በሪልስቴትና በኢንዱስትሪ ሥራዎች ላይ አተኩረው የሚሰሩ መሀንዲስ ናቸው። የ45 ዓመት ጎልማሳ ሲሆኑ በእድሜ ዘመናቸው ሁሉ ያባከኑት ጊዜ የሌለ ስለመሆኑ በአንደበታቸው ከሚናገሩት ቃላት በበለጠ ሥራቸው ምስክር ነው። በትምህርት ቤት ቆይታቸው የደረጃ ተማሪ ነበሩ። ለዚህም ውጤታቸው ወታደር ሆነው ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጡ የነበሩት ወላጅ አባታቸው እንዲሁም በመደበኛው የትምህርት መርሐ ግብር ለመማር ባይመቻችላቸውም ለትምህርት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ በማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ እስከ ስምንተኛ ክፍል የተማሩት ወላጅ እናታቸው የጎላ ድርሻ ነበራቸው።
በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት በማምጣት ከክፍል ክፍል ተዘዋውረው ለከፍተኛ ትምህርት ደርሰዋል። በወቅቱ አብላጫ ውጤት ማምጣት ከቻሉት ተማሪዎች ተርታ ቀዳሚ በመሆናቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የመጀመሪያ ምርጫቸው የሆነውን የቅድመ ኢንጅነሪንግ ትምህርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ ተከታትለዋል።
የትምህርት ምርጫቸውን ያደረጉት እንደርሳቸው አባባል ‹‹ለደሃ የሚሆን›› ማለትም ፈጥነው ገንዘብ ማግኘት የሚያስችላቸውን ሲቪል ኢንጅነሪንግ ተምረው በማእረግ ተመርቀዋል። በመሆኑም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅ በመቻላቸው ከዩኒቨርሲቲ በቀጥታ ወደ ሥራ ዓለም ተቀላቅለዋል። ከፍተኛ ውጤት ካመጡት አራት ተማሪዎች አንዱ በመሆናቸውም በተመረቁ ማግስት ቴሌ ኮሙኒኬሽን መሥሪያ ቤት በቀጥታ ቀጥሯቸዋል።
ከዩኒቨርሲቲ በቀጥታ በቴሌ ኮሙኒኬሽን መሥሪያ ቤት ሥራን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት ኢንጅነር ደሳለኝ ከበደ የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ናቸው።
አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ጣልያን ሰፈር አካባቢ ተወልደው ያደጉት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ በቴሌ ኮሙኒኬሽን መሥሪያ ቤት ያገኙት ዕውቀት እንዳለ ሆኖ በተቋሙ በሥራ ላይ ቢቆዩ ሊያጡ የሚችሉትን ጥቅሞች በማሰብ ለሁለት ዓመት ካገለገሉ በኋላ ሥራ ለቀው ወጥተዋል። የማስተርስ ትምህርታቸውን በግላቸው ተምረዋል። ከትምህርታቸው ጎን ለጎንም በግል ኮሌጆች የማስተማር ሥራን እንዲሁም የተለያዩ የዲዛይን ሥራዎችን በመስራት ገቢ ማግኘት ችለዋል።
አንድ አይነት ነገር ላይ መቆየት ትክክል አይደለም የተለያዩ አማራጮች መኖር አለባቸው ብለው የሚያምኑት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ የማስተርስ ትምህርታቸውን ባጠናቀቁ ማግስት ናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ (ኖክ) የሚቋቋምበት ወቅት ነበርና በዚሁ ድርጅት የሥራ ዕድል አገኙ። በወቅቱ ከነበሩት ኃላፊዎችም ጠንካራ የሥራ ባህልን እንዲሁም ጥልቅ የሆነ የሥራ ፍቅርን አግኝተዋል። በመሆኑም የእረፍት ቀናትን ጨምሮ ሽርፍራፊ ሰከንዶችን ሳይቀር ለሥራና ለሥራ ብቻ አውለዋል።
