እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች፣ ሰላም ናችሁ? በጣም ጥሩ ልጆች፣ በጣም ጥሩ!!! (ይህ የአባባ ተስፋዬ የቴሌቪዥን መግቢያ ንግግርን መሰረት ያደረገ መግቢያ ሲሆን)፤ ይህን ያነበበም ሆነ ሲነበብም ሆነ ሲነገር የሰማ ሁሉ አባባ ተስፋዬ (አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ)ን ማስታወሱ አይቀርም።
ልጆች፣ ዛሬ ስለ አባባ ተስፋዬ ላነሳ፣ እናንተም በሚገባ እንድታውቋቸውና ልጆች መልካም ሰብዕናን ይዘው እንዲያድጉ በማድረግ፣ በትምህርታቸው እንዲጎብዙ በማበረታታት፣ በአእምሯቸው እንዲጎለብቱ በመምከርና ማስተማር ወዘተ በኩል ያበረከቱትን አስተዋፅኦ እንድትገነዘቡ፤ ለወደፊትም ስራዎቻቸውን ፈልጋችሁ እንዳታዳምጡ፤ ወይም እንድታነቡ ለማስታወስ ነው። ትክክል አይደለሁም እንዴ ልጆች? “ትክክል ነህ” እንደምትሉኝ እየተማመንኩ ልቀጥል።
አባባ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “የልጆች ፕሮግራም” አዘጋጅና አቅራቢ ነበሩ። ፕሮግራማቸው በየሳምንቱ እሁድ እሁድ ጠዋት ስለሚተላለፍ ልጆች ብቻ ሳይሆኑ አዋቂዎች ሁሉ ይከታተሏቸው ነበር። በተለይ በእንደዚህ፣ ክረምቱ አልፎ ትምህርት ቤት በሚከፈትበት ሰዓት ለልጆች ሲያስተላልፏቸው የነበሩት ፕሮግራሞች እንዲህ በቀላሉ የሚረሱ አልነበሩም፤ በብዙ ሰዎች (ዛሬ አዋቂዎች ሆነዋል) አእምሮ ውስጥ ተመዝግበው ተቀምጠዋል።
በተለይ ልጆች አባባ ተስፋዬ የሚሰጡት ትምህርት በተረት፣ ተረትና ምሳሌ፣ አዝናኝ ቀልዶች ወዘተ የታጀቡ በመሆኑ የሚሰጡት ትምህርት፣ ምክር፣ አስተያየትና የመሳሰሉት ሁሉ በብዙዎች አእምሮ ውስጥ ታትመው
እንዲቀሩ ያደረገ ሲሆን፤ ይህንንም ጠቅለል አድርገው የሚያስውብበት፣ አሳምረው የሚገልፁበት የራሳቸው የሆነ አባባል አላቸው።
ልጆች እናንተ ከሌሎች ተለይታችሁ የምትታወቁበት ልዩ መለያ አላችሁ? አባባ ተስፋዬ ግን አላቸው።
አባባ ተስፋዬ (በ1916 ዓ.ም. ተወልደው በ2009 ዓ.ም. ነው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት) ከሚሰሯቸው ፕሮግራሞች ሁሉ፣ ከሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ሁሉ፣ ከሚሰጧቸው ምክሮች ሁሉ የማይረሳላቸው አንድ ነገር አለ። ይህ ተለይተው የሚታወቁበት መለያ አባባላቸው በተለይ ገና ፕሮግራማቸውን ሲጀምሩ በመግቢያ መልክ የሚጠቀሙበት ስለሆነ ብዙዎቻችን አንረሳውም። ዛሬም ድረስ በርካታ ሰዎች የሚያስታውሷቸው በዚሁ ማር ማር በሚለው ጣፋጭ አባባላቸው (አንደበታቸው) ሲሆን፤ እሱም፡-
“ልጆች
የዛሬ አበባዎች
የነገ ፍሬዎች።” የሚለው ነው።
በዚህ እጅግ ተወዳጅ፣ ተደማጭ በሆነው ፕሮግራማቸውና ማር ማር በሚለው አንደበታቸው (ልጆች የዛሬ አበባዎች …) ምክንያት ይመስለኛል (ነው ያሉኝ አድናቂዎቻቸው ብዙ ናቸው) “አባባ ተስፋዬ የኢትዮጵያ ልጆች አባት” የሚል ማህበራዊ ማዕረግን ያገኙት።
ልጆች “ማህበራዊ ማዕረግ” ማለት ምን ማለት እንደሆን ታውቃላችሁ? ግዴለም አትጨነቁ፤ እነግራችኋለሁ። “ማህበራዊ ማዕረግ” ማለት በምትሰሩት ስራ፣ በምትሰጡት ማህበራዊም ሆነ ሙያዊ ወይም ሌላ አገልግሎትና የመሳሰሉት ምክንያቶች አገልግሎቱን ያገኘው ማህበረሰብ ባገኘው ጠቀሜታ፣ እርካታና ለእናንተ ባለው አድናቆት ምክንያት የሚሰጣችሁ ስም ወይም ማዕረግ ነው። ልጆች ህዝብ እኮ መልካም ለሰራለት ሰው ውለታ ይከፍላል፤ ታውቃላችሁ አይደል ልጆች? አዎ፣ በደንብ አድርጎ ይከፍላል።
ልጆች አሁን ሁለ-ገቡ የሙያ ሰው አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ “አባባ ተስፋዬ” የሚለውን ማህበራዊ ማዕረግ ለምን እንዳገኙ ተገነዘባችሁ አይደል? በጣም ጥሩ። እናንተም ወደፊት እንዲህ ዓይነት ተግባራትን በመፈፀም የተለያዩ ማህበራዊ ማዕረጎችን (ስያሜዎችን) እንደምታገኙ ተስፋ አደርጋለሁ። አይደለም እንዴ ልጆች? በጣም ጥሩ።
በሉ እንግዲህ ልጆች፣ የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች፤ በዚህ አዲሱ የትምህርት ዘመን አሁኑኑ ወደ ትምህርታችሁ ብቻ በማተኮር፤ ቤተሰቦቻችሁና መምህራኖቻችሁ የሚሏችሁን በማዳመጥ፣ እራሳችሁን ከኮረና በሚገባ በመጠበቅ በዓመቱ መጨረሻ፤ ትምህርት ቤት ሲዘጋ፣ ትምህርቱም ሆነ ፈተናው ሁሉ አልቆ፣ ሰርተፊኬት ተቀብላችሁ ሰኔ ላይ 1ኛ ወጥታችሁ እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ቻው ልጆች፣ ቻው!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም