ተወልዶ ባደገባት የወሊሶ ከተማ ከወላጆቹ ጋር ህይወትን ተጋርቷል። ልጅነቱን እንደእኩዮቹ ለማሳለፍ አካባቢውን መስሎ ነው ያደገው። ቤተሰቦቹ ሀብታሞች አልነበሩም። እሱን አስተምረው ወግ ማዕረግ ለማድረስ ግን የአቅማቸውን ሞክረዋል።
አመንቴ ዕድሜው ከፍ ሲል ትምህርት ቤት ተላከ። ቤተሰቦቹ ያሻውን እያደረጉ ፣ የጎደለውን እያሟሉ አለንልህ አሉት። ከእኩዮቹ ጋር ትምህርት ቤት መዋሉ ከልብ አስደሰተው። ጠዋት ወጥቶ ሲመሻሽ የሚመለስበት መንገድ አላደከመውም። ነገን እያሰበ፣ መልካሙን ሲመኝ፣ውስጡ ረካ ፣ በትምህርቱም በረታ ።
አንድ ብሎ የጀመረው ክፍል በየዓመቱ እየጨመረ ስድስተኛ ላይ አደረሰው። የደረሰበት ክፍል ለቀጣይ ዓመታት መሰረት የሚጥልበት ሆኖም በጥንካሬው ገፋበት ። እንዳሰበው ስድስተኛ ክፍልን በድል ተሻገረ። አዲስ ዓመት እንደባተ ለሰባተኛ ክፍል አዲስ ምዕራፍ መዘጋጀት ነበረበት።
አመንቴ አሁን አዲሱን ዓመት እንዳለፉት ጊዜያት ደብተር በማዘጋጀት አልተቀበለውም። ሸፍቶ የከረመው ልቡ አርቆ ማሰቡን ቀጠለ። በጀመረው ዓመት ትምህርቱን መቀጠል አላሻውም። ካደገበት ቀዬ ከኖረበት መንደር ርቆ መሄድን አስቧል። ከራሱ ሲመክር መቆየቱ ለውሳኔ አላዘገየውም።
አንድ ማለዳ ጓዙን ሸክፎ የተነሳው ወጣት ወደ መናሀሪያው አቀና ። አውቶቡሶቹን ሲመለከት መድረሻውን አላጣውም ። ካሰበው ስፍራ ለሚያዘልቀው መንገድ ትኬቱን ቆርጦ ተሳፈረ። አዲስ አበባ አብሮ አደግ ባልንጀሮች አሉት። እነሱ ዘንድ ለማረፍ እንደማይቸገር ያውቃል። ከዓመታት በፊት አካባቢውን የለመዱት ወጣቶች ራሳቸውን ችለው ሌሎችን እንደሚረዱ ሰምቷል።
አዲስ አበባ …
አዲስ አበባና አመንቴ ለመተዋወቅ አልተቸገሩም። በእንግድነት የተቀበሉት ወዳጆቹ ዙሪያ ገባውን አላመዱት። አመንቴ ከእነሱ ሲገናኝ ታላቅ እፎይታ ተሰማው። ትምህርቱን አቋርጦ የመጣበትን ዓላማ እያሰበ ፣መልካሙን ሁሉ ተመኘ ። ዛሬን በርትቶ ከሰራ እንደሌሎቹ ይለወጣል። ኑሮው ተቀይሮ ፣ በቂ ጥሪት ቋጥሮ ህልም ውጥኑ ይሳካል ።
ውሎ ሲያድር ለቀጣይ ህይወቱ ሰርቶ የሚያድርበትን እንጀራ ፈላለገ። ፈጥኖ የተገኘለት ውሎ የጉልበት ስራ ነበር። አመንቴ በጉልበቱ ደክሞ ለማደር አላወላዳም። ገንዘብ በሚያስገኘው ሁሉ እየተገኘ ላቡን ማንጠፍጠፍ ያዘ። ለቀናት የቆየበት ስራ የዕለት ጉርሱን ሸፍኖ ለኪሱ ተረፈው።
አመንቴና የቀን ስራ ውሎ በወጉ ተላመዱ ። ድካሙ ከክፍያው ባይገጥምም ለጉሮሮው ያህል አላጣም። በየቀኑ እየለፋ ከሚያገኘው ገቢ ጥቂት ቆጥቦ ቤት ተከራየ። ራሱን ሲችል ቢደሰትም ኑሮ እያደር ከበደው። ሲያገኝ እየበላ እጅ ሲያጥረው እየተቸገረ ቀናት ተገፋ።
የአዲስ አበባ ህይወት እንደጅማሬው ያልቀናው ወጣት ስራና ገቢው አልገጥም ቢሉት ተቸገረ። እንደምንም ኑሮን ለማሸነፍ መፍጨርጨሩ አልቀረም። ሆዱና የመኖሪያው ወጪ ከሚያገኘው ገቢ ጋር አልተራመደም። ችግርና ርሀብ ፈተኑት። ቀጣዩን ፈተና መሻገር አልቻለም። ጓዙን ጠቅልሎ አገሩ ከመግባት አማራጭ ባለው ርምጃ ወሰነ። ከውሳኔው በኋላ ራሱን ያገኘው ጎዳና ላይ ሆነ ።
በጎዳና…
አሁን ላይ አመንቴ ህይወት በሌላ መንገድ አቁማዋለች ። የጎዳና ኑሮን መላመድ ከጀመረ ጊዜያት ተቆጥረዋል። የጎዳና ህይወት ይከብዳል። ቀን ጸሀዩ ሌት ብርዱ አያስተኛም። ከሌሎች ጋር መስሎ መኖር ቀላል የሚባል አይደለም። በየምክንያት፣ በየሰበቡ መጣላት ፣መቃረን ያጋጥማል ። የጎዳና ላይ ኑሮ አያስከብርም ።
አመንቴ ይህን ህይወት ከጀመረ ወዲህ ስራ የሚባል አልቀናውም። እሱም ቢሆን እጆቹን ለልመና መዘርጋት ልምዱ ሆኗል። በየቀኑ ከጓደኞቹ ጋር ከየሆቴሉ በሚወስዱት ትራፊ ምግብ ውለው ያድራሉ። ሆዳቸው ሲሞላ ጉልበታቸውን ለስራ ማድከሙ፣ አይታያቸውም።
ብዙ ጊዜ ለጎዳናዎች የበርካቶች ዓይን በጎ አይደለም። በጥርጣሬ መታየቱ ፣ አለመታመኑ የተለመደ ነው።
አመንቴ ጎዳና ከወጣ በኋላ እንዲህ አይነቱን አጋጣሚ አልፎበታል። ጥቂት ቆይቶ ግን መሰሎቹን ሊጣመር ግድ አለው። ከእነሱ ተስማምቶና ተሻርኮ ፣ የሚፈጽመውን ንጥቂያ ገፋበት።
እነ አመንቴ አንዳንዴ ከአላፊ አግዳሚው ያገኙትን ነጥቀው ይሮጣሉ። ከእጃቸው የገባውን በርካሽ ሸጠውም ለፍላጎታቸው ያውላሉ። በእነሱ ህብረት ሲጋራ ማጤስ ፣ቤንዚንና ማስቲች መሳብ የተለመደ ነው። ለዚህ ፍላጎት ማሟያ የሚፈጽሙት ንጥቂያም እንደአመቺነቱ ይከወናል።
አንዳንዴ አመንቴ ከመሰሎቹ በየምክንያቱ ይጣላል። ችግሩ ባስ ባለ ጊዜም ጠባቸውን እርቅና ስምምነት አይፈታውም። አንገት ለአንገት ተያይዘው ፣ ለድብድብ ይደርሳሉ። አመንቴ በእንዲህ አይነቱ ግብግብ ያለፈበት ጊዜ በርካታ ነው ።
አንድ ቀን ግን ከተጋጣሚው ያደረገው ድብድብ አየለ። ገላጋዮች መሀል ቢገቡም እነሱን አልፎ ጓደኛው ላይ ጉዳት አደረሰ። በዚሁ ምክንያት ለክስ የቀረበው አመንቴ በዋስ ይፈታ ዘንድ የገንዘብ መቀጮ ተጣለበት። ለድርጊቱ የሚገባውን ተቀጥቶ ማስጠንቀቂያውን ተቀብሎ ከእስር ተፈታ። ከእስር መልስ የቀደመ ልማዱ አብሮት ነበር።
መሀመድ ያሲን…
ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ኑሮ የጀመረው መሀመድ የጎዳና ላይ ኗሪ ከሆነ ጥቂት ቆይቷል፡፤ተወልዶ ያደገው ጅማ ‹‹ቁጢ›› ከምትባል የገጠር ቀበሌ ነው። እስከ ዘጠነኛ ክፍል ያለማቋረጥ ተምሯል። ወላጆቹ ገና በጠዋቱ ትምህርት ቤት ሲልኩት በእሱ ላይ ታላቅ ተስፋ ነበራቸው። ተምሮ፣ ራሱን ለውጦ፣ አገር ወገን ይጠቅማል በሚል።
