የሰው ልጅ ህልውናውን ካገኘባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ሀሳብ ነው። ህልውናውን ከሚያጣባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ደግሞ የሀይል የበላይነት ነው ይባላል። ሀሳብና ሀይል ሆድና ጀርባ ናቸው። ሀሳብ በሀይል ሲፈርስ፣ ሀይል በሀሳብ ይገነባል። ሀሳባችሁን በሀይል ሳይሆን ሀይላችሁን በሀሳብ እንድትገነቡ እያሳሰብኩ ወደ ትዝብቴ ልለፍ።
ሀሳብና የሰው ልጅ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት መልኮች ናቸው። ሀሳብ የሌለው ሰውነት ማር እንደሌለው ቀፎ ነው። ሀሳብ የሌለው ህላዊ ከእንስሳዊ ባህሪ በምንም አይለይም። ሀሳብ ይሄን አለም ውብ ያደረገ የስልጣኔ ፋና ወጊ ነው። ሀሳብ በሰው ልጅ መካከል የኑሮ ልዩነትን የፈጠረ የሰውነት አልፋና ኦሜጋ ነው።
የሰው ልጅ ከሀሳብ ተለይቶ አያውቅም። እየኖርን ያለንው አነሰም በዛም በሀሳብ ነው። ከትላንት ዛሬን ያየነው በብዙ ሀሳብ ውስጥ አልፈን ነው። ከዛሬ ወደ ነገ የምንሄደውም በሀሳብ ሰረገላ ላይ ተሳፍረን ነው። የእኛ የሆኑ ማናቸውንም ነገሮች የምንስበው በሀሳብ ማግኔት ነው። ባጠቃላይ ህይወታችን በሀሳብ የታጠረ ነው እያልኩ ነው።
ትልቁና ዋናው ነገር ምንድነው የምናስበው የሚለው ነው? እዚህ ጋ ልብ እንድትሉልኝ የምሻው አንድ ነገር ሁሉም ሀሳብ ጠቃሚ እንዳይደለና በምናስበው የሃሳብ ጥራት ልክ ህይወታችን፣ ነጋችን የሚመራ መሆኑን ነው።
አንዳንዶች በሀሳባቸው ሌሎችን ያጠምዳሉ፤ ለሌሎች ጉድጓድ ይምሳሉ። አንዳንዶች በሀሳባቸው ለሌሎች የጽድቅ መንገድ ይሆናሉ፤ ሌሎችን ይባርካሉ። እናንተ ምን አይነት ናችሁ? በውስጣችሁ የሚመላለሰው ሀሳብ ምን አይነት ነው? በሀሳባችሁ ውስጥ ለሀገር የሚሆን ምን አላችሁ?
ሀገር አስተሳሰብ ናት። ሀገር የእኔና የእናንተ መልክ ናት። በብዙ የሀሳብ ሂደት ተላቁጣ የምትገነባ የእኔና የእናንተ የሀሳብ ውጤት ናት።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ በትላንት ልጆቿ የሀሳብ አበርክቶ የተገነባች ናት፤ በእኔና በእናንተ አሁናዊ ድርጊትና እይታ ትፈጠራለች። ስለዚህ ምንድነው የምታስቡት? ለሀገርና ለህዝባችሁ የሚሆን ምን በጎ ሀሳብ አላችሁ?
በአዲስ ዓመት ማግስት ላይ እንደመሆናችን ለአዲሷ ኢትዮጵያ የሚሆን አዲስ ልብና መንፈስ ያስፈልገናል። ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች መልካም የምናስብበትና ከአሮጌነት የምንወጣበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ነን። እንደ ሀገርም እንደ ግለሰብም የሀሳብ ለውጥ ያስፈልገናል። በሀሳብ ማሸነፍን መልመድ ይኖርብናል።
የምንፈልገው ነገ ያለው ዛሬ በምናስበው ሀሳብ ውስጥ ነው። በሀሳብ ከመሸናነፍ ይልቅ በሀይል ዱላ ማንሳትና ቡጢ መሰንዘር የሚከጅለን ጥቂት አይደለንም። መንገድ ላይ ለምን ገፋኸኝ ገፋሽኝ፣ ለምን አየኸኝ አየሽኝ እየተባባሉ በትንሽ ነገር ለገላጋይ የሚያስቸግሩ አሉ። ሰፈር ውስጥ በወሰን፣ በደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ፣ በልጆች፣ ወዘተ ሳቢያ ካልተደባደብኩ የሚለው የሚዝተው ሲታሰብ በእርግጥም ከሀሳብ ይልቅ ሀይል የሚቀናቸው በርካታ ናቸው።
ቆይቷል፤ ከመገናኛ ወደ ሀያ ሁለት እየሄድኩ ሀይገር ባስ ውስጥ ነበርኩ፤ አንድ ወጠምሻ መንገድ ላይ ተሳፈረና ተደባለቀን። ቦታ ስላልነበረ ቆሞ መሄድ ግድ ነበረበትና ድንገት መኪናው ሲነቀንቀው ሳያስበው አጠገቡ የተቀመጡች ወጣት ሴት ደረት ላይ በአፍጢሙ ተደፋ።
