ልጆች የቡሄ በዓልን እንዴት አከበራችሁት? ዛሬ ስለ ቡሄ በዓል ምንነት፣ ታሪካዊ አመጣጥና ባህላዊ ትውፊቱን በተመለከተ እንመለከታለን።
ልጆች ቡሄ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃላችሁ? የሙልሙል ዳቦ፣ የጅራፍ፣ የችቦ ትርጉም ምንድነው? ስንል ጥያቄ ያቀርብንላቸው ኤልሮኢ ኤሊያስ፤ እዮሲያስ ስሜነህ፤ እዮብ ስሜነህና፤ በእምነት ሱሌማን የተባሉ ጓደኛሞች በክረምት ከተማሩበት ሰንበት ትምህርት ቤት ያወቁትን እንዲህ አካፍለውናል።
ተማሪ ኤልሪኢ ቡሄ ማለት በራ፣ ብርሃን፣ ደማቅ ማለት ነው። ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት በዓል የሚዘከርበት እና ለበዓሉም ችቦ ስለሚበራ የብርሃን በዓል በማለት የቡሄ በዓል እንላለን። ወቅቱ የክረምት ጨለማ አልፎ የብርሃን ወቅት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት የመሸጋገሪያ ወቅት ነው። “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ። በሌላ በኩልም “ቡኮ / ሊጥ “ተቦክቶ ዳቦ የሚጋገርበት “ሙልሙል “ የሚታደልበት በዓል በመሆኑ ቡሄ እንደተባለ አባቶች ካሰተማሩት ላይ አካፍሎናል።
ተማሪ ኢዮሲያስ ስሜነህ ደግሞ የጅራፍ ትርጉም በኦርቶዶክስ ቤተከርሰቲያን አስተምህሮ ምን እንደሆነ ይነግረናል። በደብረ ታቦር በዓል የጌታችን መታየቱ፤ እንዲሁም የጅራፍን ድምጹን ስንሰማ የባህርይ አባቱን የአብን ይህ የምወደው ልጄ ነው በሚል የሰጠው ምስክርነት ቃል ከነጎድጓድ ድምጽ ጋር መጥቶ ስለነበር ያንን ያስታውሰናል ብሏል።
ተማሪ እዮብ ስሜነህ በበኩሉ ችቦ ለምን እንደሚለኮስ በሰንበት ጽምህርት በት ተነግሮናል ይለናል። ችቦ የጌታችንን ብርሃነ መለኮት መገለጥ የሚያመለክት ነው። በመሆኑም ችቦ ለኩሰን በዓሉን እናከብራለን። የቀኑን መምሸት ያልተረዱ እረኞች በሜዳ ቀርተዋልና ወላጆች ከመንደር ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ ሔደው የነበረበትን ታሪኩን እያዘከርን በዓሉን ችቦ በማብራት እናከብራለን ብሏል።
ሌላው በእምነት የተባለው ልጅ በችቦ ብርሃን ልጆቻቸውን ፍለጋ የወጡ ወላጆች ዳቦ ጋግረው ይዘውላቸው ወጥተዋል። ስጦታው ቤተሰባዊነትን፣ ፍቅርንና መተሳሰብን መግለጫ ነው። ወደ ቤታችን “ቡሄ ና፣ ቡሄ በሉ” እያሉ ለሚመጡ አዳጊዎችም ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጥ “ሙልሙል” ዳቦ እንዳለም ያስታውሳል።
ልጆች እንግዲህ እነ ተማሪ ኤልሪኢ እንደነገሩን የቡሄ በዓል ትውፊታዊ አካሄዱን ተከትሎ እንዲቀጥልና ባህሉ እንዳይበረዝ የራሳችሁን አስተዋፅኦ ማድረግ ይጠበቅባችኋል። እናንተም በዚህ ሳምንት ባሳለፍነው የቡሄ በዓል ላይ በአባቶች ቤት ተገኝታችሁ እየዘመራችሁ፣ “ውለዱ፣ ክበዱ፣ ሀብት አግኙ” በማለት እየመረቃችሁና እያመሰገናችሁ፣ እንዳሳለፋችሁት አምናለሁ። በሚቀጥለው ዓመትም የቡሄ በዓልን በዚህ አግባብ በማክበር ባህላዊ መስተጋብሩ እንዲቀጥል ማድረግ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል። ቸር ይግጠመን!
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሃሴ 16/2013