ዓመለ ሸጋ ነው፡፡ በሰፈር መንደሩ ስሙ በበጎ ሲወሳ ይውላል፡፡ ትንሽ ትልቁን አክባሪ ነውና ያየው ሁሉ ይወደዋል። እናት አባቱ ስለእሱ አውርተው፣ ተናግረው አይጠግቡም፡፡ እሱ እንደሚያከብራቸው እነሱም ያከብሩታል፡፡ ዘወትር በሚያሳየው በጎ ምግባር ምርቃት ምስጋና ሲቸረው ይውላል፡፡
ሀይሉ ገና በልጅነት ዕድሜው ራሱን ለመቻል ሲፍጨረጨር ኖሯል፡፡ ይህ ጥረቱም ከራሱ አልፎ ለቤተሰቦቹ ተረፏል፡፡ የጠዋት ማታው ሩጫ ውጤት ኖሮት ፍሬው ቢያምር መርካቶ አካባቢ ስራ ጀመረ፡፡ ጎንደር በረንዳ ከተባለው ስፍራ እንጀራው ያደረገው የአሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን መጠገን ነበር፡፡ በሙያው እየበረታ ሲሄድ የራሱን ሱቅ ተከራይቶ ደንበኞችን አፈራ፡፡ የእጁን ሙያ ያዩ፣ታማኝነቱን ያስተዋሉ በርካቶች ቤቱን ጎበኙለት፡፡
ሀይሉ የሚጠግናቸውን የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ሲረከብ በቀጠሮው ሊያስረክብ ቃል ገብቶ ነው፡፡ በተባለው ቀን የሚመጡ ደንበኞችን ማስከፋት አይሻም፡፡ የተሰጠውን ንብረት በአግባቡ አክሞና ጠግኖ የተነጋገረውን ዋጋ በምስጋና ይቀበላል፡፡ በሌላ ጊዜ እሱን ያሉ ደንበኞች ሌሎችን አስከትለው ከሱቁ ብቅ ይላሉ፡፡ ሀይሉ የቀደሙ ደንበኞቹን አመስግኖ ከአዲሶቹ ደንበኞች የሚሰሩ ዕቃዎችን ፈትሾ ይቀበላል፡፡ በተባለው ጊዜና ሰአት ቃሉን አክብሮም ዕቃዎቹን ጠግኖ ያስረክባል፡፡ ይህ ማንነቱ ከብዙዎች አላምዶት የእንጀራ ገመዱን አርዝሞታል፡፡ በሀይሉ ሱቅ መደርደሪያዎችም በርካታ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ተራቸውን እንዲጠብቁ ሌሎች ተጠጋኞች በእሱ እጅ እንዲፈተሹ ፣ምክንያት ሆኗል፡፡
ሀይሉ በስራው ሲበረታና ገበያው ሲጨምር ከቤተሰብ መውጣት የራሱን ጎጆ መስራት አማረው፡፡ እስከዛሬ በእናት አባቱ ቤት መኖሩ ይበቃው ዘንድም ትዳር መመስረት ዕቅዱ ሆነ፡፡ ይህን ያወቁ ወላጆቹ ሀሳብ ዓላማውን ደገፉት፡፡ ሚስት አግብቶ ልጆች ወልዶ ወግ ማዕረግ እንዲያሳያቸው ተመኙ፡፡
ሀይሉ የእሱና የእነሱን ፍላጎት ፈጸመ፡፡ የወደዳት የወደደችውን አግብቶም ትዳር መሰረተ፡፡ የሀይሉ ጋብቻ ዕውን እንደሆነ ከወላጆቹ ጉያ ወጥቶ የራሱን ቤት ተከራየ፡፡ ሀይሉና አዲሷ ሙሽራ በአዲስ ጎጆ አዲስ ህይወት ጀመሩ፡፡
ሀይሉ ትዳር ከያዘ በኋላ ሀላፊነቱ ጨመረ፡፡ የትናንትናዋ እጮኛው ሚስቱ ሆናለችና ቤት ጎጆዬን ማለት ያዘ፡፡ የጋብቻው ህይወት ወራት አስቆጠረ፡፡ ባልና ሚስት ኑሯቸው እንዲሰምር ፣አብሮነታቸው እንዲቀጥል ፣የሚያስችል መልካም አጋጣሚም ተፈጠረ፡፡ ሀይሉና ባለቤቱ የመጀመሪያ ልጃቸውን ታቀፉ፡፡ የቤተሰቡ ደስታ ወደር አጣ፡፡ ወላጆች ከመጀመሪያ ልጃቸው የመጀመሪያውን የልጅ ልጅ ሲስሙ ደስታውን በእኩል ተጋሩ፡፡