ይቅርታ ቢጠይቃትም ወጣቷ ለምን ተደፈርኩ ይመስል በጣም ተቆጣች፤ አላስፈላጊ ነገር ተናገረች። አውቆ እንዳይደለ እኔን ጨምሮ አንዳንድ ተሳፋሪዎች ልናስረዳት ብንሞክርም አልሰማ አለች። ከዚህ በኋላ ወጣቱም በንዴት ቱግ ብሎ ክፉ ነገር ተናገራት። እነሱን ስንገላግልና ስንሸመግል መንገድ ላይ ያረፈድንበትን ጊዜ አስታውሳለሁ።
ይሄ ቀላል ነገር ነበር፤ ለጥልና ለቡጢ የሚዳርግ ነገር ሆኖ ሳይሆን በሀሳብ ማሸነፍን ባለመልመድ የመጣ ስለሆነ ነው። በሀሳብ ማሸነፍ አደጋን መቀነስ ነው። ሰዎች ፍጹም እንዳይደሉ መረዳትም ነው። እኔ ያልኩት ለምን አልሆነም በሚልና ለምን ተደፈርኩ በሚል ያልተገባ አካሄድ ብዙ ነገራችንን የምናጣ ሞልተናል።
በስራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በመንገድ ላይ በይቅርታ ማለፍ ለምንችላቸው ትንንሽ ነገሮች ቦታ ሰጥተን ያልተገባ ነገር የምናደርግ ብዙዎች ነን። በሀሳብ ማሸነፍን ባህል ማድረግ አለብን። አንድ ሰው ሲሳሳት አብረን መሳሳት ሳይሆን ከስህተቱ ታርሞ በላቀ ሀሳብ የላቀ ነገር እንዲፈጥር ማስተማር ነው።
በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሰዎች አላስፈላጊ ነገር ሲያደርጉ ስናይ ከመተቸትና ከመገፋፋት ይልቅ ተገቢውን ነገር ማሳየት ጥሩው ዘዴ ነው። ጥቂት የማንበል ወገኖች ለምንም ነገር ትችትና ወቀሳ ይቀናናል። ታክሲ ተሳፍረን መልስ ሲዘገይብን ቁጣ ቁጣ የሚለን፣ ቡና አዘን ማኪያቶ ሲመጣልን የምንገነፍል ፣ ለስድብ የምንዘጋጅ እንዲህ ነን።
በዚህ ማንነት ውስጥ ልዕልና የለም። አንድ ሰው በመልካም ሀሳብ ማስተማር ወደር የማይገኝለት የማሸነፊያ ጥበብ ነው። በሀሳብ ማሸነፍና ማስተማርን ልመዱ።
ከትላንት እስከ ዛሬ ውሀ በማያነሳ የሀሳብ ጅረት ውስጥ ነበርን። ማሸነፍ ስንችል እየተሸነፍን፣ መቆም ስንችል እየወደቅን የገዛ ራሳችን ሀሳብ ጠላት ሆኖን አደናቅፎ ሲጥለን ኖረናል። ድንቅ ነገ በድንቅ ዛሬ የሚፈጠር ነው። ድንቅ ሀገርና ህዝብ የድንቅ አስተሳሰብ ማሳያዎች ናቸው። በሀሳባችሁ ራሳችሁን እንድትፈጥሩ አዛችኋለሁ። በእናንተ ድንቅ ተፈጥሮ ውስጥ ድንቅ ሀገርና ህዝብ ይፈጠራል። ከሁሉ አስቀድማችሁ ራሳችሁን በሀሳብ ፍጠሩ።
በሀሳባችሁ ሀገራችሁን አቅኑ። በሀሳባችሁ የልጆቻችሁን ነገ ገንቡ። በሀሳባችሁ የድሀ ህዝብን ውለታ መልሱ። በሀይል ሳይሆን፣ በጉልበት ሳይሆን፣ በትችት ሳይሆን በፍቅርና በአሸናፊ ሀሳብ መራመድን ልመዱ። በይቅርታና በመቻቻል ወደ ፊት መራመድን እንማር።
የአለማችን ሀያላን ሀገራት በአሸናፊ ሀሳብ የተገነቡ ናቸው። ሀሳብ ስልጣኔ ነው፣ ሀሳብ ዘመናዊነት ነው። አንድን ሰው በመተው ካላሸነፋችሁት፣ አንድን ሰው በይቅርታ ካላሸነፋችሁት፣ በሀሳብ ካረታችሁት በቡጢና በሀይል አትመልሱትም። ይህ መንገድ ክፉ ነው፤ አጸፋውም ሊከፋ ይችላል፤ እናም መፍትሄ ሊሆን አይችልም።
ፍቅርና መተው ግን ሁልጊዜም መፍትሄ መሆን ይችላሉ። በየትኛውም ስፍራ ላይ በሀሳብ ስትልቁ ሀገርና ህዝባችሁን እያገለገላችሁ እንደሆነ አስቡ። በየትኛውም ስፍራ ላይ በሀሳብ ስትልቁ በችግሮቻችሁ ላይ የበላይ እየሆናችሁ እንደሆነ አስታውሱ። በየትኛውም መንገድ ላይ ሆናችሁ ይቅር የሚል ልብ ካላችሁ በትውልዱ አብራክ ውስጥ በጎ አሻራ እያስቀመጣችሁ እንደሆነ ልብ በሉ። በስራ፣ በትምህርት በማንኛውም የህይወታችሁ እንቅስቃሴአችሁ ውስጥ ማሸነፍ አንድ ቦታ ላይ እንዳለ ተማሩ፤ ሀሳብ ውስጥ።
መነሻና መድረሻችን ሀሳብ ነው። በሀይል የበላይነት ሳይሆን በሀሳብ የበላይነት እንመራ። በትችት የበላይነት ሳይሆን በፍቅር የበላይነት እንራመድ። በሀይል የበላይነት የሚመራ ማህበረሰብ ይብቃን። በሀሳባችን እንፍጠር። አበቃሁ፤ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 1/2014