መግቢያ፡ ታላቅ ሥራ የሚከወንባት ታላቅ ጥበብ
ያኔ ገና ድሮ የሰው ልጆች ስማቸውን ለማስጠራት አስበው ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለመሥራት ሳይንጠራሩ፤ ፈጣሪም የሰዎች ሙከራ ተሳክቶ ሰማይ ድረስ ሄደው ቤቱን እንዳያጣቡበት አስቦ እርስ በእርሳቸው እንዳይሰማሙ ቋንቋቸውን ከመደባለቁ በፊት ምድር ሁሉ የምትግባባው በአንድ ቋንቋ ነበር። የሰው ልጆች አጉል ላይሳካላቸው ጉዳይ የማይሆን ነገር አስበው፤ የቆጡን አወርድ ብለው የጉያቸውን ካጡ፣ አንዱን ልሳናቸውን በሺህ ከለወጡ በኋላ ግን የጋራ ቋንቋ ይሉት ነገር አከተመ።
የመጀመሪያውን ያህል ባይሆንም ቅሉ ከዚያ በኋላ ከሞላ ጎደል የሰው ልጆች ሁሉ የሚግባቡበት የጋራ ቋንቋ ሙዚቃ ብቻ ለመሆኑ ሉላዊ ስምምነት ተፈጥሯል። እናም ምድርን በቅጡ ሳይኖርባት ሰማይ ቤት እሄዳለሁ ብሎ በአልጠግብ ባይነቱ፣ በገዛ ቅሌቱ አንድነቱን ተቀምቶ፣ እርስ በእርሱ አልሰማማ ብሎ፣ የናቃት ምድር ላይ በየፊናው ተበትኖ የቀረው የሰው ልጅ ከጋራ ቋንቋው መደበላለቅ በኋላ በተሻለ መንገድ እርስ በእርስ የሚግባባበትን ሙዚቃ “የዓለም ቋንቋ” እያለ ያሞካሻታል።
በእርግጥም ግን ሙዚቃ እንዲህ መሞገሷ ያንስባት እንደሆነ እንጂ አይበዛባትም። እርሷ በሥርዓት በተቀመሩ፣ ጥልቅ ትርጉምን አምቀው በያዙ ኃይለኛ ቃላት ስምረት እና በፍቅር በፈለቀው በውበት በሚፈስ ጥዑም ዜማ ታጅባ፣ የላይኛውን አካላዊ ዓለም አልፋ፣ ውስጥ ድረስ ዘልቃ፣ መንፈስን የምታድስ፣ ልብን በደስታ የምታረሰርስ ሰዎች ከራሳቸውና ከላይኛው ምንጫቸው ጋር የሚግባቡባት የዓለም ቋንቋ ብቻ ሳትሆን የነፍስ ቋንቋም ናት፤ ሙዚቃ።
ምን ይሄ ብቻ፤ ሙዚቃ ተራ የጭፈራ ማድመቂያ ብቻ አይደለችም፤ ትልልቅ ሃሳቦች የሚፈልቁባትና የሚተላለፉበት፣ ለዓለምና ለዘላለም የሚጠቅሙ ወሳኝ ድርጊቶች የሚከወኑባት ዓለማዊውንና መለኮታዊውን ህላዌ አዋህዳ የያዘች ታላቅ ጥበብም ናት። በመሆኑም ከታላቁ የእስራኤል ንጉሥ ቅዱስ ዳዊት እስከ ኢትዮጵያዊው ታላቁ የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ ከማርያ ማኬቫ እስከ ቦብ ማርሌ፣ ከማይክል ጃክሰን እስከ ጥላሁን ገሰሰ… የሙዚቃ ጥበብ የታደላቸው ዜመኞች፣ ዘማሪዎች፣ ድምጻውያን በሏቸው ዘፋኞች ሙዚቃን በመጠቀም እንደየተሰጧዋቸው ዘመን የማይሽራቸው ታላላቅ ገድሎችንና ጀብዶችን ፈጽመውባታል።
በድል ተወልዶ በድል መዝሙር ሙዚቃን የጀመረው የሙዚቃው ንጉሥ “ፋሺስት ኢጣሊያ፣ ኢትዮጵያን ወርራ የቆየችባቸው ዓመታት እና የ1932 ክረምት አልፈው፣ የነጻነት ብሥራት በተሰማበት ዓመት፣ በወሊሶ ጎሮ ወረዳ፣ ሶየማ ቀበሌ፣ “መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም ከቀኑ በ10፡00 ሰዓት ወ/ሮ ጌጤነሽ ጉርሙ ወንድ ልጅ ተገላገለች” ይላል በአቶ ፈይሣ [ኃይሌ] ሐሰና ቤኛ ከ1934 ጀምሮ የተከተበው የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ” በማለት አንጋፋው ጋዜጠኛ ዘከርያ መሃመድ በጥላሁን ገሠሠ ሕይወት ዙሪያ ያሰፈረው መጣጥፍ ያመለክታል።