መሀመድ ልጅነቱን በትምህርት እንዳጋመሰ ወላጅ አባቱ በድንገት ታመሙ። ጊዜያት ያስቆጠረው የአባወራው ህመም አንድ ቀን በሞት ተቋጨ። ይህ ክፉ አጋጣሚ የመሀመድን ህይወት ፈጥኖ ሊለውጥ ግድ አለ። መሀመድ ከመንገዱ ተሰናከለ ፣ብዙ ያለመበትን ጅምር ትምህርቱን አቋረጠ። ተመልሶ ትምህርት የመቀጠል ፍላጎት ያጣው ወጣት ቀጣይ ዓላማው ከሰፈር ቀዬው መውጣት ብቻ ነበር ። እንዳሰበው ሆኖ አዲስ አበባ ለመግባት ወሰነ።
አዲስ አበባ ያገሩ ልጆች አሉ። በርካቶቹ በጉልበት ስራ አዳሪዎች ናቸው። ከነዚህ መሀል ጥቂቶቹን የሚያውቀው መሀመድ አዲስ አበባ ‹‹ወረገኑ›› ከተባለ ስፍራ አገኛቸው። መሀመድን በእንግድነት የተቀበሉት ወዳጆቹ አላሳፈሩትም። እነሱን መስሎ ያድር ዘንድ ያሉበትንና ያለፉበትን የስራ መንገድ አመላከቱት።
ወረገኑ ለመሀመድ አልቆረቆረውም። ስራ እንደጀመረ ቤት ተከራይቶ ህይወትን ቀጠለ። እንደአቅሙ የሚከፍልበት ቤት ለድካሙ ማረፊያ ሆነለት። እያደር ያጠራቀመው ገንዘብ ነገን የተሻለ እንደሚሆን አሳየው። መሀመድ በጉልበቱ አዳሪ ሲሆን ብርታትን ተላበሰ።
ከዕለታት በአንዱ ቀን በሰፈሩ የተፈጠረው አጋጣሚ የመሀመድን የህይወት አቅጣጫ ለመቀየር ምክንያት ሆነ። ‹‹ወረገኑ›› የተባለው መንደር በአፍራሽ ግብረሀይሎችእጅ ወደቀ። ይህኔ እሱን ጨምሮ በርካቶች አካባቢውን ሊለቁ ከስፍራው ሊርቁ ግድ ሆነ። ይህ ድንገቴ አጋጣሚ ለመሀመድ ከባድና ፈታኝ ሆነ። ቤቱ ሲፈርስ መጠጊያና መውደቂያ ዘመድ አጣ። የተሻለ ቤት ለመከራየት በቂ ገንዘብና አቅም አልነበረውም።
ጥቂት ቀናት በስራ ሲንከላወስ የቆየው ወጣት ቀጣይ ዕጣ ፈንታው ሲያስጨንቀው ቆየ ። ከቀናት በኋላ የደረሰበት ውሳኔ ከጎዳና ጥግ ላስቲክ ወጥሮ ህይወትን መግፋት ሆነ። መሀመድ ጎዳና ማረፍ ከጀመረ ወዲህ ስራ መስራትን አቆመ። እሱን መስለው የሚያድሩትን ተመሳስሎ ለመኖር ጊዜ አልፈጀበትም።
ጓደኝነት…
አመንቴና መሀመድ ጎዳና ካገናኛቸው ወዲህ አብሮነታቸው ቀጥሏል። ብዙ ጊዜ አብረው ማሳለፍ ልማዳቸው ነው። ሲርባቸው ትራፊ ለማምጣት ከሆቴሎች ደጃፍ ይገኛሉ። ነጥቀው ማምለጥ ሲፈልጉ አይለያዩም። አንዳቸው እየቃኙ፣ አንዳቸው ነጥቀው ያመልጣሉ። የሚያገኙትን ጉዳይ በጋራ ተካፍለው ስለነገ ሲያቅዱ ሀሳባቸው አንድ አይነት ነው። ከሲጋራ ጀምሮ በእኩል የሚጋሩት ስሜት አነጣጥሏቸው አያውቅም። ሚስጠራቸውን ጠብቀው የሚፈጽሙትን ወንጀል ‹‹ሙያ በልብ›› ማለት ከጀመሩ ቆይተዋል።
ታህሳስ 9 ቀን 2004 ዓ.ም
