ቅድመ- ታሪክ
ተወልዶ ባደገበት የገጠር ቀበሌ ወላጆቹን በስራ ሲያግዝ፣ ሲያገለግል ቆይቷል። በልጅነቱ እንደ እኩዮቹ ትምህርትቤት ቢሄድ ይወድ ነበር። የቤተሰቦቹ ችግር ግን ለዚህ ዕድል አላበቃውም። ጓደኞቹ ከቀያቸው ወጥተው ትምህርት ቤት ሲውሉ እሱ እነሱን ከማየት የዘለለ ምርጫ አልነበረውም። ያም ቢሆን ብዙ አልተከፋም። እናት አባቱን በስራ እየረዳ ከግብርናው መዋል ያዘ።
ደሞዝ ጉልበቱን ለወላጆቹ መክፈሉ መልካም ሆነለት። በየቀኑ ከእነሱ የሚያገኘው ምርቃት ብርታት ሰጠው። ደስ እያለው በትጋቱ ቀጠለ። በሬዎቹን ጠምዶ በማረሱ፣ ጎተራ ሙሉ ምርት በማፈሱ ምስጋናን ከክብር ተቸረ።
ደሞዝ የሺጥላ የልጅነት ዕድሜውን በዚህ መልኩ አጋመሰ። ዓመት አልፎ ዓመት ሲመጣም መልካም ገበሬ መሆኑን አስመሰከረ። ይህ እውነት ብዙ አልቀጠለም። የወላጅ እናቱ ድንገቴ ሞት ታሪኩን ሁሉ ቀየረው። ደሞዝ እናቱን ከሞቱ በኋላ ግራ ተጋባ ፣ተስፋው ሁሉ ጨለመ። ከእዚህ በኋላ መልፋት መድከሙ ውጤት አልባ ሆኖ ተሰማው።
ደሞዝ እናቱን ካጣ በኋላ ጥቂት ጊዜያትን በተለመደው መልኩ ቀጠለ። በሬዎቹን ጠምዶ፣ ከእርሻ ከግብርናው ዋለ። ምርቱን ሰብስቦ ከጎተራው፣ ከብቶቹን ከበረቱ አሳደረ። ሁሌ ማለዳ ከእርሻው ሲገናኝ አእምሮው ርቆ ይሄዳል። ስራውን እየከወነ፣ አፈሩን እየገለበጠ ከራሱ ጋር ይማከራል።
ደሞዝ በግብርናው ጥቂት እንደቆየ ከሰፈር ቀዬው መውጣት፣ መራቅን ፈለገ። ይህ ሃሳብ አብሮት የከረመ ነውና ለውሳኔ አልዘገየም። እንደ እኩዮቹ ባይማርም ለአቅሙ የሚመጥን ስራ እንደማያጣ ተማምኗል። በእሱ ልክ የሚያስባቸው የአገሩ ልጆች አዲሰ አበባ ዘልቀው ራሳቸውን ለውጠዋል። ቤተሰባቸውን ደጉመዋል።
አንድ ቀን ደሞዝ ሁሌም ከሚውልበት እርሻው ሳይታይ ዋለ። ማግስቱን በዓይን የፈለጉት ሁሉ በስፍራው አላገኙትም። ደጋግሞ ያለመኖሩን ያስተዋሉ የቅርብ ሰዎች ወዴት የት ሄደ? ሲሉ ጠየቁ። ስለ ደሞዝ አወቅን ፣ሰማን ያሉ ሰፈር ቀዬውን ትቶ አዲስ አበባ መግባቱን ተናገሩ።
አዲስ አበባ …
ገጠር ተወልዶ ያደገው ወጣት አዲስ አበባ ከገባ ቀናት ተቆጠሩ። በዚህ ከተማ በርከት ያሉ ያገሩ ልጆች ዓመታትን ገፍተዋል። ደሞዝ የቅርብ ዘመዶቹን ጨምሮ በስም የሚያውቃቸውን ሁሉ ካሉበት ሄዶ አገኛቸው። ሁሉም በመልካም ተቀብለው አካባቢውን አላመዱት።
