ሰሞኑን በተለየ መልኩ በድምቀት የተፈጸመው የአዲስ መንግስት ምስረታና ባዕለ ሲመት፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ታላቅ ሁነት ነበር።አዎን ኢትዮጵያውያን በእጅጉ ሲጠይቁ የኖሩት ለእዚህም ትልቅ ዋጋ የከፈሉበት አዲስ ስርዓት ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረበት ታላቅ ወቅት ነው። በአዲስ ዓመት የተጀመረው አዲስ ምዕራፍ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ፤ ለህዝቧም ለውጥ መሰረት እንደመሆኑ ሁሉም በሚገባ ተከታትሎታል።
ይህን ምዕራፍ በሚገባ አንብቦ ወደ ተግባር መለወጥ ያስፈልጋል።በአዲሱ ምዕራፍ ውስጥ የሚከተበው ታሪክ በጎነት የእያንዳንዱ ዜጋ አዎንታዊ ጥረት ውጤት ነውና እኔ ለዚህ ምዕራፍ ምን ማበርከት አለብኝ? የሚለው ነው መሰረታዊ ጉዳይ፡፡
በጎ ጅማሬን መልካምና ቀና በሆነ እሳቤና አተያይ መጀመር ለጉዳዩ ስኬት ታላቅ አበርክቶ አለውና ለአዲሱ ምዕራፍ አዲስ የሆነ አተያይ ወይም አዲስ ምልከታ መታጠቅ ይገባናል። መንግስት የመሰረተው ፓርቲም ስልጣኑን ከህዝብ በይሁንታ ተቀብሎ፤ አንተ ትሻለኛለህ ያለውን ህዝብ በምን መልክ ሊያገለግልና ምን ምን ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንዳሰበ በምስረታው ቀን ይፋ አድርጓል።
የትኩረት አቅጣጫዎቹ በኢትዮጵያዊ ወኔ ከተተገበሩና የህዝቡ ብርቱ ርብርብ ከታከለባቸው በእርግጥም በአዲሱ ምዕራፍ አዳዲስ መታደሶች በዚህች ሀገር እውን ይሆናሉ።ለኢትዮጵያ ህዳሴ ማብሰሪያነት ይሰራሉ፤ ለተባሉቱ ግዙፍና ወሳኝ ተግባራት መንግስታዊ መዋቅር ወሳኝ ቢሆንም፣ ለተግበራው የህዝብ ሚና ታላቅ መሆኑ ይታመናል፡፡
በመንግስት አቅጣጫ ተይዞባቸው ወደፊት ሊሰራባቸው ከታቀዱት ተግባራት ውስጥ ኢትዮጵያን ወደፊት የሚያራምዱ ህዳሴዋንም የሚያበስሩ አጓጊ ዕቅዶችን ተግባራዊ የማድረጉ ስራ የእያንዳንዱን ዜጋ ቆራጥነትና ትጋት ይጠይቃል።ለዚህ ደግሞ በጋራ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መስማማት አንድነትን ማጠናከርና የእርስ በርስ መግባባትን ማጠናከር እንዲሁም ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያ ከሌላው ለየት በሚያደርጋት የዘመን ቀመር መሰረት በአዲስ ዓመት መባቻ ላይ የተበሰረው አዲስ ምዕራፍ እንደ ስሙ አዲስነት እንዲላበስ በአዲስና አሻጋሪ ሀሳቦች የጎለበቱ አዳዲስ የለውጥ ሀሳቦች የሚፈልቁበት ሊሆን ግድ ይላል።መንግስት የዘመኑና የስልጣኑን ጅማሮ አዲስ ምዕራፍ ብሎ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ሊገነቡ የሚችሉ አዳዲስ አሰራሮችና አካሄዶችን እከተላለሁ በሚል ዕቅዱን ይፋ አድርጓል፡፡
