ከበር ጀምሮ ውስጥ የሥራ ክፍሉ ድረስ ሠራተኛው እረፍት የለውም። ከበር ከደንበኛ የተቀበለውን ዕቃ መዝግቦና ቁጥር ሰጥቶ ተራ ለሚያስይዘው ሠራተኛ ያስተላልፋል።እርሱም እንዲሁ ወደሚመለከተው ክፍል ያደርሳል።ቀኑና ሳምንቱ በዚህ ሁኔታ አንዱ ደንበኛ ሲሄድ ሌላው እየተተካ ባለጉዳዩ እንደአመጣጡ ይሸኛል።
ባለጉዳይ ከበዛም የዕረፍት ቀንን ጨምሮ ያለማቋረጥ ይሰራል። በዚህ ፋታ በሌለው ሥራ ሠራተኛው ጠዋት ወደ ሥራ ሲገባና በሥራ መውጫ ሰዓት ሲታይ ቁጥሩ እጅግ በጣም ጥቂት ነው። መደበኛ ልብሱን ቀይሮ የሥራ ልብስ ለብሶ የሚሰራው የሰው ኃይል ቁጥሩ ብዙ ነው። የሚረገጠው የሥራ ክፍሉ መሬት ሳይቀር በጥቁር ቅባት የተለወሰ በመሆኑ አለባበስን ጠብቆ መሥራት አይቻልም። የማጽዳቱ፣የመቀጥቀጡና ብሎን የማሰሩ ሥራም እጅን በቅባት የሚለውስ በመሆኑ እጁን ታጥቦ ምግብ ሲመገብ ወይንም ከሥራ ሲወጣ ካልሆነ የወረቀት ሥራ እንደሚሰራው እጁ ንጹሕ የሆነ ሠራተኛ በድርጅቱ ውስጥ ጥቂቱ ነው።
በሥራ ክፍል ውስጥ ከሚገኘው የተለያየ የሥራ ማሽን የሚወጣው ድምጽ ለጆሮ ይከብዳል። ይህ እንግዳ ለሆነ ሰው እረፍት የሚነሳው ድምጽ ሠራተኛው ከመልመዱ የተነሳ ላያስተውል ይችላል። ምናልባትም በተቃራኒው ሥራ ያቆመውንና የሚሰራውን ማሽን በድምጹ ላይ ይሆናል። እጅና አይን ብቻ ሳይሆን ልቦናም ከሥራ ጋር የሚሆንበት የሥራ ክፍል ነው።
ሥራ ከሰው ሕይወት ደህንነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ በሚፈጠር ጥቂት ስህተት ምናልባትም የሰው ሕይወት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። በመሆኑም እያንዳንዱ ሥራ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ይሄ ሥራ አንድ ዶክተር ቀዶ ሕክምና ለሚያስፈልገው ታማሚ ከሚያደርገው ጥንቃቄ ያልተናነሰ ነው ።
ሐኪሙ በስቃይ ውስጥ ለቆየ ታማሚ ፈውስ ሰጥቶ ወደቀድሞ አቋሙ ተመልሶ ሲያይ ከፍተኛ ደስታ እንደሚሰማው ሁሉ የዚህ ክፍል ሠራተኛም የመኪናውን አካል ችግር ፈትቶ የደንበኛው ተሽከርካሪ በትክክል ሰርቶ ሲደሰት በማየት የሚሰማው ስሜት ተመሳሳይ ነው። በያሬድ ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የመኪና የውስጥ ክፍሉን አስመርምሮ መፍትሄ ለማግኘት የሚሄደው ባለጉዳይ የተለያየ መኪና ባለቤት ሲሆን፣ የመኪኖቹ የውስጥ አካሎች እንደመኪና አይነቶቹ ይለያያሉ።
በዚህ ክፍል ውስጥ በነበረኝ ቆይታ እንደታዘብኩት የመኪና የውስጥ ዕቃ ይዞ ወደተቋሙ የሚመጣው ባለጉዳይ ፋታ አልነበረውም። ተቋሙም ተረክቧቸው ለጥገና ተራ የያዙት ብቻ ሳይሆን፣ተሰርተው አልቀው ባለቤቱ ያልተረከባቸውና ከነጭርሱም ሳይወሰዱ ዓመታትን ያስቆጠሩ የመኪና የውስጥ ክፍሎች የተቋሙን የዕቃ ማከማቻ ማጣበቡን የተቋሙ የሰው ሀብት አስተዳደር አስጎብኝተውኛል።በምልከታዬ ውጭ የተረፈ መኪና ያለ እስከማይመስለኝ ነው የታዘብኩት።
አገር ውስጥ የሚሽከረከረው መኪና መንገድ ከሚያስተናግደው አቅም በላይ ነው እየተባለ መብዛቱ በስፋት በሚነገርበት በዚህ ወቅት የተለያየ ችግር አጋጥሟቸው ለምርመራና ጥገና ተራ የሚጠባበቁትና ወሳጅ አጥተው የተከማቹ የመኪና የውስጥ ክፍሎች በብዛት መኖራቸው አስገርሞኛል።
በአንዳንድ ተቋማት ውስጥ ያለሥራ ለዓመታት ፀሐይና ብርድ ተፈራርቆባቸው የቆሙ ተሽከርካሪዎች መፍትሔ የሚያገኙት በዚህ ክፍል ውስጥ ነው። መፍትሔ ሳያገኝ የሚቀር የለም።የመለዋወጫ ዕቃ ያልተገኘለት እንኳን ቢያጋጥም ሞዲፋይድ ወይንም በቀድሞው ተመሳሳይ የሆነ ዕቃ ተሰርቶለት መኪናው እንዲሰራ ይደረጋል።
በዚህ የመኪና የውስጥ አካል በሚሰራበት ድርጅት ውስጥ እንስቶችን በብዛት አላስተዋልኩም። ጥቂቶችም ቢሆኑ በአስተዳደራዊ ሥራ ላይ የሚሰሩ ናቸው።‹‹ከባቄላ ንፍሮ አንድ ጥሬ አይጠፋም›› እንደሚባለው በማሽን በታገዘ የመኪና የውስጥ ክፍል ምርመራና የጥገና ሥራ በሚከናወንበትና ብዙ ወንዶች ሠራተኞች በሚሰሩበት ክፍል ሁለት እንስቶች ብቻ ናቸው የነበሩት። በብዙ ወንዶች መካከል መሥራታቸው ደግሞ እይታ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። ከደንበኞችም ከውስጥ ሠራተኞችም ስለ ሁለቱ እንስቶች የሰማሁት ጠንካራ ሠራተኛና በሥራቸውም ስኬታማ መሆናቸውን ነው። ጥንካሬና ስኬታቸው ደግሞ ይበልጥ ትኩረቴን ስለሳበው የጥንካሬና የስኬታቸውን ምንጭ እንዲነግሩኝና ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉኝ እንግዳ አድርጌያቸዋለሁ።
በሥራ ክፍላቸው ውስጥ ሥራቸውን እያሳዩኝ ልምድና ተሞክሯቸውን አጫወቱኝ። የሁለቱም ሙያቸው ተመሳሳይ ሲሆን፤የሚሰሩት ሥራ ቫልቭ አጀስትመንት ይባላል። የመኪናው ሲሊንደር ሄድ (ቴስታታ) የሚባለውን ክፍል በመፈተሽ ነው የሚጠግኑት። ሙያዊ የሆነውን በዝርዝር የነገሩኝን በሙሉ አልጻፍኩትም እንጂ ስለሥራቸው ብዙ አስረድተውኛል።
ወይዘሮ ሰላማዊት ደሳለኝና ወይዘሮ ተስፋነሽ ፍቅሩ ይባላሉ። በሥራ ክፍላቸው ተገኝቼ እንዳየኋቸው የሥራ ባህሪያቸው በወንበር ላይ ተቀምጠው ከሚሰሩ ሰዎች ይለያል። መጠነኛ ቢሆንም ሥራው ጉልበት ይጠይቃል። ለውበታቸውና ለአለባበሳቸው የሚጨነቁ ሴቶችን ለአፍታ በአይነህሊናዬ እያሰብኩ እንስቶቹ በምን ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንደሚሰሩ አነጻጸርኩ። ሰው የሚሠራውን ሥራ ወይንም ሙያውን የሚወድ ከሆነ ውጫዊ የሆነው ወይም እይታው ብዙም እንደማያስጨንቀው ከእንስቶቹ ተገነዘብኩ። ደግሞም ጠዋት ወደ ሥራ ሲገቡ፣ማታ ደግሞ ከሥራ በኋላ ሲወጡ እንደሌሎች ሴቶች ሁሉ ውበታቸውንና አለባበሳቸውን ጠብቀው እንደሚወጡ አጫወቱኝ። አንዳንድ ደንበኞቻቸውም በአግራሞት እነርሱ ስለመሆናቸውም በጥርጣሬ እንደሚያዩዋቸው ነግረውኛል።ሥራው እራስን ከመጠበቅ አያዳግትም ነው ያሉት። ብዙ ሴቶች በሥራው ላይ ላለመገኘታቸው እንደአንድ ምክንያት መወሰድ እንደሌለበትም ይናገራሉ።በእነርሱ የሥራ ዘርፍ ላይ ሴቶች በብዛት አለመገኘታቸው ሥራውን ከሩቅ በመፍራት እንደሆነም ይገምታሉ።