ከደሞዝ ያገር ልጆች አብዛኞቹ ጉልበታቸውን ከፍለው የሚኖሩ ለፍቶ አዳሪዎች ናቸው። ወደዚህ ስፍራ ለሚመጡ እንግዶች መጠጊያ በመሆን ሲያግዙ ቆይተዋል። ከነዚህ መሀል በጥበቃ የተሰማሩ፣ በቀን ሰራ የሚውሉ ፣ ደልለው ሸቅጠው ፣ የሚገቡ በርከት ይላሉ።
ደሞዝ በአዲስ አበባ አዲስ ህይወትን ጀመረ። አካባቢውን ተላምዶ ከሌሎች ሲግባባም መተዳደሪያውን አገኘ። የመጀመሪያ ምርጫው በቀን ስራ ገንዘብ ማግኘት ነበር። ስራውን እንደጀመረ ከበድ ቢለውም ቆይቶ ለመደው። በቀን ውሎው እየለፋ ከሚያገኘው ገንዘብ መያዝ መቆጠብ ጀመረ።
ውሎ አድሮ እሱም እንደሌሎቹ ቤት ተከራየ። ቤቱ ስራ ውሎ ሲገባ ጎኑን የሚያሳርፍበት ጎጆ ሆነው። ኪራይ እየከፈለ፣ በአቅሙ እያበሰለ ስራውን ቀጠለ። አዲስ አበባና የገጠሩ ወጣት እያደር ተግባቡ። ከተማዋ የሰጠችውን በረከት እያጣጣመ በላብ በወዙ ፣ ማደርን አወቀ።
ደሞዝ ኑሮው አዲስ አበባ ከሆነ በኋላ ህይወቱን በተሻለ ለመምራት ታገለ። የከተማ ህይወት እንደገጠር አይደለም። ትናንት ከእርሻው የሚያፍሰው እህል ዛሬ በከተማ በእጥፍ ጨምሮ ገንዘብ ይጠይቀዋል። ከማጀት የሚቀዳው እርጎ ከሞሰብ የሚቆርሰው እንጀራ ሁሉ አመጣጡ ይለያያል። የቀድሞ ህይወቱ ከዛሬ ኑሮው ፈጽሞ አይገጥምም ።
የአዲስ አበባው እንግዳ ይህ ልዩነት እያደር ሲገባው አማራጮችን ፈላለገ። በስራው ከሚያገኘው ገቢ ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ ቢያገኝ ተመኘ። ይህን ለማሳካትብዙ አልተቸገረም። በጥበቃ ለማገልገል ከጠየቃቸው አሰሪዎች በአንደኛው ቤት ሊቀጠር ተስማማ።
ደሞዝ ቀን ሲለፋ የሚውልበትን የቀን ስራ አጠናቆ ማታ ወደሚጠብቅበት የጥበቃ አዳር ይገባል። ያለበት አካባቢ የግንባታ ስራዎች የበረከቱበት ነው። ምሽቱ አስኪገፋ ጎኑን ከፍራሹ አጋድሞ ጥቂት አረፍ ይላል። ይህኔ ዕንቅልፍ በዓይኑ እየዞረ ይፈትነዋል። የቀን ድካሙ ይመለሳል።
ድካም የዋለበት አካሉ እረፍትን ቢሻም እሱ ግን አይፈቅድለትም፡ ፡ጠንከር ብሎ ከራሱ ይታገላል። የተረከበው ንብረት ፣ የወሰደው ሃላፊነት ውል ባለው ጊዜ ፈጥኖ ራሱን ያነቃል። እንደሱ በሌላ ሰራ የሚውሉ ባተሌዎች ጥበቃውን እንደ አማራጭ ይይዙታል።
