አድናቂዎቹ በተለየ የአዘፋፈን ስልቱና በሚያነሳቸው ቁም ነገር አዘል ዜማዎቹ ይወዱታል። በተለይ የኔ ደሀ፣ አምናታለሁ፣ ድሬ ድሬ የተሰኙ ዜማዎቹ ከድምፃውያን መሀከል ከፊት ያሰለፉ እጅግም የተወደዱለት ዜማዎቹ ናቸው። በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ጎልተው የተደመጡለትና ተወዳጅ ሆነው የቆዩለት ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎችም ናቸው። «የኔ ደሀ» በተሰኘ የመጀመሪያ ሙዚቃው ከሕዝብ ጋር ተዋወቀ። እስካሁን ሁለት አልበሞችና ከ6 በሓይ ተወዳጅ ንጥል ሥራዎች ለሙዚቃ አፍቃሪያን አበርክቷል። ከድምፃዊነቱ ባሻገር የተዋጣለት የሙዚቃ ግጥምና ዜማ ደራሲ ነው።
የዛሬ የዝነኞች አምድ እንግዳችን ሚኪያስ ቸርነት ትውልድና ዕድገቱ አዳማ ነው። ገና ልጅ ሆኖ ወደፊት መገኘት ያለበት የራሱን መድረሻ አሰመረ። የሙዚቃ ፍቅር በልጅነቱ አድሮ ነበር። ውስጡ የሚሻውና መሆን የሚፈልገውን ለማሳካት ሁሌም መጣር ጀመረ። ከትምህርት ቤት መልስና ዕረፍት ሲያገኝ ለህልሙ መሳካት የሚሆነው ስፍራ መመላለስ ጀመረ። ለዚህ ደግሞ አዳማ ቤተሰብ መምሪያ ዋንኛ የፍላጎቱ ማሳኪያ ሆኖ አገኘው።
እዚያ ፍላጎቱን ሊያሳካ የሚችልበት ጥሩ አጋጣሚ መኖሩንም ተረዳ። በአዳማ ቤተሰብ መምሪያ ውስጥ ትውልድን አድን የተባለ የፀረ ኤች አይ ቪ ክበብ ለግንዛቤ ማስጨበጫ መርሀ ግብሮቹ ያቋቋመው የኪነጥበብ ቡድን ደግሞ ለሚኪያስ ህልም ማሳኪያ የመጀመሪያ መድረክ ሆነው። እዚያ የሙዚቃ ጥማቱን መወጣት ጀመረ፤ ህልሙን የማሳካት ጉዞውን ተያያዘው።
ቀስ በቀስም ከሙዚቃ ቡድኑ ጋር ተዋህዶ በ15 ቀን 10 ብር እየተከፈለው ሙዚቃ መጫወት ቀጠለ። በሥነ ተዋልዶና በኤች አይ ቪ ዙሪያ ግንዛቤ የሚያስጨብጠው ቤተሰብ መምሪያ ለሚኪያስ ሙዚቀኛ መሆን ትልቅአስተዋፅዖ እንደነበረው ይናገራል። በሂደትም የተለያዩ የምሽት ክለቦች ላይ የሌሎች ድምፃውያን ሥራዎች እያቀረበ ከሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር መግባባቱን ቀጠለ።
ወደ መዲናች አዲስ አበባ በመምጣት የራሱን የሙዚቃ ሥራ የመስራት እንቅስቃሴ ጀመረ። በእርግጥ ወደ ሙዚቃ ሥራው ለመግባት እንቅስቃሴ ሲያደርግ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ገጥሞትም ነበር። ወደሙያው ሲገባ ቀድሞ የነበሩ የሙዚቃ ባለሙያዎች አዲስ እንደመሆኑ ሊያግዙት ሲገባ በአንፃሩ እሱን ላለማሰራትና ከህልሙ እንዲገታ እንቅፋትም ፈጥረውበት በፅናትና በትጋት ተወቶታል። ያ ጊዜ አስቸጋሪ እንደነበር ዛሬ በትውስታ ወደ ኋላ ተመልሶ ያነሳዋል።
በጥረትም የራሱ የሆነውን ሙዚቃ የኔ ደሀ የተሰኘው በብዙ ልፋትና ጥረት ሰር ለሕዝብ አቅርቦ ተወዳጅነትን አተረፈ። ለሌሎች ድምፃውያን ዜማና ግጥም ሰርቶ ሰጥቶ ተወዳጅነት ያተረፉ ሥራዎችም አሉት።
ዛሬ ድረስ የተለያዩ ጥዑም ዜማዎች ለሕዝብ በማቅረብ ስሙን በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ በጉልህ አስፃፈ። ከሙዚቀኞች ቴዲ አፍሮ ወይም ቴድሮስ ካሳሁን እጅጉን የሚወደውና የሚያደንቀው ድምፃዊ መሆኑን ይናገራል። እኔም ወደሙዚቃው ስገባ የሱን ሙዚቃ ስዘፍንና ዛንጎራጉር ነው በማለት ለቴድሮስ ካሳሁን ያለውን ጥልቅ ፍቅርና ክብር ይገልፃል።
ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ
የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለማሳደግ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽዖ ማበርከት ይጠበቅበታል የሚለው ሚኪያስ፤ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገት ዛሬ ላይ የሚጠበቀውን ያህል አድጓል ከሌላው ዓለም ጋር ሲነፃፀር ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራል። ኢንዱስትሪው ጠቃሚና በአገር ግንባታ ሂደት የራሱ የሆነ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም ያስረዳል። አሁን ላይ ሙዚቃውን በዋናነት ከማሳደግ ይልቅ በሙዚቃ ቪዲዮዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል የሚለው ሚኪያስ ዘመኑን የሚሻገሩ ለሙዚቃው እድገት ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ይጠቁማል።
የዕረፍት ጊዜው
አብዛኛው ጊዜውን በሥራው የሚያሳልፈው ድምፃዊ ሚኪያስ ባለው የዕረፍት ጊዜ ቤት ውስጥ መዋል ያዘወትራል። መንፈሳዊና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተፃፉ መፅሐፍት ማንበብ ውስጡ የሚደሰትበት ተግባሩም ነው። የእግር ኳስ ጨዋታ ማየት ደግሞ እጅጉን ይወዳል።
ቤት ውስጥ ምግብ ማብሰል እና ጥሩ ድባብ በመፍጠር ከቤተሰብ ጋር ጥሩ ጊዜን ማሳለፍም የዕረፍት ጊዜው የሚያስውብበት ልምዱ ነው። ከሰዎች ጋር ተግባቢና ተጫዋች ነው። በማህበራዊ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊና ሰዎችን በተለያየ መልኩ ማማከር በተቻለው መጠን መርዳትና ለሰዎች መልካም ነገር መፍጠር ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ማድረግ ያስደስተዋል።
መልዕክት ለኢትዮጵያውያን
«ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ነው፤ በቃል መግለፅ ይከብዳል፤ በራሱ ትልቅ ምስጢር ነው። የተለያዩ ብሔሮች ተጋብተው አንድ ሆነውና በፍቅር የሚኖሩባት በጠንካራ ትስስርና አንድነት የተገነባች አገር ናት። ሁላችንም ተጋብተንና ብዙ ነገር ተወራርሰን የኖርን በአንድነት የቆምን ነን። ዘረኝነት እንደ ፋሽን ጊዜአዊና ወቅት ሲያልፍ አብሮ የሚጠፋ ነው። አገራችን ሁሌም
ፀንታ ትቆያለች።
አንዳንዱ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብሎ ሊያስብና ለማፍረስም ሊሞክር ይችላል። ነገር ግን ይሄ ከንቱና ሊሆን የማይችል ክፉ ሀሳብና ተግባር ነው። ኢትዮጵያ በልጆቿ ትስስርና በአንድነት ፀንታ ወደፊትም ትቀጥላለች። በአገር ውስጥ ከውጭ የሚፈጠሩ አገሪቱ ላይ የተነሱ ጠላቶች ሁሉ በጊዜ ሂደት ይከስማሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ ሁሌም ትኖራለች። እንደ ሕዝብ አንድነታችንን አጠንክረን በጋራ ሀገራችንን እንጠብቅ፤ ለሰዎች መልካም በማድረግ ላይ እንረባረብ ያኔ ችግሮች ሁሉ ተወግደው ነገአችን የተሻለ ይሆናል። » በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረም 9/2014