ልክ የዛሬ ዓመት ጥቅምት 23 ለ24 አጥቢያ …. ከተለመዱት ሌሊቶች መሀከል አንዱ ነበር።እስከ ምሽት 5 ሰዓት ድረስ ፌስቡክ ላይ እንደለመድነው ከጓደኞች ጋር ትናንሽ ወሬዎች እያወራን አመሸን።5 ሰዓት ሲል ሁላችንም ስለተዳከምን እና ወሬውም ወደማለቁ ስለተቃረበ ወደ መኝታ ሆነ።ሰላማዊ እንቅልፍ መተኛት ተጀመረ።
ያ ሰላማዊ እንቅልፍ እንደ ወትሮው ጠዋት ድረስ አልቀጠለም። ንጋት 11 ሰዓት ገደማ አንድ ሰው ደወለልኝ። መቼም በዚያ ሰዓት ሰው ከደወለ በጎ ዜና እንደማይኖር ለመገመት የተለየ ተሰጥኦ አያስፈልግም።”ተጀመረ!” አለኝ።”ምኑ?” አልኩ በድንጋጤ።” ጦርነቱ!” አለኝ።ከዚያ በኋላ የነበረንን ምልልስ አላስታውስም። ብቻ አእምሮዬ በአንድ ጊዜ ሚሊየን ሀሳቦች ሲተራመሱበት እንደነበር ትዝ ይለኛል።
ተነስቼ ቴሌቪዠን ከፈትኩ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ እየሰጡ ናቸው፤ ይህም ሰበር ዜና በሚል ጽሁፍ ታጅቦ እየተደጋገመ እየተነገረ ነው። ሕወሓት የሰሜን እዝን አጥቅቷል፤ ስለዚህ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ምላሹን እንዲሰጥ ታዝዟል የሚል ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ።
ወደ ፌስቡክ ገባሁ። እንደኔው የደነገጡ ብዙኃን ብዙ እየቀበጣጠሩ ናቸው።እንደተባለውም ጦርነቱ ተጀምሯል።ውስጤን ስጋት ያዘው።ጦርነቱ ሀገራችን ላይ ሊያመጣ የሚችለው ጣጣ ወዲያ ይታሰበኝ ጀመር።በሰሜን ዕዝ ላይ ተፈጸመ የተባለው ጥቃት ገና በጥልቀት አልገባኝም።ጥቃት የተባለው ምናልባትም በወታደሮች ላይ የተደረገ ትንኮሳ ሊሆን ይችላል ብዬ ነው ያሰብኩት እንጂ፣ ከዚያ በላይ የከፋ ይሆናል የሚል ግምት አልነበረኝም።
የህግ ማስከበር ዘመቻው ተጀመረ። ሠራዊቱ በአስደናቂ ፍጥነት የሕወሓትን ሀይል ያፍረከርከው ያዘ።ከሦስት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ሠራዊቱ መላ ትግራይን በቁጥጥሩ ስር አዋለ።ከዚያን በኋላ ነው ስለ ጥቃቱ በደንብ ማሰብ እና መስማት የጀመርኩት።ያስደነግጣል፤ ይገርማል፤ ያናድዳል።
እንዴት ሰው 20 ዓመት የጠበቀውን፣ በአንበጣ መከላከል፣ አዝመራ ስብሰባ፣ በትምህርት ፣ጤናና መሰል ተቋማት ማስፋፋት የዋለለትን ሠራዊት ሊያጠቃ ይነሳል? ድርጊቱስ እንዴት በዚህ የጭካኔ ልክ ይፈጸማል? እንዴት በዚህ መጠን የገዛ ወገንን ለማጥቃት ዝግጅት ይደረጋል? ምንድን ነው ፍላጎታቸው? ለምን ይህን ነውረኛ መንገድ መረጡ? ወዘተ… የሚሉ ጥያቄዎች በአዕምሮዬ በተደጋጋሚ ተመላለሱ።
