ፋሽን በራሱ ዘመን የተለየና እራሱን ሚመስል ገፅታ ይዞ ይከሰታል። በቆይታም ያ ልማድና ፋሽን ወደሌላ መልክና ገፅታ ይቀየራል። አንዳንዴ ደግሞ የቀድሞ ዘመንና መልክ የሆነ ዘመን ላይ ይዘወተር የነበረ አለባበስ ወይም ፋሽን ተመልሶ ሌላ ውበት ተላብሶና የፊቱን በሚያስታውስ መልክ ይከሰታል። ዛሬ በፋሽን ገፃችን ቀድሞ እናቶች ይለብሱትና ይዘወተር የነበረው ሽፎን ዛሬ ላይ ቀን ተገልጦለት የወጣቶችና የፋሽን ተከታዮች መዘነጫ ሆኗልና ስለሱ ማንሳት ወደድን።
ሽፎን ዛሬ ላይ በዲዛይነሮች እጅጉን ባማረ ዲዛይን ተውቦ የብዙዎች ቀዳሚ ምርጫ በመሆን ላይ ይገኛል። በፊት ከነበረው ገፅታው እጅግ ተቀይሮ የጥንቱን በሚያስታውስና ዘመኑን በሚለካ መልኩ ተሰርቶ ለገበያ መቅረብና በብዙዎች መለበስም ተጀምሯል። ኢትዮጵያዊያን የልበስ ዲዛይነሮች በፈጠራቸው ያለፈን ባህል የሚያስታውሱ ኢትዮጵያዊ ባህል የጠበቁ አልባሳት እንደ አዲስ በሚያምር መልኩ በመንደፍ በወጣቶች እንዲወደድና ተለምዶ እንዲለበስ ትልቅ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በተለይም ጥንት ኢትዮጵያዊያን ኮረዶች ይዋቡበት እናቶች ለብሰው ይደምቁበት የነበረው ቀሚስ ወይም ሽፎን ዛሬ ላይ እንደ አዲስ የወጣቶች ምርጫና ተወዳጅ ልብስ ሆኗል። ዛሬም እናቶች ብቻ ሳይሆኑ ወጣቶችም ሽፎንን በኢትዮጵያዊያን ዲዛይነሮች ውበትና ምቾት ታክሎበት በመቅረቡ የወቅቱ ምርጫ የዘመኑ መዋቢያቸው አድርገውታል።
ሽፎን ልክ እንደዛሬው ወጣቶች በበዓላትና በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ተውበውና አምረውበት ከመታየቱና እንደ ፋሽን ተወስዶ የውበት መጎናፀፊያ ከመሆኑ በፊት እናቶች ላይ ተደጋግሞ ይታይ ነበር። አሁን ላይ እንደገና ዘመኑን ለክቶ ብቅ ብሏል። የዘመኑ ፋሽን የወቅቱ መድመቂያ ሆኗል። በብዙ ምክያቶች የእናቶችና ወጣቶች ቀዳሚ ምርጫ በመሆን ላይ ያለው ሽፎን ተፈላጊነቱ እጅጉን ጨምሯል።
ለንድፍ አለማስቸገሩ፣ በተለያዩ ቀለማት መገኘቱ፣በዋጋ ከጥበብ ልብስ መቀነሱ፣ ሲታጠብና ሲለበስ ቀላል መሆኑ ዋንኛ የሽፎን ልብስ ተመራጭነት ምክንያቶች መሆናቸው ባለሙያዎችና ወጣቶች ይናገራል። ሽፎን ብቻው አልያም ከሀበሻ አልባሳት ማዘጋጃ ጨርቆች አልያም ጥለትና ጥበብ ጋር ሆኖ በተለያየ መልኩ ይዘጋጃል። ይህም ሽፎን ይበልጥ ተወዳጅና ተመራጭ ያደረገው ሌላኛው ምክንያትም ነው።
በተለይም በበዓላትና በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ላይ ተለብሶ ይዋል የነበረው ሽፎን ዛሬ ላይ በሰርግና ትልልቅ ዝግጅቶች ላይ ወጣቶች ለብሰውና ተውበው የሚገኙበት ሆነዋል። ወጣቶቹ በፈለጉት ዲዛይንና ቀለም ሊያሰሩት መቻላቸው ሽፎንን ቀዳሚ ምርጫ ማድረጋቸው ይገልፃሉ። አሁን ላይ ወጣቶች ከጥጥ ከሚሰራው ጥበብ ይልቅ ሽፎንን የመረጡበት ምክንያት ሲያስረዱ በቀላሉ መገኘቱና በዋጋም መቀነሱ መሆኑን ይናገራሉ።
