የዘንድሮው የኢትዮጵያ መንግስት ምስረታ ከእስከዛሬው የመንግስት ምስረታ በብዙ ነገሮች የሚለይና የተለየ እድል ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ የሚጣልበት ነው። በተለይም አገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር ብዙ የመፍትሄ መንገዶችን ማሳየትም ይጠበቅበታል። ከዚህ ትይዩ ካለፉት ዓመታት የተለየ ሥራ መስራትም እንዳለባቸው ይታመናል። በዚህም አሁን ካለው አገራዊ ሁኔታ አንጻር በተለይም ሰብዓዊነት ላይ ትኩረት ሊደረግባው በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎችን በማንሳት ከሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ከክብር ዶክተር ኦባንግ ሜቶ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በቀደሙት ዓመታት ምን አይነት አካሄድን የተከተለ ነበር፤ እንዴትስ አለፈ፤ ለውጡ ከመጣ በኋላስ ያለው ሁኔታ እንዴት ይታያል፤ አሁንስ ምን መልክ ይዟል ይላሉ?
አቶ አባንግ፡- ከ27 ዓመታት በፊት የነበረው የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በብዙ መልኩ የተመታ ነው። በተለይም በፖለቲካው አማካኝነት በርካታ ሰዎች ከመታሰር እስከ መገደል ድረስ ብዙ ስቃይ ያስተናገዱበት ነበር። ስቃዩም ቢሆን በቀላሉ የሚዘረዘር አልነበረም። ማረሚያ ቤቶቹ በራሳቸው የስቃይ እንጂ የመታረሚያ አልነበሩም። ይህንን የሚያደርገው ደግሞ መንግስት እንጂ ግለሰቦች አልነበሩም። መንግስት ማንም የሚከራከረው አይነት መሆንን አይፈልግምና ወጣ ብሎ ለአገሩ የሚሟገት ግለሰብ ካለ ስቃዩ ይበረታል። ሊረሸንም ይችላል። ከእርሱ አልፎ ቤተሰቡም ብዙ ችግር ይደርስበታል። በአጠቃላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ከልክ ያለፈ ነበር።
ለዚህም ምንም አይነት መረጃ እንዳይገኝ ተደርጎ ሲሰራበት የነበረው አካሄድ ማሳያ ነው። በመንግስት ከፍተኛ ተቋማት የሚባሉትንም ቢሆን የሚያሽከረክራቸው እርሱ በመሆኑ ለፈለገው ዓላማ ይጠቀምበታል። ለአብነት የጸጥታና ደህንነት ክፍሉን በመያዝ ብዙ ነገሮች እንዲታፈኑ አድርጓል።
ህዝቡ መፍትሄ በማጣቱም ተቋማቱን እንዳያምን ብቻ ሳይሆን እየተሰቃየ ጭምር ችግሩን እንዳይናገር ሆኗል። ምክንያቱም የባሰ ይመጣብናልን ይፈራል። ይህ ደግሞ የእርስ በእርስ አለመተማመንን ፈጥሮበታል። ለዛሬ መራራቃችንም መሰረቱ ይህ ነው።
ዶክተር አብይ ከመጣ በኋላ ሰዎች መነጋገር በመጀመራቸው ሴራው በብዙ መልኩ ወጥቷል። የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲያስከትሉ የነበሩ አካላትም ሁሉም ባይሆኑ በብዙ መንገድ ተጠያቂ ሆነዋል። የነበሩ ጥሰቶችም ለህዝብ ይፋ ሆነዋል። ይህ ሲታይ ደግሞ መናገር የፈራው ሁሉ ብሶቱን እንዲያወጣ አድርጓል። ይህ ደግሞ በአዲስ መልኩ ጭምር የተቋቋሙ የሰብዓዊ መብት የሚጣስባቸው ስፍራዎች እንዲወጡና እንዲዘጉ አድርጓል። ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ ዋና ዋና መንግስታዊ ተቋማትም ቢሆኑ ሙሉ በሚባል ደረጃ ማሻሻያዎች ተደርጎባቸው የመንግስት ሳይሆን የህዝብ አገልጋይ እንዲሆኑ እድል ተሰጥቷቸዋል። ባለስልጣናቱም ቢሆን ሲቀየሩ የታየበት ነው። ለምሳሌ እንደ እነ ዳንኤል አይነት የችግሩ ሰለባ የነበሩ ሰዎች ቦታውን እንዲይዙት ተደርጓል።
