አንድ ሆኖ መታየትን ተመሳስሎ ፍቅር መጋራትን ፋሽን አቅርቦልናል፡፡ በተመሳሳይ ዲዛይንና ቀለም የተሰሩ አልባሳት ለብሶ አደባባይ ላይ መታየት ዝግጅቶችን ማድመቅ በተለይ የወጣቶች ባህል እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህ የአለባበስ ልማድ ደግሞ በሁሉም ተቀባይነት አግኝቶና ሰፍቶ እንደ ፋሽን ተወስዶና በአዳዲስ ንድፎች አድጎ የሰዎች መድመቂያ ሆኗል፡፡ አንድ አይነት በመልበስ ፍቅርን ማሳደግ ተመሳስሎ መገኘት አብሮነትን አጠነከረ ማለትስ ይህ አይደል፡፡
በአዳዲስ ፈጠራ በየዘመናቱ ብቅ እያሉ የዘመኑን ሰው የሚያደምቁ፣ የወቅቱን ቀለም ተላብሰው ውበትን የሚያጎሉ ፋሽኖች የዘመኑ ግኝቶች ናቸው፡፡ በየወቅቱ ብቅ እያለ በብዙዎች የሚዘወተረው ፋሽን በዲዛይነሮች ተነድፎ በልብስ ሰፊዎች ተበጅቶ ሰዎችን ያስውባል፡፡
ዛሬ በፋሽን አምዳችን ዓውዳመትና ልዩ ልዩ የጎዳና ሁነቶች ላይ በወጣቶች የሚለበሱ ተመሳሳይ ክናቴራና ልዩ ልዩ ዘመነኛ አልባሳትን እንዳስሳለን፡፡ ዛሬ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የመስቀል በአል እየተከበረ ነው፡፡ ትናንትም የደመራ በአል ተከብሯል፡፡ የትናንቱን የደመራ በአል አተኩሮ የተመለከተ በተለይ ወጣቶች ተመሳሳይ አልባሳትን በመልበስ በአደባባይ በአላትና ሁነቶች ላይ መገኘታቸው በአሉን ደማቅና አይረሴ እንዳደረጉት እንዲረዳ ከማስቻል በተጨማሪ ወጣቶቹ ተመሳሳይ ልብስ ለብሰው ተውበው መታየታቸው ልዩ የደስታ ስሜት አያሳድርበትም ተብሎ አይገመትም፡፡
ቀድሞ ሙሽሮችን ለማጀብ ሚዜዎች ብቻ ነበሩ አንድ አይነት ልብስ ለብሰው አምረውና ተውበው ይታዩ የነበሩት፤ ይህ ወግ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ በተለይ መልስ ላይ የልጁ አልያም የልጅትዋ ቤተሰቦች እህትና ወንድም በአጠቃላይ የቅርብ ዘመድ ሁሉ ተመሳሳይ አልባሳትን በዲዛይነሮች አሰርተው ተውበው እንግዶቻቸውን ይጠብቃሉ፤ተቀብለውም አምረውና ተውበው ያስተናግዳሉ፡፡
ይህ ልማድ ሰፍቶ አደባባይ የሚያስወጡ የተለያዩ ሁነቶች ወጣቶችና የሚጎራብቱ ጓደኛማቾች ተመሳሳይ ልብስ በተለይም ከናቴራ አሰርተው ልዩ መልእክት እንዲያስተላልፍ አርገው በማዘጋጀት ለብሰው መታየት ጀምረዋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን ለአውዳመት ካለን ልዩ ፍቅርና የተለየ ዕይታ በመነሳት ዐውዳመት በመጣ ቁጥር ነጭ በነጭ ለብሶ በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ ማምራትና እዚያ አምሮ ደምቆ ስርዓቱን ማድመቅ የበዛ ልምዳችን ነው፡፡
በተለይ መስቀል ደመራን በመሳሰሉ በአደባባይ ላይ የሚከወን ስርዓት ያላቸው ክብረ በዓላት ወጣቶች ከጓደኞቻቸውና ከአብሮ አደጋቸው ጋር በባህላዊ አልባሳት የሚደምቁባቸው እየሆኑ መጥተዋል፤ በዚህም እነሱም ደምቀው ዓውዳመቱንም ያደምቁታል፡፡ በደመራ፣ በጥምቀት በአላት ወቅት ወጣቶች ተመሳሳይ ካናቴራ ለብሰው ሲታዩ ክብረ በዓሉን ያደምቁታል፤ እነሱም አብሮነታቸውንና ፍቅራቸውን ያደረጁበታል፡፡
የዓውዳመት አከባበሩ ባህልና ወጉን ጠብቆ ቢቀጥል ዘመን አመጣሽ የአለባበስ ባህልና የአጋጌጥ ሁናቴውም መቀየሩ አልቀረም፡፡ ይህ መሆኑም ባህልና ስርዓቱን ፈፅሞ አልጎዳውም፡፡ ይበልጥ ከፍ ያለ እድገት አላበሰው እንጂ፡፡ አልባሳቱ ባህሉን አክለው በባለሙያዎች እጅጉን አምረው ይበልጥ ደምቀው ቀጠሉ እንጂ፡፡
ለዓውዳመት የሚለበሱት እነዚህና መሰል አልባሳት በተለይ ወጣቶች ከዘመን አመጣሽ አልባሳት ውጪ በአላትን አንዲያከብሩ እያስቻሉ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታ ቀስ በቀስ ወጣቶች አልባሳቱን በአዘቦት ቀናት አንዲልብሱና ለባህል ልብሶች ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጡ በር ይከፍታል፡፡
