በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በተለያዩ ጊዜያት ከሀገራቸው ጎን በመቆም ለወገኖቻቸው የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ዲያስፖራው በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች እና ለህዳሴው ግድብ ግንባታ እስካሁን እያደረገ ያለው ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው የህልውና ዘመቻ የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል። የህልውና ዘመቻው በድል እንዲጠናቀቅም ለሀገሩና ለወገኑ አለኝታ መሆኑን በአደባባይ እያስመሰከረ ነው።
የዲያስፖራው ማህበረሰብ በሚኖርባቸው የዓለም ሀገራት ሆኖ ሰላማዊ ሰልፎችን በማድረግ ፣ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙ የተሳሳቱና የተዛቡ አመለካከቶች በማጋለጥ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያለውን ነባራዊ እውነታ እንዲያወቀው ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው።
ከዚህ ባሻገር በዲፕሎማሲው ረገድም የኢትዮጵያ ጉዳይ በመሠረታዊነት ይዘው ብዙ ርቀት እየተጓዙ ነው። በተለይ በህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ግብጽና ሱዳን የያዙትን የተዛበ አመለካከት ለዓለም አቀፍ ተቋማትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት እንዲታይላቸው ባደረጉበት ወቅት የዳያስፖራው ማህበረሰብ ቀዳሚ ሆኖ ሲሞግትና ሲከራከር ቆይቷል ። የህዳሴ ግድቡ ጉዳይ በአፍሪካ አደራዳሪነት እንዲታይ መደረጉም በዲፕሎማሲ ረገድ መልካም ውጤት የተገኘበት ነው።
አሁን አገራችን የህልውና ዘመቻ ላይ እንደመሆኗ መጠን ከሀገራቸው ጎን በመቆም የህልውና ዘመቻው ለመከላከል እያደረጉት ያለውን አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። ባሉበት ሆነው ኢትዮጵያ ላይ የተቃጠውን ጥቃት ለመመከት የሚያስችል ትዕይንት ህዝብ ያካሄዳሉ። የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች በመጠቀም ያለውን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስረዳት በእጅጉ ጥረት እያደረጉ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ከሠራዊቱ ጎን መቆማቸውን እያስመሰከሩ ይገኛሉ።
አሁን ላይ ደግሞ ባሉበት ሀገር ሆነው ከሚያደርጉት የእውቀት፣ የገንዘብ እና የሞራል ድጋፍ በተጨማሪ ወደ ሀገራቸው በመምጣት የህልውና ዘመቻውን በመቀላቀል ላይ ናቸው። ሩቅ ሆኖ ቀን ከለሊት የሀገራቸውን ሰላም ከመሻት በዘለለ ሀገር ስትታመም፣ ወገን ሲቸገር አብረው ለመሆን ባህርና ውቅያኖሱን አቋርጠው የሀገር ጥሪ መልስ ለመሰጠት ‹‹አለንልሽ ሀገሬ›› ብለው የተገኙ ብርቱዎች እንዲሁ ተበራክተዋል።
የዲያስፖራው ማህበረሰብ በሚኖርበት ሀገር ተመችቶትና ደልቶት መኖር ቢችልም የደሃ ወገኑንና የውድ ሀገሩ መጎዳት እረፍት ነስቶታል፤ ይህ እውነታ እንደእሳት እየለበለበውም አብሮ መሆንን ፤ ለሀገር ህልውና መታገልን መርጧል ። ለዚህም ነው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ወጥኖ የሚያሴረውን የአሸባሪ ህወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ በሚደረግ የህልውና ዘመቻ ከወገን ጋር በመሰለፍ ለኢትዮጵያ አንድነት ዘብ መቆም ያስፈለገው። አገር ወዳዱ ዲያስፖራ በቁርጠኝነት ከባህር ማዶ ገስግሶ ከሀገሩ የተገኘው። በመሆኑም በእልህና በቁጭት፣በታላቅ ወኔ የህልውና ዘመቻ በመቀላቀል የሀገር አለኝታ የቁርጥ ቀን ልጅነቱን አስመስክሯል።
የህልውና ዘመቻውን በይፋ ከተቀላቀሉት ውስጥ አንዱ ኑሮውን በሀገር እንግሊዝ ያደረገው ዲያስፖራ ሰለሞን ቦጋለ ነው። አቶ ሰለሞን ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር በነበረው ቆይታ እንደገለጸው ኢትዮጵያ ከገባችበት ችግር ለመውጣት በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለሀገር ህልውና መቆም አለባቸው በሚል ዘመቻውን እንደተቀላቀለ ይናገራል።