የጥበቃ ሙያ ከባድ ሃላፊነት አለበት። በጊቢው የተከማቹ የግንባታ ዕቃዎች በተለየ ዓይን ይጠበቃሉ። ይህን የሚያውቁ የሌሊት ሌቦች ንብረቶቹን ለመዝረፍ ብቅ የሚሉበት ጊዜ አይጠፋም።
እሱና መሰል አጋሮቹ በአካባቢው ካሉ አዳዲስ ቤቶች እያደሩ የተሰጣቸውን አደራ በሃላፊነት ይወጣሉ። ኮሽ ሲል፣ ጨለማው ሲበረታ እንቅልፍ በዓይናቸው አይዞርም። ድምጽ በሰሙ ቁጥር ቆመጣቸውን ይዘው፣ ኮቴያቸውን አጥፍተው ደፈጣ ይይዛሉ። የፈሩት፣ የጠረጡት ካለም እየተጠራሩ ይተጋገዛሉ። አካባቢውን ዙሪያ ገባውን ያስሳሉ።
ይህ አይነቱ ልምድ በጥበቃዎቹ የምሽት ስራ የተለመደ ነው። ወር ሲመጣ ከቀጣሪዎቻቸው የልፋት ድካማቸውን ይቀበላሉ። የሚከፈላቸው ገንዘብ ጎዶሎን ሞልቶ ቀዳዳ ይደፍናል። ለራስ ፍላጎት ለወዳጅ ዘመድ ችግር፣ የክፉ ቀን እጅ ይሆናል።
ባልንጀሮቹ…
አምስት ናቸው። የዕድሜያቸው መቀራረብ በአንድ አውሎ በአንድ ያስመሻቸዋል። ባልንጀሮቹ ብዙ ጊዜ አብረው ሲዝናኑ ሲደሰቱ ይታያሉ። ከስራ መልስ ወደመዝናኛዎች ብቅ ባሉ ጊዜ ብርጭቆ ማጋጨት ልማዳቸው ነው። አንዳንዴ ባመሹበት ቤት ሲጫወቱና ሲዝናኑ ሰላማዊ ናቸው። አንዳንዴ ደግሞ በሞቅታ ሰበብ ያልተመቸ ባህሪን ያሳያሉ።
አምሽተው ሲገቡ አይለያዩም። ፊትና ኋላ ሆነው ይጓዛሉ። ተከራይተው የሚኖሩት በአንድ ቤት ነው። ጨለማ በሆነ ጊዜ ከመሃላቸው ዱላ የሚይዝ አይጠፋም። እያወሩ እየሳቁ፣ እየቀለዱ በስንብት ይለያያሉ። በማግስቱ ከስራ መልስ የትናንቱን ውሎና ምሽት ይደግሙታል። ሁሌም ጨዋታና ሳቃቸው፣ ቀልድና ሃሳባቸው ተመሳሳይ ነው።
ሚያዚያ 5 ቀን 2006 ዓ.ም
ቀኑን ሙሉ አምርራ የዋለችው ጸሀይ የበጋውን ሙቀት አግላዋለች። አንዳንድ መንገደኞች ዣንጥላ ዘርግተው ይጓዛሉ። አንዳንዶች ደግሞ በዛፍ ጥላዎች ተከልለው ይራመዳሉ። የሚያዚያ ወር ጅማሬ የወቅቱን ሀሩር አብሶታል። ነፋሻማው አየር በሙቀቱ የተሸነፈ፣ የተረታ ይመስላል። የጸሀይዋ ማየል ብዙዎችን እያዛለ እያዳከመ ነው።
እንዲህ በሆነ ጊዜ የቀን ሰራተኞቹ አቅም ይፈተናል። በአንገታቸው ለሚወርደው የድካም ላብ የወቅቱ ሙቀት ሰበብ ይሆናል። ለደሞዝና መሰሎቹም እንዲህ አይነት ቀናት ከባዶች ናቸው። ድንጋይ ሲያነሱ፣ ባሬላ ሲሸከሙ፣ ደረጃ ሲወጡና ሲወርዱ ከድካም ጋር ነው። የሚያዚያ ወር ሙቀት ወሩን ሙሉ ዘልቆ ከግንቦት ሲደርሰ ሃይሉን ይጨምራል። የዛኔ የባተሌዎቹ ጉልበት በእጅጉ ይፈተናል።