የታላቁን ሰው የጥላሁን ገሠሠን የሙዚቃ አጀማመርን በተመለከተም ጋዜጠኛው በመጣጥፉ እንደሚከተለው ይተርክልናል። “በ1939 ዓ.ም ጥላሁን በቀኛዝማች መኮንን ጥያቄ እና በአቶ ፈይሣ ምክር፣ ወሊሶ ከተማ በሚገኘው ራስ ጎበና ዳጨው ትምህርት ቤት እንዲገባ ተደረገ። አያቱ ወይዘሮ ነገዬም፣ ለእርሱ ሲሉ በወሊሶ ቤት ተከራይተው መኖር ጀመሩ። ጥላሁን …የወላጆቹ እርሱን ጥለው መጥፋት ሳይፈጥርበት እንዳልቀረ ከሚገመተው የመተው፣ ትኩረት የመነፈግ አልያም የብቸኝነት ስሜት ጋር ሲታገል ከመቆዘም ይልቅ ወደ እንጉርጉሮ ያደላ ነበር።
….በራስ ጎበና ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለ፣ “ሆያ ሆዬ የሚሉትን በማየት” እና “ጠላታችን ወደቀ፣ ፍፁም ጠፋ ሙሶሎኒ” የምትለዋን መዝሙር በማዳመጥ አጥንቶ ይዘምር ነበር። ይህን ያዩት የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር (ሱዳናዊው) ሚስተር ሸዳድ በአድናቆት አበረታቱት። ወንድማቸው ማህሙድ ሳንሁሪም ቤቱ እየወሰደ በሸክላ የተቀረፁ ዘፈኖችን አስደመጠው። ጥላሁንም የሰማውን በቃሉ ይዞ ማንጎራጎር ሥራው ሆነ። ከሙዚቃ ጋር ተዋወቀ።
ጋሽ ጥላሁን የአምስት ዓመት ሕጻን ሳለ ድንገት የጠፋችው ወላጅ እናቱ ወይዘሮ ጌጤነሽ ከአምስት ዓመታት በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ በመገኘቷ ከእናቱ ጋር ለመገናኘት በ1943 ዓ.ም በአሥር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣም ታሪኩ ያስረዳል። ከእናቱ ጋር ከተያየ በኋላ ትምህርቱን ይቀጥል ዘንድ ወሊሶ እንዲመለስ ቢደረግም፣ ልቡ ወደ አዲስ አበባ የሸፈተበት ጥላሁን ከሁለት ያልተሳኩ ሙከራዎች በኋላ፣ በ1944 ዓ.ም አዲስ አበባ ጠቅልሎ ገባ።
አዲስ አበባ ከመጣ በኋላም በ1947 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ማኅበር በመቀጠርና የድምጻዊነት ሕይወቱን በይፋ መጀመሩንና በዚያ በቆየባቸው የሁለት ዓመት ተኩል ገደማ ቆይታው፤ “ጥላ ከለላዬ”፣ “ጽጌረዳ ነሽ”፣ “ደጉ ንጉሥ” እና “ፍቅሬ ሰውነቴ” የተሰኙ ዘፈኖችን በመዝፈን ከሕዝብ ጋር እንደተዋወቀም የህይወት ታሩኩን በተመለከተ የተጻፉ መዛግብት ያመላክታሉ።
ሠሪው ሳይኖር ሥራዎቹ ሊኖሩ አይችሉምና ሠሪውን በዚህ መንገድ ካስታወስን የጽሑፋችን ዋነኛ ትኩረት ወደሆኑት የእናት ሃገር ኢትዮጵያ ፍቅርን፣ ክብርንና በልጆቿ ታላቅ ተጋድሎና ጀግንነት በደምና በአጥንት የተገነባ ታላቅ ማንነትን የሚገልጹ የሙዚቃው ንጉሥ ህያው ሥራዎች ከብዙ በጥቂቱ፣ ከረጅሙ በአጭሩ በጨረፍታ ወደማስቃኘት እንገባለን።
ሲጀምር በሐገር፡- ጥላ ከለላዬ ከላይ ስለ ሕይወቱና ሙዚቃ አጀማመሩ ባነሳንበት ላይ እንደገለጽነው ጋሽ ጥላሁን ሕይወቱም ሙዚቃውም የጀመሩት ከሐገር ፍቅርና ህልውና ጋር ተያይዘው ነው። በእብሪት ተነሳስቶ ታላቋን ሐገር ኢትዮጵያን ለመግዛት የመጣው በጀግኖች ኢትዮጵያን አድዋ ላይ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ፣ አይዋረዱ ተዋርዶ፣ ኢትዮጵያን ይበልጥ ዓለም ላይ ከፍ አድርጎ የተመለሰው ኢጣሊያ ለሁለተኛ ጊዜ ለወረራ መጥቶ ክንዳቸው በማይዝለው በአይበገሬዎቹ አባቶቻችን አስደናቂ ተጋድሎ በድጋሚ ድል ተነስቶ የጻነት ብሥራት ሲሰማ ጥላሁን ተወለደ። የድል ዜማዎችን እየዘመረ አደገ።