ለውጡ ከመጣ በኋላ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚከሰቱት በመንግስት ሥራ ወይም በፖለቲካው ጉዳይ ሳይሆን ግለሰቦች ጫና የሚደረግ ነው። ስለዚህም ህወሓት የሚያራምደው ሴራና አሰራር በግለሰቦች አማካኝነት በመቀጠሉ የሆነ እንጂ አሁን በተሾመው አካል የመጣ እንዳልሆነ በግልጽ ይታያል። ምክንያቱም በፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ሰዎች ሳይሆኑ እየተገደሉና ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉት ምንም የማያውቁት ናቸው። እንስሳት ሳይቀሩ የችግሩ ሰለባ እየሆኑም ይገኛሉ።
እነሻሸመኔና ቡራዩን ጨምሮ አሁን የምናየው አማራ ክልልና አፋር ክልሎች በጭካኔው ስብዕና እየተጎዱ ያለውም ለምን ስልጣኔን ተቀማሁ በሚል እንጂ መንግስት በአዋቀረው ተቋም ችግር አለያም በተከተለው አካሂድ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። የተዘራው መርዝ ቆይቶ በማገርሸቱም ምክንያት ጎረቤት ከጎረቤት እንዲገፋፋም ሆኖበታል። ትውልዱ የተሰራበት አሻጥርና የአመለካከት ችግር እንዲሁም በብሔር የማሰብ ሁኔታ ዛሬ ላይ አድጎ ጥላቻን ወደተግባር እንዲቀይረው አድርጎታልም። ስለዚህ ይህ ሁኔታ ከህገመንግስቱ ጀምሮ መሻሻል ካልቻለና ከብሔር አስተሳሰብ ወጥቶ በአገራዊ ስሜት መስራት ካልተቻለ አልሸሹም ዞር አሉ እንደሚሆን አምናለሁ። እናም አዲሱ መንግስት አዲስነቱን በኢትዮጵያዊነት ስሜት ሊያድሰው ይገባል። በብሔር ማሰብን ማስቆም ላይ መስራት አለበት።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ በእኔ አመለካከት በዝቷል እንጂ አልቀነሰም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ባለፉት ዓመታት የተሰሩ ሥራዎችና የጥላቻ ስብከቶች ናቸው። ጥላቻው ንጹሃኑ ሰርቶ እንዳይበላ እንኳን ገድቦታል። በተለይም አርሶአደሩ የእርሻ ጊዜው እንዲያልፍ ብቻ ሳይሆን ባለበት ቦታ ጭምር ተረጋግቶ እንዳይኖር ሆኗል። በህይወት መኖሩም ጥያቄ ውስጥ እየገባ ሲሆን፤ ቤተሰቡም እየተገደለበት ነው። እናም ከዚህ አኳያ አሁን ያለው ሁኔታ ከሰብዓዊ መብት አንጻር ከፖለቲከኛው ወደ ንጹሃኑ ፤ መንግስት ከሚያደርገው ወደ ቡድን ተዛወረ እንጂ ለውጥ የለውም።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ከሆነ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ከዚህ በኋላ ያለውን ሁኔታ እንዴት ሊቃኘው ይገባል ይላሉ?