ታዲያ እኛም እንደ ህዝብ እና እንደ ሀገር ወዳድ ዜጋ በአዲሱ ምዕራፍ ውስጥ የሚኖረን ሚና ምን መሆን አለበት የሚለውን መመለስ ይገባናል።የተጀመረው አዲስ ምዕራፍ በአዲሱ ዘመን መጀመሪያ ላይ መሆኑ ብዙ መልካም ነገር እንድናስብ ስለአገራችንና ህዝባችን ብዙ ተስፋ እንድናደርግ ያደርገናል።በዚህ ላይ ደግሞ ለዘመናት ሲጠበቅ የነበረው በህዝብ ይሁንታ የተመረጠ መንግስት ወደ ስራ የሚገባበት አዲስ ዓመት መሆኑ ሃላፊነታችንን ይጨምረዋል።በእዚህ ሁሉ ውስጥ የምንጠብቅ ብቻ ሳንሆን የሚጠበቅብንም ነን።በመሆኑም አዲስ ምዕራፍ ከፋቾቹ፣ የለውጥ ቀያሾቹ ራሳችን እንደመሆናችን አምነን ተቀብለን መተግበሩ ግድ ይለናል፡፡
ለአዲሱ ምዕራፍ እውን መሆን አንድ ወሳኝ ነጥብ አለ።እሱም የጋራ መግባባት እና አንድ ሆኖ ስለ አንዲት አገር መቆም ነው።ለለውጥ ሁሉ መሰረት የሆነው ዝግጁነት ለመነሳት ሁሉ መንደርደሪያ የሆነው መልካም ሀሳብ ነው።አገራዊ መግባባት ከሁሉ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። ለእዚህም ስንነሳ ቆም ብለን አንድና መተኪያ የሌላት አገራችንን ማሰብ ይኖርብናል።
እኛ ጋ ሙሉ መስሎን ለሌላው በሚያንሰው ምክንያት አልባና ራስን ብቻ በሚመለከተው ሀሳባችን ታላቋ አገራችንን መመዘንፈጽሞም የለብንም።አገራችንን የሚመጥን ትልቅ ሀሳብ ለአዲሱ ምዕራፍ የሚሆን የገዘፈ እሳቤ መላበስ ይኖርብናል።አሮጌነትን ወደ አዲሱ ምዕራፍ ይዘን እንዳንሻገር በእጅጉ መጠንቀቅ ይኖርብናል።
የተጀመረውን አዲስ ምዕራፍ በከንቱ ላለማስረጀት፣ የተዘጋጀው ታላቅ እቅድና ኢትዮጵያን ለመለወጥ የጠወጠነው ታላቅ ትልም እውን እንዲሆን እውናዊ መነሳሳት ፍሬያማ ትጋት ወሳኝ ነው።
ሁሉም ከሀገር በታች መሆኑን አምኖ መቀበል፣ የግል ፍላጎታችንን ከህዝብ መሻት ያነሰ መሆኑን መገንዘብም ይገባል።እንደ ዜጋ አብሮ መቆም የሚያስችል ትዕግስት በአብሮነት የሚያራምድ መቻል መላበስ ይኖርብናል።ያኔ ለሀገሩ ከፊት የሚሰለፍ የእውነተኛ ዜጋ ቆራጥነትን እንላበሳለን፡፡
ኢትዮጵያን የሚወዱ ስለ ኢትዮጵያ በትጋት ሁሌም መስዋዕትነት እንደሚሆኑ ሁሉ ወደ አሮጌውና ያለፈ ምዕራፍ ሊመልሷት የሚጥሩ፣ በህዝብዋና በሉዓላዊነትዋ ላይ የዘመቱ ጠላቶች ዛሬ ላይ በርክተዋልና እነዚህን በአዲሱ ምዕራፍ ድል ለማድረግ ከኢትዮጵያ በታች መሆናቸውን በትክክል ማሳየት እንደሚያስፈልግ ለዚህም መዘጋጀት ይገባናል።በአዲሱ ምዕራፍ አዲስነት የሚያላብስ ታላላቅ ሀሳብ መተግበር ወደ አሮጌነት የሚመልስ ጎታች ሀሳብ መላበስ የሚገባው ለዚህ ነው።
