መልካምነት ለሰው ልጆች የተሰጠ የበጎነት መግለጫ ምግባር ነው:: ሰው ስለሆን ብቻ ለሰው የምናደርጋቸው መልካም ነገሮች ፤ በዚህም የሚሰማን ጥሩ ስሜት ፣ ሰብዓዊነትና ፍቅርን የምንገልጽበት መንገድ ነው:: መልካምነት ዘመን የማይሽረው የበጎነት ጥግ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል :: የሰው ልጅ ምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ መልካምነት ሲነገርና ሲዘከር የኖረ የሰው የባህርይ መገለጫ ነው::
በሃይማኖታዊ አስተምሮቱም በየቤተ እምነቱ ስለመልካምነት በርካታ ትምህርት ይሰጣሉ:: አስፈላጊነታቸው ለማጽናት የሚያስችሉ ምሳሌዎችም እንዲሁ ይጠቀሳሉ:: በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በቅዱስ ቁርዓን ውስጥ በሃይማኖት አስተምሮቱ ስለመልካምነታቸው፣ ስለበጎ ሥራቸው ስማቸው በጉልህ የሚጠቀሱ እነአብረሃምን የመሳሰሉ ቅዱሳን ይጠቀሳሉ :: እነዚህ ስለመልካምነታቸው ዘወትር የሚነገርላቸው ባለገድሎች በቤተእምነቶችም አስተምሮ ቢሆን ሁልጊዜ አርአያ ተደርገው የሚነሱ ናቸው::
በዚህ ዓለም በመልካምነት ተግባራቸው ከሰሩት ሥራ ጋር አብሮ ስማቸው የሚጠቀሱ ጥቂቶች ናቸው:: የሰው ልጆችን በዘር፣ በቀለም እና በሃይማኖት ሳይለዩ ሁሉንም በእኩል መዝነው በጎነታቸውን የሚያጋሩ አሉ :: እነሱ ከሚበሉት ይልቅ የሚበላውን ያጣ ሰው ሲበላና ሲጠጣ ሲያዩ ፤ ነፍሳቸው በሀሴት የምትሞላ ሀሴት የሚያደርጉ የቅን ልቦና ባለቤቶች በየዘመናቱ ይኖራሉ::
የሰው ልጅ ዘር፣ ቀለም ሃይማኖት ሳይለዩ ፤ ድንበር ሳይገድባቸው የሰው ልጅ በመሆኑ ብቻ መልካምነት የሚያደርጉ በሥራቸው የተመሰገኑ የዓለማችን ያፈራቻቸው ጥቂት ፈርጦች አሉ :: ለሚስኪናኑ የዕለት ጉርስ የሚሰጡ ፣ በርካቶች ከጎዳና ላይ የሚያነሱ ደጋጎች የመልካምነት ምሳሌ ናቸው::
ከእነዚህ በግንባር ቀደምትነት ሰማቸው የሚነሳው በሮማውያኑ የካቶሊክ እምነት ውስጥ በምንኩስና ህይወት ቆይተው፤ ህይወታቸውን ሙሉ ድሆችን እና ረዳት የሌላቸውን በማገልገል ያሳለፉት ማዘር ትሬዛ ናቸው::
ማዘር ትሬዛ የድሆች እናት የሚል መጠሪያ ያላቸው ለብዙኃኑ ህይወት ዋጋ የከፈሉ ፤ የበጎነት ጥግና መልካም ሥራቸውን ዓለም በአንድ አፍ የመሰከረው የቅን ልብ ባለቤት ሆነው ስማቸውን ከመቃብር በላይ ያጻፉ ናቸው::
በሀገራችንም በመልካምነት ስራቸው በየዘመኑ ስማቸው የሚጠቀሱ ብዙ ሰዎች አሉ:: ኢትዮጵያዊቷ ማዘር ትሬዛ በመባል የሚታወቁት የብዙኃን ድሆች እናት አበበች ጎበና ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው :: የህይወት ዘመናቸው ወላጆች የሌላቸውን ሕጻናት አቅፈውና ደግፈው የሚይዙ ነበሩ::
አበበች ድሆች ሲርባቸው አብልተው፤ ሲታረሱ አልብሰው የእናትነት ፍቅር እየመገቡ ያኖሩ መልካምነት መገለጫ ናቸው:: በመልካምነት ጥላ ሥር ያሉ ሰዎች በሚያደርጉት መልካም ነገሮችና በጎ ተግባራት የሚረኩና ውስጣዊ ደስታ የሚያገኙ ናቸው:: በሂሳብ ስሌት ይህንን ሰው ብረዳው ሌላ ነገር አገኛለሁ ብለው የማያሰብ ለህሊናቸው ውስጣዊ ደስታቸው ከተሰማቸው በቂ መሆኑን አምነው የሚኖሩ ናቸው:: ከመልካምነት በቀር ሌላው ለምኔ ብለው ያላቸውን ሊኖራቸው የሚችለውን ሁሉ እርግፍ አድርገው ትተው መልካምነት የሙጥኝ ያሉ ናቸው::
ለበጎነት በተሰጡ ሰዎች የብዙ ሚስኪኖች ህይወት ተዋጅቷል:: ከሞት አፋፍ ላይ ያለች ነፋስ የመኖር ህልውና አግኝታለች:: በእነሱ መልካምነት የብዙዎች ህይወት ተስተካክሏል:: መልካም ሥራቸው ጎልቶ ወጥቶ አብርቷል :: እነሱ ለሰው ኖረው ቢያልፉ ትል የማይበላው፤ ነቀዝ የማያበላሸው ህያው ሥራቸውን ሁሌም ከመቃብር በላይ ሆኖ ይኖራል ::