በትዳር መሀል ልጅ ሲመጣ ሀላፊነቱ የጨመረው አባወራ ከቀድሞው ይበልጥ በስራው ታተረ፡፡ ከድካሙ መልስ ቤቱ ሲገባ ባለቤቱና ጨቅላ ልጁ ይቆዩታል፡፡ እነሱን እያሰበ የግል ግዴታውን ይወጣል፡፡ እነሱ የራሱ ሀላፊነቶች ናቸውና ሁሌም እንደ ዓይን ብሌኑ ያያቸዋል፡፡ የቤቱን ጎዶሎ እየሞላም የትዳሩን ሰላም ይጠብቃል፡፡ የሀይሉ አባት የልጃቸውን ባተሌነት ያውቁታል፡፡ ሁሌም የእሱ ህይወት ከስራ ድካም የተነጠለ አይደለም፡፡ ይህን የሚያውቁት አባት ልጃቸው ከእንጀራውና ትዳሩ ውጭ ሌላ ህይወት እንዲኖረው አይሹም፡፡
እሳቸው አብረው የሚውሉ ጓደኞቹ ማንነት አስደስቷቸው አያውቅም፡፡ሁሌም ቢሆን እነሱን ከእሱ ባዩ ጊዜ ፊታቸው ይለወጣል፡፡ ስሜታቸው ይቀየራል፡፡ይህ እውነት ደግሞ በእሳቸው ብቻ አልቀረም፡፡ ወላጅ እናቱም ስለ ባልንጀሮቹ መልካምነት አይታያቸውም፡፡ እናት ዘወትር ጓደኞቹን ባዩ ቁጥር ልጃቸውን ይመክራሉ፡፡ እነሱ ከእሱ ባህርይና ማንነት ጋር እንደማይዛመዱ እርግጠኛ ናቸው። አንዳንዴ ልጃቸውን ከመምከር አልፈው ባልንጀሮቹን ያስጠነቅቃሉ፡፡ ከእሱ ጋር ዳግመኛ ቢያገኙዋቸው ነገሩ እንደሚከብድ እያነሱ ያመራሉ፣ ይናደዳሉ፡፡
የሀይሉ ወላጆች የልጃቸውን የቅርብ ጓደኞች እንደጠሉና እንደተጠራጠሩ ጊዜያትን ቆጠሩ፡፡ ሀይሉ በቤተሰቦቹና በጓደኞቹ መካከል ያለውን ቅራኔ በመላ እያስማማ፣ የሰማውን እንዳልሰማ ማለፍን ልምድ አድርጎት ቆየ፡፡ ሀይሉ ቤተሰቦቹ ይበልጥ የማይወዱት በቀለ የተባለውን ወዳጁን እንደሆነ አሳምሮ ያውቃል፡፡ በቀለና ሚስቱ ህይወት ሁሌም ከእሱ ስር ጠፍተው አያውቁም፡፡ ስራውን በሚከውንበት ሱቁ የቀን ውሏቸውን ይገፋሉ፡፡ በቀለ ሀይሉ ሱቅ ተቀምጦ ጫት መቃምን ልምድ አድርጓል፡፡ አንዳንዴ ባለቤቱም
አብራው ትሰየማለች፡፡ ይህን የሚያዩ የአካባቢው ሰዎች ቅርበታቸው በልክ እንዲሆን ይመክራሉ፡፡ አብዛኞቹም ሰዎቹ ከጠንካራው ሀይሉ ጉያ መወሸቃቸውን አይወዱትም። ያለስራ ሲውሉ ከሀይሉ የሚቀበሉት ጉርሻ ከወላጆቹ ይበልጥ እነሱን ያበሳጫል፡፡ ሁሉም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጓደኞቹ ለእሱ እንደማይመጥኑት እያነሱ ሲመክሩት ይውላሉ፡፡ አንዳንዴም ምክንያትና ሰበብ እየፈለጉ ይወቅሱታል፡፡