ከወላጃቸው፣ ከአካባቢያቸውና ከሥራ ባልደረባቸው የወረሱት የሥራ ባህል ዛሬ ለተገኙበት የስኬት ጎዳና መሠረት እንደሆነ ያነሱት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ በተለይም ከልጅነታቸው ጀምሮ በግቢያቸው ውስጥ የተለያዩ አትክልቶችን ያለሙ እንደነበርና ሳር እያጨዱ ለገበያ በማቅረብ እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን በኢኮኖሚ ይደግፉ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከወላጅ አባታቸው መኖሪያ ቤት የተጀመረው የሥራ ፍቅርና ትጋት በሄዱበት እየተከተላቸው ዛሬ በስኬት ማማ ላይ ተገኝተዋል።
ከመደበኛ ሥራቸው በተጓዳኝ የዲዛይንና የማማከር ሥራ እንዲሁም በሀገሪቱ ግዙፍ ካምፓኒ በሆነው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ግሩፕ በትርፍ ሰዓታቸው ሰርተዋል። በካምፓኒ ውስጥ ይሰሩ የነበረው መልካም ሥራ ፍሬ አፍርቶ ካምፓኒው ውጤት ማስመዝገብ ቻለ። በዚህ ጊዜ ለውጡን ያስተዋሉት የካምፓኒው ሥራ አስኪያጅ በካምፓኒው የሙሉ ጊዜ ሰራተኛ እንዲሆኑ ጠይቀዋቸዋል። በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረትም ከኖክ ወጥተው በካምፓኒው የሙሉ ሰዓት ሰራተኛ ለመሆን እንደ እግር ኳስ ተጫዋች የዝውውር ገንዘብ ተከፍሏቸው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ግሩፕ ካምፓኒን ተቀላቅለዋል።
በወቅቱ ምንም እንኳን የ27 ዓመት ወጣት የነበሩ ቢሆንም ትርጉም ያለው ሥራ በመስራት ካምፓኒውን መለወጥ በመቻላቸው የካምፓኒው አንድ አካል በሆነው ሪልስቴት ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተመደቡ። በወቅቱ ስለሪልስቴት ምንም አይነት እውቀት ያልነበራቸው ቢሆንም በዘርፉ ተሰማርተው ከሚመጡ የውጭ ሀገር ባለሃብቶች ጋር በቀላሉ በመገናኘት ከድርጅቱ በርካታ ነገሮችን መማር ችለዋል። ይህም ተጨማሪ አቅምና የሥራ ዕድል ፈጥሮላቸው አልፏል።
ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ግሩፕ ካምፓኒ የድሬዳዋ ሲሚንቶ ፋብሪካን ሊገዛ በተሰናዳበት ወቅት ሥራን አድምተው በመስራት የሚታወቁት ኢንጅነር ደሳለኝም ከፍተኛ ኃላፊነት ተሰጣቸው። ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት በመቻላቸውም በስምንት ወራት ውስጥ ፋብሪካውን ገንብተው ተግባራዊ እንዲሆን አድርገዋል። በዚህም ከካምፓኒው ከፍተኛ ሽልማት አግኝተዋል። በወቅቱ ካገኙት ሽልማት ይበልጥ እስካሁን የዘለቀው ወዳጅነታቸው ለስኬታቸው ድርሻ እንዳለውና አሁንም ድረስ በአማካሪነት አብረው እየሠሩ ይገኛሉ።
ሁልጊዜም አዳዲስና አማራጭ ሥራዎችን መሥራት የሚወዱት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ ከዚህ በኋላ ካምፓኒውን ለቀው የግል ሥራቸውን ለመሥራት ሲዘጋጁ ከካምፓኒው መራቅ እንደሌለባቸው ታምኖበት በትርፍ ሰዓታቸው እንዲሠሩና ሲፈለጉ እንዲቀርቡ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። ቀጥለውም አይቴክ ከተባለ የአሜሪካን የውጭ ድርጅቶች ጋር በጤናው ዘርፍ ለመሥራት ተቀላቅለዋል።
