በአዕምሮ ጤና አገራችን ካፈራቻቸው በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል አንዷ ናቸው።በአሜሪካን አገር የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማስተማር ከፍተኛ ደሞዝ እየተከፈላቸው የቆዩ ቢሆኑም ከአገር የሚበልጥ የለም በማለት ለአገራቸው ለመስራት ምቾታቸውን ትተዋልም።ቀደም ሲል በሙያ እንጂ በፖለቲካው ዓለም ውስጥ ተሳትፈው ባያውቁም አገር ልትሻገር የምትችለው ሙያን ከፖለቲካው ጋር ጭምር አዛምዶ የሚሄድ አቅም ያለው ሰው ሲኖራት እንደሆነ በማመናቸው አሁን ብልጽግና ፓርቲን ተቀላቅለው ፣ የጎዛመን ወረዳን ወክለው የህዝብ እንደራሴ ሆነዋል።አዲሱ መንግስት ምስረታ ላይም አሻራቸውን ለማሳረፍ ቆርጠው ተነስተዋል።
ከአገር ውጪ ሳሉ ለአገራቸው በርካታ ሥራዎችን ሰርተዋል። በተለይም አገር ፈታኝ ችግር ውስጥ በሆነችበት ጊዜ በፍጥነት ከሚሳተፉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አንዷ ናቸው።አሁንም እንዲህ አይነት ሰው የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንደሆኑ በማመናቸው ነው ወደዚህ መጥተው ለመስራት የቆረጡት። በተለይም አገርን ችግር ውስጥ በከተተው የአስተሳሰብ ችግር ላይ ለመስራት ቁርጠኛ ናቸው።ለዚህ ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በአዕምሮ ጤና የትምህርት መስክ መመረቃቸው እንደሚያግዛቸው ነግረውናል።ይህንና መሰል አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብዙ ሃሳቦችን አንስተናልና ከዶክተር ማስተዋል መኮንንን ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንሆ አልን።
አዲስ ዘመን፡- ዘንድሮ ብልጽግና ፓርቲን በመወከል ለፓርላማ ተመርጠዋል።ለመሆኑ ምርጫው እንዴት ነበር?
ዶክተር ማስተዋል፡- ምርጫዎች ከዚህ ቀደም ስመርጥበት እንጂ ስመረጥበት አላውቀውም። ለመምረጥም ቢሆን የመሳተፌ ሁኔታም የተገደበ ነው። ምክንያቱም ከአንድ አካል ውጪ አሸናፊ የለም። ህዝብም ቢሆን የፈለገውን እያደረገ ኖሯል ብዬ አላምንም። ብዙ ክፍተቶች የነበሩበት ነው። እናም የዘንድሮ ምርጫ ተመራጭ ስለነበርኩ ብቻ ሳይሆን እውነታው ሲታይ ብዙ ነገር ለውጥ የታየበት ነበር ብዬ እወስደዋለሁ። ለዚህም ማሳያው በጭለማ ሳይቀር የሚመርጠው ህዝብ ብዙ ነበር። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጭምር በሰላማዊ መንገድ የተሳተፉበትና ለአገራቸው ሰላምን ያሳዩበት ነበር።በአጠቃላይ ከአሰራር እስከ ውጤት አንዳንድ ክፍተቶች ቢኖሩም ካለፉት አንጻር የተሻለ ይመስለኛል።
የፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ ምንም ልምድ የሌለኝ ነበርኩና ሃሳቡ ሲቀርብልኝ በቀላሉ ለመቀበል አልቻልኩም። እኔ ማገልገል የምፈልገው በሙያዬ ብቻ መሆን እንዳለበት አምናለሁ። በተለይ የማህበረሰቡ ባህልና አኗኗር እንደሚፈትነኝ ይሰማኛል። እንዳሰ ብኩትም በስንት ውጣውረድ ከተስማማሁ በኋላ ገጥሞኛል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ወጣቱ ላይ መስራት ነው የሚል ፍላጎቴ ያየለ ቢሆንም ወንድሜና የጓደኞቼ ሃሳብ ውሳኔዬን አስቀይሮኛል።ምክንያቱም ወደአገርሽ ሙሉ ለሙሉ የምትመለሽው አገርሽን ለማገልገል ከሆነ ይህ የበለጠ ያግዝሻል የሚለው አሳመነኝ።
