የኔታ ፍሬው በሚቀኙት ቅኔ ወደር እንዳማይገኝላቸው እና የተናገሩት አንዱም መሬት ጠብ እንደማይል እንዲሁም የነባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ፣ ሞሶሎኒ ፣ ክርሲፒ እና ባራቴሪ ፓስታ ቀቃይ እና ደቀ መዝሙር የሆኑት አይተ ጭሬ ልድፋው እና ልጃቸው አይተ እኩይ ግብሩ በውሸት አገር ለማፍረስ ምን እየሰሩ እንዳሉ ባለፈው አንድ ነገር ጀባ ብያችሁ ነበር ። ዛሬም ነገሩ ቀልቤን ቢስበው “ጥፊስ ይደገም” አይደል ብየ ስለየኔታ ፍሬው ቅኔ እና አይተ ጭሬ ልድፋው እና ልጁ አይተ እኩይ ግብሩ ጠፍቶ ለመጥፋት እያደረጉት ስላለው የውሸት ናዳ አቀበቱን ወጥተን መቀመጫችን መሬት አርፎ እህል ውሃ መቅመስ እስከምንችል ድረስ አንድ ወግ ጀባ ልበላችሁ።
የለመደ ልማድ ያሰርቃል ከማድ እንዲሉ የነባሮን ሮማን ፕሮቻዝካ፣ ሞሶሎኒ ፣ ክርሲፒ እና ባራቴሪ ፓስታ ቀቃይ እና ደቀ መዝሙር የሆኑት አይተ ጭሬ ልድፋው እና ልጁ አይተ እኩይ ግብሩ ወታደሮቻቸውን እና የሰፈራቸውን ሰዎች አሸዋማው በርሃ ላይ ሰብስበው የሰው ልጅ ፈጽሞ ሊያምነው የማይችል ውሸት ይዋሻሉ። ግማሹ ተሰብሳቢ ውሸታቸውን አምኖአቸው በሚነግራቸው ተእምር ተደንቀው አፋቸውን ከፍተው ያዳምጣሉ። ከመመሰጣቸው የተነሳ በአፋቸው የሚገባው አሸዋማ አቧራ እና ዝንብ የጉድ ነው። የገባው አሸዋማ አቧራ ምንአልባትም ከሁለት ብሎኬት በላይ ሳይሰራ አይቀርም። ይሄን ያልኩት እኔ አይደለሁም ፤ አፈ ቀላጤው አይተ ጭሬ ልድፋው እንጂ። አይተ ጭሬ ልድፋው እና ልጁ አይተ እኩይ ግብሩ ሲዋሹ ሰው ይተዘባናል ይሆን? የሚለው ምናቸውም አይደል። ይሉኝታ ባለፈበት ፈጽሞ አላለፉም ።
ለመሆኑ ለተሰብሳቢው ምን ቢነግሩት ነው አቧራ እና ዝንብ በአፋቸው አስኪገባ አቅላቸውን የሳቱት ልትሉኝ ትችላላችሁ። አይተ ጭሬ ልድፋው እና ልጁ አይተ እኩይ ግብሩ ወታደሮቻቸውን እና የሰፈራቸውን ሰዎች ሰብስበው ያሉትን እንደወረደ እነሆ፡-
«ከዚህ በፊት በዓለም ላይ ተሰርቶ የማያውቅ ቀይ ባሕርን ወደ ተንቤን በርሃ በመጥለፍ ውቂያኖስ የሚያደርግ እንዲሁም አቧራ እና ድንጋይን ተጠቅሞ አሳ ለማርባት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ልንጀመር መሆናችንን ነግረናችሁ ነበር። ዛሬ ደግሞ የየንታ ፍሬውን ወታደሮች ፣ አውሮፕላኖች እና ድሮኖች በአንድ ጌዜ ለማጥፋት የሚያስችል ከባድ ቶን የሚመዝኑ ቋጥኞችን ከሰማይ እንዲዘነብ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ፈጥረናል። በዚህም ከትናንት በስቲያ የየንታ ፍሬውን ወታደሮች እንዳልሆኑ አድርገን ደምስሰናል። ለምሳሌ 31ኛን፣ 32ኛን፣ 11ኛን 34ኛን፣ 21ኛን ፣ 42ኛን፣ 88ኛን ፣ 220ኛን ፣ 001 የተባለውን ልዩ ኮማንዶ፣ ናደው ዕዝን፣ ነብሮ 33ኛን፣ 52ኛን፣ 188ኛን፣ 99ኛን ክፍለ ጦሮች ሙሉ በሙሉ የደመሰስን ሲሆን ተዋጊ አውሮፕላኖችን እና ድሮኖችን ደግሞ በፈጠርነው አዲስ ቴክኖሎጂ ተጠቅመን አንድ በአንድ ማምከን ችለናል። አሜሪካ እና መሰል ሃያላን አገሮች ቴክኖሎጂውን ለመግዛት ጥያቄ አቅርበውልናል። ለቴክኖሎጂው ዋጋ ስላልተቆረጠለት ምንም ምላሽ አልሰጠናቸውም።” ሲሉ ከተሰበሰቡት መካከል አንዱ ተነስቶ “ታዲያ እንደዚህ አይነት ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ካላችሁ ከእኛ ከሰፈር ሴት ወንድ ፤ ህጻን አዛውንት ሳትሉ አንድም ሰው ሳታስቀሩ የምትወስዱን ለምን ነው?” ሲል ጠየቀ። አይተ ጭሬ ልድፋውም “እናንተን የፈለግነው እንድትዋጉ ሳይሆን ከየንታ ፍሬው የሚሞቱ ወታደሮችን እንድቆጥሩልን ነው።” ሲል መለሰለት።
ከተሰብሳቢዎች መካከል ሌላ ሰው ተነሳና እኔ ሶስት ጥያቄዎች አሉኝ። ጥያቄዎቼን እንደሚከተለው አቀርባለሁ። የመጀመሪያው ጥያቄየ 31ኛ፣32ኛ፣11ኛ፣ 34ኛ 21ኛን ፣ 42ኛ ክፍለ ጦሮችን በባለፈው ጊዜ ደመስሰናቸዋል ብላችሁ አልነበር እንዴ? በ31ኛ፣32ኛ፣11ኛ፣ 34ኛ 21ኛን ፣ 42ኛ ስም የሚጠሩ ስንት ክፍለ ጦሮች ናቸው የኔታ ፍሬው ያሉት? ወይስ የአሁ ተደመሰሱ የተባሉት 31ኛ፣ 32ኛ፣ 11ኛ፣ 34ኛ 21ኛ ፣ 42ኛ ባለፉት ሙሉ በሙሉ ተደመሰሱ የተባሉት መንትያ ክፍለ ጦሮች ናቸው? ወይስ አሁን የገጠምነው ሌላ የኔታ ፍሬውን ነው ?
ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ 220ኛ ፣ 001 ልዩ ኮማንዶ ፣ ናደው ዕዝ ፣ ነብሮ 33ኛ ፣ 188ኛ የሚባሉ ክፍለ ጦሮች የኔታ ፍሬው አሉት እንዴ? የሚለው ሲሆን ሶስተኛው ጥያቄ ደግሞ ተዋጊ አውሮፕላኖችን እና ድሮኖችን ከደመሰሳችሁ ከሰሞኑ እየመጡ የሚቀጠቅጡን ያሉ የማን ናቸው? ሲል ጠየቀ። ይህን ጥያቄ ያነሳው ሰውየ ከእነ ልጆቹ እና የሰፈሩ ሰዎች ሳይቀሩ የቀይ ባህርን ወደ ተንቤን ለመጥለፍ ወደ ሚደረገው ቁፋሮ ላይመለሱ ተላኩ።