ድርጅቱ ለቲቢ ህመምተኞችና ሀኪሞች ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ሥራን የሚሠራ በመሆኑ 30 በሚደርሱ የሀገሪቱ የክልል ከተሞች ተዘዋውረው ሰርተዋል። ይህም ሀገራቸውን የማወቅ ዕድል የፈጠረላቸው ከመሆኑም አልፎ አዳዲስ ልምዶችን አግኝተውበታል። በዚህ ወቅትም ሥራውን በዕውቀት መምራት እንዲቻል አስተምሩኝ የሚል ጥያቄ ያነሱት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ በሀገረ አሜሪካ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በጤናው ዘርፍ የኢንጅነሪንግ ትምህርታቸውን መማር ችለዋል።
በተማሩት ትምህርትም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የቲቢ በሽታን መከላከል የሚያስችልና በሽታው ከታማሚው ወደ ሐኪሙ እንዳይጋባ የሚያስችል ግንባታን ሰርተዋል። የህክምና ተቋማት ሲገነቡ በኢንጅነሪንግ ዲዛይን መሆን እንዳለባቸው በማስተማር በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች መሰል ግንባታዎች በኢንጅነሪንግ ዲዛይን እንዲገነቡም አድርገዋል።
በጉዟቸው ሁሉ ጠንክሮ በመሥራት ዝናን እና ዕውቅናን የሚያገኙት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ የግላቸውን ሥራ ለመጀመር ሲነሱ በማማከር ያልተለዩት የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ግሩፕ በኃላፊነት ሥራ ሰጣቸው። ሥራው ድሬዳዋ የሚገኘው ግዙፍና በቀን 3000 ቶን ሲሚንቶ ማምረት የሚችል ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካን መገንባት ነው። ታዲያ ሥራውን በኃላፊነት ተረክበው ለመሥራት ድሬዳዋ ላይ ቢሮ ከፍተው ህጋዊ ሆነው መሥራት ነበረባቸውና ይህን አድርገው ከቦታ መረጣ ጀምሮ እስከ ኦፕሬሽን ድረስ ያለውን ሥራ ሠርተው አጠናቀቁ።
በዚህ ጊዜ የኮንስትራክሽን ሥራ ውስጥ በጥልቀት መግባታቸውን አስተውለው ይህን ዘርፍ መቀየር እንዳለባቸው አመኑ። በወቅቱ ተፈላጊ፣ አዋጭና አማራጭ ለሆነው ኢንዱስትሪና ሪልስቴት ትኩረት በመስጠት የዲዛይን ሥራን አቋረጡ። በሪልስቴት ዘርፍ ተቀጥረው በሰሩበት ወቅት ያካበቱትን ልምድ ተጠቅመው የመሥራት ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ ወደ ሥራው ሲገቡ ደስተኛ ነበሩ። በኢንዱስትሪው ዘርፍም እንዲሁ ከማማከር ጀምሮ የዲዛይንና የግንባታ ሥራን መሥራት ጀመሩ።
ሪልስቴትና ኢንዱስትሪን ትኩረት አድርገው መሥራት የጀመሩት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ በተለይም በኢንዱስትሪው ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል። ከሰሯቸው ሥራዎች መካከልም ድሬዳዋ ላይ በቀን 45 ሺህ ኩንታል ሲሚንቶ ማምረት የሚችል ፋብሪካን የሲቪል ሥራውን በአማካሪነት እንዲሁም በውስጡ ያሉትን የኮንስትራክሽን ሥራ መሥራታቸው በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።
ከዚህ ሥራ በኋላም ንብረት እያፈሩ የመጡ መሆና ቸውን ያነሱት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ ሥራቸውን የተመለከቱ የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ሥራ ይዘው መምጣቸውን ይናገራሉ። በመሆኑም ሥራቸውን ፈልገው የሚመጡ ድርጅቶችን በሙሉ እየተቀበሉ ውጤታማ እንዲሆኑ አስችለዋል። ለግለሰቦችም ይሁን ለግል ድርጅቶች በሚሠሩት ሥራ ሁሌም ተመስግነውና ዕውቅናን አትርፈው ይመለሳሉ።