‹‹በሥራ የተገለሉ ዜጎች አገሪቱ ፈተና ላይ ስትሆን ሲጠሩ አንገታቸውን ለሰይፍ ደረታቸውን ለጥይት ለመስጠት ቁርጠኛ ሆነው ተመለሱ፤ በዘመቻውም ተሳተፉ፤ አንቺም በሙያሽ እንጂ በሌላ አገልግይ ያለሽ የለም።ሙያሽን ደግሞ የበለጠ ለመጠቀምና ተግባር ላይ ለማዋል ከዚህ የበለጠ ምንም አጋጣሚ አታገኝም የሚለው›› እንቢ እንዳልል አደረገኝ። ገባሁበትና አየሁትም። ጥሩ እንደነበርም ተሰምቶኛል። በተለይም ምርጫ ቅስቀሳውን እነርሱ እንስራው ገጠር መሄድ ያዳግትሻል፤ ከተማውን ብቻ አንቺ አድርጊ ቢሉኝም አይሆንም በማለቴ ህዝቡ የሚፈልገውን እንዳይ ሆኛለሁ።
የማያውቀኝ ማህበረሰብ እኔን እንዲመርጠኝ ሳያምንብኝም እጩው እንድሆን አልፈልግም ብዬም በሸበጥ ጫማ ሳይቀር እየተጓዝኩ ቆላማውና በርሃማ ስፍራ ቀስቅሻለሁ። ይህ ደግሞ የተመራጭነትን ስሜት፣ የአገልጋይነትን ልዩ ጣዕም እንዳይም አግዞኛል።ምን መስራት እንዳለብኝም ቢሆን ያየሁበት ነው። ስለዚህ ምርጫው ሰውን ያማከለ እንጂ ግለሰቦችን የመረጠ ነው ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ሰው ወዶና ፈቅዶ እንዲሁም አይቶ እንዳሸንፍ አግዞኛል። ይህንን እድል ሲሰጠኝ ደግሞ አብሮ ብዙ ሃላፊነት አለብሽ እንዳለኝም ይሰማኛል። እናም ወዶ ያደረገውን ወዶ እንዲኖርበት ማድረግ ላይ የምሰራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ከምርጫው በኋላ ብዙዎች ቃል በገቡት ልክ ሲሰሩ አይታይም።እርስዎ ይህንን ከመቀየርና በገቡት ቃል ልክ ከመስራት አንጻር ምን ያህል ዝግጁ ነዎት፤ ምን ያህልስ ለተመረጥኩበት አካባቢ አገለግላለሁ ብለው አስበዋል?
ዶክተር ማስተዋል፡- የተመረጥኩበትን የበለጠ አስባለሁ እንጂ ሥራዎችን መስራት ያለብኝ ግን እንደአገር ነው ብዬ አምናለሁ።ምክንያቱም ኢትዮጵያ የተቀደሰች አገር ነች።እያንዳንዱን የምዕራብ ዓለም ክፍል የማየቱን አጋጣሚ አግኝቻለሁ። ነገር ግን በምንም መልኩ እንደኛ የሆኑ አይደሉም። በሥራ እንኳን ትንሽ ሰርተው የሚያቆሙ ናቸው። በዚያ ላይ በቀላል በሽታ ይወድቃሉ።ይህም ሆኖ ሌሎችን እንበልጣችኋለን የሚሉ ናቸው። ሁልጊዜ እኛን ዝቅ አድርገው ማየት ይፈልጋሉ። ለዚህ ደግሞ ሁለት ምክንያት አላቸው።
የመጀመሪያው እነርሱን ያሳፈሩ በመሆናቸው ውስጣቸው ስለሚፈራ የዝቅተኝነት ስሜት እንዲሰ ማቸው ለማድረግ ይሞክራሉ። ሁለተኛው ጠንካራ መሆናቸውና የብዙ ነገሮች ባለፀጋ መሆናቸው ያስቀ ናቸዋል። በዚህም እነርሱን ለመግዛት ስለሚፈልጉ የእነርሱን የበላይነት ለማሳየት ይሞክራሉ።ሆኖም መቼም ተሳክቶላቸው አያውቅም፤ አይሳካላቸውም።ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን በብዙ ነገር ባለጸጋ ናቸው።ከእምነትና መተሳሰቡ ባለፈ በስራ ትጋታቸውም ማንም ሊደርስባቸው አይችልም።በተለይ ጠላት በምንም መልኩ ሊያዳክማቸው አይችልም።ይህንንም ጠንቅቀው ያውቁታል።