እርግጥ ነው አሸባሪው ትህነግ በህግ ማስከበሩ ከመመታቱ በፊት በተደጋጋሚ መቀሌ ላይ ይካሄድ ከነበረው ወታደራዊ ትርኢት አንጻር እኔም ሆንኩ ብዙዎች ሰንብቶም ቢሆን ችግር እንደሚፈጠር እናውቅ ነበር።ነገር ግን በአንድ ጎን ሕወሓት ደፍሮ ጦርነት አይጀምርም የሚል ግምት ነበረኝ።ጦርነት ቢጀምር እንኳ መደበኛው አይነት ጦርነት እንጂ እንዲህ አይነት የፈሪ ዱላ ይሰነዝራል የሚል እምነት አልነበረኝም።ግን ሆነ።
የጥቃቱ ሰለባ ወታደሮች በሰሜን ዕዝና በራሳቸውም ላይ የደረሰባቸውን ጥቃት መናገር ሲጀምሩ ቡድኑ ዘግናኝ ድርጊት መፈጸሙን ተረዳሁ፤ በወገን ላይ በተፈጸመው ጥቃት የደረሰው ጉዳት በእርግጥም ያሳዝናል፤ ያስለቅሳል።ምን ያህል ሕወሓት ለክፋት ሥራው እንደተዘጋጀ እና ምን ያህል ርህራሄ አልባ እንደሆነ በግልጽ ማየት ጀመርኩ።ያሳምማል።
እንኳን በሀገር ልጅ ላይ፤ሊያውም ለዓመታት እድሜውን እና ህይወቱን ገብሮ ለኖረ ወታደር ይቅርና ለባእድስ ቢሆን ይሄ ይገባልን? የሚለው ጥያቄ መልስ ታጣለት።ወገን አለኝ ብሎ ጀርባውን ለወገን ግንባሩን ለጥይት ሰጥቶ የቆመ ሀይል ባላሰበበት እና ባልተዘጋጀበት ሁኔታ በገዛ ወገኑ ከጀርባው መመታቱ ጭራሽ ይቅር የማይባል አረመኒያዊ ድርጊት ነው፤ ይህን ዜና ሲሰማ በራሱ ብቻ ልብ ይሰብራል።
የሚገርመው ግን ይህ ጥቃት እነሱ እንደሚሉት ራስን የመከላከል አይደለም፤ በእቅድ እና ሆን ተብሎ የተፈጸመ ነው።ከሦስት ሳምንት ዘመቻ በኋላ በርካታ የቡድኑ አመራሮች ተገድለው፣ በቁጥጥር ስር ውለው፣ ወደ ዋሻ ተመልሰው ባለበት ወቅት እና ሠራዊቱ ትግራይን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ ህዝብን እያረጋጋ ባለበት ወቅትም ጥቃቱ ቀጠለ።
ሠራዊቱን በህዝብ ማዕበል ማጥቃት ፤ ከጀርባ መምታት፤ ሆነ ብሎ በተሳሳተ መረጃ ወደ ጥቃት ቀጠና እንዲገባ ማድረግ፤ የሠራዊቱን ህዝባዊ ባህሪ እና ሰዋዊ ርህራሄ በሚፈታተን መልኩ ለጦርነቱ በማይሆኑ እና ሊተኩስባቸው በማይችላቸው ህጻናት፤ ሴቶች እና አረጋውያን እንዲወጋ ማድረግ ፤ አብያተ ክርስቲያናትን እና መስጊዶችን፤ ትምህርት ቤቶችን እና ሆስፒታሎችን እንደ መሸሸጊያ በመጠቀም መተናኮል ወዘተ ቀጠለ።ይህ ድርጊት ዛሬም አልቆመም።የጥቅምት 24 ቁስል እንዳይጠግን የሚፈልገው አሸባሪው ሕወሓት በዚህ ነውረኛ ድርጊቱ ቀጥሎበታል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ሠራዊት እንኳን በገዛ ወገኑ ጥቃት ሊደርስበት ይቅርና በክፉ መነሳት ነበረበትን? አልነበረበትም።ይህን የምለው እንዲሁ ለንግግር ማድመቂያ አይደለም።በዘመቻው ወቅት ለጥቂት ቀናትም ቢሆን በአቅራቢያ ሆኜ ስላየሁ እንጂ።