ከኮንስትራክሽን ሥራቸው በተጓዳኝ የዲዛይን እና የማማከር ሥራን የሚሠሩት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ በአሁኑ ወቅት ደረጃ አራት ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ፈቃድ አላቸው። ደረጃውን ማሳደግ የሚቻል ቢሆንም ሥራው የሚፈልገው ደረጃውን ማሳደግ ሳይሆን ዕውቀትና ችሎታን ነው ይላሉ። በእስካሁኑ ጉዟቸውም የመንግሥት የሆኑ ሥራዎችን አልሰሩም። ለዚህም የጨረታ ሂደቱ ጤናማ አለመሆኑን በምክንያትነት አንስተዋል። ይሁንና አሁን ባለው አዲሱ መንግሥት ብልሹ አሰራር ተወግዶ በአዲስ ምዕራፍ ጥሩ ነገር ይኖራል የሚል እምነት አላቸው። እንደ ዕምነታቸው ከሆነም ከመንግሥት ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በስፋት ከተሰማሩባቸው የፋብሪካ ግንባታዎች መካከል ድሬዳዋ ውስጥ ድሬ ስቲል ሙሉ ለሙሉ የማማከርና የግንባታ ሥራን ሠርተው አጠናቅቀው ማምረት ጀምሯል። ምናልባትም በሀገሪቱ ትልቁ ብረት ፋብሪካ የሆነውና ቢሾፍቱ የሚገኘውን ሲ ኤን ዲ ኢ ብረታ ብረትንም እንዲሁ ሠርተዋል። እነዚህ ድርጅቶች ግዙፍ ከመሆናቸው የተነሳ ተጨማሪ ፋብሪካዎችን መገንባት ሲፈልጉ አብረው የሚጓዙት ኢንጅነር ደሳለኝ ናቸው። በመሆኑም የሲ ኤን ዲ ኢ እህት ኩባንያ የሆነውና ኤም ደብሊው ኤ ሀይ ቴክ ፕላስቲክ ፋብሪካን በኮዬ ፈጬ ገንብተዋል። ይኸው ድርጅት በሪልስቴት ዘርፍ ውስጥ የተሰማራ በመሆኑ በሪል ስቴቱም ተሳታፊ ናቸው።
ከእነዚህ በተጨማሪም ለቁጥር የበዙ ግዙፍ ፋብሪካዎችን አዲስ አበባ ከተማ ውጭ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የግለሰቦችን እና የግል ድርጅቶችን ሥራ ተዘዋውረው ሠርተዋል። በመሆኑም ኢንጅነር ደሳለኝ ያልተሳተፉበት ትላልቅ ፋብሪካዎች በሀገሪቱ አሉ ለማለት አያስደፍርም። በቅርቡም ወደ ምርት ሂደት የገባውን ታዳሽ ብረታ ብረት ፋብሪካን ጨምሮ ደብረማርቆስ ላይ የቀርከሃ ምርቶች ማምረቻን ከሰራተኞች መኖሪያ ህንጻ ጭምር እየገነቡ ይገኛሉ። በዲዛይን ደረጃ የተለያዩ የዱቄት ፋብሪካዎች፣ የሻይቅጠል ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከመኖሪያ ህንጻዎች ጭምር ሠርተዋል።
ከፋብሪካዎች ግንባታ በመለስም በሪልስቴት ዘርፍ በኮንስትራክሽን፣ በማማከርና በዲዛይን ሥራ የሚሳተፉ መሆኑን ያነሱት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ በኮንስትራክሽን ዘርፍ 96 አባወራዎችን የሚይዝና አስር ፎቆች ያሉት የኢስት አፍሪካ ሪልስቴትን ኮንትራክተር ሆነው ገንብተዋል። ዴታ ሪልስቴትንም እንዲሁ ከቦታ መረጣ እስከ ግንባታ ድረስ ሠርተዋል።
ስድስት ኪሎ የሚገኘው ባለ አስር ወለል ህንጻ ስኬት ሪልስቴትንም እንዲሁ ለመገንባት የቻሉ ሲሆን፤ አንድነት ፓርክ አካባቢ ከሚገኙት ህንጻዎች መካከል አንዱና እየተጠናቀቀ ያለው ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች እየገነቡ ያሉት ሪልስቴትንም በመገንባት ለፍሬ አብቅተዋል። ሪልስቴቶችን ከመገንባት በተጨማሪ በማማከር ደረጃም በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሪልስቴቶች አማክረዋል። ለአብነትም በ15 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ የኢስት አፍሪካ ሪልስቴት ሙሉ ለሙሉ ፕሮጀክት ማኔጅመንቱን ይዘው እየሠሩ ሲሆን፤ በተጨማሪም ምጥቀት ሪልስቴት፣ አልሙኒየም ሪልስቴት፣ ማገር ሪልስቴትና ሌሎችም ይገኙበታል። በዲዛይን ደረጃም እንዲሁ 35 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች ዲዛይን ሠርተዋል።