እኔ የቀን ጽዋ ተረካቢ በመሆኔ ቃል የገባሁትን አደርገዋለሁ።አገሬ የጣለችብኝን ሃላፊነት መወጣት ውዴታዬ ሳይሆን ግዴታዬ ነው ብዬ አምናለሁም። ምክንያቱም በባህላችን ጽዋ በልቶ አለመክፈል ነውር ነው። ወረዳዬ ትሰራልናለች፤ አገሬም የሰጠኋትን ትከፍላለች ብላ ለዚህ አጭተውኛል። ስለሆነም ቃላቸውን አክብሬ እሰራለሁ ብዬ አምናለሁ። ወጣቱም ቢሆን አገር ያለችበት ሁኔታ በከባድ ፈተና ውስጥ በመሆኑ የቀኝ ጽዋ ተረካቢ ነውና ብዙ ነገር አብረን እንሰራለን የሚል እምነት አለኝ። አብዛኛውን ወጣት አገርን ለመረከብ አላዘጋጀነውምና ይህንን መስራት የመጀመሪያ ህልሜም ነው። ከዚህ በተጓዳኝ የጎዛመን ወረዳ ምርታማ አካባቢ በመሆኑ አርሶአደሩ በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚሰራበትን ሁኔታ በማመቻቸት ለሌላው የሚተርፍበትን መንገድ ለመጥረግ የምሰራ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ወጣቱ የአስተሳሰብ ድሃ እንዲሆን ያደረገው ምንድነው ይላሉ?
ዶክተር ማስተዋል፡- አስተሳሰብ ላይ አለመሰራቱና የትምህርት ሥርዓቱ መውደቅ ነው። ምክንያቱም አገራችን የመጀመሪያ የኢኮኖሚ ዋልታ ዘዋሪ ግብርና ሆኖ ሳለ ወጣቱ ይህንን ሙያ እንዲጠላው ተደርጎ ተቀርጿል። በዚህም የቤተሰቡ መሬት ጦሙን እያደረ ተመርቆ በትምህርት መስኩ ብቻ ሥራ ይፈልጋል። ሥራ መፍጠርንም አያስብም።ሥራ ከምፈታ ብሎ ለጽዳት ሳይቀር የሚወዳደረውም ለዚህ ነው።
በአገራችን ስራ ጠፍቷል የሚል ነገር የለኝም።ብዙ ጸጋ ያለን በመሆናችን ያንን መጠቀም እንችላለን።ወጣቱ ግን የተማረውንና ትሆናለህ የተባለውን ብቻ እያለመ ነው የሚኖረው። ይህ ደግሞ የቅርቡን እንዳያይ አድርጎታል። በመሆኑም ወጣቱ አዕምሮ ላይ መስራት የመጀመሪያው የቤት ስራችን መሆን አለበት። በአስተሳሰብ ደረጃም ልዩነት የሌለበት ሥራ እንዲኖረው ማድረግ ላይ ከትምህርት ቀረጻው ጀምሮ ሊሰራበት ይገባል። የመማር ማስተማሩ ሥራ አገራዊ ተግባር ተኮር ሥራዎችን ያቀፈ ሊሆን ያስፈልጋል።
ሥራ ያለበት ትምህርት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥን እንደአገር ያመጣል። ለውጥን በሚያመጣ መልኩ ወጣቶች እንዲሰሩም ያደርጋል። ስለሆነም መንግስት ይህንን አስቦ መስራት አለበት። ቤተሰብም ቢሆን አስተሳሰብ ለውጥ ላይ ብዙ የቤት ሥራ አለበትና ሰርቶ ሊያሳይ ይገባል። በቀድሞ ሥርዓት የእርሻ ትምህርት የሚባል ነበር። መደብ ጭምር ተሰጥቶን ልማታችንን ከነውጤቱ እናያለን። ይህ ደግሞ ሙያውን ወደነው ለመስራት ራሳችንን ዝግጁ እንድናደርግ ያግዘን ነበር።ስለሆነም ተማሪን ከማህበረሰቡ ጋር አገናኝቶ መስራት የዛሬ ተግባራችን መሆን አለበት። ይህ ካልሆነ ደግሞ የስራ ለውጥም ሆነ የአስተሳሰብ ቅየራ መቼም ሊመጣ አይችልም።ተማሪዎችም ለሌላ ስራ ራሳቸውን አዘጋጅተው አይመጡም።እናም ነገሮችን አስቦ መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ውጭ አገር እንደኖረና ብዙ ነገራቸውን እንደተጋራ ሰው በአገራችን ላይ ያለውን የውጭ ጫና እርስዎ እንዴት ያዩታል?
