አስመረት ብስራት
ልጆች እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሳችሁ። በአዲሱ አመት ሰላምና ተስፋ እንዲሁም የአዲስ ነገር ብስራት የምንሰማበት ይሁልን እያልኩኝ ለአዲስ አመት በከተማ አከባቢ ወንድ ልጆች አበባ በመሳል የመልካም ምኞት መግለጫቸውን ሲሰጡ ሴቶች ደግሞ በአበባየሆሽ ጭፈራ ያደምቁታል። ልጆች ትክክለኛውን የአበባ አየሆሽ ግጥም በመረዳት መጨፈር አለባቸው።
ልክ ጭፈራው ሲጀመር
ሆ ብለን መጣን፣ ሆ ብለን፤
ጌቶች አሉ ብለን፤
ሆ ብለን መጣን፣ ሆ ብለን፤
እሜቴ አሉ ብለን፤ በሚል የማብሰሪያ ዜማ ተጀምሮ ወደ ዋናው ግጥም ይገባል።
እውዬ (እኸ) እዋውዬ ካሽከር ተዋውዬ
ጌቶች አሉ ብዬ፣ ገባሁ ሰተት ብዬ፤
አበባይሆሽ (ለምለም)
ባልንጀሮቼ (ለምለም)፣ ቁሙ በተራ (ለምለም)፤
እንጨት ሰብሬ (ለምለም)፣ ቤት እስክሰራ (ለምለም)፤
እንኳን ቤትና (ለምለም)፣ የለኝም አጥር (ለምለም)፤
እደጅ አድራለሁ (ለምለም)፣ ኮከብ ስቆጥር (ለምለም)፤
ኮከብ ቆጥሬ (ለምለም)፣ ስገባ ቤቴ (ለምለም)፣
ትቆጣኛለች (ለምለም)፣ የንጀራ እናቴ (ለምለም)፣
የእንጀራ እናቴ (ለምለም)፣ ሁለት ልጅ አላት (ለምለም)፤
ለነሱ ፍትፍት (ለምለም)፣ ለኔ ድርቆሽ (ለምለም)፤
ከሆዴ ገብቶ (ለምለም)፣ ሲንኮሻኮሽ (ለምለም)፤
አበባማ አለ (ለምለም)፣ በየውድሩ (ለምለም)፤
ባልንጀሮቼ (ለምለም)፣ ወልደው ሲድሩ (ለምለም)፤
እኔ በሰው ልጅ (ለምለም)፣ ማሞ እሹሩሩ (ለምለም)፤
አደይ የብር ሙዳይ፣ ኮለል በይ፤ በማለት እየተቀባበሉ የሚጨፍሩት ህፃናት በተለያዩ ግጥሞችና ጭፈራዎች በአሉን ያደምቁታል።
ከገዳይ ጋራ (ለምለም)፣ ስጫወት ውዬ (ለምለም)፤
ራታችንን (ለምለም)፣ ንፍሮ ቀቅዬ (ለምለም)፤
ድፎ ጋግሬ (ለምለም)፣ ብላ ብለው (ለምለም)፤
ጉልቻ አንስቶ (ለምለም)፣ ጎኔን አለው (ለምለም)፤
ከጎኔም ጎኔ (ለምለም)፣ ኩላሊቴን (ለምለም)፤
እናቴን ጥሯት (ለምለም)፣ መድሃኒቴን (ለምለም)፤
እሷን ካጣችሁ (ለምለም)፣ መቀነቷን (ለምለም)፤
አሸተዋለሁ (ለምለም)፣ እሷን እሷን (ለምለም)፤
አባቴን ጥሩ (ለምለም)፣ መድሃኒቴን (ለምለም)፤
እሱን ካጣችሁ (ለምለም)፣ ጋሻ ጦሩን (ለምለም)፤
አሸተዋለሁ (ለምለም)፣ እሱን እሱን (ለምለም)፤
አደይ የብር ሙዳይ፣ ኮለል በይ፤
እቴ አበባ ሽታ አበባዬ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
እቴ አበባሽ ስትለኝ ከርማ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
ጥላኝ ሄደች በሐምሌ ጨለማ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
እቴ አበባሽ እቴ እያለቺኝ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
ጋሻ ጦሬን ወስዳ አሸጠቺኝ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
እንኳን ጋሻ ይሸጣል በሬ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
ከናጥንቱ ከነገበሬ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
ሄሎ ሄሎ የገደል ሄሎ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
ማን ወለደሽ እንዲህ መልምሎ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
ወለደቺኝ መለመለቺኝ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
ላፈንጉስ ዳርኩሽ አለቺኝ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
ካፈንጉስ አምስት ወልጄ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
አንዱ ዳኛ ያውም መልከኛ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
አንዱ ቄስ ቆሞ ቀድስ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
አንዱ ቂል ንፍሮ ቀቅል፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
አንዷ ሴት የሺመቤት፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፤
አንዱ ሞኝ ቂጣ ለማኝ፣ (አዬ እቴ አበባዬ)፣ በማለት ከዘመሩ በኋላ ልጆቹ ስጦታቸውን ከተቀበሉ በኋላ የቤቱን ባለቤቶች ማሞገስ ይጀምራሉ።
ይሸታል ዶሮ ዶሮ፣ የማምዬ ጓሮ፤
ይሸታል ጠጅ ጠጅ፣ የጌቶችም ደጅ፤
ሻሽዬ (እኸ)፣ ሻሽ አበባ፤
ደሞም ሻሽ አበባ፤
እራስ ሥዩም ግቢ፣ ይታያል ሲኒማ፤
የማነው ሲኒማ፣ ያፀደ ተሰማ፤
ሻሽዬ (እኸ)፣ ሻሽ አበባ፤
ደሞም ሻሽ አበባ፤
ትራሷም ባላበባ፤
ፍራሹም ባላበባ፤
እርግፍ እንደወለባ፤
የማምዬ ቤት (ለምለም)፣ ካቡ ለካቡ (ለምለም)፤
እንኳን ውሻቸው (ለምለም)፣ ይብላኝ እባቡ (ለምለም)፤
ከብረው ይቆዩን ከብረው፤
ባመት ወንድ ልጅ ወልደው፤
ሃምሳ ጥገቶች አስረው፤
ከብረው ይቆዩን ከብረው፤
ከብረው ይቆዩን በፋፋ፤
የወለዱት ልጅ ይፋፋ፤
ከብረው ይቆዩን በስንዴ፤
ወንድ ልጅ ወልደው ነጋዴ፤
ከብረው ይቆዩን ከብረው፤ በማለት መርቀው ለቀጣይ አመት ያድርሰን ብለው ተሰናበተው ይሄዳሉ። ልጆች፤ እናንተም በዚህ መልኩ ዘምራችኋል አይደል? መልካም አዲስ ዓመት።
አዲስ ዘመን መስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም