ትውልድና ዕድገቱ በደቡብ ክልል ነው።ልጅነቱን እንደ እኩዮቹ በየመስኩ ሲቦርቅ አሳልፏል። ወላጆቹ ቤት ያፈራውን አጉርሰው፣ አቅማቸው የቻለውን አልብሰው አሳድገውታል።ዕድሜው ከፍ ማለት ሲጀምር እንደመንደሩ ልጆች ትምህርት ቤት መግባት ፈለገ ፤ቤተሰቦቹ አልተቃወሙም።እርሳስና ደብተር ገዝተው የልቡ እንዲደርስ ትምህርት ቤት አስገቡት።
ፍስሀ ከሰፈሩ ልጆች ጋር አንገት ለአንገት ተቃቅፎ ትምህርትቤት መዋል ጀመረ።በጊዜው በትምህርቱ መገኘት ደስተኛ ሆነ። ቀለም ቆጥሮ ቤት ሲመለስ ወላጆቹን ያግዛል። ልጅ ቢሆንም ለእሱ የሚሆን ስራ አያጣም።የታዘዘውን እየከወነ፣ የወላጆቹን ምርቃት አገኘ።
ወላጆቹ በየዓመቱ በልጃቸው የትምህርት ለውጥ ይደሰታሉ።ነገ ከቁምነገር ደርሶ ወግ ማዕረግ ቢያሳያቸው ምኞታቸው ነው።ይህ ይሆን ዘንድ የአቅማቸውን እያደረጉ ስለልጃቸው ይጨነቃሉ። የፈለገውን እየሰጡ የፍላጎቱን ይሞላሉ።
ፍስሀ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በወጉ አጠናቀቀ። ሰባተኛ ክፍልን አልፎ ወደ ስምንተኛ ሲሻገር በዕድሜና በአስተሳሰብ ጠንክሮ ነበር። በያዘው ዓመት የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚኖርበት ያውቃል።ትናንት የበረቱ የመንደሩ ወጣቶች ዛሬ የደረሱበትን ሰምቷል።አብዛኞቹ በትምህርት ልቀው ራሳቸውን ችለዋል። ከእነሱ አልፎም ለወላጆቻቸው መከበሪያ ሆነዋል።
ስምንተኛ ክፍል መማር እንደጀመረ ልቡ ለሁለት ተከፈለ። ገንዘብ ማግኘት ራሱን ፈጥኖ መለወጥ አማረው።ሀሳቡን ዕውን ለማድረግ የተሻለውን አማራጭ መያዝ አለበት። ከቀዬው ወጥተው ርቀው የሄዱ አንዳንዶች በገንዘብ ሀይል ተለውጠዋል።በየጊዜው ብቅ ሲሉ ሁኔታቸው ይማርካል። አለባበስ አነጋገራቸው ከሌሎች የተለየ ነው።
ፍስሀ የእንዲህ አይነቶቹ ወጣቶች ለውጥ በትምህርት እንዳልተገኘ ያውቃል።ሁሉም አካባቢውን ሲለቁ ገንዘብ ለማግኘት ስራ ይዘዋል።ያገኙት ስራ ኑሮና ህይወታቻውን ቀይሯል።ይህን ደጋግሞ ሲያስበው እነሱን መሆን ተመኘ።
ራሱን በእነሱ ልክ አቁሞ ማንነቱን ለካው።ይህኔ ከጅምር ትምህርቱ ይልቅ የስራው ሚዛን አጋደለበት።ዓመታትን ተምሮ ስራ ከመፈለግ ጥቂት ሮጦ ራስን መለወጥ እንደሚበልጥ ገባው።
ውሳኔ…
ፍስሀ ደጋግሞ ሲመክርበት በነበረው ጉዳይ ከቁርጥ ውሳኔ ደርሷል።አሁን ከትምህርቱ ይልቅ ገንዘብ የማግኘት ፍላጎቱ አይሏል።ይህን ሀሳብ ለማሳካት እንደሌሎቹ ከአገር ቀዬው መውጣትና መራቅ አለበት።ፍስሀ ለዚህ ዕቅዱ ስኬት የመጀመሪያውን መዳረሻ ቆም ብሎ አሰበ።ታላቅ ወንድሙ ትዝ አለው።
የፍስሀ ታላቅ ወንድም አዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ይኖራል።ዓመታትን በዘለቀበት ከተማ ራሱን ችሎ ቤተሰብ አያሰተዳደረ ነው።ፍስሀ እሱ ዘንድ ቢሄድ ያሰበው እንደሚሳካለት እምነቱ ነው።አዲስ አበባ የብዙዎችን ህይወት ቀይሯል።የበርካቶችን ሀሳብ አሳክቷል።
ከቀናት በኋላ ፍስሀና አዲስ አበባ በአካል ተገናኙ።ለእንግድነቱ ያላሳፈረው ታላቅ ወንድም በደስታ ተቀብሎ አስተናገደው ።የአካባቢውን ኑሮና ህይወት ይረዳ ዘንድም እንደወጉ አላመደው።እንግዳው ወጣት ስፍራውን ለማወቅ ሰዎችን ለመልመድ አልተቸገረም።ፈጥኖ ከብዙዎች ተግባባ።የከተማን ኑሮ የሰዎችን ባህርይ አወቀ።
ጥቂት ቀናት ቆይቶ ለፍስሀ ስራ ተገኘለት።ስራው በዘመድ የተገኘ እንጀራ በመሆኑ ታላቅ ወንድሙ ተደሰተ።ታናሹ ራሱን ሊችል በመሆኑ እፎይታ ተሰማው።ፍስሀ ከአገሩ የወጣበትን ምክንያት ያውቀዋል፤ በጉልበቱ አድሮ ገንዘብ ለማግኘት ራሱን ለመለወጥ ነው።እንዳሰበው ሆኖ በጥረቱ ከገፋ ምኞቱ ተሳክቶ የልቡ ይሞላል።
ወያላው …
አሁን ፍስሀ ታክሲ ላይ ስራ ጀምሯል።ታክሲው የቅርብ ዘመዳቸው ነው፤ ጠዋት ማታ በሚመላለስበት ስራ ከሾፌሩ ጋር ሲባዝን ይውላል።ውሎው አድካሚና ከሰው የሚያገናኘው ነው።አንደንዴ ከሚያሳፍራቸው ተጠቃሚዎች ጋር ይጣላል።የጠቡ ምክንያት በሳንቲም መልስ፣ አልያም በታሰበው ቦታ ባለማውረድ ሊሆን ይችላል።እንዲህ ባጋጠመ ጊዜ ፍስሀ ከስድብና ጭቅጭቅ አልፎ ቡጢና ዱላ የሚገጥምበት ጊዜ ይኖራል።እሱንመሰል የታክሲ ረዳቶች በየቀኑ በዚህ አይነቱ ገጠመኝ ማለፍን ልምድ አድርገዋል።
አንዳንድ ወያላዎች ከሚያሳፍሯቸው ሰዎች ጋር መሰዳደብ ከብዷቸው አያውቅም።ምክንያትና ሰበብ እየፈለጉ ሰዎችን ያሸማቅቃሉ።በዚህ ልምዳቸው የተማረሩ አንዳንዶች በዋዛ አይለቋቸውም።ሸሚዛቸውን ሰብስበው ለጠብ ይጋበዛሉ።
አንዳንዴ ደግሞ እነ ፍስሀ የቀኑን ሁኔታ ለጥቅም ያውሉታል።በዓል ሲሆን፣ መንገድ ሲዘጋና ሰዎች ሲበዙ፤ አጋጣሚው ይመቻቸዋል፡ ዋጋ ጨምረው፣ አቅጣጫ አሳብረው ከእጥፍ በላይ ይቀበላሉ።ጠዋትና ማታ ችግር ባለ ባቸው ሰፈሮች አጋጣሚው ለጥቅመኞቹ ወያላና ሾፌሮች ሰርግና ምላሽ ነው።እያጨናነቁ ሰው በሰው ላይ ይጭናሉ።እየተኩራሩ የጠየቁትን ይቀበላሉ።
ፍስሀ በታክሲ ረዳትነት ጥቂት እንደዘለቀ ራሱን መለወጥ ፈለገ።ለውጡን ለማግኘት ርቆ መሄድ ስራውን መለወጥ አላስፈለገውም።ረዳትነቱን እንደቀጠለ መንጃ ፈቃድ ለማውጣት ታተረ።ጠዋት ማታ እየሰራ ያጠራቀመው ገንዘብ የልቡን ሀሳብ ለመሙላት አላነሰውም።ተገቢውን ጊዜ ወስዶ መንጃ ፈቃዱን ከእጁ አስገባ።
ፍስሀ አሁን በህይወቱ ላይ አንድ የለውጥ እርምጃ አክሏል።ትናንት በወያላነት የሚታወቅ ማንነቱ የሚለወጥበት ጊዜ ላይ ነው።ከዚህ በኋላ ባለፈበት መንገድ ተመልሶ መራመድን አይሻም። ባለው ልምድና ችሎታ ተጠቅሞ መኪና ማሽከርከርና ርቆ መጓዝን ይፈልጋል።
ያሰበው አልቀረም። የትናንቱ ታክሲ ረዳት የዛሬ ሾፌር ሊሆን ጊዜው ደረሰ። ታክሲ ሊያሽከረክር ተሳፋሪዎችን ሊጭን ሀላፊነቱን ወሰደ። ዘመድ ከሆነው የታክሲ ባለቤት ጋር ውል ሲፈጽም በሙሉ ልብ ራሱን ለስራ አዘጋጀ። እንዲህ በሆነ ማግስት በእሱ ታክሲ የሚ ሳፈሩ ተጠቃሚዎች በረከቱ።
ባለታክሲው
ቋሚ መተዳደሪያቸው ከሚኒባስ ታክሲው የሚገኘው የዕለት ገቢ ነው።ለዓመታት የታክሲ ሾፌር ሆነው ሰርተዋል።መላውን ቤተሰብ የሚያሳድሩበት ሚኒባስ አልፎ አልፎ ከመንገድ እየቆመ ያበሳጫቸዋል።አንዳንዴ ችግሩን ለመፍታት የሚያስወጣቸው ዋጋ አቅማቸውን ይፈትናል።
አቶ መኮንን ከታክሲያቸው እየታገሉ ለዕለት እንጀራቸው ይሮጣሉ።በሚገኘው ገንዘብ የቤተሰቡን ፍላጎት ለመሸፈን ጠዋት ማታ ስራ ላይ ናቸው።ሰውዬው ስራቸውን በአግባቡ ለመከወን ብልጭታ በሚባል የታክሲዎች ማህበር በአባልነት ታቅፈዋል።በማህበሩ የተሰጣቸውን ዕውቅና ይዘው በአግባቡ ይንቀሳቀሳሉ።
ብዙ ጊዜ የሚያዘወትሩት ሀና ማርያም የተባለውን ሰፈር ነው።መነሻቸውን ከመንደሩ አድርገው መድረሻቸውን ሳሪስ አቦ ላይ ይቋጫሉ።አንዳንዴ መስመር ለውጠው ይሰራሉ።ከሚሄዱባቸው አካባቢዎች አንዳንዶቹ ምቹ አይሆኑም።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምርጫ ያደረጉት አካባቢና መንገዱ ብልሽት ጀምሮታል።እንዲህ መሆኑ ለመኮንን ራስ ምታት ሆኖ የመኪናቸውን ጤንነት ፈ ትኖታል።
ይህን የተረዱት ባለታክሲ ሀሳባቸውን ለውጠው ወደቀድሞው ቦታቸው ተመልሰዋል።ዓመል የነሳት ታክሲያቸው ግን አሁንም ሰላም አልሰጠቻቸውም። በየምክንያቱ እያኮረፈች ከአሳቻ ቦታ አረፍ ትላለች።ባለቤቷ ህመም ብልሽቷን ሲረዱ በባለሙያዎች አሳክመውና አባብለው ዳግም ይይዟታል።እንደ ዓመሏ አስታመውም ውሏቸውን ይዘልቃሉ።
ሰኔ 20 ቀን 2007 ዓም
ክረምቱ መምጣቱን እያሳበቀ ነው።ድንገቴው ዝናብ ደማቋን ፀሀይ ደብቆ በዳመናው ይገለጣል።በሀይለኛው ነጎድጓድ የታጀበው ብልጭታ መንገደኛውን እያሸበረ ነው። የወቅቱን ባህሪይ ያወቁ በርካቶች አለባበሳቸውን ቀይረዋል።ዣንጥላ የያዙ፣ ካፖርት የደረቡ፣ በወፍራም ልብሰ የተጀቦኑ ብዙ ናቸው።
ቀጣዩ የሀምሌ ወር ከባብዶ ሊገባ እያሰበ ነው። ሰኔ ይሉት ወር ጊዜውን እንዲለቅለት ያሰበ ይመስላል። ጨለማ ከዝናብ አዝሎ፣ በረዶ ብልጭታውን ይዞ ተራውን ይጠብቃል። የክረምቱ ጊዜ እየከበደ የበጋው ወራት እየተዋጠ ነው። የጊዜው ምልክቶች ጎልተው መታየት ጀምረዋል። እሸት የሚጠብሱ፣ ድንችና በቆሎ የሚቀቅሉ፣ የጎዳናውን ዳርቻ አድምቀውታል።
አቶ መኮንን በዚህ ቀን ከሚኒባስ ታክሲያቸው ጋር ተኳርፈው አርፍደዋል። ሚኒባሷ ዓመሏ ተነስቶ ከህመም ጋር ውላለች። ባለቤቷ ዕለቱን እንዳሰቡት ባለመስራታቸው ብስጭት ገብቷቸዋል።የዛሬው ችግሯ የኤሌክትሪክ መስመር ብልሽት መሆኑን አውቀዋል። የዚህ ችግር ስር መስደድም ዲናሞው እንዲያበራ ሰበብ ሆኗል።
ባለታክሲው መኮንን መኪናቸውን እንደምንም እያባበሉ ሁሌም ከሚያሳድሩበት ስፍራ አደረሷት።በቦታው ሲገኙ ሰአቱ ከምሽቱ አንድ ሰአት ከሰላሳ ላይ ያመለክት ነበር።መኮንን አካባቢውን ቀና ብለው ቃኙ። የስራ ቦታቸው በመሆኑ አሳምረው ያውቁታል። በዓይናቸው ሰው መፈለግ እንደያዙ ከባለ ሱቁ ያሲን ጋር ተያዩ።
መኮንን ጠጋ ብለው ሁኔታውን አዋዩት።ወዲያው አደራ ከታከለበት ተማጽኖ ጋር መኪናቸውን ለምሽቱ የጥበቃ ሰራተኞች እንዲያስረክብላቸው ጠየቁት።ባለሱቁ ሀሳባቸውን በይሁንታ ተቀብሎ ያሉትን እንደሚፈጽም አረጋገጠ። በስንብት ሲሸኛቸው ባለታክሲው ዳግም የመኪናቸውን ዙሪያ በእጃቸው ፈትሸው እየተገላመጡ ወደቤታቸው አመሩ።
በማግስቱ …
አቶ መኮንን የቀን ድካማቸውን በለሊቱ ዕንቅልፍ አካክሰው ወፍ ሲንጫጫ ከቤት ወጡ።በመንገዳቸው ስለሚኒባስ ታክሲዋ መላና መፍትሄውን ያመጣሉ።ወደፊት ማድረግ ስለሚኖርባቸው እያቀዱም ወጪ ገቢያቸውን ያስባሉ።ከጠዋቱ 12 ሰአት ተኩል ሲል ከትናንቱ ስፍራ ደርሰው መኪናዋን ወዳቆሙበት አቅጣጫ አመሩ።
ከፊት ለፊታቸው የቆሙ መኪኖችን እያለፉ ባለሱቁ ያሲን ወዳለበት አቅጣጫ ተጠጉ።ትናንት ምሽት ታክሲዋን ከእሱ ሱቅ ፊት ለፊት ማቆማቸውን እርግጠኛ
ናቸው።አካባቢው ደርሰው መኪናዋን ፈለጉ።የነበረችበት ቦታ አልታያቸውም።ዓይናቸውን አላመኑም።መኪናዋ ትናንት ከነበረችበት ስፍራ የለችም።ክው… ብለው ደነገጡ።
መኮንን ከላይ ታች እያሉ በፍለጋ ባዘኑ።በእርግጥም መኪናዋ ከነበረችበት ቦታ ተሰውራለች።ጥቂት ለመረጋጋት ሞከሩ። ቆም አሉና አሰብ አድርገው ወደ ባለሱቁ ፈጠኑ። ያሲን የጠዋት ስራውን ለመጀመር ሱቁን መክፈቱ ነበር። መኮንን እየተጣደፉ የትናንቱን አደራቸውን አስታውሰው ስለመኪናቸው ጠየቁት። ፈጣን መልስ አልነበረውም።የሆነውን ሁሉ ሲያውቅ ከእሳቸው ባላነሰ ደነገጠ ።
ጉዳዩን የሰሙ ሁሉ ምልክትና መለያ እየጠየቁ ፍለጋቸውን ቀጠሉ። የሰማ ላልሰማ እየተናገረ አካባቢው ታሰሰ።አዲስ ነገር አልነበረም።ስለመኪናዋ አየን፣ ሰማን የሚል አልተገኘም። ሰውዬው በንዴት ጥርሳቸውን እየነከሱ በዓይናቸው አንድ ሰው ፈለጉ።ግራ ቀኙን እያዩ ዙሪያ ገባውን አሰሱ።
ለአፍታ በዓይምሯቸው ውል ያለውን ወጣት ባሰቡት ስፍራ አላዩትም።መላልሰው የሚያዘወትረውን ቦታ ተመለከቱ። እሳቸው እንዳሰቡት ነው።ልጁ በአካባቢው የለም።ወዲያው ልቦናቸው ጥርጣሬን አዘለ።ውስጣቸው ድርጊቱን እሱ እንደፈጸመው ሹክ አላቸው።
ሁሌም ከስፍራው የማያጡት አቡሽ ዛሬ ስፍራው ላይ አልታየም።ለምን? የበለጠ እርግጠኛ ሆነው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ገሰገሱ።የዕለቱ ተረኛ ፖሊስ ቀልጠፍ ብሎ ቃላቸውን ሊቀበል ተዘጋጀ።