ወይዘሮ ሰላማዊት ደሳለኝና ወይዘሮ ተስፋነሽ ፍቅሩ ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው።በተቋሙ ቀድማ ሥራ የጀመረችው ወይዘሮ ሰላማዊት ናት።በኋላ በተቋሙ የመቀጠር ዕድል ያገኘችው ወይዘሮ ተስፋነሽ ወይዘሮ ሰላማዊትን በማየት ነበር እንደርሷ የሙያው ባለቤት ለመሆን ፍላጎት ያደረባት።አርአያዋ እንደሆነችም ትናገራለች።
ወይዘሮ ሰላማዊት እንዳጫወተችኝ፤ተወልዳ ያደገችው አዲስ አበባ ከተማ ከዛንችስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። አሁን ትዳር ይዛ የሁለት ልጆች እናት ናት።በትምህርቷ በተለያዩ ምክንያቶች ከ12ኛ ክፍል በላይ አልዘለቀችም።ቤተሰብ መመስረቷም ከትምህርት ይልቅ ወደ ሥራ እንድታመዝን አድርጓታል። አሁን በምትሰራበት ያሬድ ኢንጂነሪንግ ድርጅት ውስጥ ዕቃ ግዥ(ስቶርኪፐር) ሆና ነው የተቀጠረችው። በተቀጠረችበት የሥራ ዘርፍ በቆየችባቸው ዓመታት ግን በማሽን ክፍል ውስጥ የሚሰሩትን ሠራተኞች ሥራ በደንብ ትከታተል ነበር።
አንድ ቀን እንደነርሱ እንደምትሆን መመኘት ብቻ ሳይሆን የሙያው ባለቤት እንደምትሆን እርግጠኛም ነበረች። ለባለሙያዎቹ የሥራ መሣሪያ በማቀበል፣ሲሰሩም በማየት የመኪኖችን የውስጥ አካልና የሥራ መሣሪያዎችን ስም ለመለየትና ለማወቅ ብሎም ለመሥራት እስከመሞከር ጥረት ታደርግ ነበር።
አሁን የምትሰራውን የመኪና አካል የሆነውን ቴስታታ ሙያ ለመቅሰም የቻለችው ቀደም ሲል በተቋሙ ውስጥ ከነበረ ባልደረባዋ ሲሆን፣ሙያውን ለመቅሰም ሁለት ዓመት ጊዜ ወስዶባታል። እርስዋ እንደምትለው የሙያው ባለቤት እንድትሆን ከፍተኛ እገዛ አድርጎላታል። በየቀኑ ስታደርግ የነበረው ልምምድ የሙያው ባለቤት እንደሚያደርጋት ካረጋገጠች በኋላ ለድርጅቱ ባለቤት በማሳወቅ ወደ ማሽን ክፍሉ ለመዘዋወር ቻለች።
በፍላጎቷ በመሆኑም ሥራው አልከበዳትም። እርስዋ የምትሰራው የመኪና ክፍል ቴስታታ መኪናው አላስፈላጊ የሆነ ድምጽ እንዳያወጣ፣ ጉልበቱ እንዳይቀንስ፣ መውሰድ ከሚገባው በላይ ነዳጅ እንዳይወስድ የሚያስችል በመሆኑ በጥንቃቄና በትዕግስት መሥራት ይጠይቃል።
አሁን ባለችበት ሙያ ከ15 አመት በላይ የቆየችው ወይዘሮ መሠረት፤ ለሥራው ያላት ፍቅር ከዕለት ወደዕለት እየጨመረ እንደሆነ ነው የነገረችኝ። ቤተሰብ፣ጓደኛ፣ዘመድ ወዳጅ አስተያየት መስጠቱ አይቀርም። እርሷ ግን ነቀፌታ እንዳልገጠማትና ነው ያጫወተችኝ ።
ወይዘሮ መሠረትን በማየት ወደ ሙያው መሳቧንና ሙያውንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቅሰም እንደቻለች ያጫወተችኝ ወይዘሮ ተስፋነሽ ፍቅሩ ደግሞ መኖሪያዋ ለድርጅቱ ቅርብ ስለነበር ብቸኛዋ የቴስታታ ማሽን ክፍል ሠራተኛ የሆነችውን ለማወቅ ዕድሉን አግኝታለች።እንደርሷ የመሆን ፍላጎትም አሳድራለች። ዕድሉን ለማግኘት የድርጅቱን ባለቤት በጠየቀችበት ወቅት ዕቃ ግዥ ክፍል(ስቶር) ውስጥ መሥራት እንደምትችል ነበር ምላሽ የተሰጣት።
እርስዋ ግን የምትፈልገውን ሥራ አጥብቃ ጠየቀች።የድርጅቱ ባለቤትም አላሳፈሯትም።ለጥያቄዋ ምላሽ ሰጧት ። ከዛም ሥራውን ለመለማመድ ጊዜ አልወሰደባትም።ሙያውን ተቀላቀለች።ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ በሥራው ላይ ትገኛለች። በግል ኮሌጅ በሂሳብ መዝገብ አያያዝ(አካውንቲንግ) ትምህርት በመከታተል ላይ ነበረች።የምትፈልገውን ሥራ በማግኘቷ ትምህርቷን አቋርጣ ሙሉ ለሙሉ አሁን በምትገኝበት ሥራ ላይ በመሆን ውጤታማ መሆኗን ትናገራለች።