ይህን የሰሙት የኔታ ፍሬው «ወአኮ ከመ እለ ወድቁ በልሳን (ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው) » ብለው ቅኔ ተቀኙ። ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው የሚለውን አባባል ሲያብራሩ በጦርነት ወቅት በጥይት ተደብድበው የተጎዱ ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን በነገረ ሰሪ አንደበት እንደጠፉ አይሆኑም። ስለሆነም የእነ አይተ ጭሬ ልድፋውን ወሬ እየሰማችሁ ልትረበሹ አይገባም ሲሉ ገበያው መካከል ለተሰበሰበው ሰው የእነ አይተ ጭሬ ልድፋውን የውሸት ሱስ ያስረዱ ያዙ። የኔታ ፍሬው አክለውም ገበያው መሃል ለተሰብሰበው ህዝብ እነ አይተ ጭሬ ልድፋው እና ልጁ አይተ እኩይ ግብሩ ሲዋሹ ለእውነት የተጠጋጋ ውሸት እንኳን መዋሸት እንደማይችሉ ይናገራሉ።
የኔታ ፍሬው ለእውነት የተጠጋጋ ውሸት ሲሉ አንድ በውሸቱ የሚታወቅ ሰው ትዝ አለኝ። ሰውየው ካልዋሸ ወግ ያወጋ አይመስለውም። አንድ ቀን የሰፈር ሰው ተሰብስቦ ስለጀግንነት ፣ ስለሰፈራቸው ሰላም ወዘተ እያወጉ ያውካኩ ነበር ። በዚህ ጊዜ ካልዋሸ ወግ ያወጋ የማይመስለው ሰው ከመቀመጫው ተነስቶ በማጨብጭብ የደራ ወግ ይዘው ያውካኩ የነበሩትን የሰፈሩን ሰዎች ወግ አስቁሞ በቅርብ ጊዜ ስለሰራው አንድ ጀብዱ ሊነግራቸው እንደሚፈለግ ገለጸላቸው። የሰፈሩ ሰዎችም ወጋቸውን አቆሙ። ውሸታሙም «ይገርማችኋል፤ አንድ ቀን የሚዳቋ ስጋ እጅግ በጣም አማረኝና ሚዳቋ ለማደን ወደ አንድ ጫካ አመራሁ። የአጋጣሚ ነገር ሆነና ገና ጫካ ከመግባቴ አንድ ሚዳቋ አገኘሁ። የጠመንጃየን ማነጣጠሪያ ሚዳቋዋ ላይ አድርጌ አንድ ጊዜ ምላጩን ሳብኩ። በተኮስኳት አንድ ጥይት የሚዳቋዋን ጆሮ እና የኋላ እግሯን መታዋት።» ሲል የውሸታሙን ሰው ወግ ሲያዳምጡ የነበሩት ሁሉም ሰዎች ውሸታሙ ሰውየ በዋሸው ውሸት ተገርመው እንባቸው እስኪፈስ ድረስ ሳቁ። ከመካከል አንድ ሰው ተነሳና «አንተ በቃ ሁሌ መዋሸት አይሰለችህም !? ምናለበት ስትዋሽ እንኳን ለእውነት የተጠጋጋ ውሸት ብትዋሽ ! እንዴት ነው በአንድ ጥይት የሚዳቋዋን የኋላ እግር እና ጀሮዋን የመታሃት!? » ብሎ አፈጠጠበት። የዋሸው ሰውየም ውሸቱን ወደ እውነት ለማስጠጋት ምን ቢል ጥሩ ነው «እኔ እኮ የኋላ እግሯን እና ጀሮዋን የመታሁት ጆሮዋን በልቷት በኋላ እግሯ እያከከች ሳለ ነው።» ብሎ አረፈው። በዚህም የተሰበሰው ወግ አዳማጭ ውሸታሙ ሰው የተናገረው ነገር ለእውነት የተጠጋ ስለነበር ሊሆን ይችላል ብሎ አመነው ይባላል ።
