ለዴሞክራቲክ ኮንጎ ነጻነት ከተዋደቁት የኮንጎ ተወላጆች መካከል ፓትሪስ ሄመሬ ሉሙምባ አንዱ እና ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው ፡፡ ፓትሪስ ሉሙምባ እ.ኤ.አ ጁላይ 1925 በኦላንጎ መንደር በቀድሞው መጠሪያው የቤልጅያን ኮንጎ በአሁኗ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ተወለደ፡፡ ፓትሪስ ሊሙምባ በተወለደባት መንደሩ በኦላንጎ በሚገኘው የፕሮቴስታንት ሚሽነሪ ትምህርቱን ተከታትሎ ጨረሰ፡፡ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ሉሙምባ በፖስታ ቤት ተቀጥሮ መስራት ጀመረ ፡፡ እ.ኤ.አ 1955 በኮንጎ የአንድ ክልል የኮንጎ የንግድ ህብረት የሰራተኞች ፕሬዝዳንት ሆኖ ተመረጠ ፡፡
እ.ኤ.አ በ1958 ሉሙምባ ቤኮንጎ ብሄራዊ ንቅናቄ (Movement National Congolais ; MNC) ተቀላቀለ፡፡ በዚህ ወቅት ሉሙምባ «ታሪክ የሚናገርበት ቀን ይመጣል … አፍሪካ የራሷን ታሪክ ትጽፋለች፤ ያም የማዕረግና የጀግንነት ታሪክ ይሆናል ! » ሲል በተደጋገሚ ይሰማ ነበር፡፡
የቤልጅየም ቅኝ ተገዢ የሆነችው ኮንጎ እ.ኤ.አ በሰኔ 30 ቀን 1960 ነጻነቷን ተቀዳጀች፡፡ በድል ማግስት የፓትሪስ ሉሙምባ ፓርቲም በሃገሪቱ የተካሄደውን የምርጫ አሸነፈ፡፡ የኮንጎዎች አብሪ ኮከብ እና በኮንጎዎች ታሪክ ከልብ የማይጠፋው ፓትሪስ ሉሙምባ የመጀመሪያው ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለመሆን ቻለ ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቤልጅየም በቅኝ ግዛት ወቅት በኮንጎዎች ላይ ያደረሰችው እልቂት እና ሰቆቃ ከመጤፍ ባለመቁጠር ቤልጅየም ኮንጎን በቅኝ ግዛት በያዘችባቸው አመታት ለኮንጎ አስደማሚ ልማት አልምተናል ሲሉ የቤልጅየሙ ንጉስ ባዶዊን ተናገሩ፡፡
በዚህ የንጉሱ ንግግር ደሙ የፈላው ታጋይ ፓትሪስ ሉሙምባ የቤልጅየሙን ንጉስ አቁሳይ የመርዝ ንግግር በመቃወም ‹‹… ምንም እንኳን ዛሬ የኮንጎ ነጻነት ቀንን በእኩልነት ከስተካከልናት ወዳጅ ሀገር ቤልጅየም ጋር አብረን ብናከብርም ማንኛውም ኮንጎሊዝ ለዚህ ድል የበቃው ለአመታት በጽናት ታግሎ በጦርነት ደሙን አፍሶ መሆኑን መቼም የሚረሳ አይደለም ፡፡ ትግሉን በምናደርግበት ወቅት በምግብ ዕጦትም ሆነ በእንግልት ተሸንፈን የተውነው ጦርነት አልነበረም፡፡ በዚህም ነጻነታችን ማረጋገጥ ችለናል ፡፡ ስለሆነም እጅጉን እንኮራለን ፡፡ ይህ የሚደነቅና ተገቢ ትግል በግዴታ ለተጫነብን አሳፋሪ ባርነት ማብቃት አስፈላጊም ነበር፡፡›› ሲል ተናገረ ፡፡
ይህን የሰሙ የአሜሪካ እና የጥቅም ሸሪኮቿ በሉሙምባ ጠንካራ ንግግር ተደናገጡ ፡፡ ተናደዱም ፡፡ ምዕራባዊንም በበላይነት በሚያሽከረክሯቸው ጋዜጠኞችም የሉሙምባን ንግግር እንደሃጢያት በመቁጠር አስተጋቡት ፡፡
