ኢትዮጵያ ክብሯን ሳታስደፍር የኖረችው አባቶቻችን በከፈሉት ከፍ ያለ ዋጋ ነው። ውቅያኖስ አቋርጠው ፤ ድንበር ዘልቀው ሉዓላዊነቷን ሊደፍሩ ያሰቡትን ጠላቶቿን መክታ ድል የተቀዳጀችው በልጆቿ የተባበረ ክንድ ነው። በዚህም ሲዘከር የሚኖር ገድል፤ ለዜጎቿ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ህዝብ የተረፈ ታሪክ ሠርታለች።
ዛሬ ኢትዮጵያ በተስፋና በፈተና ውስጥ ነች። ተስፋዋ ሃያ ሰባት ዓመት በዘርኝነት እና በጥላቻ ወጥመድ ታስረው የነበሩ ህዝቦቿ ህብረ ብሄራዊ አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲጓዙ የሚያስችል አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መጀመሯ ነው። በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ተአማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂዳ አዲስ መንግሥት መስርታለች። ተስፋ ሰጪ ጅምሮችንም አሳይታለች።
በሌላ በኩል ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅም፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየት እና ዘረኝነት የተጸናወታቸው ከአብራኳ የወጡ ልጆቿ ሊያፈራርሷት እየታተሩ ናቸው። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከማሕጸኗ ተፈጥረው ጡቷን እየጠቡ ያደጉ በመሆናቸው ልጆቿ እንበላቸው እንጂ ግብራቸው እንኳ የእፉኚት ነው። እፉኚቶች ሲወለዱ የእናታቸውን ሆድ ቀደው ነው፤ እናታቸውን ገድለው እነርሱ ይኖራሉ። የከሃዲዎቹ ምግባርም ከዚህ የተለየ አይደለም።
እነዚህ ጥቅም ያሰከራቸው ቡድኖች ታዲያ ብልጭ ያለው የለውጥ ብርሃን ገመናቸውን የሚያሳይባቸው መሆኑን ሲያውቁ ፤ስርቆታቸውን የሚደብቅላቸውን ጨለማ ለማምጣት ነፍጥ አንስተው ኢትዮጵያን እየወጓት ነው። በዚህም ብቻ አላበቁ፤ በስልጣን ዘመናቸው ተላላኪ ሆነው ሲያገለግሏቸው ከነበሩ የውጭ ኃይሎች ጋር ተመሳጥረው በመሥራት ሰላሟን አደጋ ውስጥ ጥለዋል።
በእነዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ ከሀገር ውስጥ አሸባሪዎች እስከ ምዕራባዊያን ተመሳጣሪዎቻቸው ድረስ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያልተሠሩ ሥራዎች የሉም። በተለይም የዴሞክራሲ፣ የሰላም ፣ የፍትህ አቀንቃኝ ነኝ የምትለው አሜሪካ በህዳሴ ግድብና በቀጣናው የራሷንና የሌሎችን ፍላጎት ለማስጠበቅ እየፈጸመች ያለው ደባ አሳፋሪም፤ አሳዛኝም ነው።