ዶክተር ማስተዋል፡- ውጭዎች እንደ ኢትዮጵያ የሰከነ ማንነት ያለው፤ ፈጣሪውን የሚወድና ለሌሎች ልዩ ክብር የሚሰጥን ባይነኩት ጥሩ ነበር።ሆኖም በህወሓት አማካኝነት በ27 ዓመታት ጉዞ እንዲነጣጠል አደረጉት። ብዙ የመለያየት ሥራን ሰሩብን። እነርሱ ትምህክተኞች ናቸው፤ ከሰው ልጅ ሁሉ የበላይ ነን ብለው የሚያምኑ፤ በእውቀትም ሆነ በዘር ማንም አይደርስብንም የሚሉና ሌሎችን እረግጦ በመግዛት የሚረኩ ናቸው። ይህንን አስተሳሰባቸውን የሰበረባቸው አገርን ደግሞ እነርሱም ሰብረው ማየትን ይፈልጋሉና የቻሉትን ሁሉ እያደረጉ የሚገኙት ለዚህ ነው። የሚያስገርምም አይደለም።
ነጭ ብቻ ሳይሆን ጥቁርም ሰው ነው፤ የበላይም መሆን ይችላል ብሎ በተግባር ያሳየ ከኢትዮጵያ ውጪ ማንም አይደለም። ታዲያ ይህንን አድርጋ ታናሽ እንደሆኑ ያሳየቻቸውን እንዴት ካልወደዷት እንላለን፤ በምንም መልኩ ሊነኳት አይገባም ማለትም የለብንም።እነርሱ እየፈሯት የሚንቋት አገር አድርገዋታል። በተለይ ደግሞ እንደ ህወሓት አይነት የእነርሱ ተላላኪ ሲመራትማ አለመጠቀም ለእነርሱ ሞኝነት ነው። ስለዚህም እስከዛሬ ሙሉ ለሙሉ ተገልጦ ባይታይም በደንብ የፈለጋቸውን አድርገውባታል። በአስተሳሰብ ደረጃ እነርሱን አምላኪ እንድንሆንም ብዙ ሰርተዋል።ይህንን ለማዳን ደግሞ ብዙ ልፋትን ይጠይቃል።
የሚንቋትን ግን የሚፈሯትን አገር በግላጭ ያገኟት ባንዳ በሆነው የህወሓት አመራር ጊዜ ነው። ተጠቅመውም ሲያስፈራሯት ቆይተዋል።አሁንም ለማስፈራራት እየሞከሩ ያለው የተለመደ ተግባራቸውን ለመፈጸም ነው። ከዚያ ትይዩ ደግሞ መልማት መጀመሯ ያናድዳቸዋል፤ ያስፈራቸዋልም። ምክንያቱም እርሷ በለጸገች ማለት ከቀደመው የባሰ ውርደት ያጋጥማቸዋል። ይህ እንዳይሆንም መደገፍ ያለባቸውን አካል ደግፈው ከልማት ማስተጓጎል ዋነኛ ዓላማቸው አድርገዋል።ህወሓትን ዛሬ ጭምር የሚደግፉትም ለዚህ ነው።እንደግብጽ አይነቶች በየጊዜው የተለያየ ስልት እየቀየሱ ጫና እንዲያሳርፉ የሚያደርጉትም በዚህ ምክንያት ነው።
እነርሱ አፍሪካን እንዴት ድሃ ማድረግ ይቻላል ብለው ጭምር ምርምር የሚያደርጉ፣ ስትራቴጂ የሚቀርጹና በክፍል ሳይቀር ተማሪዎችን የሚያስተምሩ ናቸው። በዚህም እንደኢትዮጵያ ያለች ለመበልጸግ የምትሰራ አገር እድሉን አይሰጧትም። ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀም ሊያፈርሷት ይሞክራሉ።በአሽሽና መሰል ሱሶች የደነዘዙ ስለሆኑ ብዙ ለመስራት አይችሉም።ጉልበታቸውም ልፍስፍስ ነው። በዚህም ጉልበት የሚያገኙት ከአፍሪካውያን ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን መስራት ከጀመሩ ያከትምለታል።
ጉልበት ብዝበዛ ቀርቶ ለአገር መስራት ይጀመራልና አገራቸው ድባቅ ትመታለች።ብልጽግናው ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ይሆናል።ብዙ የተፈጥሮ ሀብትም በዚያው ልክ ያመልጣቸዋል።ስለዚህም ይህንን አርቀው ስለሚያዩበምንም መንገድ ሁኔታውን አይፈቅዱም። ሥራቸውና ተግባራቸው ጫና የሆነውም ከእነዚህና መሰል ነገሮች የመነጨ ነው።
የአንድነትንና የመመከትን ጥቅም እነርሱ እንደ ኢትዮጵያውያን ኖረውት አያውቁትም።እናም በዚህ እንደምናሸንፋቸው እምነት አለኝ።ሃይላችን አንድነታችን እንደሆነም ግልጽ ነው። ምክንያቱም እንደነሱ በመሳሪያም ሆነ በቴክኖሎጂ አልበለጸግንም። በእነርሱ ልክ ልንታገላቸው የማንችላቸው ብዙ ችግሮችም አሉብን። ሆኖም እኛ በመልማትና ራሳችንን በመሆን እናሳፍራቸዋለን።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያውያን አሁን የተጋረጠባቸውን የውጭ ፈተና እንዴት ድል ማድ ረግ ይችላሉ?
ዶክተር ማስተዋል፡- ከላይ እንደጠቆምኩት ነው። መጀመሪያ አንድነትን ማጠናከር ከምንም በላይ ያስፈልጋል። ነጮች ማለትም እንደ አሜሪካ አይነት አገሮች ህዝብን ከምንም በላይ ይፈራሉ። ምክንያቱም ህዝብ በህብረት ውስጥ ከሆነ ማሸነፍ እንደሌለ ያምናሉ። በተለይም እንደ ኢትዮጵያን አይነት በባህልና በታሪክ የተሳሰረን ህዝብ በምንም መልኩ ነቅነቅ እንደማያደርጉት ያውቃሉ። ስለሆነም መፍትሄው እነሱ እንዳሰቡት ሳንበታተን እጅ ለእጅ ተያይዘን የጀመርነውን ልማት ለውጤት ማብቃት ነው።
ብዙ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች አሉብን።ሆኖም ቅድሚያ የሚሰጠው የትኛው ነው ብሎ ለይቶ መከላከል ለነገ የሚባል አይደለም። ይህ ደግሞ ሉአላዊነትን ማስከበር ሲሆን፤ ምዕራባውያኑ እየደገፉ የሚያሰሩትን ጠላት ድባቅ መምታት ላይ መረባረብ ያስፈልጋል።በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የተለያዩ ዲፕሎማሲዎችን መጠቀም መሰረታዊ ነገር ነው።አምባሳደሮችንና ዲያስፖራውን በመጠቀም የኢትዮጵያን እውነታ ለማያውቀው ማስረዳት ይገባል። ይህ ተግባር ሁለት አይነት ጠቀሜታን ይሰጠናል። የመጀመሪያው አውቆ የሚያጠፋውን አውቀውብናል በሚል ዝም የሚያሰኘው ሲሆን፤ ሁለተኛው ያላወቀው አውቆ ከእኛ ጎን እንዲሰለፍ ያግዘናል። አሁን ከጎናችን እንዳሰለፍናቸው አገራት አይነት።
ሚዲያውም ቢሆን ጊዜያዊ ሳይሆን ተከታታይ ሥራ መስራት አለበት። በየጊዜው ያለውንና የሚከሰተውን ነገር ቀድሞ እውነታውን ለዓለም ተደራሽ በሚሆን መልኩ በተለያዩ ቋንቋዎች ማስረዳት ይጠበቅበታል።አሁን በሁሉም አቅጣጫ እየተሰራ ያለውን የማሳወቅ ሥራ ማጠንከርና ማበረታታም ያስፈልጋል። ማንም ሰው በአገሩ ጉዳይ ላይ ብቻዬን ሰርቼ ምን ለውጥ አመጣለሁ ማለት የለበትም። ጓደኞቹ ሰምተውት ለሌሎች ጓደኞቻቸው የሚያጋሩበት ብዙ መንገድ አለ።ስለሆነም በቻለው ሁሉ ስለአገሩ መዘመር ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት የሚያደርገውን ነገር እርስዎ እንዴት ተመለከቱት፤ ድርጊቱ ከኢትዮ ጵያዊነት ስብዕና የወጣ አይደለም ይላሉ?