የሙዚቀኝነት ሥራውን ደግሞ በአዲስ አበባ ከነ ስሙም በሐገር ፍቅር ማህበር በይፋ ጀመረ። እናም በሐገር ፍቅር ማህበር በቆየባቸው የሁለት ዓመት ተኩል ገደማ የመጀመሪያ የሙዚቃ ሥራዎች መካከል “ጥላ ከለላዬ” በሚል ስለ ሃገሩ ያዜመው ዜማ ዘመን ከማይሽራቸው የንጉሡ ሥራዎች መካከል አንዱ ሆነለት።
“ለውዲቷ ለእናት ኢትዮጵያ ታጥቄ ጠንክሬ
የምሰዋላት ነኝ እኔስ ለሃገሬ
ጠላቶቿን እቃወማለሁ አጥብቄ በብርቱ
ስለ ሀገር ፍቅር ገባኝ በእውነቱ
አያት ቅድመ አያቴ ተወለዱብሽ
እምዬ እናት አገር ለእኔም ሀገሬ ነሽ
ኑሪ በነጻነት ኮርተሸ” አላት።
በሀገር ፍቅር ማኅበር “ጥላ ከለላዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ”ን በመጫወት በይፋ የተጀመረው ጥላሁን ፣ለወላጆቹ ብቸኛ ልጅ ሆኖ በሕዝብ ውስጥ የኖረው ጥላሁን፣ ሀገሩ ኢትዮጵያን የወላጆቹ ምትክ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን ደግሞ ወንድምና እህቶቹ አድርጎ የሚያስብ፣ “የእኔ ሐብት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው” የሚል ልባዊ እምነቱን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚናገር ነበር።
የጥበብ ሕይወቱን ስለ ኢትዮጵያ እየዘመረ አሟሽቶ፣ ስለ ኢትዮጵያ እየዘመረ ኖሮ፣ ስለ ኢትዮጵያ እየዘመረ ውብ ድምፁን፣ ጣፋጭ ቅላፄውን፣ አቻ ያልተገኘለት የመድረክ አቀራረብ ጥበቡን አሻራ፣ እንዲሁም ልዩ የሀገር እና የሕዝብ ፍቅሩን አውርሶ የሄደው ጥላሁን ገሠሠ፣ በድምፁ ሐውልቱን የተከለ ታላቅ ከያኒ ነው።
ሀገር በጠላት ስትጠቃ ከወታደር እኩል የሚዋጉት የንጉሡ ዘፈኖችመቸም ይች ታላቅና ባለ ብዙ አኩሪ ታሪክ አገር አልሆንላቸው እያላቸው እንጂ ከከፍታዋ ሊያወርዷት ክብሯን ሊያዋርዱት ያልሞከሩ የሉም። ከእነዚህ ልክ አያውቄ የኢትዮጵያ ደመኛ ጠላቶች አንዱ ደግሞ አላዋቂነትና ትዕቢት ልቡን አሳብጦት በ1969 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ የፈጸመው፤ በማያስደፍሩት የእሳት አጥሮቹ የኢትዮጵያ ጀግኖች ልኩን ቀምሶ አፍሮ ተመልሷል እንጂ።
የጥላሁን ድምጾች በሰላም ጊዜ ብቻ ሳይሆን በመከራ፣ በጦርነት ጊዜም ይዘፍናሉ። ዜማና ግጥሞቹ የሚዘፈኑት በመከራ ጊዜ ስለሆነ “እንደ ማሽላ ሳር እስቃለሁ” እያሉ አይደለም፤ እሳት ነበልባል ሆነው ጠላትን እያቃጠሉ፣ ጠላትን እያሳረሩ፣ የወገንን ልብ ደግሞ በፍቅር እያቃጠሉ ሞራልና ጀግንነቱን እያቀጣጠሉ ነው የሚዘፍኑት።
እስኪ በዚያድባሬ ወራሪ ላይ ላይ ተተኩሰው፣ ከጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆችና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ተባብረው የጠላትን ጦርና ሥነ ልቦና እስከወዲያኛው ካንኮታኮቱ የጥላሁን እሳተ ነበልባል ኃያል ስንኞች መካከል “ዘማች ነኝ እኔም ለሃገሬ” ከሚለው ዜማ ላይ የተወሰዱትን እንመልከት፡-
የመጣው ቢመጣ ምን ጦር ቢነቀነቅ
ከሀገሬ ድንበር ላይ ነኝ የማልል ንቅንቅ
ምንም ስለሌለኝ የሚበልጥ ከሀገሬ
ቢሰጥ ደስ ይለኛል ሥጋየ እንኳን ላውሬ
ዘማች ነኝ ቆራጥ እኔም ለሃገሬ
አልሻም ተደፍራ ለማየት ድንበሬ
….
