የሬጌ አብዮት ኢትዮጵያ ውስጥ የቀሰቀሰ፤ ስሎው ሮክ በእሱ ቀለም ሲሰማ ለጆሮ ለዛ ያለው ቢያደምጡት የማይሰለች መረዋ ነው።የሙዚቃ አፍቃሪያን ሁሉ በኢትዮጵያዊ ቀለምና በራሱ ለዛ ስለማንጎራጎሩ፤ ስለሚያነሳቸው ጠንካራ ይዘት ያላቸው ዜማዎቹ፣ ለየት ባለ የቋንቋ አጠቃቀምና አገላለፅ ሁሉን ክህሎት በአንድ ያሟላ እንደነበር ይመሰክራሉ።የማይሰለቹና ጥልቅ ሀሳብ ያላቸው ዜማዎቹ ሲሰሙ ይመስጣሉ።
እርሱ ውስጣዊ ስሜትን በሚቆጣጠር መልዕክት አዘል ጥዑም ዜማዎቹ ይታወቃል፤ ድምፃዊ እዮብ መኮንን።
እዮብ በምስራቃዊ የአገራችን ክፍል ጅግጅጋ ከተማ ጥቅምት 12,1967 ተወለደ። ልጅ ሆኖ ለሙዚቃና ለኪነ ጥበብ ልዩ ፍቀር ነበረው።እዮብ የጀግናም ልጅ ነው።አባቱ ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ለአገሩ በቆራጥነት የተዋጋ ጀግና ወታደር ነበር።
በአፍላ እድሜ ላይ ሳለ የኦሮሚኛ ቋንቋ አቀንቃኝ የዶክተር አሊ ቢራን ዘፈን ደጋግሞ ያዳምጥ እንደነበር በህይወት ሳለ በሰጠው ቃለመጠይቅ ጠቁሟል።እድሜው ሲጎለምስ ደግሞ የቦብ ማርሌ ሙዚቃን ደጋግሞ መስማት ያዘወትር ነበር።እዮብ ውስጡ አንዳች የጥበብ ብልጭታ አድሮበት ነበርና ተስጥዖውን ለማውጣት አንድ የሆነ አጋጣሚ መፈለግ ጀመረ። ሁሌም በኪነጥበብ ስራዎች በተለይ በሙዚቃ ይሳብ የነበረው እዮብ በፎቶግራፍ ባለሙያ ሆኖ ጅግጅጋ ላይ አስገራሚ የሆኑ ፎቶዎችን ሲያነሳ ቆየ።
የካሜራ ባለሙያነቱ አስትቶ ወደ ሙዚቃ ህይወት እንዲገባ ያደረገው አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ።የሚኖርበት ከተማ ጅግጅጋ ላይ ከመሀል አገር አዲስ አበባ የሙዚቃ ዝግጅት ለማቅረብ ከተገኘ አንድ የሙዚቃ ቡድን ጋር ይገናኛል።የሙዚቃ ባለሙያዎቹ በእረፍት ሰዓታቸውም እዮብ መድረክ ላይ ወጥቶ አስገራሚ የሆነ የሙዚቃ ችሎታውን ሲያሳያቸውና ሲዘፍን አይተው ማለፍ አልፈለጉም።አንተማ ምርጥ ሙዚቀኛ መሆን ትችላለህ።ለዚህ እኛ ምቹ ሁኔታ ልንፈጥርልህ እንችላለን አሉት።በወጣቱ ህልመኛ ፊት ላይ ሳቅ በረከተ።በግብዣው ተደሰተ።
በደንብ ቀርበውም ብዙ ነገሩት፤ ለስራው ምቹ ወደሆነበት አዲስ አበባ እንውሰድህም የሚል ጥያቄ አቀረቡለት።ጥያቄያቸውም ያለማወላዳት ተቀበለ።አዲስ አበባ እዮብን ተቀብላ ያላተን ሰጥታ ብቁና ድንቅ ድምፃዊ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሬጌ አብዮተኛ አደረገች።በወቅቱ ከሙዚቃ ቡድኑ ጋር ወደ አዲስ አበባ አብሯቸው መጣ።የድምፃዊ ሀይልዬ ታደሰ ፋልከን የተሰኘ የሙዚቃ ክለብ ውስጥ የሙዚቃ ስራ ማቅረብ ጀመረ።