አቶ ኦባንግ፡– መንግስት የሚያስፈልገው በዋናነት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ ነው። ይህ ዋነኛ ተግባሩ መሆኑን አውቆ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል። ለይስሙላና ለስልጣን የሚያመቻቸው ነገር ሊኖር አይገባም። ከዚህ በፊት ለስልጣኑ ከተመቸው የማንም ጉዳይ ጉዳዩ አይሆንም። የብሔር ጸቦችም ያስፈለጉበት ምክንያት ስልጣን እንዲቆይ ለማድረግና ደጋፊን ለማብዛት ነው። ስለሆነም አሁን ይህ ቅድሚያ ሊታሰበብበት የሚገባ ጉዳይ ሊሆን ያስፈልጋል። ህዝብ እንጂ ስልጣን ቅድሚያ የሚያመቻቹት ነገር መሆን የለበትም። አሁን የብሔሮች ደህንነት ሳይሆን የዜጎች ደህንነት ካልቀደመ ብዙ ዋጋ ይከፈላል። ስለዚህም መንግስት ህዝቡ እንዲያምነው በዚህ ላይ መስራት ይኖርበታል። በህዝቡና በመንግስት መካከል መተማመን እስካልተፈጠረ ድረስ አዲስ መንግስት ሊመሰረት አይችልም። ተመሰረተም ቢባል ቅቡልነቱ ከቀደመው የተለየ አይሆንም። ስለሆነም በህዝብ ዘንድ አመኔታ የሚጣልባቸውን አካላት ያሳተፈ ሥራ ሰርቶ ውጤቱን በተግባር አዲስነቱን በዓይን ማሳየት ይጠበቅበታል።
የውይይት መድረኮችን በነጻነት መክፈትና የጉዳይ ወሰን ሳይኖር ውይይት እንዲደረግ መፍቀድ ያስፈልጋል። ምክንያቱም በመነጋገር ውስጥ መደማመጥና የተግባር ለውጥ ይመጣል። ከሁሉም በላይ መንግስት ያለበትን ችግር እንዲያይም ያግዘዋል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ መፍትሄ ለመስጠት ቀላል ይሆንለታል። ስለዚህም ይህንን አውቆ መስራት የመጀመሪያ ተግባሩ መሆን አለበት። በተጨማሪ ስህተቶቹን አምኖ ለማስወገድ መሞከር ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን አገር ካለችበት ችግር ለመውጣት ምን አይነት ስትራቴጂ መከተል ያስፈልጋል?
አቶ ኦባንግ፡- የመጀመሪያው አገራዊ መግባባትን የሚያመጣ ስትራቴጂ መከተል አለባት። ለአገራችን ዋነኛ ፈተና የሆነው በነጻነት አለመወያየትና አገራዊ መግባባት ላይ አንድ አይነት ምልከታ አለመኖር ነው። አገራዊ መግባባት ሊኖር ይገባል በሚል ብዙው ቢስማማም ቅንነት ባለመኖሩ ሁሉም የራሱን ሃሳብ ብቻ እንዲያራምድ ሆኗል። ይህ ደግሞ መበታተንን እንጂ መግባባትን መቼም ሊያመጣው አይችልም።
አገራዊ መግባባት ማለት ህዝብ ለህዝብ ተቀራርቦ መመካከር ሲችል የሚመጣ ነው። ነገር ግን የህዝብ ለህዝብ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ባለስልጣኑና ሹማምንቱ አለያም የተመረጡ አካላት ይወያያሉ። የችግሩ ሰለባ የሆነው ብሶቱን ሳይናገር ይቀራል። ይህ ደግሞ ቂም እያረገዙ ጥላቻቸው እያደገ እንዲሄድና ያልተፈለገ ነገሮች ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል። እያደረጋቸውም ነው።
ብሔራዊ መግባባት የስልጣን ጉዳይ ሳይሆን የመኖርና አለመኖር ጉዳይ ነው። ስለዚህም ከአንድነታችንና ከልዩነታችን የትኛው እንደሚጠቅመን አሁን መመልከት ይኖርብናል። የብሔር ፖለቲካ ጥሩ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የት በደረስን ነበር። ነገር ግን እርሱ የት ላይ እንደአደረሰን በሚገባ ኖረነው አይተናል። ስለሆነም አዲሱ መንግስት ሰው መሆንን ያስቀደመ ተግባር ማከናወን ላይ ትኩረቱን ማድረግ ይኖርበታል።
የትም አገር ላይ ሰው በብሔሩ ሲፈናቀል ሰምተን አናውቅም። እኛ አገር ግን እየሆነ ያለው ይህ ነው። ይህ የመጣውም የአሸባሪውን አሰራርና ለእርሱ እንዲመቸው ያደረገውን ህገመንግስት በመከተላችን ነው። ስለሆነም ያለፈውን ችግር ላለመድገም የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን መጠቀም ለአዲሱ መንግስት አዲስነቱን የሚያቀዳጀው ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን አገር ካለችበት አኳያ የአዲሱ መንግስት ሲመሰርት ምን መልካም አጋጣሚዎች እና ፈተናዎች ያጋጥሙታል ብለው ያስባሉ?
