በ1967 ዓ.ም መጨረሻ በበታችነት ስሜት ደደቢት በረሃ የወረደው አሸባሪው የህወሓት ቡድን፤ ደርግ ማለት አማራ ነው፤ አማራን ማጥፋት ደርግን ማጥፋት ነው የሚል አጀንዳ በግልጽ ይዞ በትጥቅ ትግል ሲንቀሳቀስ ነበር። የኢትዮጵያን ህዝብ እንደሰም አቅልጦ እንደብረት ቀጥቅጦ ለመግዛት እንቅፋት ይሆንብኛል ብሎ ያሰበውን የአማራ ህዝብን እንደህዝብ ጠላቴ ብሎ በፖለቲካ ርዮት ዓለሙ ቀርጾ ተነሳ።
ነገር ግን ይህ መሰሪ ቡድን 17 ዓመት የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ በነበረበት ወቅት “ጥሌ ከደርግ ጋር ነው” በሚል የአማራን ህዝብ እያሞኘ እና እያታለለ ህዝቡን ደጀን አድርጎ የደርግ ሰራዊት ሲመጣበት ከአማራ እናቶች ቀሚስ ስርና የዱቄት ማስቀመጫ እቃ ውስጥ እየተደበቀ በአማራ ትከሻ ለአራት ኪሎ ቤተመንግሥት ሊበቃ ችሏል።
ይህ አሸባሪ ቡድን የአማራን ህዝብ እያታለለ ስልጣን ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ ስልጣን ላይ በቆየበት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ “እንዳሻዬ አዛዥ ናዛዥ እንዳልሆን ያደርገኛል” በሚል ስጋት የአማራ ህዝብ ላይ ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና በደል ሲያበዛና አንገቱን ሲያስደፋ ከመኖሩ ባሻገር በሌሎች እህት ወንድም ህዝቦች እንደጠላት በጥርጣሬ አይን እንዲታይ ማድረጉን መናገር ለቀባሪ ማርዳት ነው።
ባለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብን ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ከሰሜን እስከ ደቡብ እንደሰም አቅልጦ እንደብረት ቀጥቅጦ የገዛው አሸባሪው ቡድን የበደልና የግፍ ጽዋ ሞልቶ መፍሰሱን ተከትሎ፤ ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ በከፈለው መራራ መስዋትነትና የህዝብ የቁርጥ ቀን ልጆች በሆኑት የለውጡ ኃይሎች አማካኝነት ከጠዋት እስከ ማታ ሳያስበው ስልጣኑን ሳይወድ በግድ እጁ ተቆልምሞ በተቀማ ማግስት የማፊያው ቡድን ተጠራርጎ መቀሌ ሊመሽግ ችሏል።
የኢትዮጵያ ካንሰር የሆነው ህወሓት ከቀን እስከ ማታ ሳያስበው ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት ተነቅሎ በመማጸኛ ከተማው መቀሌ መሽጎ ዳግም በትረ ስልጣኑን ለመቆጣጠር ሰይጣን የሚጸየፈውን ወንጀል በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ሲሰራ ከርሟል። ይህ ጁንታ ቡድን ይባስ ብሎ መንግሥት ለሰላም የዘረጋውን እጅ እንደሽንፈት በመቁጠር ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ከጀርባው ወጋ። ይህንን ተከትሎ መንግሥት ሳይወድ በግድ ላለፉት ስምንት ወራት በክልሉ ህግን የማስከበር ዘመቻ ውስጥ እንዲገባ አደረገ።
ነገር ግን ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበለትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ክልሉን ለቆ ወጥቷል። “ለውሻ ከሮጡለት፣ ለልጅ ከሳቁለት” እንደሚባለው መንግሥት ያለምንም ውጊያ ለትግራይ ህዝብ ሰላም ሲባል ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ አሸባሪው ህወሓት በእርሱ ኃይል የተገኘ ድል በማስመሰል መንግሥት ክልሉን ለቆ በወጣ ማግስት “ከአማራ ህዝብ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለን፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን” በሚል በተለይ ኢትዮጵያን የማፍረስ ራዕዩን ለማሳካት በአማራና በአፋር ክልል የለየለት ወረራና ዘረፋ ውስጥ ገብቷል።
ይህ አሸባሪ ቡድን በአፋር ክልል እያደረሰ ያለው ፖለቲካዊ፣ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ግፎች እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይ በአማራ ክልል እያደረሰ ያለውን ዘረፋ ብናይ ከሰሜን ወሎ ጀምሮ እስከ ደቡብ ጎንደር ባካሄደው ወረራ በአላማጣ፣ በቆቦ፣ በወልድያ፣ በመርሳ፣ በላልይበላ፣ በንፋስ መውጫና በጋይንት ከተሞች የሚገኙ ሆስፒታሎችን ሙሉ ለሙሉ ዘርፏል። እንዲሁም ከሰሜን ወሎ ጀምሮ እስከ ደቡብ ጎንደር በሚገኙ የወረዳ ከተማ እና ትንንሽ የገጠር ከተሞች የሚገኙ ጤና ጣቢያዎችና የጤና ኬላዎችን በተመሳሳይ ዘርፎ ወደ ትግራይ ክልል እየጫነ ወስዷል።