በብዙ ወንድ ሠራተኞች መካከል ሆኖ መሥራት ለየት እንደሚል ትናገራለች። የሚያደርጉላቸው እንክብካቤ በሥራቸው እንዲበረታቱ የሚያደርግ በመሆኑ ለሙያው የበለጠ ፍቅር እንዲኖራቸው አስችሏቸዋል። አብዛኛው ደንበኛ በማሽን ክፍል ውስጥ ስለሚሰሩት ሥራ በቂ እውቀት ስለሌለው አንዳንዴ ከሥራ ክፍል ውጭ የደንበኛ መኪና ላይ በመውጣት ፍተሻ በማድረግ የመሥራት አጋጣሚ ይኖራል።
አንዳንድ ደንበኞች በሥራዋ ላይ ጥርጣሬ ያድርባቸዋል።ስለችሎታዋ የሚገነዘቡት ከሥራው በኋላ ነው። ብሎን ለማሰር ጉልበት አይኖራትም ብሎ የገመታትን አንድ ደንበኛ ሁሌም አትዘነጋውም ።እርሱ አትችልም ያላትን እንዲሞክረው አደረገች።ከእርሷ ይልቅ አቅም ያነሰው እርሱ እንደነበር አጫውታኛለች።ሴቶች ወንዶች የሚችሉትን ሥራ አይችሉም ብለው የሚገምቱ አንዳንድ ወንዶች ግምታቸው ስህተት እንደሆነ የሚገነዘቡት ሥራውን ካዩ በኋላ እንደሆነና በሂደትም የተሳሳተው አመለካከት እየተቀየረ እንደሆነ ነው የገለጸችው።
ስለእንስቶቹ የሥራ ትጋትና አቅም ያሬድ ኢንጂነሪንግ ድርጅት የሰው ሀብት አስተዳዳሪ አቶ አምደጊዮርጊስ ሞገስን ጠይቄያቸው፤‹‹ቀድማ ወደ ሥራው የገባችው ወይዘሮ ሰላማዊት በመሆኗ ሙያውን በደንብ ተክናዋለች።ሥራዋ ከወንዶቹ ይልቃል እንጂ አያንስም።ፍላጎትዋም ከፍተኛ ነው።እርስዋን በማየት የገባችው ወይዘሮ ተስፋነሽ የእርሷን አርአያ ነው የተከተለችው››በማለት ስለሥራቸው ምስክርነት ሰጥተውናል። ስለመልካም ፀባያቸውም ባህሪያቸውና የሥራ ትጋታቸው፣በሥራ ላይ ያላቸውን መተጋገዝ ሌላው አርአያ የሚሆን እንደሆነ በሥራ ለሰባት አመት አብረዋቸው በቆዩባቸው ጊዜያቶች ለማረጋገጥ መቻላቸውን ተናግረዋል። እንደ አንድ አስተዳደር ኃላፊም ሥራቸውንና ባህሪያቸውን ለመገምገም ችለዋል።
እንስቶቹ አሁን ከተሰማሩበት ሥራ ውጭ የመሥራት ዕቅዱ የላቸውም።ይልቁንም የገንዘብ አቅም ቢያገኙ የራሳቸውን ድርጅት ከፍተው፣በዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያ ሆነው ለሌሎችም የሥራ ዕድል ፈጥረው እውቅና ማትረፍ ነው ምኞታቸው።የጋራዥ ሥራ ከፍተኛ የመነሻ ገንዘብ እና ሰፊ የሥራ ቦታ ይጠይቃል።
የሥራ ማሽኖቹ ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ስለሚገቡ ያንን ለማሟላት አቅም ይፈልጋል። እንስቶቹ አሁን በሚገኙበት የቴስታታ ማሽን ሥራ ላይ በመድረሳቸው፣ብዙ ሴቶች ባልተሰማሩበት ዘርፍ ላይ መገኘታቸውና ሰርተው በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን ማስተዳደር መቻላቸውን የስኬታማነታቸው ማሳያ አድርገው ይገልጻሉ።ጥረታቸውን በማየት የሙያው ባለቤት ላደረጋቸው የድርጅቱ ባለቤት አቶ ያሬድና ለሙያ አጋሮቻቸውም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2014