የሰው ልጅ በህይወት ለመኖር ከሚያስፈልጉት መሰረታዊና ቁልፍ ጉዳዮች መካከል ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ስለመሆኑ ብንናገር እርግጥ ነው አዲስ ነገር አልነገርናችሁ ይሆናል። እነዚህን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ገንዘብ የሚያስፈልግ ስለመሆኑ ብንነግራችሁም እንዲሁ ይህም ሳይታለም የተፈታ ነው ልትሉ ትችላላችሁ። ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ ሥራ መሥራት የግድ ነው ብንላችሁም ታዲያ ሥራ ሰርቶ ገንዘብ ማግኘት ምኑ ነው አዲስ ነገር በማለት አጉተምትማችሁም ይሆናል።
ግና ነገሩ ወዲህ ነው። ሰዎች የሚሰሩትን ሥራ ምን ያህል ወደውትና ተረድተውት እንዲሁም አዋጭና አማራጭ የሆነው የትኛው ሥራ ነው? ማን ምን ይሰራል? በሥራውስ ምን ተጠቀመ ብለን ብንጠይቅ ብዙ አዳዲስ፣ አስገራሚና አስተማሪ ነገሮችን እናገኛለን። እርግጥ ነው ለብዙዎቻችን ሥራ ማለት በመንግስት አልያም በግል ድርጅት ተቀጥሮ በመስራት ደምወዝተኛ መሆን መቻል ይመስለን ይሆናል። ከፍ ሲልማ ማንኛውንም አይነት ከትንሽ እስከ ትልቅ ያለ የንግድ ሥራ መስራት ብቻ ሊመስለንም ይችላል።
ይሁንና አብዛኞቻችንን በአንድ ሊያግባባን በሚችል አንድ አረፍተ ነገር ስንስማማ ማንኛውም ሥራ ክቡር እንደሆነ ስንመሰክር ‹‹ሥራ ክቡር ነው›› እንላለን። ታዲያ በዛሬው የስኬት አምዳችን እንግዳ ያደረግናቸው በረጅሙ ቢጫ ቱታ፣ በሰፋፊ ባርኔጣቸውና በረጅም ላስቲክ ጫማቸው እንዲሁም ማንነታቸውን በሚሸፍን ክንብንባቸው በብዛት የምናውቃቸው የየዕለት ገመናችንን ሸፋኝ የሆኑ ጀግኖቻችን ናቸው።
እነዚህ የያንዳንዳችንን ገመና ከመሸፈን አንስተው ሀገር መንደሩን አካለው ከተማዋን ጽዱና ውብ የሚደርጉ ጀግኖቻችን ከማናችንም በበለጠ የሥራ ክቡርነት የገባቸው ስለመሆናቸው ተግባራቸው ምስክር ነው። አሸብር፣ አየሎምና ጓደኞቻቸው የደረቅ ቆሻሻ የህብረት ሥራ ማህበርን የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ለማድረግ ስንነሳ ጓደኛሞቹ በሥራ ክቡርነት አምነው ብዙዎቻችን የማንደፍረውን ደፍረው የሰሩ፤ በስራቸውም ከምንም ተነስተው የተሻለ ተከፋይ በመሆን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ መሆን በመቻላቸው ለብዙ ወጣቶች አስተማሪ እንደሚሆኑ በማመን ጭምር ነው።
ትውልድና ዕድገቱን በተለምዶ ገርጂ ኢምፔሪያል ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያደረገው የአሸብር፣ አየሎምና ጓደኞቻቸው የደረቅ ቆሻሻ የህብረት ሥራ ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅና የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ቢኒያም መንግስቴ ስለማህበሩ አነሳስና ማህበሩ አሁን ያለበትን የስኬት ደረጃ፣ የአባላቱን ውጤታማነት እንዲሁም ስለ ሥራው አጠቃላይ ሁኔታ ይናገራል።
የዛሬ 11 ዓመት ደረቅ ቆሻሻን ቤት ለቤት በመዘዋወር በሸክም ለመሰብሰብ አስር ወጣቶች ሆነው ሲጀምሩ በቀዳሚነት አካባቢያቸውን ውብና ጽዱ ማድረግን ዓላማ አድርገው ነበር። ከአስሩ ወጣቶችም አምስቱ በተለያየ ምክንያት ሲገለሉ በአምስት ወጣቶች ሥራው መቀጠል ችሎ ከጽዱነት ባሻገርም ተከፋይ መሆን ችለዋል። ከአምስቱ ወጣቶች በተጨማሪ በወረዳው ከሚገኙ ሌሎች የደረቅ ቆሻሻ አንሺዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር ወረዳውን ተደራሽ ማድረግ እንዲችሉ ወደ ዩኒየን አደጉ። ወደ ዩኒየን ባደጉ ጊዜም 43 አባላት ሆነዋል።