በርካቶች ያልሄዱበት መንገድ ጥቂቶች ተጉዘው መልካም ጅማሮሽ አሳይተዋል:: አርአያነታቸው ለትውልድ ሲዘከር የሚኖር ነው:: መልካምነት ይከፍላል እንዲህ አይደለ ታዲያ:: አሁንም የእነዚህ ደጋጎች መልካም ፈለግ የተከተሉ ብቅ ብቅ እያሉ ነው :: እነሱ የሄዱበት መስመር ተከትለው ለሚስኪናን አለንላቸው የሚሉ ሰማቸው ያልተጠቀሰም እንዲሁ አሉ::ካላቸው ላይ ቀንሰው ለሌላው ወገናቸው በማካፈል መልካም ሥራን ገንዘባቸው ያደረጉ ::
የሀገራችን እሴት ከሆኑት ውስጥ በመልካምነት ጎዳና በመረዳዳትና በመደጋገፍ ከራስ ቆርሶ ለወገን ማጉረስ የኖረ ባህላችን ነው:: ያለው ካለው ላይ ቀንሶ፤ ለሌለው የመስጠት ባህል በእጅጉ የተለመደ ነው:: በየጊዜው በተለያዩ በጎ አድራጊዎች እነዚህ ተግባራት እየተከወኑ ይገኛሉ::
ከሀገር መሪው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የጀመረው የማዕድ ማጋራት የመልካምነት ቱሩፋት ለበርካቶች መንገድ የመራ ነው:: በተለይ የኮቪድ ወረርሽኝ በሀገራችን ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ለአቅመ ደካማና ረዳት ለሌላቸው ሚስኪናን እንዲሁም በጎዳና ላይ ላሉ ልጆች በማዕድ ማጋራት በርካቶች እጃቸውን የዘረጉበት የበጎነትና የመልካምነት ሥራ ተሰርቷል:: የጠቅላይ ሚኒስትሩን በጎ ጅማሮች የተከተሉ በርካቶች እጃቸውን ዘርግተው ለወገኖቻቸው ያላቸውን ለማካፈል ሳይሳሱ እያደረጉት ይገኛሉ::
መሪ መንገድ አሳይ ነውና ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ በርካታ ተግባራት እየፈጸሙ ይገኛሉ:: የመልካምነትና የበጎነት ሥራቸው ለበርካታ ዓመታት ሳይጠገኑ ቀርተው በበጋ የፀሀይ ሐሩሩን ፤ በክረምት ደግሞ ዝናቡ መቋቋም አቅቷቸው አይዟችሁ ባይ ያጡ የአቅመደካሞች ጎብኝቷል::
እነዚህን አቅመደካሞች ዘንበል ብለው ያዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤቶቻቸውን በሚያምር ሁኔታ አሠርተው አስረክበዋቸዋል:: በወቅቱ ከአቅመ ደካሞቹ ፊት ሲነበብ የነበረው ከልብ የመነጫ ስሜት የሚነካ ደስታ በምንም ሊተካ የማይችል ነው::
ታዲያ መልካሙን ተግባር በአርአያ መከተል ብልህነት ነው:: የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ሳይቀሩ ይህንን መልካምነት በመከተል በመሪው መንገድ እየተመሙ ነው:: በትንሹ የጀመረ መልካምነት ፍሬው ብዙዎችን ያጠግባልና የጀመሩትን ማስቀጠል ይገባል::
እንደመሪያችን በድንገት ሚስኪናን ደጅ ተገኝቶ ለዘመናት ሲመኙ የኖሩት ፍቅር ማሳየት ከምንም በላይ ዋጋ ውድ ነው:: ለመልካምነት የሚያስፈልገው ቅን ልቦና ብቻ ነው:: ኖረንም አልኖረንም አብረናቸው ሆነን ከጎናችን ስናደርጋቸው ከዚህ በላይ ምንም ትልቅ ነገር የለም::
መልካምነት በቀናት ብቻ ሊገደብ የማይገባው ሳይሆን የህይወት መርህ ሆኖ በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ተግባር መሆን አለበት:: በዘመናችን ከኛ የሚጠበቀውን መልካምነት ነው :: በመልካምነት ጎዳና እጅ ለእጅ ተያይዘን በአንድነት ከተጓዝን የማንሻገር ችግር የማንደርስበት መንገድ አይኖርም:: ካለንበትም ፈተና ለዘለቄታው መውጣት የምንችለው በመልካምነት ነው።ለዚህ ደግሞ እራሳችን ማዘጋጀት ይጠበቅብናል ።
ትንሳኤ አበራ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3/2013