ከኔ በእድሜ እኩያዬ የሚሆኑ ወይም የሚያንሱ ወጣቶች ጸሀይና ብርድ እየተፈራረቀባቸው፤በቀን አንዴ ብቻ ኮቾሮ እየተመገቡ፤ የወጣትነት አምሮታቸውን ትተው ፤ ሚስቴን እናቴን ልጄን ሳይሉ ለሀገር መንነው በተራሮች አናት እና በሸለቆ ጥልቀት በእግር መሳሪያ ተሸክመው ሲጓዙ ፤ ሲዋጉ ፤ ሲሞቱ እና ሲቆስሉ አይቻለሁ።እነዚህ ወጣቶች ከኔ ወይም ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ ለሀገር ግድ የሚላቸው ስለምንድን ነው? እንዲሁ የሀገር ፍቅር እና ለመስዋእትነት ያለ ቁርጠኝነት እንጂ ከማናችንም የተለየ እዳ ኖሮባቸው እይደለም።
ታዲያ እነዚህን ጀግኖች እንኳን ከጀርባቸው መውጋት በሙሉ ዓይንስ ማየትስ ይገባ ነበር? በስስት የሚታዩ ነበሩ።እነዚህ ጀግኖች ባይኖሩ ኖሮ ሀገራችን እንዳለባት ጠላት ብዛት እና እንደክፋታቸው ጥልቀት እስካሁንስ ትቆይ ነበር? ይህ ሠራዊት ባለፉት ሦስት ዓመታት ድንበር ከመጠበቅ ባለፈ አንዴ በሰሜን አንዴ በምስራቅ አንዴ በምዕራብ እየሄደ ሁከት ሲያበርድ እና ሰላም ሲያወርድ ባይውል ኖሮ ይህች ሀገር አሁን እነሶሪያን አትሆንም ነበር?
ብዙ ተቋማት ቀላል የሚባለውን የሲቪል ሥራ እንኳን መስራት አቅቷቸው የሚፈጥሩትን ችግር ሲታግስ እና ሲያርም የከረመው ይህ ሠራዊት አይደለምን? ታዲያ ይህን ሠራዊት ማጥቃት ስለምን ታሰበ?
ግልጽ ነው።ይህ ተቋም ከተመታ እና ከፈረሰ ሌላውን ነገር መቆጣጠር እና ሀገሪቱን መስበር እነሱ እንደሚሉት ማፍረስ ቀላል ስለሚሆን ነው።የጥቅምት 24ቱ ጥቃት አላማ ይሄው ነበር።ጥቃቱ ሠራዊቱን ብቻ ሳይሆን በዋነኝነት ሀገሪቱንም ኢላማ ያደረገ ነበር።
በዚያ ጥቃት ከጀርባ የተመታችው ኢትዮጵያ ነበረች። የቆሰለችው ኢትዮጵያ ነበረች። ሠራዊቱ ላይ የደረሰው ጥቃት በዚህ ልክ ህመሙ ሊሰማን ይገባል።ሀገሪቱ ተመትታ ቁስሏ የማይሰማው ዜጋ ደግሞ እሱ አንድም ጁንታ ነው፤ አሸባሪው ሕወሓት ነው፤ አልያም የሀገር ጉዳይ የማያሳስበው ነፈዝ ነው።
ጥቅምት 24 የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተካደበት ታሪካዊ ቀን ነው።ይህ ቀን እንደ የካቲት 12 ቀን መዘከር የሚገባው ትልቅ ቀን ነው።በዚያን ቀን የቆሰልነውን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲያውቀው እና እንዲሰማው ሆኖ በታሪክ መዝገብ መስፈር አለበት።ጥቅምት 24ን ባሰብን ጊዜም ሠራዊቱን እና በዚያ ቀን የደረሰበትን ክህደት ብቻ ሳይሆን ከዚያ በኋላም የቀጠለውን የነውረኞች ክህደት እና ሠራዊቱ ያን መክቶ ሀገርን ያዳነበትን ጥበብ መዘከር አለብን።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014