ወጣት ማህሌት ከተማ የአዲስ አበባ ነዋሪ ስትሆን ቄራ አካባቢ በሚገኝ ጉሊት ገበያ ውስጥ አንድ በሩ ላይ የበዙ የሽፎን አልባሳት ሰቅሎ ጠበብ ባለች ሱቁ ውስጥ በልብስ ስፌት ላይ ያለ ወጣት ጋር ቆማ አገኘኋት። አሁን ላይ በስፋት እየተለበሰ ስላለው ሽፎን ልብስ አወራኋት። ማህሌት ልታሰፋ የመጣችው ሽፎን መሆኑን ነግራኝ በበዓላትና በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ስትገኝ ሽፎን መልበስ እንደምታዘወትር ትናገራለች።
ማህሌት ሽፎንን ተመራጭ ያደረገችበት ምክንያት ስታስረዳ በቀላሉና በተፈለገ ዲዛይን ባጠረ ጊዜ ማሰራት መቻሉና ሲለበስም ውበት የሚያጎናፅፍ በመሆኑ ነው።
ከሀበሻ ጥበብ ልብስ ይበልጥ ሽፎኖች በዋጋ አንሰውና በተለያየ ቀለማት መገኘታቸው ሌላው የሽፎኖች ተመራጭነት አሳድጎታል። የሽፎን አልባሳት አሁን ላይ በብዙ ወጣቶች በፋሽንነት ተለምደው እንደሚለበሱ ወጣት ማህሌት ትናገራለች።
በፊት ላይ እንደተፈለገ ተሰርቶ ስለማይለበስ በእናቶች ብቻ ይለበስ እንደነበረና አሁን ላይ ሽፎን የሁሉም ዘመናዊ ፋሽን ምርጫ ሆኗል። ወጣቶች በሚፈልጉት ዲዛይን ማሰራት መቻላቸው ተመራጭ እንዳደረገውም ከቅር ጊዜ ወዲህ የሽፎን ልብስ ትዕዛዝ ደጋግሞ የሚቀበለው ወጣትመሀመድ አረጋ ይናገራል።የልብስ ስፌት ባለሙያው መሀመድ እንደ ማህሌት ሁሉ ወጣቶች በዋነኝነት የሚመርጡት የሽፎን ጨርቅ መሆኑንና ለበዓላትና ለልዩ ልዩ ዝግጅቶች በሚፈልጉት መልክ አሰርተው እንደሚለብሱ ያስረዳል።
የጨርቆቹ በተለያየ ቀለምና ዓይነት ገበያ ላይ በስፋት መገኘቱም ሌላኛው ሽፎን ተመራጭ ያደረገው መሆኑንም ይናገራል። ሽፎን በበዓላት ወቅት በስፋት የሚለበሱት ከጥጥ የተሰሩ የሀገር ባህል ልብሶችን በመገዳደር ላይ ይገኛል። በወጣቶች ሁሉ ለመልበስ ምቹ መሆኑና ለማጠብም የማያስቸግር ውበትንም የሚያላብስ በመሆኑ ሽፎን ተመራጭ አድርጎታል።
ኪስን በማይጎዳና ሰውነትን ያስውበውና እጅግ በተዋቡ ቀለማት ደምቆ በሚዘጋጀው ሽፎን መድመቅ የወቅቱ ፋሽን ሆኗል። ሊለብሰው የፈለገ ሰው በፈለገው ዲዛይንና ቀለም መርጦ በባለሙያዎች አስለክቶና አሰፍቶ ሽክ ብሎ በፈለገው ድግስና መርሀ ግብር ላይ መገኘት ይቀለዋል። እነዚህ የወቅቱ ተመራጭ የሽፎን አልባሳት መስሪያ ጨርቆች በብዛት አገር ውስጥ የሚመረቱ ሲሆን አልፎ አልፎም ከውጪ አገር ይመጣሉ።
ሽፎን አልባሳት የሚመረጡበት ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ከበዓላትና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች ውጪ በአዘቦት ቀን በተፈለገ ዲዛይን ተሰርቶ ሊለበስ መቻሉ ነው። በስራ ቦታና በተለያዩ ሁነቶች ወጣት ሴቶች ይህንኑ ምቹ ጨርቅ አሰፍተው ይዘንጡበታል። አምረው ደምቀው ይታዩበታል። በዋጋውም ከሌሎች አልባሳት ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝና ኪስ የማይጎዳ መሆኑ የተመረጠበት ሌላኛው ምክንያት ነው። በእርግጥ በተለየ ዲዛይን የተሰሩና በሽፎን ጨርቅነታቸው ጥራት ከፍ ያሉት ዋጋቸው እጅግ ውድ የሆኑም የሽፎን ቀሚሶችም ገበያው ላይ በስፋት ይገኛሉ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2014