በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሰሞኑን ብስጭት የተጫነው መግለጫ አውጥቷል። የብስጭቱ ምክንያት እነሱ እንደሚሉት ከሆነ ስማቸው ያለ አግባብ በመጥፋቱ ነው። እኔ እንደሚመስለኝ ከሆነ ግን በድብቅ የሚሰሩት አደባባይ ስለተገለጠባቸው ነው የጨረሱት።
ችግሩ ስትናደድ ደግሞ ሌላ ሚስጥር ታሾልካለህ። ”እኛ እርዳታ የሰጠነው ለተረጂዎች እንጂ ለተዋጊዎች አይደለም። ምናልባት ተዋጊዎች ከተረጂዎች ዘርፈው ይሆናል” የሚል ነገር ጽፈዋል። ያው ህወሓት ሰርቆ ነው ለማለት ነው በዘወርዋራው። ራሳቸውን ነጻ ለማድረግ ሲሞክሩ አጋራቸውን ሌባ ብለውት አረፉት። ሳይወዱ በግድ እውነቱን አውጡት ማለትም አይደለም። በእርግጥ ይህ ሚስጥር ነው ለማለት ይከብዳል። ምክንያቱም ህወሓት የእርዳታ እህል እንደምትሰርቅ እና እንደምትሸጥ 1977 ምስክር ነው። ሰዎቹ መስረቅ እና መሸጥ ዋነኛ ተሰጥኦአቸው ነው።
አሜሪካኖቹ ግን ደግሞ ጁንታውን ብቻ አይደለም ያዋረዱት፤ ራሳቸውንም ነው። በመግለጫቸው መጨረሻ ላይ በአሁኑ ወቅት “ከኢትዮጵያ ህዝብ 7 በመቶ የሚሆነውን የምንቀልበው እኛ ነን” በማለት እስከ ዛሬ በዲፕሎማቲክ ቋንቋ ሲያሽሞነሙኑት የከረሙትን ግብዝነት ፍንትው አድርገው አውጥተውታል ። እርግጥ ሰዎቹ ድሮም ቢሆን በግብዝነት አይታሙም። ልዩነቱ በፊት እንዲህ ግብዝ ሲሆኑ እሺ እያለ የሚያጎነብስላቸው አመራር ነበር። አሁን ያ የለም። ለዚያም ነው ብስጭታቸው።
ድሮ ለ7 ፐርሰንቱ ስንዴ ስለምንሰፍር ለ93 ፐርሰንቱ ፖሊሲ እናውጣ ሲሉ እሺ ይባሉ ነበር። አሁን ደግሞ አርፋችሁ የምትሰጡትን ስጡ አልያም 93 ፐርሰንቱ ሰባት ፐርሰንቱን መቀለብ ይችላል ስለዚህ መሄድ ትችላላችሁ እየተባሉ ነው። ይህን መልስ አልጠበቁትም ነበር። ስለዚህም እንዴት እንዲህ እንባላለን ፤ እንዴትስ ስማችን በክፉ ይነሳል ፤ ሁሌም መደነቅ ብቻ ነው ያለብን ብለው ተናድደዋል።
ለማንኛውም አሜሪካውያኑን እንዲህ ያበሳጫቸው ነገር ምንድን ነው? ያልን እንደሆነ ሰሞኑን አንድ የተማረከ የአሸባሪው ህወሓት ኮሎኔል ይዞት የተገኘው ምግብ ጉዳይ ነው። ምግቡ የጦር ሜዳ ስንቅ አይደለም። የአዘቦት ምግብም አይደለም። የእርዳታ ምግብ ነው። የእርዳታ ምግብነቱ ለተረጂዎች እንጂ ለተዋጊዎች አይደለም። ነገር ግን የአማራ እና የአፋር ህዝብን በወረረ አሸባሪ እጅ ተገኘ። እንዴት?
እሱማ ግልጽ ነው። ያው የአደባባይ ሚስጥር ስለሆነ መናገር አያስፈልገውም። አስገራሚው ነገር ግን ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? እስካሁን ማስገባት የምንፈልገውን ያህል እርዳታ ማስገባት አልቻልንም ብለው የሚያማርሩት ነገር ነው። አሰባችሁት የፈለጉትን ያህል ምግብ ማስገባት ቢችሉ..መላው የጁንታ ወታደር በሀይል ሰጪ ምግብ ጥጋብ እለቱን አዲስ አበባ ገብቼ ካላደርኩ ብሎ ሲንቀዠቀዥ የወገንን ጥይት ያባክንበት ነበር።
እርግጥ ነጮቹ ይህን ሀይል ሰጪ ምግብ ለሽብር ተኛው ለምን እንደሚያቀብሉ እንገነዘባለን። የመጀመሪያ እቅዳቸው መሳሪያ ማቀበል ነበር። ለሱም አንዴ በአየር እንወርውር ፤ ሌላ ጊዜ ከሌላ ሀገር ቀጥታ እንብረር ፤እሱ አልሆን ሲል የሱዳን ኮሪደር ይከፈትልን ፤ እሱም አልሆን ሲል ሌላ አዳዲስ ዘዴ እየፈለጉ ጥረዋል። ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ከታሪክ ተምሯልና አልሰማችሁም አላቸው።