ሀይሉ የእነሱን ጨምሮ የወላጆቹን ቅሬታ በየቀኑ ያስተናግዳል፡፡ለጊዜው ሀሳቡን በይሁንታ ተቀብሎም ተመልሶ ከእነሱ ይገጥማል፡፡ወላጆቹ ከእነዚሁ ጓደኞቹ ጋር ሆኖ የደረሰበትን ክፉ አጋጣሚ ከታላቅ በደል ይቆጥሩታል። አንድ ቀን አምሽቶ ሲገባ ለደረሰበት ድብደባና ጉዳት ተጠያቂ የሚያደርጉት እነበቀለን ነው፡፡ የዛኔ ያለ ፍላጎቱ ባመሸበት መዝናኛ ለእነሱ ሲል ጥቃት አስተናግዷል፡፡ በዚህም ሳቢያ በእጁ ጉዳት አጋጥሞ ጥርሱ እስከመነቃነቅ ደርሷል፡፡ይህን ሁሉ በደል እሱ እንጂ ወላጆቹ ፈጽሞ አይረሱትም፡፡ ክፉን እያስታወሱ ድርጊቱን ደጋግመው ያወሱታል፣ ቀንና ቦታውን እየጠቆሙም ዳግም እንዳይሳሳት ይመክሩታል፡፡
ሀይሉ የወላጆቹን ምክር እንደልምድ መቁጠሩን ቀጥሏል፡፡ አንዳንዴ ከጎኑ ያሉ ባለሱቆች ምክራቸውን ይደግሙለታል፡፡ ለእነሱም ቢሆን የተለየ ምላሽ የለውም፡ ፡ የሁሉንም ሀሳብ እንደነገሩ እየሰማ እንደዋዛ ያልፈዋል፡፡ ሀይሉን የሚያውቁ ብዙዎች ጓደኞቹ በእሱ መጠቀማቸውን አይወዱትም፡፡ በየቀኑ ከሱቁ ጎራ እያሉ ጫትና መጠጥ ማዘውተራቸው ከልብ ያበሳጫቸዋል፡፡ይህ ሁሉ ሲሆን ሙሉ ወጪያቸው የሚሸፈነው በሀይሉ አቅምና ኪስ ብቻ መሆኑን አሳምረው ያውቁታል፡፡
በቀለን የሚቀርቡት አንዳንዶች በነገረኛነቱ ይለዩታል። እሱ በየደረሰበት ሁሉ ከሰዎች ለመጣላት ቅርብ ነው ይሉታል፡፡ሁሌም ሀይሉን ይዞ የሚንቀሳቀው በቀለ ባልንጀራውን ያለፍላጎቱ ይዞ የሚወጣበት አጋጣሚ የበረከተ ነው፡፡ አንዳንዴ ሀይሉ ይሉኝታውን ትቶ ወደቤቱ ይገባል። በአብዛኛው ግን በበቀለ ጉትጎታ ተሸንፎ አብሮት ሲዝናና ያመሻል፡፡
ልብስ ሰፊው…
ደረጀ በላይ ተወልዶ ካደገበት አቧሬ አካባቢ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሯል፡፡ ወላጆቹን ጨምሮ እህት ወንድሞቹ በልብስ ስፌት ሙያ ይተዳደራሉ፡፡ እሱም ቢሆን ልጅነቱን የገፋው ከዚሁ ሙያ ጋር ነበር፡፡ ደረጀ አስረኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀ እንደ እኩዮቹ የትምህርት ውጤቱን አልጠበቀም፡፡ልብስ መስፋት መተዳደሪያው ይሆን ዘንድ ምርጫ አደረገው፡፡ ፒያሳ ዶሮ ማነቂ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ የጀመረው ስራ በርካታ ደንበኞችን አፍርቶለታል፡፡ እሱን ብለው ቤቱን የሚያዘወትሩ እንግዶች የሚፈልጉትን ልብስ ሰጥተው በቀጠሯቸው ይመለሳሉ። ደረጀ ቀን ከሌት ሰርቶ የተሰጠውን ልብስ በተባለው ቀን ያደርሳል፡፡
ወላጆቹ በፍቺ ከተለያዩ ቆይተዋል፡፡ አባቱና እህት ወንድሞቹ አብረው ቢሆኑም ወላጅ እናቱ ከእነሱ ርቀው በሌላ አገር ይገኛሉ፡፡ ደረጀ ከአባቱ በወረሰው ሙያ መላ ቤተሰቡን ያስተዳድራል፡፡አንዳንዴ ደግሞ የሙዚቃ ሙያውን ተጠቅሞ በመዝናኛ ቤቶች ሲያንጎራጉር ያመሻል።
