቀው ዘንድ ያመነው ያገሬ ልጅ ብሎ ሀሳቡን ያለጥርጣሬ የጣለበት ሴረኛ ዘግናኝ በሆነ መልኩ ታረደ።ለጠላት ያዘጋጀው አፈሙዙን ያለርህራሄ አብሮት ለዓመታት በተዋደቀ ጓዱ ላይ አዞረ፤በአረመኔነት ቃታውን በሰራዊቱ ላይ ሳበ።
አብሮ ግንባር ላይ የታገለውን ለአገሩ ዳር ድንበር መከበር ሳይሰስት የተፋለም ሰራዊት ጭለማን ተገን በማድረግ በሴራ የክፋት ጥግ ተገበሩበት።ሰራዊቱ ወገኑን ሊጠብቅ ጀርባውን በሰጠ፤ ሙሉ እምነቱን ጥሉ ጓዴ ባለው ሴራ ተጎነጎነበት።አገሩን ሊከላከል ከ20 ዓመታት በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሕይወቱን በአስቸጋሪ ሁኔታ ያኖረው ሰራዊት ባመነው እና እራሱን ለዓመታት በሰጠለት ተከዳ።
ቀድመው ውስጥ ውስጡን ለክፉ ዓላማና ተግባር ሲያሴሩ በቆዩን ለጭፍጨፋ በተዘጋጁ ግፋዋን ሰራዊቱ በጭካኔ በተኛበት ተጨፈጨፈ።ባመነው ተገደለ፣አብሮት በበላ ጓዱ በክህደትና በጭካኔ ታረደ።ያሳደገቻቸው እናታቸውን ጡት የነከሱ ባንዳዎች፤ ውድ አገራቸውን ለእኩይ ዓላማ የካዱ ክፉዎች፣ የተወለዱበት ምድር የጠሉ ሴረኞች የአገር መከታ የሆነውን መከላከያ ተዳፈሩ።
የሰራዊቱ ተጋድሎ
ከራሱ በላይ አገሩን የሚወደውና ስለ አገሩ ክብርና ሉዓላዊነት መስዋዕት ለመሆን ፈፅሞ ሰስቶ የማያውቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ባላሰቡትና ባልጠበቁት ሁኔታ ለዚያውም ወገኔ ባለው ጥቃት ተከፈተበት።አጠገባቸው ያለው ጓዳቸው በሌላ አገር በከዳ ሴረኛ ሲቀጠፍ አይተው እጅጉን ተቆጡ።በሴረኞች የተጠነሰሰው ሴራ ሲያዩ አመረሩ።
የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሴረኞቹን ጥቃት በተቻላቸው አቅም ለመመከት ጥረት ማድረግ ግድ ሆነባቸው።አገር የጣለባቸው አደራ የወገን ጦር የታጠቀው መሳሪያ ላለማስነጠቅ በአንድ ጎን እረሳቸውን ከጥቃት ለመከላከል ደግሞ ሌለው ግባቸው አድገው ጥቃቱን መከላከል ብሎም እራሳቸውን ለማዳን ተንቀሳቀሱ።
ወገን ነው ባሉት የተከፈተባቸው ጥቃት፣ጓዴ ባሉት ያዩት ክፋት የተቆጡት የዚያን ዕለት ቆራጦች የሰራዊቱን ትጥቅ ለማስነጠቅ ተጋደሉ።ብዙዎች የአገራቸውን ክብር ላለማስደፈር ተናነቁ።የሰራዊቱን ትጥቅ በሴረኞች ላለማስነጠቅ የአገራቸውን ክብር በከሀዲዎች ላለማስረከብ እስከመጨረሻው ተፋለሙ።በዚህም ብዙዎች የማይተካ ውድ ህይወታቸውን ቀድመው ባሴሩት የእናት ጡት ነካሽ ግፉዋን ተነጠቁ።
የህግ ማስከበር አዋጅ
የአገሪቱን ሉዓላዊነት ማስጠበቅ፣ የህዝቡን ሰላም ማረጋገጥ፣ ሰራዊቱን መታደግና የተቃጣበት ጥቃት የመከላከል ብሎም የህግ የበላይነት የማስፈን ኃላፊነት ያለበት መንግሥት የመከላከያ ሰራዊቱ በአገሩ ላይ የተቃጣው የከሀዲያን ጥቃት ያመክን ዘንድ ትዕዛዝ
አስተላለፈ።ህዝቡ የሰራዊቱ ደጀን ሆኖ ጠላት እንዲመክትና አካባቢውን ከሴረኞች ይጠብቅ ዘንድ አዋጅ አስነገረ።
ጥቅምት 25፤ 2013 ንጋት
የአገር መከታው ሰራዊት የሉዓላዊነት ክብር መጠበቂያው የሆነው መከላከያ በሴረኞች በግፍ መጨፍጨፉ ኢትዮጵያውያን ሰሙ።ይህን ጊዜ የአገራቸው መደፈር አስቆጣቸው፣የሰሜን ዕዝ ላይ የተቃጣው ጥቃት አስቆጫቸው።ይህ ቀን እልፍ ኢትዮጵያውያን ክህደት የሰሙበት ሚሊዮኖች የሰራዊቱን በግፍ መጨፍጨፍ ሰምተው ያዘኑበት ሆነ።
በአገሪቱ ላይ የተቃጣው ክህደት በኢትዮጵያ ላይ የተደረገው ድፍረት በሰሜን እዝ የሰራዊቱ አባላት ላይ የተፈፀመው ሰቅጣጭ ጭፍጨፋ ህዝቡን አስቆጣ።በየአካባቢው አደባባይ በመውጣት በሰላማዊ ሰልፍ በሰራዊቱ ላይ ግፍ የፈፀሙትን አወገዘ።ከሰራዊቱ ጎን መሆኑን ገለፀ።በኢትዮጵያ አገሩ የመጣ ጠላት መቼም እንደማይታገስ በተግባር መግለፅ ጀመረ።