አቶ መኮንን ለመኪናቸው መጥፋት የመጀመሪያው ተጠያቂ አቡሽ ደምሴ የተባለው ሰው መሆኑን በእርግጠኝነት ተናገሩ።ፖሊሱ ቃላቸውን ሲመዘግብ ተጠርጣሪውን በህግ እንደሚፋረዱት ደግመው ደጋግመው ገለጹ።
ከአንድ ቀን በፊት…
ፍስሀ በዚህ ቀን የተለመደውን የታክሲ ስራ ሲከውን ውሏል።ከምሽቱ 4 ሰአት አካባቢ ሀና ማርያም ከተባለው ስፍራ ደረሰ። አስፓልት ዳር ተደርድረው ከቆሙት መኪኖች በርክተዋል።ከእነሱ መካከል አንደኛዋ ሚኒባስ ከአይኑ ገባች።
ሌሎቹን እያለፈ አጠገቧ ደረሰና የፊት መስታወቱን ከውጭ በኩል ዝቅ አደረገው።የጋቢናውን በር ሲሞክረው ብርግድ ብሎ ተከፈተ።እየተጣደፈ በያዘው ቁልፍ ሞተሩን ቀሰቀሰው።ጊዜ ሳይፈጅ ፈጥኖ ተነሳለት።መኪናውን ይዞ ወደ ጀሞ መንገድ ሲፈተለክ በወጉ ያየውና የጠረጠረው አልነበረም።
ጀሞ ሲደርሰ መኪናውን ከታክሲዎች ማዞሪያ አስጠግቶ ቦታ አስያዘው።
አዳሩን ከሚያውቀው ረዳት ቤት አድርጎም በማለዳ ወደታክሲው አመራ።ሞተሩን አንቀሳቅሶ ሜክሲኮ ለመድረስ ጊዜ አልፈጀም።ጊዜው ማለዳ በመሆኑ መንገድ ሳይዘጋ ካሰበው ደረሰ።ረዳቱን ይዞ ከሜክሲኮ እየተመላለሱ ጀሞ ሁለት ቢያጆ ሰሩ።
በታክሲው ለሶስተኛ ጊዜ ለመስራት ሲንቀሳቀሱ ካርብሬተሩ ላይ ችግር ተከሰተ።እሱን ለማሰራት ከአንድ ሜካኒክ ጋር እንደቆሙ አቶ መኮንንና አብረዋቸው የነበሩ ፖሊሶች ዓይን ውስጥ ወደቁ።ይህን ያየው ረዳት በፍጥነት ሮጦ አመለጠ።ፍስሀ በቀን የሰራውን 400 ብር እንደያዘ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የፖሊስ ምርመራ…
ተጠርጣሪው በህግ ጥላ ስር እንደዋለ መርማሪው ሳጂን መለሰ የኋላው የዕምነት ክህደት ቃሉን ተቀበለ።ስለድርጊቱ በትክክል ያመነው ፍስሀ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋገጠ። መርማሪው ቃሉን በወንጀል መዝገብ ቁጥር 570/08 ላይ በአግባቡ መዝግቦም ለቀጣዩ ሂደት ዶሴውን ወደ ዓቃቤ ህግ አስተላለፈው።
ውሳኔ
ነሀሴ 12 ቀን 2007 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የፌዴራል አራዳ ፍርድ ቤት በተከሳሹ ላይ የመጨረሻውን የፍርድ ውሳኔ ለመስጠት በቀጠሮው ተገኝቷል።ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ የቀረበበትን የሰውና የሰነድ ማስረጃ አገናዝቦም ጥፋተኝነቱን አረጋገጧል።በዕለቱ በሰጠው ውሳኔም ግለሰቡ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የ 8 ዓመት ጽኑ አስራት ይቀጣልኝ ሲል ብይን ሰጥቷል።
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መስከረም 15/2014