አቶ ኦባንግ፡– አሁን እየመጣ ያለው አንድነትና መረዳዳት ምቹ ሁኔታ ነው ብዬ አስባለሁ። በዚህ ላይ መጨመርና ማሳደግ ብቻ ነው የሚጠበቀው። ኢትዮጵያዊነት አሁን አንሰራርቷል፤ ግን ማጠንከርን ይፈልጋል። በተመሳሳይ እኛ ድሃ አለመሆናችን አስቻይ ሁኔታው ነው። ምክንያቱም በተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በጉልበት ከዓለም አገራት የተሻልን ነን። እናም ያንን በአግባቡ መጠቀም መቻል ብቻ ነው የሚጠበቅብን። ስለሆነም አዲሱ መንግስት ይህንን እያሳየ መስራት ከቻለ ብዙ ለውጦች ይመጣሉ።
በፈተናነት ይገጥሙታል ብዬ የምገምታቸው ብዙ ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው ህገ መንግስቱ ላይ ያሉ ተገቢነት የሌላቸው ነገሮች ናቸው። ከፋፋይ የሆኑና ለስልጣን ማራዘም ብቻ የሚያገለግሉ ሃሳቦች ብዙ ናቸው። ስለዚህም እነዚህን ማስወገድ ካልተቻለ ፈተናው ቀላል አይሆንም። በተለይም በብሔርና በክልል መከፋፈሎች ኢትዮጵያዊነትን ያደበዝዛሉ። እንደ አገር ለመስራትም እንቅፋት ይሆናሉ። አንድነትንም ቢሆን ይሸረሽራሉ። ይህ ደግሞ አሁን ያለውን ችግር በስፋት እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው።
እናም እዚህ ላይ በስፋት መስራት ያስፈልጋል። የቆይታ ጊዜያቸውን መሰረት ሲጥሉ ለራሳቸው ምቾት ሳይሆን ለህዝባቸው አድርገው መስራት ይኖርባቸዋል። ከግለሰብ የጀመረ የአመለካከት ለውጥም መምጣት አለበት። ለራሳችን የምንፈልገውን ለሰውም እንዲሆን ካልፈቀድን መቼም ሰላም አይመጣም። ስለሆነም እንደሰው መኖርን በማሰብ ላይ መስራትም ይገባል። ምክንያቱም ከአገር ስንወጣ ኢትዮጵያዊነትን እንጂ የምናስበው ብሔር የለንም። በዚህም መንግስት የብሔር የበላይነትን ሳይሆን የህግ የበላይነትን ማስከበር ላይ ትኩረቱን አድርጎ መስራት ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- የመገፋፋት ፖለቲካ ባለበት አገር ውስጥ ሾልኮ ወጥቶ አገርን ማጉላት ላይ አዲሱ መንግስት ትልቅ ሃላፊነት እንዳለበት እሙን ነው። ይህንን በድል ለመወጣት ማን ምን ማድረግ አለበት?
አቶ ኦባንግ፡– ውሸት ፍቅር ከሆነ መቼም ማሸነፍ አይቻልም። አንድነትም ወሬ ከሆነ መቼም ጥንካሬን ሊያላብሰን አይችልም። በማስመሰልና በውሸት የተጣለ መሰረትም ቢሆን እንዲሁ የቀደመ ታሪክን ይደግማል እንጂ አዲስ መንግስት ሊመሰርት አይችልም። ስለሆነም ከወሬ ወጥቶ መስራት አገርን ወደ ድል ያመጣልና ይህንን ማድረግ ያስፈልጋል።
አመለካከት ክስረትም ድልም ነው። ከዚህ አንጻር አመለካከትን በአገራዊ ስሜት መስራት ፤ ከጎጠኝነት አስተሳሰብ ማላቀቅ የመጀመሪያው የድል ለውጥ ማምጫ ነው። በመሆኑም አዲሱ መንግስት እያንዳንዱን ዜጋ ከብሔሩ ይልቅ አገሩን እንዲያስቀድም የሚያደርግበትን አሰራር መቀየስና ተግባራዊ ማድረግ ከቻለ ሌላው የድሉ ባለቤት የሚሆንበትን መንገድ ያገኛል።
ሌላው ለህዝቡ ቅርብ የሆኑ ሰዎችን በመጠቀም ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት መሞከር ፉክክሩን ያጠበዋል። አገርም ወደ ድል ጎዳና እንድትጓዝ ያደርጋታል።
አዲስ ዘመን፡- የኢኮኖሚ ጉዳይ ለሰብአዊ መብት ጥሰቱ መባባስ ዋነኛ ችግር እንደሆነ ይታሰባል። በቀጣይ ይህ ሁኔታ እንዳይስፋፋና ችግር እንዳይሆን ከማድረግ አንጻር አዲሱ መንግስት ምን መስራት አለበት ብለው ያስባሉ?