ዶክተር ማስተዋል፡– ይህ የዛሬው ድርጊቱ አይደለም።ጽንፍ ወጥቶ በአይናችን የምናየውና የምንሰማው ጭካኔ ስለበዛብን እንጂ በስነልቦና ከዚህ በፊት በ27 ዓመታት ጉዞ ከዚህ የበለጠ አድርጎብናል። ቡድኑ ሲመሰረት ጀምሮ የነበረና የተደረገም ነው። አብዷል ተብሎ ህክምና አልተደረገለትም እንጂ የአዕምሮ ጤና ችግር ያለበት ነው።መሰረታዊ ችግሩም አስተሳሰብን የያዘ ነው። ውጪዎቹ ሲሰሩት የአስተሳሰብ ድሃ አድርገውታል። አልችልም ብሎ ዝቅ ብሎ ሲያጎበድድላቸው ቆይቷል።እነርሱ የፈለጉትንም አስተምረውታል። ከዚያ እዚህ ላለው አመራርና ተከታይ ልጆቹ የእርሱን በውጭ የተቃኘ አስተሳሰብ አስተጋብቷል። አስተምሯቸውንም እንዲኖሩት አድርጓል።
ስትራቴጂያቸው አገርን ወግቶ የበታች የሚያደርግ ነው።ለዚህ ደግሞ በብሔር መከፋፈልና የእርስበእርስ ጦርነት ማስነሳት ወሳኝ ነገር አድርጎት ተንቀሳቅሷል። ስለዚህም ያላቸውን መርዘኛ አስተሳሰብ በአሸባሪው በኩል እንዲያሰፉት ሆነዋል።የአዕምሮ ጤናቸው ሲዛባም ይህንን ማምጣቱ አይቀርምና አድርገውታል።በብርና በጥቅም አስረዋቸው መርዛማ አስተሳሰባቸውን ዘርተውባቸዋል።ያንን ለማድረግ ሲጥሩ ደግሞ ዓይናቸው ተጨፍኖ ፤ ልባቸው ሞቶ ጽንፍ የተሞላበትን ተግባር እንዲያከናውኑ አድርጓቸዋል።በእርግጥ እንደ አዕምሮ
ጤና ባለሙያዊነቴ ይህንን ሳየው የአዕምሮ ጤናቸው ሙሉ ለሙሉ መስራት እንዳቆመ ይሰማኛል።ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ራስን እስከማጥፋት የሚደርስ ሥራም ሊያሰራቸው ይችላል።ስለዚህም የተማሩትና 27 ዓመት ሙሉ እንዲኖሩት የተደረገው መርዛማ አስተሳሰብ ለዚህ ጭካኔ ድርጊት አጋልጧቸዋል።
በሃይማኖት፣ በብሄር መጣላት፤ ጽንፍ መያዝና በጭካኔ ሰውን መግደል ከአዕምሮ ጤና መዛባት የሚመጣ በሽታ ነው።ፅንፈኞቹ የአሸባሪው ህወሓት አባላትም የአዕምሮአቸው ጤና የተዛባ፣ ነገር ግን የሚረዳቸውና ህክምና የሚያደርግላቸው ያላገኙ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የአገር ውስጥ ችግርንስ እንዴት መቋቋምና የውስጥ ባንዳዎችን መለየት ላይ መሰራት አለበት ይላሉ?
