የመግለጫው ሙሉ ቃል
ኢትዮጵያ በዘመናዊው ታሪኳ የሕወሓትን ያህል የውስጥ ጠላት ገጥሟት አያውቅም። ይህ ሀገር አጥፊና አሸባሪ ቡድን ‹ኢትዮጵያን እንደፈለግኩ አድርጌ እስካልገዛኋት ድረስ መፍረስ አለባት› ብሎ የተነሣው በሕዝባዊ ለውጥ የበላይነቱን ካጣበት ቀን ጀምሮ ነው። ከዕለተ ውልደቱ አንስቶ ግጭትና ቀውስን እንደ መሣሪያ፣ ጥላቻንና ክፍፍልን እንደ ስልት፣ ክህደትና ደባን እንደ ዘዴ ቆጥሮ ሀገር የማፍረስ እቅዱን ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየ ዘረኛ ቡድን እንደነበር የሚታወቅ ነው።
ብሔር ከብሔር እንዲጋጭ፣ ሃይማኖት ከሃይማኖት እንዲናከስ፣ ሕዝብ ከሕዝብ እንዲጠላላ፣ የሀገርነት ስሜት ከዜጎች ልብ ተፍቆ እንዲጠፋ ሳያሰልስ ሠርቷል። ይኼ ሁሉ ሆኖ ቡድኑ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን የይቅርታ ልብ ሳይቸረው አልቀረም። ስህተቱን አርሞ ዳግም ሀገር የመምራትና ሕዝብን የማስተዳደር እድል ተሰጥቶትም ነበር።
ዳሩ ግን እኩልነትን እንደ የበታችነት የቆጠረው ሕወሓት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ያቀረበለትን የይቅርታና የሰላም ገበታ ገልብጦ፣ የተዘረጋለትን የፍቅርና የመደመር እጅ ነክሶ በለውጡ ማግሥት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ተጠቅልሎ መቐለ ገባ። በትግራይ ክልል በቆየባቸው ዓመታት በአንድ በኩል ከሀገር መከላከያ ሠራዊት መሳ ለመሳ የሚሆን ወታደራዊ ኃይል እየገነባ፣ በሌላ በኩል የለውጡን ሂደት ለማደናቀፍና ለእኩይ ሥራው ከሚተባበሩት ኃይሎች ጋር ሆኖ ሕዝብ ትከሻ ላይ የመከራ ቁልል እንዲጨምር ሲተጋ ከረመ።
በትብብር ሀገር ያቆዩ ሃይማኖቶችንና ተከታዮቻቸውን በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስ በርስ ለማናከስ የግጭት ድንጋዮችን ሲፈነቅል ቆየ። በመጨረሻም አገር የማፍረስ የቆየ ዕቅዱ አካል የሆነውን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከ20 ዓመታት በላይ ሲጠብቀው የኖረውን ሰሜን ዕዝ ከጀርባው በመውጋት ትጥቁን ለመንጠቅና ኢትዮጵያንም አደጋ ላይ ለመጣል ዘግናኝ ተግባር ለመፈጸም በቃ።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአፋርና የአማራ ልዩ ኃይሎች፣ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አንድ ሆነው በመነሣት፣ በሦስት ሳምንት ውስጥ፣ ሕወሓት ከዋና ማዘዣው መቀሌ ወጥቶ ወደ ተንቤን በረሃ እንዲወርድ አድርጎታል። የመከላከያ ኃይላችን በዚህ የሕግ ማስከበር ዘመቻው የተነጠቀውን መሣሪያ በማስመለስ፣ የታገቱትን የሰሜን ዕዝ አባላት በማስለቀቅ፣ ዋና ዋና ወንጀለኞችን ይዞ ለሕግ በማቅረብ፣ እንዲሁም የጥፋት ቡድኑን ወታደራዊና ፖለቲካዊ አቅም በማመናመን የተሰጠውን ተልዕኮ በሚገባ ተወጥቷል። ይኼን ተከትሎ መንግሥትም በቀውሱ ጉዳት የደረሰበትን የትግራይ ሕዝብ መልሶ ለመገንባት አንድ መቶ ቢሊዮን ብር የፈጀ የመልሶ ግንባታና የሰብአዊ እርዳታ የማቅረብ ሥራዎችን ሠርቷል።
የትግራይ ገበሬ በተደጋጋሚ ባጋጠመው የእርሻ ሥራ መስተጓጎል የተነሣ በረሀብ እንዳይጠቃ በማሰብ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ እንደነበር ይታወቃል። መንግሥት የተኩስ አቁሙን ሲያውጅ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ሕወሓት ራሱን ለማደራጀትና የጥፋት ተግባሩን ሊገፋበት እንደሚችል ቢታወቅም የመንግሥት ፍላጎት የነበረው የትግራይ ሕዝብ በተለይም አርሶ አደሩ በተገኘው የጥሞና ጊዜ ተጠቅሞ የሽብር ቡድኑ ከሚያደርስበት ኃላፊነት የጎደለው ወከባና እንግልት ተላቆ ሳይረበሽ የልማት ሥራውን እንዲሠራ ስለሆነ የመከላከያ ሠራዊት ያለ ምንም ማቅማማት የትግራይን መሬት ለቅቆ እንዲወጣ ተደርጓል።