ደረጀን በዚህ ሙያው የሚያውቁት አንዳንዶች አድናቆትን ይቸሩታል፡፡ ወደፊት በተሻለ ስራ እንዲገኝም መንገድ እያመላከቱ፣ ምሳሌ እያጣቀሱ ያበረቱታል፡፡
ደረጀ አንዳንዴ በሙዚቃ ስራ ሌቱን ያጋምሳል። እንዲህ በሆነ ጊዜም ተጨማሪ ገንዘብና የውስጥ እርካታ ያገኛል። አንዳንዴ ደግሞ ከቀን ስራው መልስ ሆን ብሎ ሊዝናና ከመጠጥ ቤቶች ይገባል፡፡ በአጋጣሚው ከሚያገኛቸው ጋር እየተጫወተና እየጠጣ ማምሸትን ልምድ አድርጓል። ፒያሳ ዶሮ ማነቂያ አካባቢ የሚገኙ ምሽት ቤቶች ደረጀን ለመሰሉ ወጣቶች በራቸው ክፍት ነው፡፡ ያሻቸውን እያቀረቡ የፍላጎትን ይሞላሉ፡፡ በሙዚቃ ጨዋታ አጅበው ምሽታቸውን ያደምቃሉ፡፡ከእንዲህ አይነቶቹ ቤቶች መጫወት፣መዝናናት፣መጨፈር ተለምዷል፡፡ በእነዚህ ስፍራዎች በምሽት ስራ የሚተዳደሩ ሴቶችን ጨምሮ ሌሎችም የራሳቸውን እንጀራቸውን ያበስላሉ፡፡ በአካባቢው የመንገድ ዳርቻ የሚገኙ አንዳንዶች ምሽቱን የቀን ያህል ይሰሩበታል፡፡ በርካቶች በመጠጥ ናውዘው፣ በስካር ድካም ያነጋሉ፡፡‹‹በቃን››ያሉትም ሌሊቱን አጋምሰው ወዳሻቸው ይሄዳሉ፡፡
ሚያዚያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም
ሀይሉ በዚህ ቀን እንደተለመደው ከስራው ላይ ውሏል፡፡ ቀኑን ሙሉ ሲያስተናግዳቸው የዋሉ ደንበኞች እንዲጠገን የሰጡትን ኤሌክትሮኒክስ በቀጠሯቸው ወስደዋል፡፡ በተመሳሳይ ዕቃዎች ተበላሸብን ያሉ የያዙትን እያሳዩ ፣ችግሩን እየጠቆሙ፣የእጅ ሙያውን ሽተዋል። ሀይሉ ከሱቁ የደረሱ ደንበኞቹን በአግባቡ እየተቀበለ በትህትና ያስተናግዳል፡፡ ወደሱቁ የሚመጡ እንግዶች ስለ ዕቃዎቻቸው የሚነግሩትን እያደመጠ መፍትሄ መላውን ያስቀምጣል፡፡
በጥገና ሱቁ ቴሌቪዥን፣ኮምፒውተር፣ቴፕና መሰል ዕቃዎች ተደርድረዋል፡፡ ሁሉም በእሱ እጅ የሚታዩ በአቅም ችሎታው የሚፈተሹ ናቸው፡፡ሀይሉ ቀኑን ሙሉ አንገቱን ደፍቶ በሚውልበት ስራው ሁሌም ውጤታማ ነው፡፡ ብዙዎች ያቃታቸውን የጥገና ስራ መፍትሄ ማበጀቱ በበርካቶች ያስመርጠዋል፡፡
ዕለቱን ሲደክም በዋለበት ስራ ላይ እንዳለ በቀለ ወደሱቁ ዘለቀ፡፡ ለሀይሉ አፍላ የስራ ሰአት ነውና ከእሱ ጋር ለማሳለፍ አልተቻለውም፡፡ በቀለን እንዲቀመጥ ጋብዞት ወደጀመረው ጥገና አቀረቀረ፡፡ ባለሱቅ ጎረቤቶቹ በቀለ ወደ እሱ ማለፉን ሲያስተውሉ ነደዳቸው፡፡ እንደተለመደው በክፉ ዓይን ገረመሙት፡፡
