የሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የመከራ ጉም ለብሶ ሳይ ያልገባኝ..ያልገባችሁ ስል መጣሁ። ባህር ከሆነው የተንኮልና የክፋት ተሰጥኦው.. ከከረመውና ከሰሞነኛው የህወሓት የጠብ ቁርሾ እያጠቀስኩ አስነብባችኋለሁ።
ያልገቡኝ እንዳልገቧችሁ ተስፋ በማድረግ ወደ ትዝብቴ ልለፍ። ሀገራችን የብዙ ባህልና ስርዐት ባለቤት፣ ነውርን የሚያውቁ ፈርሀ እግዚአብሄር ያደረባቸው ነፍሶች መኖሪያ ናት። ጥንታዊ የግሪክ ሀፍትን ጨምሮ የእስልምና እምነት መስራቹ ነብዩ መሀመድ እንደመሰከሩላት የእውነት የፍትህ ሀገር ናት። ይሄን ሁሉ የሆነች ሀገር ዛሬ በከሀዲያን ስትናወጥ ማየት ከማመሙም ባለፈ ኢትዮጵያዊነት የት ሄደ ያስብላል?
ዋናው ጉዳዬ ስለ ኢትዮጵያ ቅርስና ተፈጥሮ ማውራት ሳይሆን፣ እኚህን ከሀዲያን ስላበቀለችው ትግራይ ማውራት ነው። ከአሸባሪው ህወሓት መነሻ መንደር ትግራይ ያልገቡኝ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ትግራይና ትግራውያን ለኢትዮጵያ ደማቅ ቀለሞች ናቸው። ኢትዮጵያን ሲኩሉ..ኢትዮጵያዊነትን ሲቀልሙ የኖሩ ህዝቦች። በባህል፣ በሀይማኖት፣ በወግ ስርዐት ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ጋር የተጋመዱ የተሳሰሩ ሀገር ወዳዶችም ናቸው።
ግን ያልገባኝ..እናተንም ያልገባችሁ..እንዴት ከጉያዋ በቅለው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሱ ሀይሎችን ማስቆም አቃታት የሚለው ነው። እንዴት እኚህን ከሀዲ ቡድኖች መታገል አቃታቸው? በብዙ ድካም ያደመቋትን ሀገር ሲያደበዝዙባቸው እንዴት ዝም አሉ? በኢትዮጵያ ሲመጡባቸው እንዴት አስቻላቸው? ስል እጠይቃለሁ።
ሌላው ያልገባኝ እናንተንም ያልገባችሁ ነገር..የህወሓት መነሻ ትግራይ. በመንፈሳዊና በአለማዊ ቅርሶቿ ኢትዮጵያን በአለም ያስተዋወቀች ሆና ሳለ..እንዴት ሆኖ እነዚህን ነፍሰ በላ አበቀለች ስል ሁሌ ራሴን እጠይቃለሁ፤.መልስ ያልተገኘለት ጥያቄ።
የጽላተ ሙሴ፣ የአክሱም ጽዮን መገኛ፣ የአልነጃሺ ስፍራ በምን አይነት ሁኔታ ሀገርና ህዝብን የሚያውኩ ወረበሎች በቀሉባት? ጠዋት ማታ ጸሎትና ስግደት የሆነባት፣ በሰንበትና በአዘቦት የተንስኡ ድምጽ የሚሰማባት እግዚአብሄራዊቷ ስፍራ ለነዚህ ነውረኛ ቡድኖች መሸሸጊያ በመሆኗ እከፋለሁ።
የኢትዮጵያ የስልጣኔ እንብርት ከዚህ ሁሉ በላይ ፈጣሪን የሚያውቁ ለፈጣሪ የቀረቡ ህዝቦች የሚኖሩባት ሆና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጠልሸት ደፋ ቀና ለሚሉ ከሀዲያን መደበቂያ መሆኗ ያልገባኝ..እናተንም ያልገባችሁ ነገር ነው። ይሄንን ነውር ከየት አመጡት?