አይተ ጭሬ ልድፋው ግን ለእውነት የተጠጋ የሚባል ውሸት አያውቅም። ቢያውቅም ለእውነት አስጠግቶ መዋሸት እንደሞት እና ሽንፈት ነው የሚቆጥረው ። ለዚህ አንድ ማሳያ ልንገራችሁ፡- በደብረ ታቦር ግንባር ነው አሉ ፤ አይተ ጭሬ ልዳፋው ምን ቢል ጥሩ ነው «እኛ እዚህ ከገበሬዎች ቤት እየገባን ሊጥ እየቀማን የምንጠጣው አዲስ አበባ እያለን ውስኪ ሰልችቶን እንደነበር የኔታ ፍሬው እና ደጋፊዎቹ እንዲረዱን ስለፈልገን ነው። እንደምታውቁት በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ ውድ እና ለጤና በአንደኛ ደረጃ የተቀመጠው ጁስ የሊጥ ጁስ ነው። እና ይሄን ከአርሶ አደሮች እየሰረቅን መጠጣታችን ጤናችንን ለመጠበቅ ያለንን ቁርጠኝነት አመላካች ነው። ስለዚህ ሁሉም ሰው ከማንኛውም ገበሬ ቤት በመግባት ሊጥ እየሰረቀ እንዲጠጣ እና ለእኛም እንዲያመጣ ጠንክሮ መስራት ኖርበታል» ሲሉ ትዕዛዝ አስተላለፉ። የኔታ ፍሬው መቼ የዋዛ ናቸው። ይህን ውሸት ሲሰሙ ምን ቢሉ ጥሩ ነው «ነፍስ ርኅብት መሪርኒ ጥዑመ ያስተርእያ (የተራበች ነፍስ መራራው ሁሉ ጣፋጭ ይመስላታል።)» ሆኖ ነው እንጂ እንዴት ነው የሊጥ እና የውስኪ መጠጥ ለውድድር የሚበቃው ። እነሱ አዲስ አዲስ አበባ በነበሩ ጊዜ «ነፍስ ጽግብት ጻቃውዓ መዓር ትሜንን (የጠገበች ነፍስ የማር ወለላ ትረግጣለች።» እንዲሉ ጥጋባቸው አላስችል ብሏቸው አይደለም ሊጥ መጠጣት ይቅርና ውስኪ አንኳን ለመጠጣት እንዴት ስልችቷቸው እንደነበር የአደባባይ ሚስጠር ነው ። «በዝ ግብርኪ ፣ ተገድፍኪ (በዚህ ስራሽ ወጥተሽ ወደቅሽ።)» እንዲሉ በጥጋባቸው አይደል ከባለኮኮብ ሆቴል ተባረው እንደ አይጥ በየበርሃው እና በየዋሻው ሲሹለከለኩ የሚውሉት እና የሚያድሩት ።
መቼም የእነ አይተ ጭሬ ልድፋው ውሸት አያልቅም ። ከሰሞኑ ደግሞ «ድሮን እስከ አብራሪው በዙ 23 በመምታት ጥለናል» ሲሉ ሰማን። ይህን በሰማሁ ጊዜ በ1928ቱ የጣሊያን ወረራ የሃዲስ አለማየሁ የእራስ እምሩን ጦር ሰብስበው ስለቆርቆሮ አሞራ (አውሮፕላን ) የሰበኩት ስብከት ትዝ አለኝ። በርግጥ የሃዲስ አለማየሁ ስብከት አገርን ከወራሪ ለመታደግ ነው። የአይተ ጭሬ ለድፋው ስብከት ግን አገርን ለወራሪ አሳለፎ ለመስጠት መሆኑን መሰመር አለበት። በ1928ቱ የጣሊያን ወረራ ጊዜ ወራሪውን የጣሊያን ሃይል ለመመከት ወደ ምእራብ ትግራይ ጦር ይዘው ከዘመቱት አገረ ገዥዎች መካከል አንዱ የጎጃሙ ራስ እምሩ ናቸው።
ጣሊያን በ1928 ኢትዮጵያን ሲወር የቆርቆሮ አሞራ (አውሮፕላን) ይዞ መምጣቱ በስፋት በአገሪቱ ይወራ ነበር። ነገር ግን ስለቆርቆሮ አሞራ የሚያውቅ አንድም ሰው አልነበረም። በመሆኑም ስለቆርቆሮ አሞራ ምንነት የሚያስረዳ አንድ የዘመናዊ ትምህርት የተማረ ሰው በጎጃም ክፍለ አገር ተፈልጎ ታዋቂው ደራሲ ሃዲስ አለማየሁ ተገኙ። ሃዲስ አለማየሁም የሰራዊቱን ሞራል ለመገንባት በሚል ብቻ አይተውትም