አቶ ኦባንግ፡- ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚደርስበት በፖለቲካ ብቻ አይደለም። በማህበራዊውና በኢኮኖሚም ችግር ይጣሳል። በዚህም ከኢኮኖሚ አንጻር ስናነሳ አሁን ላይ ብዙ ችግሮችን ማንሳት እንችላለን። ጥሩ መኝታ፣ ጥሩ ምግብና ጤና አለማግኘት የኢኮኖሚው ችግር የሚያመጣቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ናቸው። ይህ ደግሞ እየሆነ ያለ ነው።
የኑሮ ውድነቱ ብቻ አሁን ላይ ብዙዎችን ወደከፋችግር እየከተታቸው ይገኛል። ለዚህ መንስኤው ደግሞ ሰላም አለመኖር ነው። ሰላም ካለ መስራትና መልማት ይኖራል። ይህ ካለ ደግሞ መሰረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች በቀላሉ ይሟላሉ። ነገር ግን በሰላም እጦት ይህ አልሆነም።
ሀብት ለማፍራት ሰው ያስፈልጋል። አሁን ደግሞ ሰዎች እየሞቱ ናቸው። እየተሰደዱና እየተፈናቀሉም ነው። በዚያ ላይ መተማመንም አልተቻለም። የምንገበያየው ከብሔራችን ብቻ እንዳልሆነ ቢታወቅም በተዘራው ክፉ ዘር ምክንያት ይህም ሰዎችን እያሳጣን ይገኛል። ስለዚህ መንግስት በዚህ ላይ መስራት እስካልቻለና ሰላምና መረጋጋቱን እስካልፈጠረ ድረስ አሁንም የኢኮኖሚ ችግሩ የማይቀጥልበት ሁኔታ የለም።
ሥራ ላጣው ወጣትም ህልም ካለ ተግባር ይኖራልና የሚያልመውን ነገር ሊያሳየው ይገባል። ከውጭ ለምነን ችግሮችን መቋቋም እንደማንችልም ለእያንዳንዱ ዜጋ ማስረዳትና ወደ ሥራ እንዲገባ ማድረግ ላይ ስትራቴጂ መንደፍም ዋነኛ ተግባሩ ሊሆን ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የደህንነት ጉዳይ አሁንም ለሰብአዊ መብት ጥሰቱ መንስኤ ነው። ከዚህ አንጻርስ ከአዲሱ መንግስት ምን ይጠበቃል?
አቶ ኦባንግ፡- ሰላምና ጸጥታ የሚረጋገጠው ጁንታ የሆነውን ሰው ለይቶ ማውጣት ሲቻል ነው። በአሸባሪው አስተሳሰብ ውስጥ ያሉ አመራሮችና ተቋማት በደንብ መፈተሽ ይኖርባቸዋል። ማህበረሰቡም ይህን የሚያረጋግጥበትን ሁኔታ ማየት ይኖርበታል። በተለይም መንግስት ለህዝብ መስራቱን ማረጋገጥ አለበት። በጁንታው አሰራርና አካሂድ እየተጓዙ አዲስ ነን ለማንም የሚዋጥ አይሆንም። ስለዚህም አስተሳሰቡን የሚያራምዱ ሁሉ ከስልጣናቸው መውረድ አለባቸው። አሁን ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በስፋት የሚያራምዱት እነርሱ እንደሆኑ እየታወቀ አዘኔታ ለእነርሱ ማሳየት ግን በርቱ እንደማለት ነው። ስለሆነም መንግስት በዚህ ላይ ሊሰራ ይገባል።
አብዛኛው በሚባል ደረጃ አዲሱ መንግስትን የተቀላቀለው የኢህአዴግ አመራር ነው። ይህ ደግሞ የቀደመ አስተሳሰብን በአንድ ጊዜ ለማውጣት ያስቸግረዋል። ስለሆነም አዲስ አሳቢ ማድረግ ላይ ካልተሰራ ብዙ ችግሮች ይፈጠራሉ። በተለይም ከጸጥታ አካላት ጋር በተያያዘ ብዙ ነገሮች መሰራት ይኖርባቸዋል። ራሳቸው ጁንታ ሆነው ጁንታ የሚሉ ብዙ ናቸው። በመሆኑም እነዚህን አካላት ነጥሎ እርምጃ መውሰድ ላይ አዲሱ መንግስት ቁርጠኛ መሆን ይኖርበታል።