‹‹ከወገኖቼ ጋር ሆኜ የትጥቅ ትግሉን በመቀላቀል የሀገር ህልውና በድል በመወጣት፤ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ሆኜ ነው የመጣሁት›› የሚለው አቶ ሰለሞን፤ የሚወዳትን ሀገሩን ጥሎ ለመሰደድ ያበቃው የአሸባሪው ህወሓት ግፍና በደል መሆኑን ገልጧል። ‹‹27 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ተበድሏል፤ እኔ አላሰራ ሲሉኝ ነው ሀገሬን ጥዬ የወጣሁት›› ይላል። ኑሮውን በእንግሊዝ ሀገር ያደረገው አቶ ሰለሞን፤ በውጭም ሆኖ በኢትዮጵያ ውስጥ የተቀሰቀሰውን አመጽ በተመለከተ በኢትዮጵያ ካሉ ወገኖቹ ጋር መሆኑ ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ንቅናቄ በመፍጠር ለውጥ ለማምጣት ይሰራ እንደነበር ጠቅሶ ፤ በዚህም የተነሳ የተለያዩ በደሎች ሲደርስበት እንደቆየ ይናገራል።
አቶ ሰለሞን እንደሚለው ፤ አሁን ላይ እየሆነ ያለው ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን ኢትዮጵያን በማፍረስ ያለመ ሴራ ነው ። ለዚህም ደግሞ የትውልድ ተወቃሽ እንዳንሆን ሁሉም በአንድ ሆኖ የጁንታውን ቡድን ደምስሰን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ሁሉም ብሔሮች ተቻችለው የሚኖሩባት ሀገር መስርተን መኖር አለብን ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል።
‹‹እኔ በምኖርበት እንግሊዝ ሀገር በሰዓት 17 ፓውንድ እየተከፈለኝ ዘና ብዬ መኖር እችላለሁ፤ ሆኖም ግን በዚህ ጊዜ ሀገሬ እኔን ትፈልጋለች ለሀገሬ መስዋዕትነት ለመክፈልም ዝግጁ ነኝ ›› ብሏል።
የዲያስፖራው የህልውና ዘመቻ ተሳትፎን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንደስን ግርማ በበኩላቸው ዲያስፖራው በሞራል፤ በገንዘብ እንዲሁም በዲጂታል ዲፕሎማሲ ረገድ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለማክሸፍ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችና ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።
አቶ ወንደሰን እንደሚሉት ፤ ዲያስፖራው ከሀገር ድህነት ጋር በተያያዘ የሚያደርገው ተሳትፎ በሁለት መልኩ ማየት ይቻላል። የመጀመሪያው ሀብት የማሰባሰብ ሲሆን፤ ሁለተኛው በፐብሊክ ዲፕሎማሲ መስክ የሚያደርገው ተሳትፎ ነው። በሀብት ማሰባሰብ ሂደቱ በሰሜን እዝ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመ ጥቃትን አስመልክቶ ዲያስፖራው በራሱ ፍላጎቱና ተነሳሽነት ሀብት ለማሰባሰብ ጥረት አድርጓል። በዚህም አስፈላጊ የሆኑ መደኃኒቶችን የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።
በመጀመሪያው ዙር ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ ለህልውና ዘመቻው በሚደረግ ድጋፍ ሦስት ሳምንት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ 36 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል። ይህ የሚያሳየው ዲያስፖራው በሀገሩ ላይ እየተቃጣ ያለውን ጥቃት ለማስቆም ያለውን ቁርጠኝነት ነው ።
ከዚህ ባሻገርም ዲያስፖራው በርካታ ህዝባዊ ትዕይንቶች በተለያዩ ሀገሮች በማድረግ በሀገሩ ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት አቅሙ የፈቀደውም ሁሉ እያደረገ ነው። በዲፕሎማሲ ረገድ መልዕክቶችን በመቅረጽ ከፍተኛ የቲውተር ዘመቻ እያደረገ በመሆኑ እነዚህ የቲውተር ዘመቻዎች በምዕራባዊያን ላይ ተፅጽኖ እያሳደሩ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ለአብነትም በኒውዮርክ ታይምስ የፊት ለፊት ገጽ ‹‹በትግራይ ያሉ ህጻናትን በጦርነቱ ተቀላቅለዋል›› የሚል አይነት መልዕክት ያዘለ ዘገባ መቅረቡ የሚታወስ ነው። ዲያስፖራው በቲውተር ዘመቻው ህጻናትን ለጦርነት ማሰለፍ የጦር ወንጀል መሆኑን በመግለጽ ባደረገው ዘመቻ ምክንያት ኒውዮርክ ታይምስ የለጠፈውን ጽሁፍ ለማንሳት ችሏል።
ዲያስፖራው የተዛቡ አመለካከቶችን ለማስተካከል በሚያደርገው ዘመቻ ምዕራባዊያን የሚፈልጉትን ያህል ተፅዕኖ ማድረግ አልቻሉም ያሉት አቶ ወንደሰን፤ በተለይ በአውሮፓ ‹‹ዲፊንድ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን እንዳለ ጠቁመዋል።
ቡድኑ ፅሁፎችን በመጻፍ በራሳቸው ሚዲያ ሆነ ዓለም አቀፍ ሚዲያን ተጠቅመው ያሉ ነባራዊ እውነታዎች የሚገልጹበት መሆኑን ጠቁመው፤ በአፋርና በአማራ ክልል የተፈጠሩ የበርካታ ንጹሀን ሰዎች ሕይወት አልፏል፣ የንብረት ውድመትና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን አስመልክቶም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቃቸው ጥረት እየተደረገ ነው። በዚህ ረገድ ዲያስፖራው እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አቶ ወንደሰን ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2013