በአክሱም ስልጣኔ ኢትዮጵያን አድምቀው የጻፉ እጆች ዛሬ መሳሪያ ይዘው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጫካ ሲገቡ ማየት አይገርምም ትላላችሁ። በያሬድ ድጓ ልሳን..በዘርዐያዕቆብ እምነት ሀይል ኢትዮጵያን የሳሉ ህዝቦች ዛሬ በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ለማደብዘዝ ለማፍረስ ሲዘምት ጉድ ያስብላል።
አዛውንቶች ማስታረቅ ሲገባቸው፣ የሀይማኖት አባቶች ማውገዝ ሲገባቸው በለው እያሉ ማጨብጨባቸው ካልገቡኝ ውስጥ ይበልጥ ያልገባኝ ነው። ብዙ ነገር እናውቃለን.፤ ብዙ ነገርም ሰምተናል። የተከበረን የማምለኪያ ስፍራ የፈጣሪ የክብር ስፍራ መሆኑ ቀርቶ ለመሳሪያ ማከማቻና ለምሽግ ሲውል ሰምተናል። ኢትዮጵያን ለማፈረስ ለተነሱ ሀጢያተኞች መደበቂያ ተደርጓል። የጽላቱ ማረፊያ ንጹሁ ቤተመቅደስ የወንበዴዎች ዋሻ ሆኖ ሞትን መከሩበትም። ይህን ሁሉ ሳስብ ይሄ ቡድን እግዚአብሄርን ከሚፈራ ህዝብ መካከል እንዴት በቀለ እላለሁ? ይሄ ቡድን በአባቶቹ ሀይ ባይ ሳያገኝ እንዴት መረን ተለቀቀ እላለሁ፤ ደጋግሜ እላለሁ።
ህወሓት የአጋንት መልክተኛ ነው፤ አጋንት በህወሓት ውስጥ ሆኖ እየሰራ ይመስለኛል። ኢትዮጵያ በታሪኳ በዚህ ቡድን እንደደረሰባት ያለ ውርደትና ክህደት አልገጠማትም። የጭካኔ ጥጉ ያልደረሰበት ስፍራ የለም።
ህጻናትን ጨምሮ ነፍሰ ጡር ሴቶችን በመድፈርና በመግደል ማንነቱን አሳይቷል። ምንም የማያውቁ እንስሳትን በአሰቃቂ ሁኔታ እየገደለ..ንጹሀናን እያፈናቀለ፣ ኢትዮጵያን ግብጽና ሱዳን ለመሳሰሉ ባዕድ ሀገራት አሳልፎ ለመስጠት እየቆመረ ያለ ቡድን ነው።
ይሄ ሁሉ አልበቃ ብሎት የአለም አቀፍ ህግጋትን በመሻር የአምልኮ ስፍራዎችን በከባድ መሳሪያ ሲደበድብ፣ የሀገር ቅርስን ሲዘርፍና ሲያወድም የኖረ ነው። የትግራይ ህዝብ፣ የትግራይ የሀይማኖት አባቶች ይሄን ቡድን የማውገዝ አቅም ያጣሉ ብዬ አላስብም ነበር። ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዳወገዙት እነሱም ሊያወግዙት ይችሉ ነበር፤ ለምን ዝምታን እንደመረጡ አልገባኝም። ቤተክርስቲያንን ለምሽግና ለመሳሪያ ማከማቻነት ሲጠቀም ተው እንደማለት የዝምታቸውን ሚስጢር አልደረስኩበትም።
ሁሉም የሀይማኖት ተቋማት፣ ሁሉም የሀይማኖት አባቶች ሀገርና ህዝብን በተመለከተ አላማቸው አንድ ነው፤ ሰላምና ፍቅርን መስበክ፤ አንድነትን ማምጣት። አሁን እየሆነ ያለው ግን ይሄ አይደለም። በኢትዮጵያ ምድር፣ በአማራና በአፋር ክልል እንደዚሁም በትግራይ ምድር እንዲሁም በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች በጁንታው የጭካኔ ዱላ የሆነውና እየሆነው ያለው የንጹሀን ሞትና ስቃይ ግን የነዚህ አካላት የዝምታ መልስ ነው እላለሁ።
ምንም የማያውቁ ንጹሀን እየደረሰባቸው ያለው ግፍና መከራ የኢትዮጵያን መፍረስ በሚፈልጉ አንዳንድ ግለሰቦችና ተቋማት መልካም ፍቃድ እየሆነ ያለ ነው።
የህዝቦችና የሀይማኖት አባቶች ዝምታ ለጁንታው ቡድን ሽፋን ከመስጠት ባለፈ ሌላ ትርጉም ይኖረዋል ብዬ አላስብም። አንድ አሸባሪ ቡድን የሀይማኖት ተቋምን ተገን አድርጎ ሰው ሲገልና ሀገር ሲያወድም ዝም ያለን የሀይማኖት መሪ እርሱን የሰላም መሪ…የህዝብ አገልጋይ ነው ብዬ ለመናገር እቸገራለሁ። ሌላ ድብቅ አላማ ላይኖረው ስለመቻሉ ማስረጃ የለኝም። ይልቅ ከጁንታው ቡድን ለይቼ አላየውም።
አለም ላይ ግፈኞችን በመቃወም ለሀገርና ህዝብ ተገን የሆኑ በርካታ የሀይማኖት አባቶችን እናውቃለን። የራሳቸውን ጥቅም ወደ ጎን ብለው ለሰላምና እውነት የለፉ ብዙ የሀገር ባለውለታዎች አሉ። በንጉሱ ጊዜ ከሀዲውን የጣሊያን ጦር በመቃወም ከህዝብ ጎን በመቆም ራሳቸውን ለሞት የሰጡ በርካታ የሀይማኖት አባቶች ነበሩን። ከነዚህ ውስጥ አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ናቸው። አቡኑ በዚህ እውነት ውስጥ ያለፉ የእኔና የእናንተ የክፉ ቀን የጽናት ተምሳሌት ናቸው። በሞታቸው ኢትዮጵያን የመለሱልን፣ በእውነታቸው አርነት ያወጡን የክፉ ቀን ማስታወሻችን።
ዛሬም ኢትዮጵያን የሚያድን የሀይማኖት አባት ያስፈልገናል። ዛሬም ከራስ ጥቅም ይልቅ ሀገርና ህዝብን ያለ እውነተኛ ነፍስ እንሻለን። የሀይማኖት አባቶች ከዳር ቆሞ የሚመለከቱ ሳይሆኑ ጥፋተኛን በማውገዝና በመቃም ወገተኝነታቸውን ሊያሳዩን ይገባል እላለሁ። ቤተክርስቲያን እያፈረሰ፣ አማኝ እየገደለ ሀገርና ታሪክ ለማውደም የተነሳን ከሀዲ ሀይል መቃወም የሚያህል ለሀገርም ሆነ ለትውልድ ውለታ አለ ብዬ አላስበብም። እስኪ ምን ውለታ አለ? ያልገባኝ..ያልገባችሁ። አበቃሁ..ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን መስከረም 19/2014