ዶክተር ማስተዋል፡– ጉዳዩ አንድና አንድ መልስ ሊሰጠው የሚችል ጉዳይ አይደለም።ምክንያቱም ለምሳሌ አሸባሪው ህወሓትን መንግስትም ሆነ ህዝብ ከሚችለው በላይ ታግሶታል፤ ለምኖታልም። ለአገር የሚበጀው መጣላት ሳይሆን መዋደድ ነው ብሎታል። ነገር ግን ሊቀበለው አልቻለም። ይልቁንም ከውጪው ጠላት ጋር በመተጋገዝ አገሩን ወደመውጋቱ ገባ።ስለሆነም ኢትዮጵያዊነቱ ቆርቁሮት ካልተመለሰ በስተቀር ለማከም ብዙ ማገዶ ይፈጃል። ስለዚህም እንደእኔ እምነት እንደ ህወሓት አይነቶችን ቦታቸውን እንዲያውቁ ካልተደረጉ በስተቀር መፍትሄ አይኖረውም።
አንድ የአዕምሮ ህመምተኛ ሊያጠቃ ሲመጣ መከላከል ግድ ነው። ከዚያ ውጪ ዝም ብለን ካየነው ህይወታችንን ሊቀጥፈው ይችላል። አሸባሪው ህወሓትም የዚህ አይነት ባህሪ የያዘ ነውና አገርን ከማውደሙ በፊት ቀድሞ እርሱን መግታት የውዴታ ግዴታ ነው።ይህ ደግሞ ህወሓትን ብቻ ሳይሆን ውጪዎችንም እረፉ እንደማለት ይቆጠራል። 27 ዓመት ሙሉ የፈለጋቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ምንም ያልነካቸውን የማህበረሰብ ክፍልም ለይተው ጫናቸውን ሲያሳርፉበት ነበር። አሁን እንኳን በእናወራርዳለን ስሜት በቀል በሚል ተልካሻ
ምክንያት በጭካኔ እያጠፉት ነው። በእምነት ተቋማትና የአገር ንብረት ላይ እያደረሱ ያለው ውድመትም እንዲሁ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ስለሆነም ለአገሩ የማያስብ ቡድንን እሽሩሩ ማለት አገርን ከማፍረስ አይተናነስምና ዘመቻውን አጠናክሮ ይህንን አሸባሪ ከምድረገጽ ማጥፋት ለነገ የሚተው መሆን የለበትም። ከዚህ ጎን ለጎን የትግራይ ህዝብም የኢትዮጵያ ህዝብ ነውና ብዙዎች እንዳይረግፉ ቤተሰቦቻቸውን መክረው ከዚህ ችግር ቢታደጓቸው እላለሁ።
ሲቪል እየመሰሉ የሚገቡ ሰዎችን ወንጀለኛ፣ አሸባሪ፣ የአገር ጠላት እያሉ መለየትም አዳጋች ነው። ምክንያቱም ማህበረሰቡን መስለዋል። ይህ የሚለየው ልውጥ ሰው በሚታይበት ጊዜ በየአካባቢው ለሚመለከተው አካል አስታውቆ ማንነቱ ከተጣራ በኋላ ነው። ስለዚህ የእያንዳንዱ ዜጋ ሥራ ከፍተኛ እንደሆነ ማመን ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ህወሓት ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሳለ አስተሳሰቡ ግን ከኢትዮጵያውያን ሥነልቦና የወጣ ነው። ይህንን ከየት አመጣው ይላሉ?
ዶክተር ማስተዋል፡- ከላይ እንዳልኩት ነው። ከምዕራባውያኑ የተማረው ነው። 27 ዓመታትን ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር ኑሮው ውጭው ዓለም ላይ ነው። በዚህም የውጭዎችን አስተሳሰብ ለራሱ አድርጓል። ይህ ሲባል ደግሞ ኢትዮጵያዊ ጠል አስተሳሰብን ከእነርሱ ተምሯል።ምዕራባውያን አንድን አገር በምንም መልኩ ሲደግፉ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ያስቀድማሉ። ፍላጎታቸውን የሚተገብርላቸው መንግስትንም ይሻሉ። ህወሓት ደግሞ ለዚህ የተመቸላቸው ሆኗል። ስለዚህም ስብዕናው የመጣው ከእነርሱ አስተሳሰብ ነው።