ቤልጅየምበቅኝ ግዛት ወቅት በኮንጎ ህዝብ ላይ ያደረገችው አረመኔያዊ ተግባር ይቅር በሉኝ ማለት ሲገባት ይባሱኑ ለኮንጎሊሶች የነጻነት ፣ እኩልነት ፣ እድገት ፣ ተስፋ ብርሃን የፈነጠቅን መሪያቸው ፓትሪስ ሉምባ ላይ ጥርሷን ነከሰች፡፡ አሜሪካም ከኮንጎ በገፍ ስትዘርፍ የነበረው የዩራንየም ፣የአልማዝ እና የመዳብ ማዕድን ጥቅሟ እንደሚቋረጥ ስለገባት ሉሙምባን ለማጥፋት በመርዝ የተለወሰ መጥመድ በሲአይኤ በኩል አጠመደች ፡፡
በሉሙባ አቋም ስጋት የገባቸው አሜሪካ እና ቤልጅየም በስውር በፈጠሩት ሸፍጥ እ.ኤ.አ በ1960 በኮንጎ የወታደሮች ዓመፅ ተቀሰቀሰ፡፡ ከአመጹ በስተጀርባው የቤልጅየም እጅ እንዳለበት ከሉሙምባ አዕምሮ የተሰወረ አልነበረም፡፡ የኮንጎ ቀውስ እየተባባሰ ሲመጣ ሉሙምባ የካታንጋና የደቡብ ካሳይ ተገንጣዮችን ለመቋቋም የሚያስችለውን እርዳታ ከአሜሪካና ከተባበሩት መንግሥታት ጠየቀ፡፡ ሉሙምባ ኮንጎን አንድ ለማድረግ ብዙ ቢጥርም ሰሚ አላገኘም፡፡ መልስ የተነፈገው ሉሙምባ ፊቱን ወደ ሶቭየት ኅብረት አዞረ፡፡ ወቅቱ ቀዝቃዛው ጦርነት የተፋፋመበት ስለ ነበር አሜሪካ በዓይነ ቁራኛ ትከታተለው ጀመር፡፡
በተቀጣጠለው የኮንጎ አመፅ ሰበብ ቤልጅየም ‹የዜጎቼን ደኅንነት ያሳስበኛል› በማለት ስድስት ሺሕ የሚሆኑ ወታደሮቿን ወደ ኮንጎ ‹‹ካታንጋ›› ላከች፡፡ ሉምባም የቤልጅየምን ተንኮል ለአለም ህዝብ አሳወቀ፡፡ ነገር ግን ከራሳቸው ጥቅም ውጭ ማንም ምንም ቢሆን የማያስጨንቃቸው አሜሪካ እና ጭራቸውን እየቆሉ የሚከተሏት አውሮፓዊያን ኮንጎ በቤልጅየም እጅ እየደማች እና ለመሞት እያጣጣረች እያዩ እንዳላዩ ሆኑ ፡፡ ምዕራባዊያን በሚያደርጉት ጫና ምክንያት በኮንጎ የተቀሰቀሰው ወታደራዊ አመፅ ተባባሰ ፡፡ ይህን ተከትሎ የኮንጎ ሰዎች በአውሮፓውያኑ ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀመሩ፡፡
የሉሙምባ አማሟት
በምዕራባዊያን የሚደገፈው ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ የሚመራው የመፈንቅለ መንግሥት ሉሙምባ በመኖሪያ ቤቱ እንዳለ እንዲገድ አደረገ፡፡ ሉሙምባም ለሃገሬ በማለቱ በምዕራባዊያን ሴራ በመፈንቅለ መንግስት ተይዞ ታሰረ፡፡ ሶቭየት ኅብረት ሉሙምባ እንዲፈታ ስትል ለተባበሩት መንግሥታት አሳወቀች፡፡ የተባበሩት መንግስታት ደርጅት የማን ሆነእና ነው የሶቤት ህብረትን ጥያቄ የሚመልሰው ፤ የማይታሰብ ነው ፡፡
የሥልጣን ጥመኛው ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ ግን “ሉሙምባ ለኮንጎ ሕዝብ ዕልቂት ጥፋተኛ ነው” በሚል ፈረጀው፡፡ በዚያው በተያዘበት ቀን ምሽት ሉሙምባ ወደ ካታንጋ ሊረሸን ተወሰደ፡፡እንደ እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 17, 1961 ላይመለስ ኮንጎን ወደፊት የመሻገር ህልሙን እንደያዘ በክፋት ጥርሶች ተበላ ፡፡
