ዘራፊነት ፣ ተንኮልና ዋሾነት የአሸባሪው ህወሓት መገለጫ ባህሪያት ናቸው። ያውም ከጥንስሱ ጀምሮ የተጠናወተው አብሮት ተወልዶ አድጎ ጥርሱን የነቀለበት። በግልጽ የሚፈጽማቸው እኩይ ድርጊቶቹ ለዚህም ምስክሮች ናቸው። ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውሉ የዕለት ደራሽ ድጋፎች መዝረፉ የቆየበት እኩይ ተግባሩ ነው። ገና በረሃ ሳለ የጀመረው ከ40 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የክፋት ጥግ ማሳያ። በተለይ በ1977 ዓ.ም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተከሰተውን ረሃብ ምክንያት በማድረግ ለተጎጂዎች የሚደረገው ድጋፍ በመዝረፍ የዘረፈውን የእርዳታ እህል የጦር መሳሪያ እስከመግዛት መድረሱ በወቅቱ የቢቢሲ የአፍሪካ ዴስክ ኤዲተር የነበረው ማርቲን ፕላውት አጋልጦ እንደነበር የሚታወስ ነው።
የአሁኑ የህወሓት ቀንደኛ ደጋፊ ማርቲን በወቅቱ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ተጎጂዎች ከምዕራባያዊ ከተላከው 100 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 5 ሚሊዮን ዶላሩን በወቅቱ የነበሩት የህወሓት አመራሮች ለጦር መሳሪያ ግዥ መጠቀማቸውን ያጋለጠ ዘገባ ሠርቶ ነበር ።በዚህም የተነሳ አብዛኛው የእርዳታ እህል ለተፈለገለት አላማ አለመድረሱን አጋልጧል።
ለጭካኔው ልክና ድንበር የለሹ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወገኖቹን ለሞት አሳልፎ የመስጠት ተግባር ከጫካ ይዞት የመጣውን የአውሬነት ባህሪይ ነው። ፍጹም ሰብዓዊነት ብሎ ነገር የማይገባው ደንቆሮ ለመሆኑ ነጋሪ አይሻውም ። አውሬ ያገኘውን ነጥቆ ከመብላት በስተቀር ወገኖቼ በረሃብ እያለቁ ነው ብሎ የሚስብበት አእምሮ አልተሰጠውም። አሸባሪው ባህሪው የአውሬ ነውና በወገኖቹ ላይ ፈጽሞ ማሰቢያ ህሊና ተነፍጓታል። ለትግል ጫካ ገባሁለት የሚለው የትግራይ ህዝብ በረሃብ አለንጋ እየተገረፈ እንኳን ለሰብዓዊ እርዳታ የሚሆን የዕለት ጎርሱን ከህዝቡ አፍ ነጥቆ የሚበላ አውሬ መሆኑን በይፋ አስመስክሯል ።
ለውጥ ብሎ ነገር የማይገባው በአረጀና በአፈጀ አስተሳሰብ ወደ ኋላ የሚጎተተው አሸባሪ ቡድን ዛሬም ያው የትናንቱ ነው። እንዲያው ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉት ሆኖ ብሶበት ወደ ጥልቁ መቀመቅ በፍጥነት እያስገመገመ ይገኛል። ግን መቼም ቢሆን አላማ አድርጎት የተነሳውን ሀገርና ህዝብ የማጥፋት ሴራ ከግብ ለማድረስ ፍጥነቱን ጨምሯል። የተለያዩ ለጆሮ ቀፋፊ የሆኑ አስቀያሚ ድርጊቶች መፈጸም ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል። ‹‹ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ›› እንዲሉት ሆኖ ዛሬም በድጋሚ የዘራፊነት አመሉ አገርሽቶበት ይህንኑ ድርጊት ሲፈጽም አይተናል። የጭካኔ ድርጊት ፈጽሞ የሰው ባህርይ የሌለው አረመኔያዊ የአውሬነት ባህርን የተላበሰ መሆኑ በአማራና በአፋር ክልል የፈጸማቸው ጥቁር ጣበሳን የጠሉ አሰቃቂና ዘግናኛ የዘረፊነት ድርጊቶቹ በታሪክ የማይረሱ ሆነው ተመዝግበዋል ።
ጠብ ጫሪነቱን በመከላከያ ሠራዊት ላይ በፈጸመው ደባ ይፋ ካደረገ በኋላ መንግሥት ህግ ለማስከበር በወሰደው እርምጃ ክንፉን ቢመታም የተረፉት ጥቂት ርዝራዦች ዛሬም እንቅፍት መሆናቸው አልቀረም። መንግሥት ለትግራይ ህዝብ የጥሞና ጊዜን ለመስጠት ክልሉን ለቆ በመውጣቱ አጋጣሚ ለመጠቀም ተፍጨርጭሯል። መቼም ፕሮፖጋንዳ የዕለት እንጀራው በመሆኑ ከመነሻ እስከመጨረሻ ድረስ ማለቂያ የለሽ ውሸት እየደረደረ ቋቅ እስኪለን ሲግተን ኖሯል ።
መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ለክልሉ እንዳይደረስ እያደረገ ነው ። የትግራይ ህዝብ በረሃብ ሊያልቅ ነው እያለ ሲከሰስ ቆይቷል። የእርዳታ እህል ወደ ክልሉ እንዳይገባ መሠረት ልማቶችን በማወደም መግቢያ መስመሮች እየዘጋ በአፋር በኩል ደግሞ ወደ ክልሉ ሲጓጓዝ የነበረው የእርዳታ እህል እንዳይገባ ሲያደርግም መቆየቱ የሚታወስ ነው።በቅርቡም የሚደርሱ የእርዳታ እህል ጭነው ትግራይ ክልል የገቡ መኪናዎችን እዛው በማስቀረት ለጦርነት እየተጠቀመበት ይገኛል። ከሃዲው የጥፋት ቡድን ድሮም ቢሆን ለህዝቡ አስቦ የማያወቅ መሆኑ ህዝብ እንዲራብ በማድረግ ሆን ብሎ ህዝቡን ለመጉዳት መነሳቱ በድጋሚ በአፍንጫችን ሥር በፈጸመው አሳፋሪ ተግባር አሳይቷል።