ስለዚህ ያላቸው መፍትሄ የጁንታውን ወታደር ሀይል ሰጪ ምግብ እየሰጡ እና ራሱ ደግሞ ሀሺሽ ሲጨምርበት ቆመው እየተመለከቱ ሰውን ወደ መሰሪነት መቀየር ነበር። በእርዳታ ምግብ ሆዳቸው ያበጠ ፤ በሀሺሽ ናላቸው የዞረ የህወሓት ተዋጊዎች ታዲያ በጨበጣ እየዘለሉ ወደ ግንባር ሲገቡ የተቀበላቸው የመከላከያ ጠመንጃ ነበር።
በመሠረቱ የእርዳታ እህል ሲዘጋጅ በደንብ ተቀምሞ ነው። ያው ሰዎች በጦርነት ጋር በተያያዘ ችግር ውስጥ ሲገቡ መፈናቀል ይከሰታል፤ ምግብ ለማምረትም ሆነ ለማዘጋጀት የሚሆን ሁኔታ አይገኝም፤ ይህ ሲሆን በምግብ እጥረት እንዳይጎዱ ተብሎ በተመጣጠነ መልኩ የሚሰራ ነው። በዋነኛነት በምግብ ዝግጅቱ ታሳቢ የሚደረጉት ደግሞ ህጻናት እና እናቶች ናቸው። እነዚህ ሰዎች በጦርነት ምክንያት በሚያጡት የተመጣጠነ ምግብ የተነሳ ብዙ ጉዳት እንደሚገጥማቸው ይታወቃል። በተለይም ህጻናት የመቀንጨር አደጋ ያጋጥማቸዋል ተብሎ ይታሰባል።
እና ታዲያ ይህ በተለይ ለህጻናት የተላከ እርዳታ እንዴት ጦርሜዳ መሀል ተገኘ ሦሰት መላምቶችን ማስቀመጥ እንችላለን ። የእርዳታ እህሉ ጦርሜዳ የተገኘው አንደኛ እነሱም እንደሚሉት እና ሁላችንም እንደምናውቀው ህወሓት እንደ ልማዱ ዘርፎት ነው። ሁለተኛ ጦር ሜዳው ላይ ህጻናት ስላሉ ነው፤ እሱንም በየቀኑ እያየን ነው። ሦስተኛ ደግሞ ጦር ሜዳ ያሉት ትልልቅ ሰዎችም የመቀንጨር ችግር ስላለባቸው ለማሰብ እንዲያግዛቸው ነው። ሦስቱም ያስኬዳል።
ሌላኛው አናዳጅ ነገር ደግሞ ምን መሰላችሁ፤ እንደዚህ የተመጣጠነ ሀይል ሰጪ ምግብ ቀልብ እየተሰፈረለት የተዋጋው ሀይል አማራ ክልል በየአርሶ አደሩ ቤት ገብቶ ሊጥ መስረቁ ነው። አመል እኮ ከባድ ነው። ለውጊያ ወጥቶ ሊጥ ፍለጋ በየአርሶ አደሩ ጓዳ መገኘት አስነዋሪ ነገር ነው። ግን የጁንታው ወታደር ከሆንክ ምንም ችግር የለውም። ምክንያቱም የምትዋጋው ለመብላት ብቻ ነዋ። ሌላ ከፍ ያለ አላማ የለህም። ግን ለምንድን ነው ህዝብ የእለት እንጀራ ለማግኘት ጦርነት ውስጥ የሚገባው? ምክንያቱም ህወሓት 30 ዓመት ሙሉ እንዴት መልክአ ምድሩን ተንከባክቦ አረንጓዴ እና ምርታማ ማድረግ እንደሚችል ሳይሆን እንዴት ምሽግ መቆፈር እንዳለበት ሲያስተምረው ነዋ የኖረው።
በነገራችሁ ላይ አሜሪካውያኑ ከሀገሪቱ ህዝብ 7 በመቶውን የምናበላው እኛው ነን ያሉበትን ፉከራ በደንብ አገላብጠን ስናየው ፤ከነሱ ግብዝነት ባለፈ ከሚመግቡት 7 በመቶ ህዝብ 5 በመቶ ገደማው ያለው አንድ ክልል ውስጥ ነው። ከዚህ አምስት በመቶ ህዝብ መሀከል ደግሞ አብዛኛው ላለፉት ሦሰት አሥርት ዓመታትም በሴፍቲኔት ፕሮግራም ውስጥ የታቀፈ እና በመንግሥት ቀለብ የሚሰፈርለት ህዝብ ነበር።
በሴፍቲኔት የሚኖር ህዝብ ጦርነት ውስጥ ገብቶ እንዲዋጋ የሚያደርገውን አካል ግን አሜሪካውያኑ ለመኮነን ድፍረት የላቸውም። ምክንያቱም እነሱ የሚፈልጉት በቋሚነት በነሱ ምጸዋት ታምኖ የሚኖር ህዝብ መፍጠር ነውና። ለዚያም ነው ህወሓትን ተቆጥቶ ጦርነቱ እንዲቆም እና ህዝብ ወደ እርሻው እንዲመለስ ከማድረግ ይልቅ ለምን ብዙ እርዳታ አላስገባንም ብለው እየተነጫነጩ ያሉት።
የሆነ ሆኖ አሁን አሜሪካውያኑ የያዙት ነገር እያነቡ እስክስታ ነው። ስማቸው በመጠራቱ እና ግብራቸው በመጋለጡ ቢናደዱም የሰፈሩት ቀለብ ያሰቡበበት ቦታ ደርሶ የአሸባሪ ቡድኑ ጠግቦ እየተዋጋላቸው ስለሆነ ደስ ብሏቸዋል። ችግሩ ቀለብ የሚሰፈርለት ነገር ግን የሚዋጋለት አላማ የሌለው ጦር በመጨረሻ መሸነፉ የማይቀር መሆኑ ነው። ለዚህ ደግሞ ከአሜሪካ የአፍጋኒስታን ተሞክሮ በላይ ጥሩ ማሳያ አይገኝም።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2013