ሉዶ ዴ ዊቴ የተባለው የሥነ ማኅበረሰብ ምሁሩ (The Assasination of Lumumba) በሚል በአሳተመው የምርምራ ፅሁፍ ሉሙምባ፣ በገዳይ ቡድኖች ወደ ካታንጋ ጫካዎች ተወስዶ መረሸኑን አመላክቷል፡፡ የስነ ማህበረሰብ ምሁሩን ጨምሮ እንዳመለካተውም ስለ ፓትሪስ ሉሙምባ ግድያ ምንጭና ፍንጭ እንዳይገኝ በሚል የገዳዩ ቡድን መሪ የሆነው ጌራልድ ሶቴ ከወንድሙ ጋር በመሆን የሉሙምባን አስክሬን ከተቀበረበት በማውጣት ሰውነቱን በሳለ መጋዝ ቆራረጧል፡፡ ጭካኔው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በድኑን በሰልፈሪክ አሲድ አሟምቷል ፡፡ ጌራልድ ሶቴ የገደላቸውን ሰዎች አካል በናሙናነት የማስቀረት ልማድ ስለነበረው ከሉሙምባ አካል ጥርሱንና ጣቱን መውሰዱን በምርመራው ተረጋጧል፡፡
በዚህ የግድያ ዕቅድ ውስጥ የአሜሪካ እጅ (ሲ.አይ.ኤ) እንዳለበት የሲ.አይ.ኤው ዳይሬክተር አለን ዱልስ‹‹ሉሙምባ ትልቅ ሥልጣን ከጨበጠ የተመሰቃቀለ ነገር መምጣቱ የማይቀር ነው›› በማለት የሉሙምባ መገደል አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው እንደነበር በጥናቱ ሉዶ ዴ ዊቴ አመላክቷል ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንድ ወቅት የገዳዩ ገራልድ ሶቴ ልጅ ጎደሊቭ ሶቴ ለ ‘ሁሞ’ መጽሔት አባላት አባቷ ከሉሙምባ ያስቀረው አካል እንዳለ አሳይታ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ቤልጅየም የሉሙምባ ቤተሰቦችን የዘገየ ይቅርታ ጠየቀች፡፡ አሜሪካ ግን እስካሁን በሉሙምባ መሞት የረካች አትመስልም ፡፡
እዚህ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊገነዘበው የሚገባው ነገር አሜሪካ እና የጥቅም ሸሪኮቿ አንድም ቀን ሰብዓዊነት የሚባለው ነገር አሳስቧቸው እንደማያውቅ ነው ፡፡ ስለሆነም አሁን ላይ በትህነግ አማካኝነት በሃገራችን የተፈጠረው ቀውስ አሜሪካ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እጅ እንዳለበት በማሰብ የተደገሰልንን የጥፋት ድግስ ለመቀልበስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እጅ ለእጅ በመያያዝ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊተባበር ይገባል መልዕክቴ ነው ፡፡
አሸብር ኃይሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/2013