እዮብ የተፈጠረው ለሙዚቃ ነበርና መድረክ ላይ ወጥቶ የሌሎች ድምፃዊያን ስራዎች ሲያቀርብ በብዙዎች ተደነቀ፤ ባለሙያዎችም ተስፋ ጣሉበት።በዚህ የሙዚቃ ክለቡ ውስጥ የክብር ዶክተር አሊ ቢራና የቦብ ማርሌን ዘፈኖች ደጋግሞ ያቀርብ ነበር።ይህም ቀስ በቀስእውቅናን ዝናን ማትረፍና ወደራሱ ስራዎች የመግባት ዕድል እንዲያገኝ ረዳው።
በኢትዮጵያ ሚሊኒየም መባቻ ይህ የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ “እንደ ቃል” የተሰኘ አልበም ለሙዚቃ አፍቃሪያን አቅርቦ እያደር ተቀባይነትን አገኘ፤ በእርግጥ ይህ ተወዳጅ አልበም መጀመሪያ ላይ ብዙም አልተሰማም ነበር።እየቆየ ግን ሙሉ በሙሉ ሁኔታዎች ተለውጠውተወዳጅነትን አተረፈ።ብዙዎች ሙዚቃዎቹን ተቀባብለው ሰሙት በአዲስ አቀራርብና የአዛዜም ስልቱ አደነቁት።ስሙ በመላው ሀገሪቱ ናኘ።ስራው ሁሉም ጋር ተዳረሰ፡፡
የሙዚቃው ተሎ አለመወደድ ግራ አጋብቶት የነበረው እዮብ አልበሙ ከተለቀቀ በኋላ ቶሎ ምላሽ በማጣቱ ስራ ሊቀይር ማሰቡን፤ አንድ ወቅት ላይ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ላይ ገልጸል።እዮብ በዚህ አልበሙ ከፍያለ የሙዚቃ ችሎታውን ማሳየቱን የተመለከቱ ብዙዎች ሬጌ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዮቱ ተቀጣጠለ ብለው በእዮብ ብዙ ተስፋን ጣሉ።
ቀጥሎ ያቀረበው “እሮጣለሁ” የተሰኘ አልበሙ ደግሞ የእዮብ የሙዚቃ ልዩ ክህሎትና የግጥም ችሎታው የዜማ ምርጥ ደራሲነቱንና ሁለገብ የረቀቀ ችሎታውን ፍንትው አድርጎ ገለጠው።ከበፊቱ በበለጠ ስምና ዝናው ናኘ።መድረክ ላይ እሱ ወጥቶ ሙዚቃዎቹን ሲያቀርብ የሙዚቃ አድናቂዎች ተከትለውት በውዴታ አብረውት ያዜማሉ።ወደውት በተለየ ፍቅር ያጅቡታል።የመድረክ ፈርጥ መሆኑንም በብዙዎች ተመሰከረለት።
ነሀሴ 12 ቀን 2005 ኢትዮጵያዊን እጅግ መሪር ዜና ሰሙ፤ የሬጌ ሙዚቃ ስልትን ኢትዮጵያዊ ቀለም አላብሶ ዘርፉን ከፍ ያደረገ የሬጌ ሙዚቃ እንዲደመጥ ምክንያት የሆነው እዮብ በወጣትነቱ ድንገት ማረፉ ተሰማ። እሩቅ አልሞ በሙዚቃው ዘርፍ ብዙ ሊሰራ የነበረው የሬጌው አብዮተኛ ሳይታሰብ ህልፈቱ ተሰማ፡፡
ነገን ላየው እጓጓለሁ …….
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 16/2014