ሁሌም አዳዲስ ነገር በሚፈጥሩ በዲዛይነሮች ጥረት ዛሬ ላይ ወጣቶች በተለያየ ዲዛይን ያሰሩትን ከናቴራ በመልበስ ጓደኛሞች አንድ አይነት ውበት ተላብሰው ይታያሉ፡፡ የሚፈልጉትን ጨርቅ መርጠው ያሻቸውን ጥቅስና መልዕክት ከናቴራው ላይ እንዲፃፍላቸው አልያም እንዲቀልምላቸው አዘው በበዓላት ቀን አንድ አይነት በመልበስ ይዋባሉ፡፡
በትዕዛዝና በተፈለገ ንድፍ በወደዱት የቀለም ምርጫ የሚዘጋጁት እነዚህ አልባሳት ወይም ከናቴራዎች በበዓላት ላይ በስፋት እየተለበሱ ናቸው፡፡ በከናቴራዎቹ ላይ ባህልን፣ እምነትን፣ የሚያንፀባርቁ የሀገር ፍቅርን የሚያመላክቱ ልዩ ልዩ ጥቅስና ቀለሞች
ይታተማሉ፡፡ ይህም በወጣቶቹ ተመርጦ እንዲለበስና ተለምዶ እንዲወደድ አድርጎታል፡፡ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ወጣት ጓደኛሞች፣ አብረው የሚማሩ ተማሪዎች፣ ማህበርተኞችና የተቋማት ሰራተኞች አልያም በተለየ ምክንያት የተሰባሰቡ ቡድኖች በልዩ ትዕዛዝ የሚዘጋጁ አልባሳት በመልበስ አምረውና ተውበው በአደባባይ በዓሎችና ልዩ ልዩ ሁነቶች ውስጥ መገኘታቸው ተለምዷል፡፡
በዓውዳመት ሰሞን ላይ ማተሚያ ቤቶችም ስራ ይበዛባቸዋል፤ የተለያዩ ዲዛይኖችን አዘጋጅተውና በከናቴራ ላይ ጥቅሶችን አስፅፈው ለሚለብሱ ደንበኞቻቸው አልባሳትን የሚያዘጋጁ ማተሚያ ቤቶችንና በአዲስ አበባ ተዘዋውረን ስንመለከት ያረጋግጠነውም ይህንኑ ነው፡፡ ህትመት ቤቶቹ በተለይ የመስቀል ደመራና በመሳሰሉ የአደባባይ ክብረ በዓላት ላይ ትዕዛዝ ከደንበኞቻቸው በመቀበል የተዋቡ ዲዛይኖችን አዘጋጅተውና በከናቴራ ላይ ፅሁፍና ምስሎችን አትመው ለሽያጭ ለማቅረብ በእጅጉ ይታትራሉ፡፡
ከናቴራዎቹ የተለያየ ዋጋ የሚያወጡ ሲሆን ጨርቆቹ እንደተሰሩበት ጥሬ እቃና እንደተነደፈበት ንድፍ አልያም ዲዛይን ስራ እንዲሁም በላያቸው ላይ እንደሚታተመው ቀለም ዓይነት ይለያያል፡፡ ዋጋቸው በአማካይ ከ150 ብር እስከ 375 ብር ድረስ ይደርሳል፡፡ በቡድን ለሚመጡ ደንበኞች መጠነኛ አስተያየት አድርገውም ያዘጋጃሉ፡፡ ህትመት ቤቶቹ ከሚቀበሏቸው ልዩ ልዩ ትዕዛዞች በተጨማሪ በከናቴራዎቹ ላይ ከሚታተሙ ፅሁፎችና ምስሎች ባሻገርም የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ የሚገልፁ ልዩ ልዩ ምስሎች ታትመውባቸው ለገበያ ይቀርባሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከናቴራዎቹ ባህላዊ ይዘትን እንዲላበሱ ለማድረግ የተለያዩ ጥለቶችና ባህላዊ ምስሎች ተደርጎባቸው እየተዘጋጁ ለገበያ ይቀርባሉ፡፡ በአገር ባህል አልባሳት ላይ የሚደረጉ ጥለቶችንና ልዩ ልዩ የባህላዊ አልባሳት መስሪያ ጥበብ ጨርቆችም በከናቴራዎቹ ላይ መታከል ደግሞ በራሱ አልባሳቱ ከባህላዊ አልባሳት እንዲመሳሰሉና እንዲለመዱ አድርጓቸዋል፡፡
እነዚህ በወጣቶች የሚዘወተሩ አልባሳት ለክብረ በዓሎቻችንም ልዩ ድምቀት ፈጥረዋል፡፡ ትናንትና በደማቅ ሁኔታ በተከበረው የመስቀል ደመራ በዓል ላይ ወጣቶች በህብረት ከተለያየ አካባቢ ወደ መስቀል አደባባይ ሲጎርፉ የተጎናጸፏቸው ተመሳሳይ አልባሳት ለበዓሉ ምን ያህል ድምቀት ሰጥቶት እንደነበር መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአንዱ ሰፈር ወጣቶች ከሌላው ሰፈር ወጣቶች በአለባበሳቸው ተለይተው ነው አደባባይ የወጡት፤ ይህም አደባባዩን ልዩ የቀለም እና የጥበብ ህብር እንዲላበስ አድርጎታል፡፡
ወጣቶች በቀላሉ በየህትመት ቤቱ በፈለጉት መልኩ የሚሰሩት ከናቴራና መሰል አልባሳት የመረጡበት እና በፋሽንነት ሰፍቶ የሚለበስበት ዋንኛ ምክንያት በሚያምር ዲዛይን መቅረቡ በዋጋም ደረጃ አለመጋነኑና እንደምርጫ ማሰራት መቻሉ ዋንኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 2014 ዓ.ም