‹‹ሥራ የምሰራው ለብር አይደለም፤ ለብር ብዬ ባልሰራሁ ቁጥር ብር እራሱ ይከተለኛል›› የሚሉት ኢንጅነር ደሳለኝ ለሙያቸው ትኩረት ሰጥተው መስራት በመቻላቸው ስኬታማ መሆን ችለዋል። ብርም እነሆ እርሳቸውን ተከትላለች።
የማስተማርና የመጻፍ ተሰጥኦ ያላቸው ኢንጅነር ደሳለኝ በጉዟቸው ሁሉ የተማሩትን እና ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች በማስተላለፍ ሌሎች እንዲጠቀሙ ማድረግ ያስደስታቸዋል። ተማሪ ሆኖ ከእርሳቸው ዕውቀትን ማግኘት ላልቻለው እና በሥራ አጋጣሚ ወደ እርሳቸው ቀርቦ የማማከር ዕድሉን ላላገኘው የማህበረሰብ ክፍል መድረስ አለብኝ ብለው በማሰብ በሪልስቴት ዘርፍ መጽሐፍ ጽፈው አበርክተዋል። ይህም ሌላኛው ስኬታቸው ነው።
መጽሐፉን ከመጻፋቸው አስቀድመውም ይጎድለኛል ያሉትን ዕውቀት ለማሟላት ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ማስተር ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ተማሩ። ምክንያቱም ለሪልስቴት ተብሎ የሚሰጥ ትምህርት አልነበረምና ነው። ታድያ የመመረቂያ ጽሁፋቸውን በሪልስቴት ላይ አድርገው በሀገሪቱ ያለውን የዘርፉን ችግር በመፈተሽና መፍትሔ ያሉትን ለመጠቆም ጥረት አደረጉ። በመሆኑም የመመረቂያ ጽሁፋቸውን መነሻ በማድረግ ሪልስቴት ኢንቨስትመንት አስተዳደርና ግብይት የሚለውን መጽሐፍ ጽፈው ለገበያ አቅርበዋል።
በትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው “ነብር” የሚል ቅጽል ስም ያገኙት ኢንጅነር ደሳለኝ፤ ነብርነታቸው አብሯቸው የዘለቀ በመሆኑ ጠንካራና ትጉህ ሰራተኛ ናቸው። ያላቸውን ዕውቀት ሁሉ ሳይሰስቱ መስጠት በመቻላቸውም ብዙ አትርፈዋል። ሁለገብ የሚመስል የበርካታ ሙያዎች ባለቤት ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት በሪልስቴትና በኢንዱስትሪ ሥራዎች ላይ አተኩረው የሚሰሩ መሀንዲስ ናቸው።
የሥራ ዕድልን አስመልክቶም ከመቶ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚነት የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉ ሲሆን፤ በየጊዜው በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሠራተኞችም በኮንትራት ቀጥረው ያሠራሉ። ከዚህ ባለፈም አብረዋቸው ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞች እራሳቸውን ችለው ኮንትራክተር በመሆን የግል ሥራ እንዲሰሩ ከፍተኛ ድጋፍ ያደርጋሉ። የድጋፉ ተጠቃሚ ሆነው እራሳቸውን ችለው የሚወጡ ሰራተኞችም በርካታ ናቸው።
ኢንጅነር ደሳለኝ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች ሥራን በጥራት መሥራት በመቻላቸው ከ20 በላይ የምስጋና እና የተሳትፎ ምስክር ወረቀቶችን አግኝተዋል። በቀጣይም ከአዲሱ መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን ሰዎች ላይ በተለይም ወጣቶች ላይ በመሥራት ለሀገር ትልቅ አስተዋጽኦ ለማበርከት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። እኛም ዕቅዳቸው ተሳክቶ ሀገር አትርፋ ማየትን ተመኘን ሰላም!
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2014