ሀይሉ ከበቀለ ጋር መዋል ከጀመረ ወዲህ ከልብ ጓደኛው ጋር ተራርቋል፡፡ ጓደኛው በቀለን ጨምሮ መሰል ጓደኞቹን ማየት አይሻም፡፡ይህ ሀሳቡን ለሀይሉ ባጋራው ጊዜ የልቡን አልሞላለትም፡፡ በዚህ ምክንያት ወዳጅነታቸው ላልቶ ለመለያየት በቅተዋል፡፡ይህን እውነት የሚያውቁ ነጋዴ ጎረቤቶቹ በቅርብ ጓደኛው ቦታ የነበቀለ መተካት ሲያናድዳቸው ኖሯል፡፡ ጥላቻቸውን በግልምጫ እየገለጹም ተቃውሟቸውን ያሳያሉ፡፡ ሀይሉ ከበቀለ ጋር እስከ አስር ሰአት አብሮት ቆየ፡፡እሱን ከሸኘም በኋላ ወደስራው ተመለሰ፡፡
ምሽት 2ሰአት ከ30 ማለት ሲጀምር በቀለ ተመልሶ ወደ ሀይሉ ሱቅ መጣ፡፡ ብቻውን አልነበረም፡፡ ነፍሰጡር
ሚስቱ አብራው አለች፡፡ ወደሱቁ መጠጋት እንደያዙ ነጋዴ ጎረቤቱ ሱቃቸውን እየዘጉ ነበር፡፡ ሰውዬው ለምን ሲመሽ እንደመጡ በቀለን ጠየቁ፡፡ በቀለ ባለቤቱ መዝናናት ስላማራት መምጣት እንዳስፈለጋቸው ፈጥኖ ተናገረ፡፡ የጥንዶቹን መምጣት ያስተዋለው ሀይሉ ሀሳባቸው ቢገባው ካቀረቀረበት ቀና ብሎ ምሽቱን ውጭ መቆየት እንዳማይሻ አሳወቃቸው፡፡
በቀለ የሰማውን ማመን አልቻለም፡፡ እየደጋገመ አብሯቸው እንዲያመሽ ለመነው፡፡ ሀይሉ ውስጡን እየከፋው ዛሬን ውጭ ማምሸት እንደማይፈልግና ፈጥኖ ወደቤት መግባት እንዳለበት ተናገረ፡፡ በቀለ በቀላሉ አልተወውም፡፡ መልሶ መላልሶ ተማጸነው፡፡ ሀይሉም እየተጨነቀ ቁርጡን ነገረው፡፡ ውስጡን ሰላም እንደማይሰማው እየተረበሸ መሆኑንና ነገሮች ሁሉ እንደቀፈፉት አሳወቀው፡፡ ጥቂት ቆይቶ ውዝግቡ በባልና ሚስቱ አሸናፊት ተጠናቀቀ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላም ሀይሉ እየደበረው ሱቁን ዘግቶ ምሽቱን ከእነሱ ሊጋራ አብሯቸው ተጓዘ፡፡
ከጭፈራው ቤት…
ምሽቱ ገፍቷል፡፡ በጭፈራው ቤት የሚገኙ በየጠረጴዛቸው የሚጎነጩትን ይዘዋል፡፡ ሁሉም በመዝናናት ስሜት መጫወት ጀምረዋል፡፡ ሙዚቃው ፣በየአፍታው እየተቀየረ ታዳሚውን ያዝናናል፡፡ ሀይሉ ከባልና ሚስቱ ጋር ወደውስጥ ዘልቆ ከአንድ ጥግ ተቀመጡ፡፡ ወንበር አግኝተው መጠጣት እንደያዙ ልብስ ሰፊው ደረጀ ተቀላቀላቸው። ደረጀ በብርጭቆ አፕሬቲቭ እየተጎነጨ በሙዚቃው ይወዛወዛል፡፡ በቀላሉ ተግባቡት፡፡በቅርብ እንደሚያውቁት ሁሉ በጨዋታ አዋዝተው ቀረቡት፡፡
ደረጀ ከአንድ የሚያውቀው ወጣት የብሉቱዝ ሙዚቃ እያዳመጠ የራሱ ምርጫ እንዲከፈትለት ጠየቀ፡፡ ወጣቱ ፍላጎቱን አክብሮ የወደደውን እንግሊዝኛ ዘፈን ከፈተለት። በሙዚቃው እየደነሰ እነሀይሉ አጠገብ ከነበረ ባዶ ወንበር ላይ ተቀመጠ ፡፡ በዚህ መሀል ስለ በቀለ ነፍሰጡር ሚስት ጨዋታ ተነሳ፡፡ ደረጀ ከልቡ እየሳቀ ክርስትናው ይሰጠኝ ሲል ቀለደ፡፡ በድጋፍ ተጨበጨበለት፡፡ ጨዋታው ደመቀ።ዳንሱ ቀጠለ፡፡
