በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ እትማችን በ19 60ዎቹ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ይዟቸው ከወጣ ዘገባዎች ጥቂቶቹን ላስነብባቸው ወደናል:: በዚህም የተለያዩ ማህበራዊ፣ ህጋዊና ወጣ ያሉ አስደናቂ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል::
የዋልጋ ደላና ድልድይ ተሠራ
ግዮን ፤(ኢ-ዜ-አ-) በጨቦና ጉራጌ አውራጃ ግዛት በወሊሶ ወረዳ የሐሮና ደገዩ አጥቢያ ነዋሪዎች በመተባበር የዋልጋ ደላና ወንዝ ድልድይ በጥሩ ሁኔታ በእንጨት ሠርተው በአገልግሎት ላይ እንዲውል አደረጉ::
ይህ የዋልጋ ደላና ወንዝ ለብዙ ዓመቶች በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት ያደርስ እንደነበር ተረጋግጧል:: ይኸው ወንዝ የወሊሶንና የአመያን ወረዳ ግዛቶች የሚያዋስን መሆኑን የወሊሶ ወረዳ ግዛት ዋና ጸሐፊ አቶ ኃይሌ ንጉሤ ገለጡ::
( መስከረም 15 ቀን 19 61 ዓም)
ልጆች ለተጧሪዎች ልብስ ገዙ
አዲስ አበባ (አ-ዜ-አ-) በመካከለኛ ወረዳ ግዛት አካባቢ የሚገኙት ተማሪዎች በሠፈሩ ለሚኖሩት ተጠዋሪ ሽማግሌዎች ልብስ ገዝተው ጥቅምት ፫ ቀን ፲፱፷፩ ዓ.ም አለበሱ::
ተማሪዎቹ ለልብስ መግዣ ገንዘብ የሰበሰቡት በዕረፍት ጊዜያቸው በገዛ ኃጢያቴ ሲኦል ሆነ ቤቴ በሚል አርዕስት ያዘጋጁትን ቲያትር ለወላጆች በማሳየት ባገኙት ገቢ ነው::ከዚሁ ቲያትር ተማሪዎቹ ያገኙት ገቢ ፹፰ብር ከ፸፭ ሳንቲም ሲሆን፤ ለአራት ችግረኞች ሽማግሌዎች የቀንና የሌሊት ልብስ ገዝተው አልብሰዋል::
ተማሪዎቹ ቲያትሩን ባሳዩበት ጊዜ በወረዳ ግዛቱ የተቋቋመው የዕድር ማኅበር ድንኳን በመስጠት የረዳቸው መሆኑ ተገልጧል:: ከዚሁ በቀር ተማሪዎቹ ወላጆች ላደረጉላቸው ድጋፍና ርዳታ ምስጋና አቅርበዋል::
( ጥቅምት 7 ቀን 19 61 ዓ.ም )
ቦርሣ የጠፋው
አንድ ቦርሳ በምዕራብ ዓባያ ወረዳ ውስጥ ወድቆ በውስጡ ካለው ገንዘብ ጋር ተገኝቷል::ግን እስካሁን የቦርሳው ባለቤት አለመገኘቱ ታውቋል::
ቦርሳውን ወድቆ ያገኙት ተንጋ አለንቦና ሁለት አበሮቹ ፤እቦርሳው ውስጥ ያለውን ገንዘብ ለመካፈል ሞክረው ነበር በመባል በምዕራብ ዓባያ ወረዳ ግዛት ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦባቸዋል::
ስለዚህም የቦርሣው ባለቤት ነኝ የሚል ሰው፤ ጥቅምት ፩ ቀን እምዕራብ ዓባያ ወረዳ ግዛት ፍርድ ቤት ድረስ ቀርቦ እንዲያስታውቅ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ::ወድቆ የተገኘው ቦርሳ ምርመራውን ያጣሩትም የወረዳው ግዛት ፖሊስ አዛዥ ምክትል የመቶ አለቃ እንዳለ በቀለ ናቸው::
( መስከረም 16 ቀን 19 61 ዓ.ም. )
በሕግ የተከለከለ ቡና የሸጡ ተቀጡ
ዐሰበ ተፈሪ፤(ኢ-ዜ-አ-) በሕግ የተከለከለ ፯ ኲንታል ቡና በዐሰበ ተፈሪ ከተማ ውስጥ ለመሸጥ ሲሞክሩ የተያዙት አራት ሰዎች እያንዳንዳቸው በ፲፭ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ የጢሮ ወረዳ ፍርድ ቤት ፈረደ::
እነዚህም ወይዘሮ ፋጡማ አብደላ ወይዘሮ አበራሽ ወልደሚካኤል አቶ መሐመድ አብዱላሂና አቶ ሙሉ ሸዋ መርሻ የተባሉት ናቸው:: የተያዙትም በቡና ቦርድ ሠራተኞች አማካይነት መሆኑ ታውቋል:: ፍርድ ቤቱ አድራጎቱን በማስረጃ ካረጋገጠ በኋላ፤እያንዳንዳቸው ፲፭ ብር እንዲከፍሉ ሲበይን ፤በእጃቸውም የተገኘው ፯ ኲንታል ቡና ለመንግሥት በውርስ ገቢ እንዲሆን ወስኗል::