አሜሪካ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ነኝ እያለች ከማንም በላይ ድምጿን ከፍ አድርጋ ትጮሃለች:: በዕርዳታ፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ስም በገባችባቸው ሀገራት ሁሉ ዋንኛ የችግር ምንጭ እየሆነች ለከፋ ችግር ስትዳርጋቸው ኖራለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ጉዳይ የያዘችው አቋምም የዚሁ ሴራዋ አንዱ ማሳያ ነው። አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እውነታ እንዳላየና እንዳልሰማ ትሆናለች፤ ይልቁንም ኢትዮጵያ የራሷን ጉዳይ በራሷ እንዳትፈታ በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ በመግባት ተሰሚነቷን ተጠቅማ ተጽዕኖ ልታሳድርባት እየሞከረች ነው። ያም ብቻ አይደለም፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ሳይቀር የእኩይ ዓላማዋ ማስፈጸሚያ እንዲሆኑ ትዘውራቸዋለች።
ይህንን እውነታ በተጨባጭ ለማየት አንዳንድ ጥቄዎችን ማንሳትነ ተገቢ ነው። የአሜሪካ መንግሥትም ይሁን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩ አሸባሪዎች ለሚፈጽሙት ሰብዓዊ መብት ጥሰትና ወንጀል ጆሯቸውን መስጠት ያልፈለጉት ለምንድነው? ሉዓላዊት በሆነች ሀገር ጣልቃ እየገቡ መንግሥት ላይ ጫና የሚያሳድሩት ለምንድነው ? በትግራይ ክልል ለተፈናቀሉና ለተጎዱ ዜጎቻችን የተቆረቆሩትን ያህል በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉልና በሌሎችም አካባቢዎች ግፍ ስለተፈጸመባቸው ዜጎቻችን መቆርቆር ያልቻሉት ለምድነው ? እነ ሲኤን ኤን፣ ቢቢሲና አልጀዚራን የመሳሰሉ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች የሽብር ቡድኖቹ በንጹሐን ላይ የሚያደርሱትን ግፍና ኢሰብዓዊ በደል ማጋለጥ ያልፈለጉት ለምንድን ነው? የአሸባሪው ድምፅ መሆን ለምን ፈለጉ? ምዕራባውያኑ ለምንድነው ህዝብ ከመረጠውና ከወደደው መንግሽት ጎን መቆም ያልፈለጉት?
አሜሪካ እንደ አልሻባብና ቦኮሃራም የመሳሰሉትን አሸባሪ ብላ ከፈረጀች ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩትን የህወሓት ጽንፈኛ ቡድንና ሸኔን አሸባሪ ለማለት ለምን አልደፈረችም ? እውነት አሜሪካ አሸባሪ ያለቻቸው ቡድኖች በሰው ልጅ ላይ የፈጸሙትን ግፍ ያህል አሸባሪዎቹ የትህነግና የሸኔ ቡድኖች ሳይፈጽሙት ቀርቶ ነው? አይደለም። ለዚህ የጋሊኮማን፣ የማይካድራን፣ የጭናን፣ የአጋምሳን፣ የቆቦን ጭፍጨፋዎች ብቻ ማስታወስ ይበቃል። ሸኔ በወለጋ ዞን በንጹሐን ላይ የሚፈጽመው ጭፍጨፋም የዚሁ አካል ነው።
አሸባሪው ህወሓት አሁንም በንጹሐን ላይ ግፍና በደሎችን እያደረሰ ነው ፤ ግፉ ከሰው አልፎ ወደ ሚመገባቸው እንሰሳትና አዝርዕትም ተሸጋግሯል። በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶችን መዝብሯል፤ ሃይማታዊ ተቋማትን አውድሟል፤ ምዕራባውያኑ ለምን ይህን ሁሉ ወንጀል ከሚፈጽም ቡድን ጋር እጅና ጓንት መሆን ፈለጉ ?