እንዲሁም በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ጎንደር የሚገኙ ከ15 በላይ ወረዳዎች የሚገኙ የመሰናዶና የሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም የመጀመሪያ ደረጃና አጸደ ህጻናት ትምህርት ቤቶች ባሻገር ባንኮች፣ የቁጠባ ተቋማት፣ የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት በጥቅሉ የመንግሥት ተቋማት ቁራጭ ወረቀት ሳይቀር ተዘርፈው ወደ ትግራይ ተጭነዋል። በተመሳሳይ በዋግ ህምራ ዞንና በሰሜን ጎንደር አዳርቃይ፣ ጠለምት በመሳሰሉ ወረዳዎች ላይ መሰል ዝርፊያዎችን ፈጽሟል።
በሌላ በኩል በአማራ ክልል በወረራ በያዛቸው ከተሞች ላይ ህጻናትን በመድፈር፣ ወጣቶችን ይዘው “ለኛ ተዋጉ ሲሏቸው አንዋጋም” ያሉትን አደንዛዥ እጽ በመርፊ በመስጠት ጦር ሜዳ በማሰለፍ በወንድሞቻቸው እጅ እንዲሞቱ ከማድረግ ባሻገር በመርፌ እየመረዙ አያሌ ቁጥር ያላቸው የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶችን ገድለዋል። ጦርነቱ ተቋጨ እንኳን ቢባል ህብረተሰቡ በኢኮኖሚ እንዳያንሰራራ ለማድረግ ጁንታው የዘረፈውን ዘርፎ ወደ ትግራይ ከመውሰድ ባለፈ መውሰድ የማይችለውን በማቃጠል፣ አፋቸው የማይናገሩ ከብቶችን በመግደል ዓለም ላይ ታይቶ ተሰምቶ የማይታወቅ ዘረፋና ወረራ በአማራ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ይገኛል።
በአጠቃላይ ወራሪው የትህነግ ኃይል በአማራ ክልል በወረራ በያዛቸው ከተሞች ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ውድመት የፈጸመ ሲሆን፤ ለአብነት “መንግሥት ሰሜን ወሎን እንደገና ለመገንባት ከእንግዲህ በትንሹ 7 ዓመት ያስፈልጋል” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናግረዋል።
ይህ አሸባሪ ቡድን የአማራ ህዝብ ላይ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ በሁለንተናዊ ዘርፍ የለየለት ወረራ እየፈጸመ ይገኛል። ጁንታው ይህን ሁሉ መከራና ግፍ በአማራ ህዝብ ላይ እየፈጸመ፤ ነገር ግን በወረራ በተቆጣጠራቸው ከተሞች “እኛ ጥላችን ከብልጽግና መንግሥት ጋር እንጂ ከህዝብ ጋር አይደለም” በሚል በማር በተለወሰ መርዙ የአማራን ህዝብ ዛሬም እንደትናንቱ ለማሞኘት ሲዳዳ ይስተዋላል።
የአማራ ህዝብ ሆይ! ጁንታው የሚፈልገው የብልጽግና መንግሥት ከሆነ የአማራ ህዝብ የአብራኩ ክፋይ ለምን ልጆች ይደፍራል፤ ለምን መርዞስ ይገድላል? የህዝቡን መገልገያ ሆስፒታሎችና ትምህርት ቤቶች፣ ባንክ ቤቶችን ስለምን ከጥቅም ውጪ ያደርጋል? ስለዚህ ይህ የማፊያ ቡድን ከ12 ዓመት ህጻን እስከ 68 ዓመት አዛውንት አሰልፎ እየፈጸመ ያለውን ወረራ “እሾህን በሾህ እንዲሉ” መላው ህዝብ ከደቂቅ እስከሊቅ በነቂስ ወጥቶ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታሪካዊ ጠላቱን ድባቅ ሊመታ ይገባል።
አሁን ላይ ጁንታው በወገን ጦር ከፍተኛ ጉዳትና ምት እየደረሰበት በመሆኑ፤ በክልሉ በወረራ ተቆጣጥሯቸው ከነበረው የተለያዩ ከተሞች እግሬ አውጭኝ እያለ እየፈረጠጠ ይገኛል። ስለዚህ ህብረተሰቡ ጁንታው በወረራ ይዟቸው በነበሩ ከተሞች የዘረፈውን ንብረት ይዞ እንዳይወጣ በር በሩን በመጠበቅ የዘረፈውን ንብረት ካለማስጣል ባለፈ ለወሬ ነጋሪ እንዳይቀር አድርጎ ወደ ክልሉ የገባውን ወራሪ ቡድን ግብዓተ መሬቱን በአማራ ክልል መፈጸም አለበት።
በሌላ በኩል የአማራና የአፋር ክልል ህዝቦች አጎራባች ሆነው ተገኝተው የችግሩ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ ሆኑ እንጂ ይህ ጁንታ ቡድን ለየትኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደማያንቀላፋ ባለፉት 27 ዓመታት ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት አሳይቷል። ስለዚህ ቡድኑ እንደለመደው መላ የኢትዮጵያ ህዝብን አንገት ለማስደፋት፣ ለመውረርና ለመዝረፍ የአማራና የአፋርን ህዝብ ቀድሞ የማዳከም ሥራ እየሰራ መሆኑን ሁሉም ክልሎችና ብሄር ብሄረሰቦች በውል ተገንዝበው፤ እኚህን “የእፉኚት ልጆች” በተባበረ ክንድ ታሪክ ማድረግ ካልተቻለ የትኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ እና አካባቢ ሰላምና ደህንነት መቼም አይረጋገጥም።
ከራማአ ማዶ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22/2013