ደሞዝ ሚያዚያ 5 ቀን እንደለመደው ከስራው ላይ ውሏል። የዕለቱ ሙቀትና ጸሀይም ከማለዳው እስከማምሻው አብሮት ዘልቋል። የቀኑን ውሎ እንደጨረሰ እጅና እግሩን ተጣጠበ። የስራ ልብሱን ለውጦ ጫማውን በሌላ ቀየረ። ከአካባቢው ሲርቅ ቀጣዩን ስራ ያስብ ነበር። ከቆይታ በኋላ የምሽት ግዴታው ይቆየዋል። የጊቢው ጥበቃ።
አምስቱ ባልንጀሮች የዚህ ቀን አብሮነታቸው ገና በጊዜ ነበር። ሁሉም ከስራ መልስ ጎራ ከሚሉበት መዝናኛ ሰብሰብ ብለው አምሽተዋል። ምሽቱ እየገፋ ጊዜው መንጎድ ሲጀምር ወደቤት ለመሄድ ተስማሙ። ፊትና ኋላ ሆነው የሰፈራቸውን መንገድ ሲጀምሩ ከምሽቱ 4፡30 ሰአት ከሰላሳ ሆኖ ነበር።
የባልንጀሮቹ መንደር ከዋናው መንገድ አለፍ ይላል። ከጨለመና ሰአት ከገፋ ለብቻ መጓዝ ያስፈራል። አካባቢው ወንዝና ጉድባ ይበዛዋል። ይህን ቦታ የቅናሽ ቤት ኪራይ የሚሹ ነዋሪዎች ይመርጡታል። ባልንጀሮቹም በአካባቢው ለመኖር ምክንያታቸው ሆኗል። ሁሉም የሚያገኙት የወር ገቢ ከኪስ ተርፎ ለቅንጦት አይበቃም። ችግራቸውን ለማቃለል ከሚያገኙት ተጋርተው የቤት ኪራዩን ይከፍላሉ። ይህን ማድረጋቸው የኑሮ ጫናውን አቅልሏል።
ምሽቱን ሲዝናኑ የቆዩት ጓደኞች ወደመንደራቸው እያቀኑ ነው። አልፈዋቸው የሚሄዱት ሰፈሮች ጨለማ ውጧቸዋል። የአብዛኞቹ ጊቢዎች በራፍ በጊዜ ተከርችሟል። በአካባቢው የሚገነቡ የማህበር ቤቶች በዘበኞች እየተጠበቁ ነው። ደሞዝ ከነዚህ ቤቶች በአንደኛው የምሽት ጥበቃ ላይ ይገኛል።
በጊቢው ለሚገነባው መኖሪያቤት የሚውሉ የግንባታ ዕቃዎች ከመጋዘን ተቀምጠዋል። ደሞዝ ከቆርቆሮ ማደሪያው እየወጣ ዙሪያ ገባውን ያዳምጣል። ልክ እንደሱ ሁሉ በአካባቢው ያሉ ጥበቃዎች ሃላፊነታቸውን በንቃት ይወጣሉ። አብዛኞቹ የአንድ አገር ሰዎች ናቸው። ከመሃላቸው የቅርብ ዘመዳሞች ይገኙበታል።
አሁን አምስቱ ጓደኞች ደሞዝ ከሚሰራበት አካባቢ ተቃርበዋል። አብዛኞቹ በእጆቻቸው ድንጋይ ጨብጠዋል። መኩሪያ የተባለው ጓደኛቸው በሞባይሉ የከፈተው ሙዚቃ ጨለማውን ጥሶ መሰማት ጀምሯል። ሁሉም ደማቁን ሙዚቃ እያዳመጡ አብረው ይዘፍናሉ።
መንገዳቸው ቀጥሎ ደሞዝ ካለበት ጊቢ በራፍ ሲደርሱ ድንጋይ ከያዙት አንደኛው ወደቤቱ አቅጣጫ አሻግሮ ወረወረ። እሱን ተከትለው ሁሉም የእጆቻቸውን ድንጋይ ወደጊቢው አሳልፈው ወረወሩ።
የድንጋይ ውርወራው ያለማቋረጥ ቀጠለ። ጓደኛሞቹ ድንጋይ ከመሬ እያነሱ፣ ያነሱትን እየወረወሩ ድርጊቱን ደጋገሙት። ተከታትለው ከቆርቆሮው መጋዘን ላይ
ያረፉ ድንጋዮች የአካባቢውን ዝምታ ሰበሩ። የድብደባ ጫና ያረፈበት የቆርቆሮ ጣራ እንደጥይት ማንባረቅ፣ መጮህ ያዘ። አካባቢው በድንጋይ ሩ ምታ ተናወጠ።
ከስራ መልስ የሌት ልብሱን ቀይሮ ከመኝታው አረፍ ያለው ደሞዝ የሚሰማው ድንገቴ ነውጥ አስደንግጦ አባነነው። እንደተዋከበ ተንደርድሮ ከደጅ ወጣ። ሰዎችን እያየ ነው። ወዲያው ከአምስቱ ባልንጀሮች ጋር ፊት ለፊት ተጋፈጠ። ሁሉንም አንድ በአንድ እያየ አፈጠጠባቸው። ጉዳዩን ከመጠየቁ በፊት ‹‹ና… ውጣ..ና ውጣ›› ሲሉ አዋከቡት። አንዳቸውንም ከዚህ በፊት አይቷቸው አያውቅም።
የእሱን ወደእነሱ መጠጋት እንዳዩ ሁሉም የእጃቸውን ድንጋይ ወደ ጊቢው መወርወራቸውን ቀጠሉ። ደሞዝ መረጋጋት አልቻለም። እንደደነገጠ ድርጊታቸውን ተቃወመ። እየቀረባቸው ሲመጣ ውርዋሮውን ወደ እሱ አዙረው ሊያጠቁት ሞከሩ። ክፉኛ ደነገጠ።
ዝቅ እያለ ፣ ከእሩምታው ለማምለጥ ተጣጣረ። አልቻለም። ከአንዳቸው የተወረወረ ድንጋይ በአናቱ አልፎ የግራ ክንዱን አገኘው። ስቃዩ ከፋ ። እጁን እያሻሸ በሽሽት አፈገፈገ። ብዙ አልራቀም። ከቅርብ የተወረወረ አንድ ድንጋይ የቀኝ እግር ጉልበቱ ላይ አረፈ።
እያነከሰ እንደምንም አጎነበሰ። ወዲያው ተለቅ ያለ ድንጋይ ከእጁ ገባ። እሱን ጨብጦ ከኋላ ተከተላቸው። የድንጋይ ውርወራው ጦርነት ተፋፋመ። እየሮጠ፣ እየጮኸ ‹‹የሰው ያለህ ፣ድረሱልኝ›› ሲል ተጣራ። ጩኸቱን የሰሙ የአካባቢው ዘቦች ከያሉበት ብቅብቅ አሉ። የሚያውቁት ሰው በጎረምሶች ተከቦ እየተዋከበ ነው።
ደሞዝ የሰዎቹን መድረስ እንዳየ ወደ ጊቢው ሮጠ። ሲመለስ ለጥበቃ የሚይዘው ወፍራም ዱላ ከእጁ ነበር። ዱላውን ይዞ ከኋላቸው ተከተለ። ድንጋይ ውርዋሮው ቀጠለ። ደሞዝ በዱላው እየመከተ ፣መልሶ እየወረወረ ቀረባቸው። ሌሎች መምጣታቸውን ሲያዩ ፍጥነታቸው ጨመረ። እየተባረሩ ፣ እየተሯሯጡ ወንዙ አጠገብ ደረሱ። ሳይሻገሩ ደሞዝ መኩሪያ የተባለውን ወጣት ፊት ለፊት አገኘው። ድንጋዩን ከመወርወሩ በፊት በዱላው ቀደመው።