እውነቱ ግልጽ ነው ፤ ዛሬ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ተስፋን አሻግረው እየተመለከቱ ነው። ይህንን አሻግረው የሚያዩትን ተስፋቸውን በእጃቸው ለማስግባት ከፍ ባለ መነቃቃት ላይ ይገኝሉ። ይህ መነቃቃት ብዙዎችን አስደንግጧል። ለጥቁር ህዝቦች አዲስ የተስፋ ብርሃን እንደሚፈነጥቅም ተስፋ እየተደረገበት ነው።
ይህ አይቀሬ ታሪካው እውነታ ያስደነገጣቸው ኃይሎች ከውስጥ ጠላቶቻችን ጋር በመቀናጀት ሀገርን አስከ ማፍረስ የሚዘልቅ ሴራ ሸርበው እየሠሩ ነው። በሀገሪቱ አሻንጉሊት መንግሥት አስቀምጠው ያሻቸውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
መላው ህዝባችንም እስከ ሀገር ማፍረስ የዘለቀውን ሴራ ለመቀልበስ እጅ ለእጅ ተያይዞ ጠላቶቹን የመመከት፤ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማስከበር ወሳኝ የህልውና ዘመቻ ላይ ይገኛል።
ይህ የህልውና ዘመቻ ለመንግሥት የሚተው ሳይሆን የመላውን ህዝባችንን ሁለንተናዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። በዚህ አስቻጋሪ ወቅት እያንዳንዱ ዜጋ በሀገሩ የልማትም ይሁን የሰላም ጉዳይ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ይጠበቃል። በተለይም ለሰላምና ለሉዓላዊነታችን ጉዳይ መላው ህዝባችን ሆ ብሎ መነሳት ይኖርበታል።
አሸባሪው ቡድን ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ዘልቆ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሰው ልጅ ላይ ይፈጸማሉ ተብለው የማይገመቱ ግፎችን ሲሠራ ሰንብቷል፤ አሁንም ይህንኑ ተግባሩን አጠናክሮ ቀጥሎበታል።
በአንድ በኩል የፌዴራል መንግሥት ጦርነት ከፈተብኝ እያለ የድረሱልኝ ጥሪ እያሰማ ዓለምን ያደነጋግራል፤ ወትሮም የሴራው አካል የሆኑት አሜሪካና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ይህንኑ ያስተጋቡለታል። በሌላ በኩል አራት ኪሎን ለመቆጣጠር ቀናት ብቻ እንደቀሩት እያወራ ለደጋፊዎቹ ተስፋ ይሰጣል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ተለዋዋጭ መልክ ያለው ነው። ንጹሐን ላይ ግፍ እየሠራ ፤ አንሰሳትን እየረሸነ፣ የሃይማኖት ተቋማትን እያወደመ፤ እየዘረፈ ተበዳይ ሆኖ ይቀርባል። ሲፈልገው ሀገር እንደሚያፈርስ፣ ኢትዮጵያን እንደሚበታትን ፣ አደባባይ ወጥቶ ይፎክራል፤ የባንክ ፣ ቴሌ፣ የመብራት፣ የውሃ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን እያወደመ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ሰላም ፈላጊ ሆኖ በመቅረብ ዓለምን አማልዱኝ ብሎ ይጮሃል።
ቡድኑ በንጹሐን ዜጎች ላይ ታይቶ የማይታወቅ ግፍ ሲፈጸም ከሀገር ውስጥ ሚዲዎች በስተቀር ትንፍሽ የሚል አካል አይኖርም። እሱ ጩኸት ሲያሰማ ግን አብሮት የማይጮህ የለም። ይህ በውሸት ተጸንሶ በውሸት ያደገ ቡድን ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ህዝብ ሲያታልል የነበረበትን ስልቱን አሁን ዓለምን ለማታለል እየተጠቀመበት ነው። ዓለም እውነታውን እስኪረዳ ድረስ ሊጠቀምበት ይችል ይሆናል። እውነትና ንጋት እያደር ስለሚገልጥ፤ ዓለም የዚህን ቡድን ገመና የሚያወቅበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ለማንኛውም አንድ ሆነን ጠላቶቻችንን የምንመክትበት ጊዜ አሁን ነው። የሀገራችንን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ የመኖር ዋስትናችንን ማረጋገጥ ይገባናል። ህዝባችንን ሊበታትኑ፤ ሀገራችንን ሊያፈርሱ የሚረባረቡትን ማስቆም የምንችለው አንድ ሆነን በመታገል ነው። የውጭም የውስጥም ጠላቶቻችን ያሰቡትን እንዳያሳኩ የምናርጋቸው አንድ ሆነን ስንቆም ነው።
ያየነውን የብርሃን ጭላንጭል አጥፍተው ያለፈውን የጨለማ ዘመን ሊያመጡብን እየተፍጨረጨሩ ላሉ አሸባሪዎች ዕድል አንስጣቸው። አንድ ላይ ቆመን ሀገራችንን እንታደጋት፤ ድላችንን እናፋጥን ፤ ልማታችንን እናረጋግጥ። ኢትዮጵያ ትጣራለችና ክንዳችንንና እውቀታችንን አስተባብረን እንቁምላት።
ሜላት ኢያሱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2014