የ43 ሰው ጉልበት፣ ጋሪና ከፍተኛ የመስራት ፍላጎት እንዲሁም ተነሳሽነትን ሰንቀው ወደ ሥራ የገቡት አሸብር፣ አየሎምና ጓደኞቻቸው የደረቅ ቆሻሻ የህብረት ሥራ ማህበር ‹‹ቆሻሻ ሀብት ነው›› የሚለውን አባባል በተግባር ማየት ችለዋል። በወቅቱ ስለ ደረቅ ቆሻሻ ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋትና ሥራውን በዕውቀት ለመምራት በነበራቸው ፍላጎት በራሳቸው ጥረት የተለያዩ ሙከራዎችን ያደርጉ እንደነበር አቶ ቢኒያም ይናገራሉ። በዚህም የደረቅ ቆሻሻ ሥራ በዓለም ላይ ካሉ የተለያዩ ሀገራት በክፍያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለ የሥራ ዘርፍ ስለመሆኑም ባደረጉት ጥረት መረጃውን አግኝተዋል።
በዓለም ሁለተኛ ደረጃ ተከፋይ የሆነው የደረቅ ቆሻሻ ሥራ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ሲያድግ በኢትዮጵያም ሁለተኛ ተከፋይ እንሆናለን በሚል ተስፋ ስራቸውን አጠናክረው በመቀጠል በወር አራት ሺ ብር ያገኙ ነበር። ከሚያገኙት ገቢ 20 በመቶውን ተቀማጭ በማድረግም ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ ግብአቶችን ለማሟላትና ሀብት ለመፍጠር ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል።
በዚህም በመጀመሪያ አንድ አይሱዙ በመግዛት ሥራውን በዕውቀት የታገዘና የተቀላጠፈ ማድረግ ችለዋል። ቀጥለውም ኦባማ አይሱዙ የተባለውን መኪና ከተቀማጫቸው ገዝተው በሚሰጡት የተቀላጠፈ አገልግሎት ክፍያቸውም ከአራት ሺ ወደ 12 እና 13 ሺ ብር የሚያገኙበት አጋጣሚ ተፈጠረ። በየወሩ የሚቆጥቡት ገንዘብ ወደፊት ያላቸውን ሰፊ ራዕይ ዕውን የሚያደርጉበት ነውና ዘመናዊና በአንድ ጊዜ ከፍተኛ መጠን ያለውን ቆሻሻ ማንሳት የሚችል ኮምፓክተር ማሽን መግዛት ችለዋል።
ይህ ዘመናዊ ማሽን በየቦታው የሚዝረከረኩ ቆሻሻዎችን ከማስወገዱም በላይ ስምንት አይሱዙ መኪና የሚጭነውን ቆሻሻ በአንድ ጊዜ ማንሳት የሚችል ነው። የማኅበሩ ተቀማጭ ከሆነው ገንዘብ አጠቃላይ ሁለት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺ ብር አውጥተው በመግዛት ሥራቸውን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ይበልጥ ማሳለጥ ችለዋል።
የደረቅ ቆሻሻን በማንሳት ተደራጅተው በከተማዋ ውስጥ ከሚገኙ ከ200 በላይ ማህበራት መካካል አሸብር፣ አየሎምና ጓደኞቻቸው የደረቅ ቆሻሻ የህብረት ሥራ ማህበር ግንባር ቀደም በመሆን ዘመናዊ የቆሻሻ ማንሻ ኮምፓክተር መግዛት መቻላቸውን ያነሱት አቶ ቢንያም ማሽኑን በማከራየትም ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ያሉ በሀገሪቱ የክልል ከተሞች ዛሬም ድረስ ደረቅ ቆሻሻ በጋሪ እየተሰበሰበ መሆኑን አንስተዋል። በቀጣይ በክልል ከተሞች ሳይቀር ተደራሽ ለመሆን ያላቸውን ዕቅድ ሲያብራሩም ቆሻሻ ሀብት እንደመሆኑ በስፋት ሰርተው ወደ ውጭ ሀገር መላክም የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል። ቆሻሻ ከአውሮፓ ወደ ቻይና ይላካል ብለዋል። በተለይም በቻይና ሀገር የተለያዩ የቆሻሻ አይነቶችን በመለየት ለተለያዩ አገልግሎቶች ያውሉታል። ‹‹በእኛ ሀገር ደረጃ ቆሻሻውን ተጠቅመን ማምረት ባንችልም ቆሻሻውን ወደ ውጭ ልኮ ገቢ ማግኘት ግን ይቻላላ›› የሚሉት አቶ ቢንያም፤ ለተግባራዊነቱም ጥናት እያደረጉ እነደሆነ ተናግረዋል።