ሰምተውትም ስለማያውቁት የቆርቆሮ አሞራ ያወሩ ጀመር። ከተናገሩት ንግግርም የቆርቆሮ አሞራ በጣም ደካማ ነች። አይደለም በአልቢን ፣ መውዜር እና ዲሞፍተር ተመተው ይቅርና በሽጉጥም ከተኮሳችሁ በአንድ ጊዜ ነው የምትጥሉት እያሉ ለሰራዊቱ ሰበኩ። ሰራዊቱም የቆርቆሮ አሞራዋን አግኝቶ በአልቢን እና ዲሞፍተር መትቶ ጥሎ ለጎጃሙ አገረ ገዥ ራስ እምሩ ግዳይ በማቅረብ እስከሚሸለም ቋመጠ። የዘመቻውም ቀን ደረሰ። ወደ ምእራብ ትግራይ ግንባር ደረሱ። የቆርቆሮ አሞራዋም መጣች። ጠመንጃ ያለው ሰው ሁሉ ተኮሰ። አንድም የመታት አልነበረም። ይልቁንም የወገንን ጦር እንዳሆን አድርጋ ተጫወተችበት። ሃዲስ አለማየሁም ነጉን ባዩ ጊዜ በተናገሩት በማፈር «የማያውቅ ሰው ሲናገር አያፍርም» ሲሉ ራሳቸውን ወቀሱ። እነ አይተ ጭሬ ልድፋው ግን እያወቁ ሆነ ብለው የሰው ልጅ ሊያስበው የማይችለውን ውሸት እየዋሹ የሰፈራቸውን ሰዎች ሊያስጨርሱ ቆርጠው ተነስተዋል። የሰፈራቸው እናቶችም ልጃቸው በእሳት እየተበላ እንደሆነ ስላወቁ ልጅ ባልወለዱ ሴቶች ቀኑ።
የኔታ ፍሬውም የእናቶችን ለቅሶ ሲመለከቱ «ብፁዓት መካናት ዘኢወልዳ ወይም ያልወዱ ብፁዓት ናቸው ። የወለዱ አበዱ ። » ሲሉ ተቀኙ
እነ አይተ ጭሬ ልዳፋው ከሰሞኑ በየኔታ ፍሬው በትረ ሙሴ በደረሰባቸው መቀጥቀጥ የመጨረሻቸው እየደረሰ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል። ለዚህም የአይተ ጭሬ ልድፋውን ውሸት በመገናኛ ብዙኃኗ ስትፈጭ የነበረችው «ምስርም» የየኔታ ፍሬውን ጥንካሬ አይታ ብርክ ይዟታል። ጎረቤት ሜሮይም ሰላም አጥታ እንደተራበ ወታደር በሶ መበጥበጡን ይዛለች። ኢትዮጵያን የነካ የለውም በረካ ! አይደል
አሁን ላይ የየኔታ ፍሬው ለሕዝባቸው «ትንቢት ይቀድሞ ለነገር (ትንቢት ይመራል ልጓም ይገራል።» እንዲሉ የሸህ ሁሴን ትንቢት ሊፈጸም መቃረቡን እያየን ነው ። ስለሆንም የእነ አይተ ጭሬ ልድፋውን አድሜ ለማሳጠር «ብዙኃን ይመውኡ (አንድነት ሃይል ነው ።)» እንዲሉ «በአንድ ላይ እንቁም» ሲሉ ጥብቅ ትእዛዝ አስተላፈዋል። ሕዝባቸው ተከትሏቸው ይተም ይዟል። የአይተ ጭሬ ልድፋውም «ሞቱ ለኃጥእ ጸዋግ (የሃጢያተኛ አሟሟት የከፋ ነው ።)» እንዲሉ አሟሟቱ የከፋ እንደሆነ ከአሁኑ እያየን ነው። የየኔታ ፍሬው ሕዝብ ሆይ የአይተ ፍሬውን ውሸት ምንም ሳትሰማ ትግልህን ከጫፍ አድርስ ተብለሃል!። በሉ ከድሉ ማግስት ከተራራ ጫፍ እንገናኝ ። እስከዚያው ቸር እንሰንብት ።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2014