( መስከረም 22 ቀን 19 61 ዓ.ም )
አባ ጅብ ገደሉ
ጅማ ፤(አ-ዜ-አ-) አቶ ሲራጅ ፈይሳ የተባሉ ሰው መኖሪያ ቤታቸውን ሰብሮ ሊበላቸው የቃጣውን ጅብ ጉሮሮውን አንቀው ከሞት ዳኑ::
ኗሪነታቸው በከፋ ጠቅላይ ግዛት በሊሙ አውራጃ በሊሚ ሰቃ ወረዳ በኩማ ምክትል ወረዳ ጎጀቦ ቀበሌ የሆነው እኝህ ሰው ባለፈው መስከረም ፲፬ ቀን ሌሊት አንድ ጅብ ቤታቸውን ሰብሮ ገባ:: ከዚያም የታሠረች ላማቸውን ለመብላት ሲተናነቅ ነቅተው ለማስጣል ሲሞክሩ አውሬው ላሟን ትቶ ወደ እርሳቸው አፉን ከፍቶ ሲዘል በሁለት እጃቸው ጉሮሮውን አንቀው ከያዙ በኋላ በጩኸት የጎረቤት እርዳታ ጠየቁ::
አባ በቀለ የተባሉት ጎረቤታቸውም ከውጪ ደርሰው ጅቡን በስለት በመውጋት ገድለው በማስጣል ከሞት መዳናቸውን የክፍሉ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ የ፲ አለቃ አንበሴ ወርዶፋ ገልጠዋል::
(መስከረም 30 ቀን 19 61 ዓ.ም.)
ተማሪውን አዞ በላው
ጎሬ ፤(ኢ-ዜ-አ-) ውሻለ አውያ የተባለ አንድ የ13 ዓመት ተማሪ በአዞ ተበልቶ ሞተ:: ነዋሪነቱ በኢሉባቡር ጠቅላይ ግዛት በጋምቤላ አውራጃ በጋምቤላ ከተማ የነበረው ውሻለ አውያ ይህ አደጋ የደረሰበት ባለፈው ጥቅምት ፫ ቀን ባሮ ከተባለው ወንዝ ውስጥ ገብቶ ገላውን ሲታጠብ ነው::
ሟቹ እጅና እግሩን ጨርሶ በአዞው የተበላ ሲሆን የቀረው ሰውነቱ ለቤተዘመዶቹ ተሰጥቶ እንዲቀበር የተደረገ መሆኑን የጠቅላይ ግዛቱ ፖሊስ የወንጀል መከላከል ክፍል ዋና ሹም ምክትል የመቶ አለቃ የኔ ዓለም አናጋው ገለጡ::
(ጥቅምት 13 ቀን 19 61 )
አምና በአዲስ አበባ ፬ሺ፯፻፹፮ ውሾች ተገድለዋል
የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የከተማውን ሕዝብ በመጥፎ ውሻ በሽታ ከሚደርስበት ጉዳት ለመጠበቅ በወሰደው እርምጃ ፬ሺ፯፻፹፮ ተልከስካሽ ውሾች አምና ተገድለዋል::
ማዘጋጃ ቤት ለከተማው ሕዝብ ደኅንነት የሚያደርገው ጥረት ከፍያለ ሆኖ ፤ለማኅበራዊ ኑሮ የማያስቡ ሰዎች ውሻ አሳድገው የትም በመልቀቃቸው የሚያደርሱበት ጉዳት ፈጽሞ ሊወገድ አልቻለም:: በዚህም ምክንያት አምና በመጥፎ ውሻ ለተለከፉ ፪ሺ፯፻፶፪ ሰዎች ማዘጋጃ ቤት ነፃ ሕክምና አድርጓል::
ስለዚህ ውሻ የሚያሳድጉ ሁሉ ውሾቻቸውን በደንብ በመያዝ ለኅብረተሰቡ ጤንነት እንዲጠነቀቁ በዚህ አጋጣሚ ምክራችንን እንለግሳለን:: የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የሕዝብ ንብረት ማስፋፊያና መሥሪያ ቤት::
(መስከረም 29 ቀን 19 61 )
8 እግሮች ያሉት ጥጃ ተወለደ
ዲላ ፤(ኢ-ዜ-አ-) በደራሳ አውራጃ በይርጋጨፌ ወረዳ በኢኡድ ቀበሌ አንዲት ላም ስምንት እግር ያለው ጥጃ ወለደች :: የተወለደው ጥጃ ከአራት ደንበኛ እግሮች ሌላ በቋንጃውና በጉልበቱ ላይ አንዳንድ ተጨማሪ እግሮች ያለው ነው:: ጥጃው ለሁለት ቀናት በሕይወት ከቆየ በኋላ የሞተ መሆኑን አቶ ሽመልስ ጣሰው ገለጡ::
ይህንን አስገራሚ ጥጃ ባለፈው ጥቅምት ፮ ቀን የወለደችው ላም የአቶ ቀቀቦ ሣሎ መሆኗ ታውቋል::
(ጥቅምት 13 ቀን 19 61 ዓ.ም)
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2014