ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ይነገራል። ለዚህ ደግሞ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። ብዙ ወደኋላ መሄድ ሳይጠበቅብን በአዲስ አበባና እምቅ የቱሪዝም ሃብት ባላቸው አካባቢዎች ላይ “መዳረሻዎችን” ለማልማት የሚደረገው ጥረት መመልከት ይቻላል። በቀጥታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ባሻገር በጠቅላይ ሚኒስትሩ የበላይነት እጅግ ግዙፍ የሆኑ “የቱሩዝም ልማት” ስራዎች እየተከናወነ ነው። ግለሰቦች ማህበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የዚሁ ጥረት አካል ናቸው።
በዋናነት በመንግስት በኩል የቱሪዝም ዘርፉን ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራና የውጭ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። በዚሁ መሰረት የቱሪዝምን ዘርፍ ለማልማት ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በተጨማሪ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትና የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የተባሉ ተቋማት ተመስርተው ሲሰሩ ቆይተዋል። ላለፉት ጥቂት ዓመታት የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት በቀድሞው የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራ የነበረ ሲሆን የተቋቋመው ዘርፉን ወደላቀ ደረጃ የማሸጋገር ዓላማ አንግቦ ነበር።
ከላይ ካነሳነው የመንግስት ጥረት ባሻገር ደግሞ ግለሰቦችና የግል ካምፓኒዎች ዘርፉን በመቀላቀል ተደማሪ አቅም ለመፍጠር ይንቀሳቀሳሉ። ከነዚህ ውስጥ ፕሮሞተሮች፣ የቱሪዝም ማርኬቲንግ ባለሙያዎች አማካሪዎችና የሆቴልና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ ባለሃብቶች እንዲሁም የአስጎብኚ ማህበራት ይገኙበታል። ከነዚህ መካከል ደግሞ ከሰሞኑ ዘርፉን ለማነቃቃትና ህብረት ለመፍጠር እየሰሩ የሚገኙ “የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚዎች ማህበር የተመሰረቱበትን አንደኛ ዓመት በልዩ የፎቶ አውደ ርእይ አክብረውት አልፈዋል።
የፎቶ አውደርዕይና የምስረታ በዓል
የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር የተመሰረተበትን አንደኛ ዓመት አክብሯል። “ኢትዮጵያን በቱሪስት አስጎብኚዎች ዕይታ” በሚል ርዕስ የፎቶ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ሙዚየም ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ እለት ተከፍቷል። አውደ ርዕይ መስከረም 30 ቀን እስከ ጥቅምት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ለህዝብ ክፍት ሆኖ ቆይቷል። የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ካሳ “የአውደርዕዩ ዓላማ ኢትዮጵያን ማስተዋወቅና አስጎብኚው ከማህበረሰቡ ጋር ያለው መስተጋብር ምን እንደሚመስል ማሳየት ነው” ብለው ባለሙያዎች ያሰባሰቧቸውን ፎቶዎች ለእይታ በማቅረብ በቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃትን በመፍጠር ገቢ ማግኘት መሆኑንም ገልጸዋል። ፕሬዚዳንቱ ለመርሃ ግብሩ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
አውደ ርዕይውን የቱሪዝም መዳረሻና መሠረተ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው የተሾሙት የቱሪዝም ኢትዮጵያ የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ፣ የአማራ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ እና የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አቢዩ ተሰማን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶች ታድመውበታል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2014 ዓ.ም