ዳገት ቁልቁለቱን ወጥቼ ወርጄ
የመደብ ጠላቴን አጋድሜ አርጄ
የእናቴን ነጻነት ስሟን አስጠርቼ
ብሞት ደስ ይለኛል እኔም ለሀገሬ
ታዲያ ይሄ የጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች የእሳት ክንድ ሲጨመርበት በእርግጥስ ጠላትን አቃጥሎ አመድ አርጎ የእናት ኢትዮጵያን ክብር ከፍ ከማድረግ በቀር ሌላ ያስመኛልን? የሆነውም እንደዛ ነው! በዚህ መንፈስ የሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ከተጫወታቸው ሀገራዊ ዘፈኖች ውስጥ በ1969 የተጫወተው “አጥንቴም ይከስከስ” እንዲሁም በ1979 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስቱዲዮ ተቀርፆ ለሕዝብ የቀረበው “ቃል ኪዳን” የተሰኘው ግጥሙ በሻምበል ክፍሌ አቦቸር የተጻፉ ዘፈኖችም ሁሌም የማይረሱ የሃገር ዘብ የሆኑ የጥበብ ውጤቶች ናቸው።
“ቃል ኪዳን” የተሰኘው የታላቁ የሙዚቃ ጥበበኛ ዜማ ከሃገር ቤት አልፎም ዘፈኑ ባሕር ማዶ ለሚኖሩ ወገኖች ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ “የእናት ሀገር ጥሪ” የቀረበበት ህያው ሥራ እንደሆነም ይነገራል።
ዛሬም እነዚህ ህያው የጥበብ ጥይቶች በዓለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ የማሃይምነት እብሪት ከገዛ ማህጸኗ ወጥቶ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጦርነት በከፈተው ታህተ ሰብዕ ጁንታ ላይ እየተተኮሱ ነው። ከጀግናው የሃገር መከላከያ ሠራዊትና ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር ሆነው ከሃዲውን የታሪክ አተላ እያሳደዱ እየለበለቡት ነው።
በቅርቡም በልጆቿ የተባበረ ክንድ ከሃዲው ላይመለስ ይቀበራል፤ ኢትዮጵያም እንደወትሮው ሁሉ በውድ ልጆቿ አጥንትና ደም በነጻነት ከፍ ብላ ዘላለም በክብር ትኖራለች። ምክንያቱም ታላቁ የጥበብ ንጉሣችን እንዳለው እኛ ኢትዮጵያውያን የሰው ልጆች የእኩልነት ተምሳሌትና የእውነተኛ ክብር ምንጭ ከሆነችው ከውዷ እናታችን፣ ከታላቋ ሃገራችን የሚበልጥብን ምንም ነገር የለምና!
ፍጻሜውም በኢትዮጵያ ፍቅር
ህይወትን በፍቅርና በድል፣ የሙዚቃን ጥበብም በሃገሩ ፍቅር “ጥላ ከለላዬ ኢትዮጵያ ሀገሬ” ብሎ የጀመረው ታላቁ ጥላሁን ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረውን ረጅሙን የሙዚቃ ሕይወቱን የደመደመውም “ቆሜ ልመርቅሽ” በተሰኘ በግሩም ሁኔታ አሁን ያለንበትን የፈተና ጊዜ ቀድሞ የተነበየና የኢትዮጵያን ትንሳኤ በሚመኝ የፍቅር አልበም ነው።
ትንቢትሽ ሲፈጸም ከመሬት ጠብ አይበል
ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ገድልሽ ይንበልበል
ሠንደቅሽ ከፍ ይበል ይቁም ለዘላለም
ሰላም ፍቅር ደስታ
ይታይብሽ በዓለም
ሴራው ይክሸፍበት
የመጣብሽ አድማ
እጁን ሳር ያድርገው
ጉልበቱን ቄጤማ
ካቀባበለብሽ
ብረት ከደገነ
አምላክ ያግዝልሽ
ላንች እየወገነ
አሜን እማማ!
አበቃን።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2014