ስለዚህች ታላቅ ሀገር የምንከፍለውን ሁሉ ላለመቆጠብና እሷን በአዲሱ ምዕራፍዋ ለማደስ ዝግጁ መሆን ይኖርብናል።አንዲት ሀገር ናትና ያለችን አንድ የሆነ የጋራ ዓላማና መድረሻ ግብ ሊኖረን ይገባል።በሀገር ላይ የሚኖር አለመግባባት ፈፅሞ አይሰራም። በሀሳብ ልዩነት አምነን የእኛን ለሌሎች በስርዓት ማሰማት የሌሎችን ደግሞ አክብረን መስማት ወደ አንድነትም ማቀራረብ ካልሆነም አቻችሎ ማዝለቅ ይገባል።
አሮጌው ምዕራፍ ላይ የእኛ ሁናቴና አኳኋን ሁሉ እንዲህ ነበር።በአንድ ጉዳይ ላይ እየተነጋገርን የማንግባባ፤ በአንድ ርዕስ ላይ እያወራን የማንደማመጥ ነበርንና ወደመግባባት መድረስ ከባድ ሆኖብን ዛሬ ላይ ደርሰናል። የሀሳብ ልዩነትን አክብረን መነጋገር እየቻልን እየተደማማጥንም እኮ ነው የመነጋገር ውጤት የሆነው መግባባት ላይ መድረስ አቅቶን አሁን ላይ የተገኘነው።
ወደ አንድ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ደግሞ ይህንን እናድርግ።መጀመሪያ ጉዳዮቻችን ምንድናቸው? የትኞቹስ ናቸው የሚለዩን ? አንድ የሚያደርጉንስ የትኞቹ ናቸው? ብለን እንለያቸው።ነገራችን አልገባ ጉዳያችን አልሳካ ያለን ለምን ይሆን? ብለን እናጢን።ለመፍትሄው ለመንደርደርና አላግባባ ያለንን ጉዳይ በቅጡ ለመለየት እና ለመረዳት ብሎም ለማቀራረብ ያስችለናል።
እንደ ህዝብ ለዘመናት አብረው በፍቅር ያቆዩን እሴቶችን ማጠናከር በአዲሱ ምዕራፍ የሚጠናክር ተግባራችን መሆን ይኖርበታል።አብሮ መሆን፣ ትስስርንን ማጠንከር፣ አንድነትን ማጉላት ለዜጎቿ መከታ የሆነች አገር የመገንባቱ ሂደት ማፋጠኛ መንገድ ናቸው።ከወቃሽነት የተላቀቀ በራሱ የለውጥ አበርክቶ ላይ ሚናውን ለማበርከት ዝግጁ የሆነና መፍትሄ አመላካች ማህበረሰብ መገንባት እንዲሁም ለችግሮች አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥ መፍትሄ ማበጀት ይገባል።
ኢትዮጵያ ሰፊና ለሁላችን የምትበቃ በጋራ ለመበልፀጋችን ምቹና የተፈጥሮ ፀጋ የታደለች ምድር ናት።እኛ አዲሶቹ ትውልዶች ደግሞ የዚህችን ውብ አገር ክብርና ሉዓላዊነት ጠብቀን ወደፊት እንድናራምዳት አደራ የተጣለብን ባለጊዜዎች ነን።
እናም ብዝሀነትን ተቀብለን፣ አንድነትን አጠንክረን፣ ልዩነት ላይ ተግባብተንና ተስማምተን ለሀገራዊ ለውጥና ለአዲሱ ምዕራፍ የየግላችን አዎንታዊ ሚና መወጣት ይጠበቅብናል።ለዚህች ሀገር በሀሳብ ልዩነት ያመነ፣ ጉዳዮችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት ልምድ ያካበተ፣ ዴሞክራሲያዊ ልምዱ የዳበረ ዜጋ፣ ለአዲሱ ምዕራፍና ለአዲስ አኩሪ ታሪክ መበሰር እጅጉን ያስፈልጋታልና አዲስ መንፈስ እንላበስ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 29/2014