ዳሩ ግን ሕወሓት እወክለዋለሁ ለሚለው ሕዝብ ምንም ዓይነት ርህራሄ የማሳየት ፍላጎት አላደረበትም። በርሃ እያለ ያደራጀውን ጦር በመያዝ፣ የትግራይንም ሕዝብ ከልጅ እስከ አዋቂ እያስገደደ በማሰለፍ፣ የአማራና የአፋር ክልል መሬቶችን በኃይል መውረሩን ገፋበት።
የሽብር ቡድኑ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ከነበረው የጦርነት ባሕርይ በመውጣት ጦርነቱ ሌላ ገጽታ እንዲኖረው አድርጓል።
በተሳሳተ ትርክትና የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ የተጠለፈ ህዝባዊ አሰላለፍ በመፍጠር መጠነ ሰፊ ወረራ መፈጸሙና እየፈጸመ መሆኑ ይታወቃል። እድሜያቸው ከ12 እስከ 65 ዓመት የሚደርሱ ወንድና ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችንና ነፍሰ ጡሮችን፣ ካህናትና ሼኮችን ሳይቀር እያስገደደ በማሠማራት ወደ አማራና አፋር ክልሎች አዝምቷል።
የዚህ የጥፋት ዘመቻ ዋና ዓላማ በጭካኔ፣ በዝርፊያ፣ በውድመትና በሽብር ሀገር ማፍረስ እንደሆነ በተግባሩም በንግግሩም ሲገልጽ ቆይቷል። በየደረሰበት አካባቢ ሴቶችን ከመድፈር፤ ንጹሐንን ከመረሸን፤ መሠረተ ልማቶችን ከማውደም፤ የመንግሥትና የግለሰብ ሀብቶችን ከመዝረፍ፤ የቤት እንስሳቶችን በጥይት ከመግደል አልተቆጠበም። ሕዝብን እያሸበረ እንዲሰደድ ሲያደርገውም ቆይቷል።
ሕወሓት የጀመረውን ሀገር የማውደምና የማፍረስ ተልዕኮ በመደበኛ ወታደራዊ አደረጃጀት ብቻ መቀልበስና መቅበር አይቻልም። መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በማነቃነቅና ባለቤት በማድረግ የሀገርን ህልውና ከሁሉ አቀፍ ጥቃት መከላከል ያስፈልጋል። የምንከተለው የዘመቻ ስልት የሽብር ቡድኑን አቅምና የክፋት ምኞቱን በመስበር ሀገር የማፍረስ ህልሙን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማምከን መሆን አለበት። አቅሙን መስበር ስንል የሽብር ቡድኑ ያሰለፈውን መሣሪያና ወራሪ ኃይል በመደምሰስ ዕኩይ ፍላጎቱን ለመጨረሻ ጊዜ መቀልበስ ማለታችን ነው። የክፋት ምኞቱን መስበር ስንልም የሽብር ቡድኑ ሕወሓትም ሆነ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ህቡዕና ግልጽ ሚና ያላቸው የክፋት ኃይሎች አንድ ርምጃ ከመራመዳቸው በፊት አስር ጊዜ ለማሰብ እንዲገደዱ ማድረግ ነው።
ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ብቻ ሳትሆን የጀግንነት መለኪያም ናት። እንኳንስ የሚያደራጀው፣ የሚያስታጥቀውና የሚያሠማራው አግኝቶ፣ መንግሥት የለም ባለበት ጊዜ እንኳን፣ የሀገር ፍቅር ያለው ኢትዮጵያዊ ምን ዓይነት ተአምር ሊሠራ እንደሚችል በአምስት ዓመቱ የጣልያን ወረራ ወቅት ታይቷል። የራሱን ስንቅ ቋጥሮ፣ የራሱን ጠመንጃ ወልውሎ፣ የራሱን አደረጃጀት ፈጥሮ በሚያውቀው ዱርና ገደል ገብቶ፣ ፋሺስት ጣልያንን ከቆመበት እንዳይቀመጥ፣ ከተቀመጠበት እንዳይተኛ አደርጎታል። ያ ሕዝብ፣ ያ ወኔ፣ ያ ኢትዮጵያዊነት ዛሬም ከእነ ሙሉ ክብሩ አለ።
‹እግርና እግር ምን ቢጋጩም፣ ለመድረስ ግን በአንድ አቅጣጫ አብረው መጓዝ አለባቸው› ይባላል። ሕወሓት የኢትዮጵያ የወቅቱ አንደኛ፣ አደገኛና ቀንደኛ የደኅንነት ሥጋት ነው። የዚህን የጥፋት ቡድን ተልዕኮ ለመቀልበስ፣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አንድ ሆነን መነሣት አለብን። የሚያጋጥመንን ሕመም ችለን፤ የሚደቀንብንን ፈተና ተቋቁመን፣ የውስጥ ክፍተቶቻችንን ሞልተን፣ ጠንክረንና ነጥረን በመውጣት የጥፋት ቡድኑን ምኞት እናመክናለን። ሕዝብን በጅምላ ጠላት አድርጎ የሚፈርጅበት አካሄዱ፣ ሒሳብ የማወራረድ ጥማቱ፣ ሀገር የማፍረስ ከንቱ መሻቱ እና ሀገርና ሕዝብን ለውጭ ጠላቶቻችን አሳልፎ የመስጠት ክህደቱ እስከወዲያኛው ያከትማል።
ዛሬ ባህር ዳር ተገኝተን ይሄንን የኢትዮጵያ መከራ የሆነ ጠላት በሕዝባዊ ኃይል እንዴት መክተን፣ ቀልብሰንና ደምስሰን እንደምንቀብረው መክረናል። በወኔና በቆራጥነት፣ በእልህና በቁጭት የተነሡ የሀገር ልጆች በአነስተኛ መሥዋዕትነት የጥፋት ቡድኑን ተልዕኮ ለማምከን ዝግጁነታችንን ደግመን አረጋግጠናል። ድላችን የሚሳካው በተነሳሽነታችን ልክ ነውና፣ እንደ አንድ ልብ መካሪና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አንድ ክንድ ተግባሪ ሆነን የተነሣብንን ጠላት አሳፍረን እንሸኘዋለን። የሽብር ቡድኑ ጀንበር ስታዘቀዝቅ፣ ያኔ ለሀገራችን የንጋት ጨረር ይፈነጥቃል። ለዚህም ታሪካዊ ሥራ ሠርተን ታሪክን እንደምንቀይር ምንም ጥርጥር የለውም።
መላው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትና የሁሉም ክልል የጸጥታ ኃይሎች በየአውደ ውጊያው እየተዋደቁና ክቡር መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚገኙት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት የማይተካ ክብርና ፍቅር ነው። እኛም ሆንን መላው ኢትዮጵያውያን በማንኛውም ሁኔታ አብረናችሁ መሆናችንን እያረጋገጥን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለዘላለም በጀግንነት የሚዘክሯችሁ መሆኑን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።
ስለሆነም የጀመራችሁት ታሪካዊና ፍትሐዊ ተጋድሎ በድል እንደሚጠናቀቅ ለአፍታም ቢሆን አንጠራጠርም። በዚህ አጋጣሚ ለእናንተ ለብርቅዬ ጀግኖቻችን ያለንን ፍቅርና አክብሮት በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም በይፋ ልንገልጽላችሁ እንወዳለን።
በመጨረሻም አሸባሪው ሕወሓት የከፈተብን ጦርነት ሕዝባዊ ጦርነት ስለሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጦርነቱን ስፋትና ጥልቀት በመረዳት እንደወትሮው ሁሉ ከጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሁሉም ክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሰለፍ አገርን ከጥቃት እንድንከላከል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የአገራችን ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ባለሀብቶችና ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶችና በአገር ውስጥና በውጭ አገር የምትኖሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ የምንገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ በአንድ ልብ የምንመክርበት፣ በጋራ የተሰነዘረብንን ጥቃት በጋራ የምንመክትበት፣ ብቸኛ አገራችንን በማፍረስ በዓለም አደባባይ እርካሽና ክብር የለሽ ዜጎች ሊያደርጉን የተነሱ የውስጥ ባንዳዎችንና ኢትዮጵያ ጠል ኃይሎችን ያለአንዳች ልዩነት በመፋለም አኩሪ ገድል የምንፈጽምበትና ታሪክ የምንሠራበት መድረክ ላይ እንገኛለን። ስለሆነም በሚቀርብላችሁ ማንኛውም አገራዊ ግዴታ ላይ በመሳተፍ ኢትዮጵያን ለማዳን እንድትዘምቱ ጥሪያችንን በድጋሚ እናስተላልፋለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!!
በሀገር-አቀፉ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የሕግ አስፈፃሚዎች የግንኙነት መድረክ
ጥቅምት፣ 2014 ዓ.ም
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2014