ኢትዮጵያ እንድትሆንላቸው የሚፈልጉትን ለህወሓት አስተምረውታል። ከዚያም አልፈው በቤተሰብ የተመሰረተ መንግስቱን በእግሩ እንዲቆም አድርገው ለታል።ያም በአገራቸው ተቀምጦ እነርሱ ያሉትን እያደረገ ፣ ቤተሰቦቹን ማንደላቀቅ ነበር። ይህ አካል ሲባረር ደግሞ ብዙ ነገር ሁለቱም ቀረባቸው። ወደመናደዱ የተገባውና እነርሱ ያስተማሩትን፣ አሁንም የሚመክሩትን እንዲተገብር ሆነ።አሁንም ከጎንህ ነን ስለሚሉትም ያንኑ የነበረበትን ባህሪና አስተሳሰብ በተግባር ማሳየቱን ቀጠለ።
የሰው ልጅ አስተሳሰብና ሥነልቦና በሁለት መንገድ ይገነባል።አንደኛው በትምህርት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በማህበረሰቡ ነው።እነዚህ አካላት ደግሞ ኢትዮጵያዊነታቸው በደም በስጋ አለ።አብዛኛው ኑሯቸው ግን በውጭ በመሆኑ ጭካኔን እንዲለማመዱት ሆነዋል።በሀሽሽ ሲደገፍ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ እንዲደነዝዙ ያደርጋቸዋል። ስለሆነም በአስተሳሰብና በሥነልቦና ከኢትዮጵያዊነት የወጡት ለዚህ ነው።
ህወሓት ከራሱ አልፎ የትግራይ ወጣትን ከሌላው ማህበረሰብ ጋር እንዳይቀላቀል ያደረገ ቡድን ነው።ምክንያቱም እርሱ የተማረውን ዘርግፎ አስተምሯል።‹‹አንተ የበላይ ነህ፤ አንተ የተለየህ ህዝብ ነህ፣ አማራ፣ ኦሮሞና እንትን የተባለው ብሔር እንዲህ ሲያደርግህ ነበር ፤ እነርሱ ካልጠፉ ደግሞ እናንተ መኖር አትችሉም ወዘተ›› በማለትና የሀሰት ትርክት እየነገረ በማሳደግ ጥላቻን ዘርቶባቸዋል።በትምህርት ጭምር ጭካኔን በአዕምሯቸው እንዲሰርጽ ሰርቷል።ይህ ደግሞ የአዕምሯቸው ጤና እየተዛባ የሚሄድ ወጣት እንዲፈጠር አድርጓል።
የአዕምሮ ጤና ሲባል አስተሳሰብን፣ ሥነምግባርና ተግባርን፣ ማህበራዊ መስተጋብርንና ስሜትን ይይዛል። ስለዚህም እነዚህ ነገሮች የአካባቢው ማህበረሰብ በሚፈልጋቸው ልክ ተሰባስበው መገኘት ካልቻሉ ጤናችን ይዛባል። እነዚህ አካላትም በዚህ ደረጃ ላይ ይገኛሉና ድርጊታቸው ከዚህ የመነጨ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። ለአብነት የተረጋጋ ስሜት ላይ አለመሆናቸውና ተስፋ መቁረጥ ላይ መድረሳቸው ብቻ ጤናቸው እንደተዛባ በግልጽ ያሳየናል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት እድሉን እንስጥዎት?
ዶክተር ማስተዋል፡- አንድ ነገር ብቻ ነው ማለት የምፈልገው።ይኽውም ሲመጡ ከፋፈሉን፤ ሲወጡ ግን አንድ አድርገውናልና አሁንም አንድነታችንን እናጠንክር። አሁን ያለውን ችግር የመፍታትና ያለመፍታት ግዴታ የኢትዮጵያውያን ነው። ስለሆነም አደራ የምለው ሲሄዱ፣ሲሞቱና ሲፈርሱ የፈጠሩልን አንድነት ኢትዮጵያን ለማስቀጠል የሚያስችለን ነውና እሱን አጥብቀን እንያዝ።
አስተሳሰባችን ሀብታችን ነው።ሌላው ክልል ላይ ይህ ተደረገ መባባሉ ይብቃን።ቅናት ካለብን እኛም ጋር እንዲሆን እንስራ።ለአንድ ክልል የዘነበ ዝናብ እኛም ጋር እንደሚደርስ እናስብ።ለክልላችን ብቻ ሳይሆን ለአገራችንም የምናስብ መሆንን ዛሬ ማሳየትን እንጀምር። አንድ ክልል አንዱ የኢትዮጵያ ክፍል እንደሆነ አስበን እንስራ።ኢትዮጵያዊነት ከሁሉም ይቅደም።መንፈሳዊ ቅናት እንጂ ሰይጣናዊ ቅናት የእኛ መለያ አይሁን።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
ዶክተር ማስተዋል፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2014