አሸብር፣ አየሎምና ጓደኞቻቸው የደረቅ ቆሻሻ የህብረት ሥራ ማህበር በየዕለቱ የወረዳቸውን ደረቅ ቆሻሻ በሶስት ፈረቃ ተዘዋውረው በሁለት አይሱዙ ያነሳሉ። የተሰበሰበውን ቆሻሻም በፈርጅ በፈርጁ ለይተው ከመኪና ወደ ኮምፓክተር በመጫን መልሶ ጥቅም ላይ የሚውለውንም ሆነ ሌላውን ወደ ረጲ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ያደርሳሉ። ባቀረቡት የቆሻሻ መጠንም በኪሎ የወጣለትን ዋጋ በማባዛት ተከፋይ ይሆናሉ።
ቆሻሻ ማንሳት ለበርካቶች የተናቀ ሥራ ከመሆኑም በላይ ማህበሩ ቆሻሻውን ማንሳት ባለበት ሰአት ሳያወጡ የጸዳ ሰፈር የሚያቆሽሹ በመኖራቸው የሚያስመሰግን ሥራ አለመሆኑን አቶ ቢኒያም ሲያነሱ በተለይም ተምረዋል ስልጡን ናቸው የሚባሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ከሌሎቹ በበለጠ ለሥራው ትልቅ እንቅፋት ናቸው ይላሉ። ለአብነትም አብዛኛው በዝቅተኛ ደረጃ ያሉት የማህበረሰብ ክፍሎች ቆሻሻውን ለይቶ ያቀርባል። ይህም ሥራቸውን ቀልጣፋ የሚያደርግ ስለመሆኑ ለአብነት ይጠቅሳሉ።
አንዳንድ አካባቢዎችም ባዕድና ስለታማ የሆኑ የቆሻሻ አይነቶችን ጭምር ቀላቅለው በማቅረብ ሰራተኞችን ለአደጋ የሚጋልጡ በመሆናቸው ሥራውን ፈታኝ ያደርገዋል። ይሁን እንጂ እነዚህን እና መሰል ችግሮችን በመቋቋም አሸብር፣ አየሎምና ጓደኞቻቸው የደረቅ ቆሻሻ የህብረት ሥራ ማህበር ውጤታማ የሆነ ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ።
ቤት ለቤት በመዘዋወር እያንዳንዱን አባወራ እያገኙ ዕለት ዕለት ቆሻሻ ከሚያነሱት አባላት መካከል 15 የሚደርሱ ምንም ያልነበረቻው የጎዳና ተዳዳሪ የነበሩ ዜጎች ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚ በመሆን እራሳችውን ችለው ወልደው ጭምር የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆን ችለዋል። ይህም የማህበሩ ስኬት ነው የሚሉት አቶ ቢንያም፤ ሥራው ፈታኝና አድካሚ በመሆኑም አብዛኛው ሰራተኞች ወንዶች ሲሆኑ ሰባት ሴቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
‹‹ማንኛውንም ሥራ ጣት እየቀሰሩ ከማዘዝ ይልቅ ሰርቶ ማሰራት ውጤታማ ያደርጋል›› የሚሉት አቶ ቢኒያም ምንም እንኳን የማህበሩ ሃላፊ ቢሆኑም ከማንኛውም ሰራተኛ እኩል ወርደው መስራት በመቻላቸው ከሰራተኞቻቸው ጋር ያላቸው ቀረቤታ እጅግ ሰላማዊና መከባበር መደማመጥ የተሞላበት መሆኑን ይናገራሉ። ሰራተኞችም ሥራቸውን በፍቅርና በጉጉት ይሰራሉ። በመሆኑም ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል።