አገራዊ ጉዳይን ትቶ ብሔሩ ላይ ትኩረት የሚያደርግና የሚያቀነቅነውንም በሚገባው ደረጃ አቅጣጫውን እንዲያስተካክል ማድረግም ያስፈልጋል። የአካባቢው ሰውም ራሱን እንዲጠብቅና ችግር ፈጣሪዎችን እንዲለይ በማድረግ ጸጥታና ደህንነትን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። ሰውኛ እሳቤን የሚያራምዱ ሰዎችን በመምረጥና በሙያቸው በማሰማራት መስራትም ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሙያ የሌለው ራሱን ለማቆየት የማይፈጽመው ወንጀል አይኖርም። እናም ይህንን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መስራት ለጸጥታው መጠበቅ ሁነኛ መፍትሄ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ነገ ለምንገነባት ኢትዮጵያ ምን አይነት አወቃቀር ያስፈልጋል፤ ታች ያለውንስ አመራር እንዴት መለወጥ ይቻላል ?
አቶ ኦባንግ፡- የትኛውም አገር የሚተዳደረው በህግና በህግ ነው። በዚህም ህገመንግስታዊ አወቃቀርን መጠቀም ህግን ከመፈጸም አኳያ ታይቶ የሚደረግ ከሆነ ለውጡ በሚገባ አገርን ይገነባል። ነገር ግን ህጉ ሌላ አወቃቀሩ ሌላ አፈጻጸሙም እንዲሁ ሌላ ከሆነ መቼም አገር አትገነባም። ምክንያቱም ሁሉም ለግለሰቦች ጥቅም እየሆነ ያለ ነው።
ከአገር በላይ፣ ከህዝብ በላይ በመንግስትነት ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ይታሰባሉ። ይህ ደግሞ ወደላይ እንጂ ወደታች የሚያይ እንዳይኖር ያደርጋል። እስከዛሬ እየሆነ ያለውም ይህ ነው። በየቀበሌው ጭምር ያለው አመራር ታላቅ ተደርጎ ይታሰባል። ህዝቡ ግን ተጠቃሚነት የለውም። ይህ መሆኑ ደግሞ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን አለመተማመን አስፍቶታል።
ከዚህ ቀደም በነበረ ታሪክ ሰውን ሳይሆን እንሰሳትን ነበር የምንፈራው። አሁን ግን ጎረቤታችንን ጭምር እንድንፈራና እንድንጠራጠረው ሆነናል። ይህንን ያመጣው ደግሞ ቀደም ሲል የነበረው መንግስትና ቡድን ነው። ስለሆነም በእነዚህ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድና ቀጣይም ዋጋ እየከፈልን እንዳንጓዝ መቋጫ ማበጀት ዋነኛ ሥራው መሆን አለበት።
አዲሱ መንግስት የራሱ ሳይሆን የአገርና የህዝብ መንግስት መሆን ላይ መስራት አለበት። አዲስ ማለት በአመለካከትና አስተሳሰብ አዲስነትን ማሳየት፣ በፖለቲካም እሳቤ አዲሱን መሆን፣ በአካሄድና በአደረጃጀት አዲስ ሥራ መስራት ነው። ስሙና ተግባሩ የማይገናኝ ከሆነ አሮጌውን እንጂ አዲሱን እንዳልመሰረተው መረዳትም ያስፈልጋል።
አሮጌው ዘመን ሲወጣ አዲሱ ገባ ስንል ካልተለወጥንበት አሮጌውን እየኖርን ሳንሻሻል እንደምንቀር ሁሉ አዲስ መንግስት መሰረትን ብለን የትናንቱን የምንኖረው ከሆነ ሁሉም ነገራችን ተቀባይነትን ያጣል። በተለይም ህዝቡ አሮጌውን ማስተናገድ ከዚህ በኋላ የሚችል አይደለም። ስለሆነም አዲሱ መንግስት እንደስሙ አዲስ መሆን ይጠበቅበታል። አዲስነት ተግባራዊ መገለጫው መሆን አለበት።
በማስመሰልና በውሸት የሚደረጉ መሿሿሞች መቆም አለባቸው። በብሔር ላይ ጥገኛ የሆኑ አሰራሮችም መቅረት ይኖርባቸዋል። እውነትና ሥራ የተዛመደበት ተግባርን መከወንም ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ቀደም ሲል የኖርንባቸው መልካም ባህሎችና ታሪኮች ስላሉን እነርሱን መጠቀም ብቻ ነጋችንን እንድንሰራው ያግዘናል።
አዲስ ዘመን፡- ነገ ብዙ ጥያቄዎች እንደሚነሱ እሙን ነው። ይህንን ተረድቶ የአገሪቱን ብልጽግና ከማረጋገጥ አኳያ ምንምን ተግባራት መከናወን ይኖርባቸዋል፤ የተለያዩ አካላት ፓርላማውን ስለተቀላቀሉ ጥያቄውን ለመመለስ የሚረዱበትስ ልክ ምን ያህል ነው ?