አራት ሰአት ሊሆን አካባቢ ደረጀ ሂሳቡን ከፍሎ እነ ሀይሉን ተሰናበተ፡፡ አለፍ ብሎ ወደበሩ ከማምራቱ በርከት ብለው ከሚገቡት መሀል አንድ ቡጢ ተሰነዘረ፡፡ ቡጢው ብዙዎችን አልፎ ከደረጀ መሀል ግንባር ላይ አረፈ፡፡ ጩኸት ግርግሩ አየለ፡፡ገላጋይ መግባቱን ያወቁ ቡድኖች ደረጀ ወድቆ ፣እሰኪረታ ደበደቡት፡፡ እንደምንም ከእጃቸው አምልጦ ወደቤቱ ገሰገሰ፡፡
ከደቂቃዎች በኋላ ወደሆቴሉ ሲመለስ በሹራቡ እጅጌ የሽንኩርት ቢላዋ ይዞ ነበር፡፡ውስጥ ሲገባ የሆቴሉ መብራት ፈዞ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ መሀሉን አልፎ ወደ አንድ ጠረጴዛ አመራ፡፡ ሶስት ሰዎች ተቀምጠዋል፡፡ አንደኛውን በጨረፍታ አስተዋለው። በጋራ ካጠቁት መሀል እሱ እንዳለበት እርግጠኛ ሆነ፡፡ ጊዜ አላጣፋም፡፡ ቢላዋውን ከሹራቡ አውጥቶ ደረቱ ላይ ወጋው፡፡ በስለት ተወግቶ ከመሬት የወደቀው ስራ ወዳድ ታታሪው ሀይሉ ነበር፡፡
ደረጀ ወዲያው በመጣበት ፍጥነት እየተጣደፈ ወደቤቱ አመራ፡፡ ካሰበው ደርሶ ቢላዋውን አልጋ ስር ወረወረና ከቤት ወጥቶ ከአንድ ሆቴል አልጋ ይዞ አደረ፡፡
የፖሊስ ምርመራ
ወንጀሉ በተፈጸመ ማግስት ከፖሊስ ጣቢያ የደረሱት የሀይሉ ወላጅ አባት በልጃቸው ግድያ የመጀመሪያ ተጠያቂ በቀለንና ባለቤቱን አደረጉ፡፡ ፖሊስ ‹‹የፍትህ ያለህ›› ካሉት አባትና ከወንጀሉ ስፍራ ያገኛቸውን መረጃዎች ይዞ ምርመራውን ቀጠለ፡፡ መርማሪው ረዳት ኢንስፔክተር ሲሳይ ተሾመ ተጠርጣሪው ተይዞ እንደቀረበ ሙሉ ቃሉን ተቀበለ። ደረጀ የሰጠውን የዕምነት ክህደት ቃል በወንጀል መዝገብ ቁ1139/12 ላይ መዝግቦም ዶሴውን ለዓቃቤ ህግ የክስ መዝገብ አሳለፈ፡፡
ውሳኔ
ሀምሌ 18 ቀን 2013 ዓ.ም በችሎቱ የተሰየመው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተከሳሹ ላይ የመጨረሻውን ውሳኔ ለማሳለፍ በቀጠሮው ተገኝቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከህክምና ማስረጃና ከሰዎች ምስክርነት የቀረበለትን ማስረጃዎች አገናዝቦም ተከሳሹ ጥፋተኛ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በዕለቱ በሰጠው የፍርድ ውሳኔም ተከሳሽ ደረጀ እጁ ከተያዘበት ጊዜ አንስቶ በሚታሰብ የአስራሁለት ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጣልኝ ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡
መልካምስራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን መስከረም 8/2014