የሰራዊቱ የድል ግስጋሴ
የአገሩ ሉዓላዊነት መደፈር ያስቆጨው የሰራዊቱ በግፍ መጨፍጨፍ ያስቆጨው ሰራዊት መንግስት ያዘዘውን የህግ ማስከበር እርምጃ መውሰድ በጀመረ በቀናት ውስጥ አስደናቂ ድሎች ማስመዝገብ ጀመረ።የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከዳር ለሰራዊቱ ደጀን መሆኑን በተለያዩ ድጋፎች አረጋገጠ።ሰራዊቱ እራሱን በአስደናቂ መልኩ መልሶ በማደራጀት የአገር ህልውና የተዳፈረውን የውስጥ ከሀዲ ሴራ ለማክሸፍ ታላቅ ተጋድሎ ማድረጉን ቀጠለ።
አገሪቱን ለማተራመስና የህዝቡን ሰላም ለመንሳት ብሎም የአገር ህልውና ለማሳጣት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በተለያዩ አቅጣጫዎች ውጊያ የከፈተው ቡድን በሰራዊቱ ክፉኛ ይመታ ጀመር።ሲጀምር የአገሪቱ መከላከያ ላይ እጁን ያነሳው ወንጀለኛው ቡድን በሰራዊቱ እየደረሰበት ባለው ሽንፈት ምክንያት በንፁኃን ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ማድረግ ተያያዘ።በዚህም ኢትዮጵያውያን እጅጉን ተቆጡ።ሰራዊቱም ሕዝብን ለማትረፍና ህገወጦችን ለመያዝ ለፍርድም ለማቅረብ ብርቱ ትግል አደረገ።
በተለያዩ አቅጣጫዎች አገር ለመናድ የከፈቱት ጦርነት በሰራዊቱ መልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ይከሽፍ ጀመር።ሁሌም ድል አብሳሪ የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እጅግ በፈጠነ የውጊያ ስልት ለዓመታት ሲዘጋጅ የቆየው የወንጀለኛው ቡድን ጦር መክቶ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተደራራቢ የድል ዜናዎችን አበሰረ።
የአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ለማፍረስ በሰሩ፣ የሰሜን ዕዝን በግፍ የጨፈጨፉ፣ በአገሪቱ ላይ ባሴሩና የኢትዮጵያን ሰላም ባደፈረሱት የቡድኑ ዋና ዋና መሪዎች እርምጃ ተወሰደ፣ በርካቶቹም በህግ ቁጥጥር ስር ዋሉ።ሰራዊቱ በቡድኑ ተዘርፈውበት የነበረውን መሳሪያ አስመለሰ። የግፈኞቹ መነሻ የሴረኞቹ መዳረሻ የሆነው ሁሉ በቁጥጥሩ ስር በማዋል የኢትዮጵያ ህዝብ የጣለበትን አደራ ተወጣ የቀሩትን የህግ ማስከበር ሥራዎቹ ላይ ቀጠለ።
ዛሬን በትላንት መነፅር
ዛሬም የዚህ ቡድን ሴራ ኢትዮጵያን ማመሱ ቀጥሏል።በምዕራባውያን ሴራ አፈር ልሶ የተነሳው ቡድን ጦር ሰብቆ ወገን መውጋቱን ሽብር አስፋፍቶ ኢትዮጵያን ማድማቱን ቀጥሎበታል።በደልና ክፋቱ በእጥፍ ጨምሮ ለአገር ህልውና አደጋ መሆኑን አባብሶ ቀጥሏል።ሁሌም አሸናፊ አሸናፊ የሆኑት የኢትዮጵያ ልጆች የዚህ ቡድን ሴራ በማክሸፍ እንዳይነሳ ለመቅበርና አገራቸውን ከተጋረጠባት አደጋ ለመታደግ ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ዛሬም እንደ ትላንቱ አሸናፊነት ልማድዋ ነውና አገሬ ጠላቶችዋን ድል ትነሳለች።የኢትዮጵያውያን ህብረት ጠንክሮ ጠላቶችዋ በልጆችዋ ክንድ ተደቁሰው ይከስማሉ።ይህች የተስፋዋ ምድር ኢትዮጵያ ዳግም ነፃነትዋን ታውጃለች፤ ዳግም ሰላምዋን ታረጋግጣለች ደግም ህዳሴዋን እውን ታደርጋለች።አበቃሁ፤ድል ለኢትዮጵያ አገሬ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014