አቶ ኦባንግ፡- ይህ መሆኑ ብዙ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ እድል የሚሰጥ ነው። ሃሳብ መጣ ማለት ደግሞ መፍትሄው ታየ ማለት ነው። ስለዚህ አሁን የሚመሰረተው መንግስት ጥያቄዎቹን የሚፈታበትን ብዙ እድል ያገኛል ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን እውነትም አዲስ መሆን እንደሚችል ካመነ ብቻ ነው።
በፓርላማ ውስጥ ብዙ ያለመስማማቶች ይኖራሉ። ነገር ግን አሸናፊ ሃሳብ መምጣት ይችላል። ለዚህ ደግሞ አሁን የገባው ተፎካካሪ ሃይል ብቃቱን ማሳየት ይጠበቅበታል። ብልጽግናም ቢሆን ብዙ የቤት ስራ አለበትና ከቀደመው የተሻለ መሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት። ስህተቱን ማመንና ከስህተቱ ለመማርም ዝግጁ መሆን ወደቀደመ ስህተት እንዳይገባ ያደርገዋልና አዲሱ መንግስት ይህንን እውነት መጠቀም ይኖርበታል።
አዲሱ መንግስት ከሁሉም በላይ በአለመስማማት ውስጥ አገርን አስቀድሞ መስራት መለያው ሊሆንም ይገባል። መተማመን ላይም በስፋት መስራት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን የሚመሰረተው መንግስት ምን አይነት ማህበረሰብ እንዲፈጠር መስራት አለበት ይላሉ?
አቶ ኦባንግ፡– መንግስት ማለት ህዝብ ነው። በአሰራር ስለተለያየና ይህንን አስቦ የሚሰራ ስለሌለ ነው የተለያየ የመሰለው። ስለሆነም አዲሱ መንግስት ከህዝብ ያልተለየ ሥራ በመስራት ማህበረሰብን ከእንደገና መፍጠር ይጠበቅበታል። የማይለያይ፣ ለአገሩ የሚያስብና ስለ አገሩ የሚሞት ማህበረሰብን እንዲታይ ማድረግም ዋነኛ ተግባሩ መሆን አለበት።
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉም በሚባል ደረጃ ህዝቡ አገሩ በውስጡ የተጻፈችለት ነው። ትንሽ ከኮረኮሩት ስሜታዊ ሆኖ ስለ አገሩ ሆ ብሎ የሚነሳ ነው። ነገር ግን በተሰራበት ሥራ ያንን አገራዊ ፍቅሩን እንዳያወጣው ሆኗል። እንዳይናገረውና ለሌላው እንዳያስተምረውም ታምቋል። ስለሆነም አዲሱ መንግስት መስራት ያለበት ስለአገሩ የሚዘምርበትን ነጻ መድረክ መፍጠር ነው። ነጻነቱን ማወጅና የቀደመ የመተባበር ባህሉን በኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲያመጣውና እንዲያጎለብተው ማገዝ ነው።
አንተ የእንትና ወገን ነህ እያሉ መለያየቱን ማስቆም ይጠበቅበታል። ልዩነት ሳይሆን አንድነት ዳግም መሰበክ አለበት። ዛሬ ድረስ እያተረፈን ያለው ቢታፈንም ያልጠፋው አንድነታችን ነው። እናም የአዲሱ መንግስት ዋነኛ ተግባር ማህበረሰብ ፈጠራ ላይ የነበረውን እንዲያመጣው ነጻ ፈቃድ መስጠት ብቻ ይመስለኛል። ህዝቡ በራሱ በአዕምሮው ውስጥ ያለ እውነታው ስለሆነ ያወጣዋል። በዚህም ለውጥ የሚባለው ተግባራዊ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ከተደራሽነት አንጻር፣ ከፍትሃዊነትና አሳታፊነት ላይ እንዲሁም ሀብትን በፍትሃዊነት ከማዳረስ አንጻር ምን መስራት አለበት?
አቶ ኦባንግ፡– አሰራሮችም ሆኑ አደረጃጀቶች መዋቀር ያለባቸው በሙያ እንጂ በብሔር አለያም በወዳጅነት ሊሆን አይገባም። ይህ ከሆነ ክልሌ፣ ብሔሬ የሚለው አሰራር አይኖርም። ሥራው ሁሉ አገር ተኮር ሙያ ተኮር ብቻ ይሆናል። ስለዚህም ለፍትሃዊነት አሰራር እነዚህ አካሂዶች ጠቃሚ ናቸው የሚል እምነት አለኝ።
የእኛን አቋም የሚቀበሉና የሚያራምዱ አካላት ይግቡና ይስሩ ከተባለ ግን አሁንም የጸብ መነሻ የነበሩ ተግባራት ይቀጥላሉ። ስለሆነም አዲሱ መንግስት እውቀትና እውቀት ተኮር ሥራ መስራት አለበት። ሲሳሳት መመለስና እንቢ ማለትም የህዝቡ ግዴታ እንደሆነ ማሳየትም ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- በዲፕሎማሲ ሥራዎች ዙሪያስ አዲሱ ፓርላማ ምን መስራት አለበት?
አቶ ኦባንግ፡- መጥፎ ነገሮችን የሚናገሩ ሰዎችን ማስተካከል ብቻ ሳይሆን ጥሩ ግንኙነቶችን ማጠንከርም ነው ዲፕሎማሲን የሚገነባው። ስለዚህ እንደ አገር አሁን ቴክኖሎጂው በረቀቀበት ወቅት ውሸት በበዛበት ጊዜ ሁሉንም መስማት ዋጋ ያስከፍላል። እናም የምንሰማውንና የምንሰራውን መምረጥ ይጠበቅብናል።
ኢትዮጵያን የሚጠሏት እንዳሉ ሁሉ የሚወዷትም መኖራቸውን ማሰብም ያስፈልጋል። እነዚህን ደግሞ መጠቀምና ወዳጅነታቸውን እንዲያጠነክሩ ማድረግም ዲፕሎማሲውን ለማስፋት ይበጀናል። ለዚህ ደግሞ ዲፕሎማቶችን፣ በተለያዩ አገራት የሚኖሩና ቋንቋውን የሚችሉ ኢትዮጵያውያንን መጠቀም አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያን መንግስት እንደራሳቸው መንግስት አድርገው እንዲያምኑ ማድረግ ላይ አዲሱ መንግስት ሊሰራ ይገባል። ቀደም ሲል የነበረው አሰራር ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ምክንያቱም በቢሮክራሲና በተለያዩ ነገሮች እያሰረ እነርሱን አገራቸውን እንዳይወዱ አድርጓል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያውያኑ የሌላ ደጋፊ፣ የሌላ አገር አገልጋይ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። እናም ይህ ጉዳይ መፈታት የሚገባው ጉዳይ ነው።
አዲሱ መንግስት ለዲፕሎማሲው እድገት ካሰበ በትልልቅ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የሚሰሩ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በብዙ መንገድ መሳብ አለበት። የመጀመሪያው እነርሱን ማሳመንና ለአገሩ የሚሰራ ማድረግ ነው። ከዚያ የሚያገለግሉት አገር ሁሉ የኢትዮጵያ ደጋፊ ይሆናል። ይህ ደግሞ ጫናዎችን ያቀላል፤ አሰራሮችን ያስተካክላል፣ አገራችንን የሚደግፋትንም ያበዛል። በዚህም የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማማ ላይ ያደርሰናል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
አቶ ኦባንግ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 24/2014