ማህበሩ ካስመዘገበው ፋይናንስና ግብአት በላይ ስኬታማ ነው ለማለት ትናንት እጃቸውን ዘርግተው ከሰዎች ምጽዋት ሲቀበሉ የነበሩ 15 ጎዳና ተዳዳሪ የነበሩ ዜጎች ዛሬ እራሳቸውን ችለው ለሌሎች ተርፈው ማየት ትልቁ ስኬት ስለመሆኑና ትልቅ ደስታ የሚሰጣቸው እንደሆነም ይናገራሉ። ከዚህም ባለፈ የሚኖሩበት አካባቢ ጽዱ ሆኖ ማየት በራሱ ስኬት ነው። ከኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው የበለጠ የሚያስደስታቸው እንደሆነ አስረድተዋል።
የቆሻሻ ምንጩ በሰፋ ቁጥር የገቢ መጠናቸውም የሚጨምር መሆኑን ያነሱት አቶ ቢንያም ከበጋ ወቅት ይበልጥ በክረምት ከፍተኛ መጠን ያለው ቆሻሻ የሚሰበስቡ እንደሆነ ይናገራሉ። ለዚህም ምክንያቱ በክረምት ህጻናት ቤት ውስጥ የሚውሉ በመሆናቸው፣ አትክልትና ፍራፍሬ የሚደርስበት ወቅት መሆኑ ቆሻሻ ይበዛል። በተጨማሪም በዝናብ የራሰው ቆሻሻ ክብደት መያዝ በመቻሉ ከበጋ ወቅት በበለጠ ገቢ ማግኘት ያስችላቸዋል።
ቤት ለቤት ደረቅ ቆሻሻን መሰብሰብ ፈታኝ የሚያደርገው በርካታ ነገር መኖሩን የጠቀሱት አቶ ቢንያም በተለይም ዓለም አቀፍ ስጋት ሆኖ የቀጠለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሀገሪቱ በተከሰተበት የመጀመሪያዎቹ ወቅቶች ላይ ይፈተኑ እንደነበር ያነሳሉ። በወቅቱ ወረርሽኙ በሰዎች ጤና ላይ ካሳደረው ጫና በበለጠ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎችን ገድቦም ነበር። ይሁንና ለጤና ስጋት የሆኑ ሶፍትና የተለያዩ ነገሮችን በመሰብሰብ ጭምር የደረቅ ቆሻሻ ሥራ ሳይቋረጥ መስራት ተችሏል። ምንም እንኳን ወቅቱ እጅግ ፈታኝ የነበረ ቢሆንም ከአባላቶቻቸው መካከል ችግር የገጠመው እንዳልነበር ተናግረው ለዚህም ፈጣሪያቸውን አመስግነዋል።
በአሁኑ ወቅትም በደማቁ ቢጫ ቱታቸው የሚታወቁት የጽዳት አርበኞቹ ወደፊት ትልቅ ራዕይን ሰንቀው ሥራቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል። አካባቢያቸውን ከማጽዳት ባለፈ በሌሎች አካባቢዎችም ተንቀሳቅሰው መስራት የሚችሉበትን ሁኔታ እያመቻቹ ሲሆን በተለይም ከፍተኛ መጠን ያለውን ቆሻሻ ማንሳት በሚችለው ኮምፓክተር ማሽን ተጠቅመው በክልሎችም ተደራሽ ለመሆን ያላቸውን ዕቅድ ተግባራዊ ሊያደርጉ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
ደረቅ ቆሻሻ ከመሰብሰብ ባለፈም ማህበሩ በቀጣይ ከብት የማርባት ዕቅድና ፍላጎት ያለው መሆኑን ያነሱት አቶ ቢንያም፤ ሃሳቡ የመጣላቸው ሰርክ ከሚሰበስቡት የደረቅ ቆሻሻ ጋር በተያያዘ ነው። ቤት ለቤት ተዘዋውረው የሚሰበስቡት የደረቅ ቆሻሻ የተለያየ አይነት ብስባሽና ለከብቶች መኖ መሆን የሚችሉ የቆሻሻ አይነቶች ይገኛል። ይህም አንድ ግብዓት በመሆኑ ለሥራው ምቹ እንደሆነ ይናገራሉ። ለዚህም ወረዳውን ቦታ ጠይቀው ወደ ከብት እርባታ ለመግባት የጠየቁት ቦታ እስኪፈቀድላቸው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ።
ደረቅ ቆሻሻን በሸክም፣ በጋሪ ብሎም በመኪና ከፍ ሲልም ኮምፓክተር ዘመናዊ የቆሻሻ ማንሻ መግዛት የቻሉት አሸብር፣ አየሎምና ጓደኞቻቸው የደረቅ ቆሻሻ የህብረት ሥራ ማህበር በአሁኑ ወቅት አባላቶቹ ጥሩ ተከፋይ ከመሆናቸው ባለፈ 10 ሚሊዮን ካፒታል መድረስ ችለዋል። እኛም በአዲሱ ዓመት ያሰቡት ተሳክቶ ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆኑ በመመኘት አበቃን::
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን መስከረም 4/2014