ይህ ቀን ለሁለቱ ባልንጀሮች የተለየ አልነበረም። እንደወትሮው ከላስቲክ ቤታቸው ከሱስ ከልምዳቸው ጋር ውለዋል። ቀን የቀማመሱት እህል ውሀ በቂያቸው አልነበረም ። አንዳንዴ እስከ አዳር የሚያዘልቃቸውን ምግብ ያገኛሉ። አንዳንዴ ደግሞ ከነጭራሹ ሳይቀምሱ መዋላቸው የተለመደ ነው።
አመሻሹን ከአንዱ ሆቴል ብቅ ብለው የምግብ ትራፊ ማምጣት እያሰቡ ነው። እግረ መንገዳቸውን ስራ የሚሉትን ንጥቂያ ካገኙ ዓይናቸውን አያሹም። ለዚህ ሀሳብ እንዲያመች የሰአቱን መምሸት ተስማምተውበታል። ጊዜውን ከላስቲክ ቤታቸው አሳልፈው ወዳሰቡት ለመሄድ ተዘጋጅተዋል።
አሁን ጊዜው ከምሽቱ አራት ሰአት እያለ ነው። ከሆቴሉ ደጃፍ የቆሙት አመንቴና መሀመድ ትራፊ ምግብ እንዲሰጣቸው ፌስታላቸውን ይዘው ቆመዋል። ገርጂና አካባቢው ጭርታ እየዋጣው ነው። አብዛኞቹ የሆቴሉ እንግዶች ጉዳያቸውን ጨርሰው ስፍራውን ለቀው መውጣት ጀምረዋል። ጓደኛሞቹ ከበራፉ ቆመው የትራፊውን መውጣት እየጠበቁ ነው።
ድንገት የባልንጀሮቹ ዐይኖች ከአንድ መንገደኛ ላይ አረፈ። ሰውዬው ሞቅ እንዳለው ያስታውቃል። በአንድ እጁ ሲጋራ እያጤሰ በሌላው እጁ ሞባይሉን ይዟል። አመንቴና መሀመድ ዓይናቸውን ሳይነቅሉ አፈጠጡበት።
ጥቂት ቆይቶ በእጅ ስልኩ መነገጋር ጀመረ። ሁለቱም ሰውዬው ስለሚያወራው ጉዳይ መስማት አላስፈላጋቸውም። በእጁ ያለውን ሞባይልና ሲጋራ ጠጋ ብለው አስተዋሉ። ሞባይሉ ደህና ዋጋ የሚያወጣ መሆኑ አልጠፋቸውም። መንገዱን ይዞ ወደፊት መራመድ ሲጀምር በአጭር ርቀት ተከተሉት።
የሲጋራው ጢስ በንፋስ እየተመራ ለአፍንጫቸው ደረሰ። አሁንም ጨለማውን ተተግነው ከጀርባው ተከተሉት። ሰውዬው በስልክ ማውራቱን ቀጥሏል። እየተጣደፉ አጠገቡ ደረሱ ። ሰውዬው ኮቴ ቢሰማው ድንገት ዞር ብሎ አስተዋላቸው። ይህኔ ሁለቱም ተጣድፈው የያዘውን ሲጋራ እንዲሰጣቸው ጠየቁት። አላመነታም። ጥቂት ብቻ የሳበለትን ሲጋራ ሳያጠፋ ለአንዳቸው አቀበለና መንገዱን ቀጠለ ። ባልንጀሮቹ ሲጋራውን ተቀባብለው እያጤሱ በዓይናቸው መናበባቸውን ያዙ ።
የፊትና ኋላው ጉዞ ቀጠለ። የሁለቱም ዓይኖች ከሰውዬው እጅ ላይ ያለውን ሳምሰንግ ሞባይል ለመንጠቅ ተዘጋጀ። ጊዜው እየገፋ ነው። መንገደኛው ጨለማው ውስጥ እስኪገባ የቸኮሉት ሁለቱ የቦታውን አሳቻነት ሊጠቀሙበት ተጣድፈዋል።
ወደ ቦሌ አፓርታማ ሲቃረቡ አመንቴ ከሰውዬው የተቀበለውን ሲጋራ እያጤሰ ከጎኑ መራመድ ጀመረ። ሰውዬው ቀና ብሎ ተመለከተው። ከደቂቃዎች በፊት ሲጋራ የሰጠው ወጣት መሆኑን ሲያውቅ ተረጋግቶ ያወራው ጀመር። ከእነሱ ጀርባ መከተሉን የቀጠለው መሀመድ ምልክት እስኪሰጠው እየጠበቀ ነው።
ጥቂት ቆይቶ ሁሉም ወደጨለማው አቅጣጫ ዘለቁ። ይህኔ አመንቴ የሰውዬውን እጅ እንደመጨበጥ ብሎ ያዘው። ይህን ያስተዋለው መሀመድ ከመሬት ድንጋይ አንስቶ ጭንቅላቱ ላይ መታው። ወዲያው በቁመናው ድፍት ያለው ተጓዥ ራሱን ስቶ በግንባሩ ወደቀ ። ከወደቀው መንገደኛ ኪስ የገቡት ባልንጀሮች እየተጣደፉ ሳምሰንግ ሞባይሉንና የኪስ ቦርሳውን አወጡ። ከአንደኛው ኪስ ያገኙትን አስር ብርም ወደራሳቸው ኪስ አስገቡ። መንገደኛውን ከመንገድ ጥለው ከሚያድሩበት የላስቲክ ቤት ሲደርሱ ጊዜው የለሊቱ አጋማሽ ላይ ነበር።
በማግስቱ…
አሁን የንጋት ወፎች መንጫጫት፣ መንገደኞች ወደጉዳያቸው መውጣት ጀምረዋል። ከአንድ ስፍራ በልቡ ተደፍቶ የወደቀው ሰው የብዙዎችን ዓይን እየሳበ ነው። ሁኔታው ያስደነገጣቸው አንዳንዶች ጠጋ ብለው ተመለከቱት። እየተንቀሳቀስ ፣ እየተነፈሰ አይደለም። ፈጥነው ለፖሊስ ጠቆሙ።
በአረቄ ቤቱ…
ወጣቱ ከአንድ ቀን በፊት ሞባይሉ በመጥፋቱ ሲበሳጭ አድሯል። በማግስቱም ይህን ስሜት እንደያዘ ከዘመዱ አረቄ ቤት ጎራ ብሏል። እየደጋገመ የሆነበትን ሲያወራ የሰሙት አመንቴና መሀመድ ቀረብ ብለው ሞባይል እንደሚሸጡ ነገሩት። ወጣቱ በአጋጣሚው ተገርሞ ዋጋውን ጠየቃቸው። አንድ ሺህ ስምንት መቶ ብር አሉት ። ደግሞ ጠየቃቸው። በአንድ ሺህ ብር ተስማሙ።
የፖሊስ ምርመራ…
የሟችን አስከሬን አንስቶ ተጠርጣሪዎችን ማሰስ የጀመረው ፖሊስ የእጅ ስልኩን የገዛውን ወጣት በቁጥጥር ስር ለማዋል ጊዜ አልፈጀበትም። ወጣቱ በፖሊስ ቃሉን ሲሰጥ ከሁለቱ ባልንጀሮች እጅ በአንድ ሺህ ብር መግዛቱን አልደበቀም። መርማሪ ፖሊስ ዋና ሳጂን መንግስቱ ታደሰ በወንጀል መዝገብ ቁጥር 651 /10 ቃሉን መዝግቦ ሰዎቹን እንዲጠቁም ጠየቀው። ወጣቱ አላንገራገረም። ይገኙበታል ከተባለ ስፍራ በመውሰድ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አደረገ።
ውሳኔ…
ነሀሴ 5 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የልደታው ከፍተኛ ፍርድ ቤት በከፍተኛ የውንብድና ወንጀል ክስ ለተመሰረተባቸው ሁለት ግለሰቦች የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮው ተገኝቷል። ፍርድ ቤቱ ጓደኛሞቹ በፈጸሙት የግድያ ወንጀል ጥፋተኛነታቸውን አረጋግጧል። በዕለቱ በሰጠው ውሳኔም እያንዳንዳቸው እጃቸው ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራ ስድስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2014