አሸባሪው በመንበር ስልጣን በነበረበት ወቅት እንኳን ከተረጂነት ያልተላቀቀውን ህዝብ በድጋሜ በግፉ አለንጋ እየገረፈው ይገኛል። ድሮም በሴፍቲኔት ድጋፍ ውስጥ የቆየው በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠር የትግራይ ህዝብ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉት ሆኖ ጦርነቱ በርካቶች ለችግር እየዳረገ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ታዲያ ከወገኖቹ አፍ የሰብዓዊ እርዳታ እየነጠቀ መብላት የለመደው አሸባሪ ፊቱን ወደ አማራና አፋር በመመለስ በለኮሰው እሳትም የብዙዎች ሆድ ባዶ ያስቀረ ተግባር መፈጸሙን ቀጥሏል።
ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው እንደሚባለው ሆኖ በአፋር ክልል ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውለውን እህል የተከማቸ በመጋዘን ማቃጠሉን በሰማን ማግስት ውሎ ሳያደር በአማራ ክልል የግለሰቦች ንብረት ከመዝረፍ ባሻገር ለሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ የሚውል የእህል መጋዘን በመዝረፍ አሳፋሪ ተግባሩን ደገመው። አልመች ብሎት እንጂ አላማውስ እስከአራት ኪሎ ያለውን ጉዞ ለመጀመር ያለመ ነበር።
አሸባሪ ለህዝቡ የተላከው የሰብዓዊ እርዳታ መዝረፉን ከኢትዮጵያ ከፍ አድርጎ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ላይ እጁን አሳረፈ ። ባለፉት ሳምንታት የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (USAID) የሆኑ የእርዳታ መጋዘኖችን መዝረፋቸው እውን ሆነ። የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተልዕኮ ዳይሬክተር ሾን ጆንስ እንደተናገሩት የህወሓት አማጺያን በደረሱባቸው ስፍራዎች የሚገኙ የእርዳታ መጋዘኖችን ዘርፈዋል እና የታጠቁ ሰዎች ከዜጎች ምግብ ሰርቀዋል። ሾን ጆንስ ‹‹ ህወሓት በገባባቸውና ጦርነት በከፈተባቸው ሁሉም የአማራ አካባቢዎች መጋዘኖችን ዘርፏል፤አቃጥሏል፤ ተሽከርካሪዎችን ዘርፏል። ውድመት ፈፅሟል›› ሲሉ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።
አክለውም በተለይ የህወሓት ኃይሎች በገቡባቸው የአማራ ክልል አካበቢዎች በርካታ የእርዳታ መጋዘኖቻችን ስለመዝረፋቸው እና መጋዘኖቹ ባዶ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ አለ ማለታችው ሰምተናል።
አሸባሪው የምግብ ዕርዳታው የሚያስፈልገው በተለይ ተጎጂ ለሆኑ ሕፃናት፣ ነፍሰጡር እና ጡት ለሚያጠቡ እናቶች መሆናቸው የጠፋው አይመስለኝም። እነዚህ ዜጎች ህይወት ላይ ሞት ፈርዶ እኔ ልኑር ማለት ምን የሚሉት እብደት ይሆን? ይህ ድርጊት በዚሁ መዘዘኛ ጠብጫሪ እኩይ ተግባር ከቦታዎች የተፈናቀሉ ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ተፈናቃይ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት ለማስተጓጎል ያለመ ነው። ነገሩ አዲስ ባይሆንም ቡድኑ መጨረሻው ሲደርስ ህልውና አደጋ ውስጥ ሲገባ ህይወቱን ለማቆየት እንደ አበደች ውሻ ሁሉንም በመልከፍ ተስፋ መቁረጡን ማሳያ ነው።
ኢትዮጵያ ለማፍረስ ቀን ከለሊት በሚያወጠነጥነው ተንኮል ፣ ሴራና እኩይ ተግባሩ ተወዳዳሪ የለሹ አሸባሪው ህወሐት በዘመን ስልጣን ላይ ያለውን ታሪኩን እንኳን ብንመለከተ ይህኑን የዘራፊነት ሴራ አጎልቶ የሚያሳየን ነው። ሀገር እንደሀገር እንደትቀጥል በፍጹም አይሻምና ዙሪያ ገባውን፤ ዳር ድንበሩን በማካለል የሀገሪቱን ሀብት ሙጥጥ አድርጎ ለብቻው ሲዘርፍና ሲያግበሰብሽ እንደኖረ ሁላችንም የምንዘነጋው ተግባር አይደለም።
ይህንን ለሰሚ ግራ የሚገባ የእናት ጡት ነካሽ አሸባሪ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ግብዓተ መሬቱን ለመፈጸም ኢትዮጵያውያን ከየአቅጣጫው በአንድነት መንፈስ ተነስተዋል። ሁሉም ኢትዮጵያውያን ይህንን ነቀርሳ ነቅሎ ለመጣል በሚደረግ ጥረት የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት። አበቃሁ።
ትንሳኤ አበራ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2013