በመኩሪያ ጭንቅላት ደጋግሞ ያረፈው ወፍራም ዱላ ለመነሳት ዕድል አልሰጠውም። ጥቂት አቃስቶ ከመሬት ተዘረረ። ይህኔ የአካባቢው ዘቦች ከኋላ ደረሱ። የሰዎቹን ድንገት መምጣት ያዩት አራቱ ጓደኛቸውን ሳያነሱ ወደፊት ሮጡ። በስፍራው ከደረሱት ዘቦች አንዱ የደሞዝ አጎት ነበር። አጎት ከመሀል ገብቶ ሊገላገል ሞክሯል። አሁንም ጠበኞቹን ካልተከተልኩ የሚለውን ደሞዝ እንዲረጋጋ እየገሰጸ ነው።
ዘቦቹ ደሞዝን ይዘው ሲመለሱ ጉዳቱ የከፋው መኩሪያ ከመንገዱ ወድቆ ነበር። ባልንጀሮቹ ወንዙን አቋርጠው ተበትነዋል። ቁስለኛው ከወደቀበት ሆኖ የስቃይ ድምጽ ያሰማል። ጠበኞቹ መሸሻቸውን ያስተዋሉ የደሞዝ ወገኖች ወደመጡበት ተመልሰዋል።
የፖሊስ ምርመራ
የዕለቱ ተረኛ ፖሊስ በራሱ ፈቃድ ከጣቢያው የተገኘውን ወጣት የዕምነት ክህደት ቃል መቀበል ጀምሯል። ደሞዝ ትናንት ምሽት የተፈጠረውን ድርጊት አንድ በአንድ እያስረዳ ነው። ደሞዝ ትናንት ምሽት በጠቡ ምክንያት በእሱ እጅ ስለሞተው ወጣት ከልቡ ተጸጽቷል። ጉዳዩን የያዘው መርማሪ ፖሊስ ዋና ሳጅን ሲሳይ ተሾመ የጠቡን ምክንያትና የነበረውን እውነታ ከምስክሮች ቃል አገናዝቦ ‹‹እጠረጥራቸኋለሁ›› ያላቸውን ሌሎች ዘቦች በቁጥጥር ስር አውሏል።
ውሳኔ
ህዳር 8 ቀን 2010 ዓም በችሎቱ የተሰየመው የልደታ ከፍተኛ ፍርድቤት በተከሳሽ ደሞዝ የሺጥላ ክስ የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮ ተገኝቷል። ፍርድቤቱ በወንጀሉ ተባባሪ ነበሩ የተባሉ ሌሎች የጥበቃ አባላትን ጉዳይ በመርመር ጠበኞቹን ጠርቶ ጠይቋል። እነሱም ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ፍርድቤቱ በዕለቱ በተከሳሹ ላይ ባስተላለፈው ውሳኔ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የዘጠኝ ዓመት ጽኑ አስራት እንዲቀጣ ወስኗል። የተቀሩት የጥበቃ አባላት ግን በወንጀሉ ተሳትፎ ያለማድረጋቸውን አረጋግጦ ሁሉም በነጻ እንዲሰናበቱ ሲል በይኗል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መስከረም 22/2014