የኦሮሚያ ክልል ካለው የቆዳ ስፋትና አብዝቶ ከቸረው የተፈጥሮ ሀብትና ስነምህዳር አኳያ ከቀሪዎች ክልሎች የተሻለ የማዕድን ሀብት በዓይነትም በብዛትም እንዳለው ይነገራል። ክልሉ ባሉት ሃያ አንድ በሚሆኑ ዞኖቹ ውስጥ የከበሩና ከፊል የከበሩ እንዲሁም ለኢንዱስትሪና ለግንባታ ግብአትነት የሚውሉ በርካታ ማዕድናት እንዳሉትም ይገመታል።
ልክ እንደ ሌሎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የማዕድን ሀብትን በጥናት ለይቶ ጥቅም ላይ የማዋሉ ችግር በዚሁ ክልልም የሚታይ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገር አቀፍ ደረጃ እስከ ክልል ድረስ በማዕድን ዘርፉ በተሠሩ የለውጥ(ሪፎርም)ሥራዎች በርካታ ለውጦች መጥተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ክልሉ ከማዕድን ዘርፉ ለተገኘው ሀገር አቀፍ የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድረጉም በላይ በክልልሉ ከማዕድን ፍቃድ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ከእቅድ በላይ መፈፀም ችሏል።በተመሳሳይ ካቀደው በላይ ለብሄራዊ ባንክ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ አቅርቧል። በማዕድን ዘርፍ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠርም የድርሻውን ተወጥቷል።
በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ዞኖች መካከል አንዱ የሆነው ምሥራቅ ሸዋም በተመሳሳይ በሰፊ የማዕድን ሀብት ክምችቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ከከበሩ እስከ ለኢንዱስትሪና ኮንስትራክሽን ግብአትነት የሚውሉ የማዕድን ህብቶችን አቅፏል። ይሁን እንጂ ዞኑ ያሉትን ሰፊ የማዕድን ሀብቶች በከፊል እንጂ እስከአሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ እየተጠቀመ እንዳለሆነና ከዚሁ ከማዕድን ሀብቱ ጋር በተያያዘ አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ ከምሥራቅ ወለጋ ማዕድን ልማት ፅህፈት ቤትየተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።
አቶ ግርማ ምትኩ የምሥራቅ ወለጋ ማዕድን ልማት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ፅህፈት ቤቱ በዋናነት በዞኑ ያሉ ማዕድናትን የማጥናትና ክምችቱን የመለየት ብሎም የማልማትና የማስተዳደር ሥራዎችን ይሠራል። በዚህ ዓመት ፅህፈት ቤቱ 38 ኪሎሜትር ስኩዌር የሚሸፍን ማአድናትን ለማጥናት አቅዶ 45 ነጥብ 92 ኪሎሜትር ስኩዌር ያህሉን መሸፈን ችሏል። በዚሁ መሰረት በዞኑ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ክምችት በዘጠኝ ወረዳዎች ላይ እንደሚገኝ ተረጋግጧል። ሳንድ ስቶን ወይም በተለምዶ የአምቦ ድንጋይ ተብሎ የሚጠራው ማዕድን ክምችትም በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ እንዳለም ታውቋል።
አይረን ኦር የተባለው ማዕድንም በሁለት ወረዳዎች ላይ ክምችቱ እንዳለ ተለይቷል። ለኮንስትራክሽን ግበአትነት የሚውል የባዛልት/ጥቁር ድንጋይ/ ከምችት እንዳሉም ታውቋለ። ወርቅም በዞኑ በሦስት ወረዳዎች ላይ መኖሩ እንዲሁም ግሪቪል እና ግራናይት የሚባሉ ማዕድናት በዞኑ በስፋት እንደሚገኙም ተረጋግጧል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ በጥናት ከተለዩት ማዕድናት ውስጥ በአሁኑ ወቅት ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉት ውስጥ አንዱ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ሲሆን፣ በሌቃ ዱለቻ ወረዳ ላይ የጥናት ፍቃድ ወስደው አራት ባለሀብትች ማዕድኑን ወደ ሥራ አስገብተዋል። በዚህ ዓመት ወደ 10 ሺ ሜትሪክ ቶን ምርት ያመርታሉ ተብሎም ይጠበቃል። በሌላ በኩል ደግሞ ለኮንስትራክሽን ግብአትነት የሚውለው ባሳለት /ጥቁር ድንጋይ/ እና አሸዋ ማዕድናት በኢንተርፕራይዝ ደረጃ በብዛት ተመርተው ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ። በዚህ ዓመትም ወደ 4 ሺ 272 ሥራ አጦች በማህበር ተደራጅተው በእነዚህ ማዕድናት ላይ ሠርተው ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው።
ሌሎቹ ግራናይት፣ ሳንድስቶን፣ ገራቪልና ወርቅን የመሰሉ ማዕድናት በብዛት ወደ ሥራ ገብተው ጥቅም ላይ አልዋሉም። ለዚህም ማዕድናቱን ለማምርት የቴክኖሎጂ ማነስ፣ የካፒታል እጥረት እንዲሁም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር በዋና ምክንያትነት ይጠቀሳሉ። በተለይ ደግሞ ግራናይት፣ ሳንድስቶንና ገራቪል የተሰኙ ማአድናትን ለመጠቀም ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ በመሆኑ አስከአሁን ድረስ ማዕድናቱን አምርቶ መጠቀም አልተቻለም። አሁንም ገና የልተጠኑና ያልታወቁ በዞኑ ይኖራሉ ተብለው የሚገመቱ ማዕድናት ቢኖሩም በካፒታል ውስንነትና በላብራቶሪና ቴክኖሎጂ እጥረት እንዲሁም በሰው ሀብት ማነስ ምክንያት ማምረት አልተቻለም። ማአድናቱን አጥንቶ ለማምረት ባለሀብቶች ወደ አካባቢው የመምጣት ፍላጎት ማነስ ከፀጥታ ችግር ጋር ተዳምሮ የዞኑን የማዕድን ሀብት በሚገባው ልክ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም።
ከዚሁ የዞኑ ማዕድን ዘርፍ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍም በተለይ በዘርፉ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት ፅህፈት ቤቱ ባለው የሰው ኃይል ሥራዎች ለማከናወን ጥረት እያደረገ ይገኛል። በዚሁ የሰው ኃይልም ጥናቶችን ማካሄድ ተችሏል።
ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆንም የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም በጋራ እየሠራ ይገኛል። በዞን ደረጃ በባለሀብቶችም ሆነ በኢንተርፕራይዞች እነዚህ ማዕድናት ለምተው ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሠራም ይገኛል። በዞንና በወረዳ ደረጃ ያሉ ሥራ አስፈፃሚዎችም ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጡና ድጋፍ እንዲያደርጉም የተሠሩ ሥራዎች መከናወናቸውንም አቶ ግርማ አመልክተዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013