
ዓለም የጉልበተኞች የራስ ወዳዶችና ትምክህተኞች መፈንጫ የሆነች ያህል መስላ የታየችባቸውን የተለያዩ ዘመናትና ወቅቶችን አሳልፋለች። ይህንንም እውነታ ለመቀልበስ የከፈለችው ዋጋም በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ማለፉም የአደባባይ ሚስጥር ነው።
በተለያዩ ዘመናት በዓለማችን የተለያዩ ክፍሎች የተነሱ ግለሰቦች እና ቡድኖች በግልጽም ይሁን በስውር ላስቀመጧቸው በራስ ወዳድነት የታወሩ አደገኛ ዓላማዎች ስኬት ከሁሉም በላይ ንጹሀን ከፍ ያለ ዋጋ ከፍለዋል። እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ለእኩይ ዓላማዎቻቸው ስኬት በየዘመኑ አዳዲስ የፖለቲካ ትርክቶችን ፈጥረዋል።
ከዚህም ባለፈ ጽንፈኝ የተቃርኖ አስተሳሰቦችን በመፍጠር አለሙን በተለያዩ ተጻራሪ ጎራዎች በመክፈል ዓለማችን መረጋጋት እንድታጣ፣ የሰው ልጆች የእለት ተእለት ህይወት ሳይቀር ከፍ ያለ ስጋት ላይ እንዲወድቅና ዓለም ልትጠፋ ደረሰች የተባለላቸውን የፈተና ወቅቶች እንድታሳልፍ አድርገዋታል።
ይህ በአብዛኛው የጥቂት ቡድኖችንና የቡድኖቹን ፍላጎት መሰረት ያደረገው ጡንቻንና ከጡንቸኝነት የሚቀዳ የፖለቲካ አስተሳሰብ ከሁሉም በላይ የሶስተኛው ዓለም ሀገራትን፣ በተለይ ደግሞ የአፍሪካ አህጉር ህዝቦች የተረጋጋ ሕይወት እንዳይመሩ በየዘመኑ መልኩን እየቀያየረ ዋጋ እያስከፈላቸው ይገኛል።
እነዚህ ህዝቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቃርኖ የቆሙ ሀይሎች በሚያደርጉት ተጽዕኖ የማስፋት ግልጽና ስውር ሴራዎች ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሾች ናቸው። ይህም በየዘመኑ ራሳቸውን ሆነው ዕጣ ፈንታቸው ላይ እንዳይወስኑ በማድረግ ጥላ የሆነ ህይወት እንዲኖሩ እያስገደዳቸው ነው።
እነዚህ ህዝቦች ከቅኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ ራሳቸውን ለመሆኑ ያደረጓቸው መራራና እልህ አስጨራሽ ትግሎች ብዙ ዋጋ እንዲከፍሉ ቢያደርጋቸውም፣ በተቃርኖ የቆሙ ኃይሎች በሚያደርጉት ተጽዕኖ የማስፋት ግልጽና ስውር ሴራዎች ተገዥ በሆኑ ባንዳዎች ምክንያት በየዘመኑ የሚያደርጓቸው ትግሎች ትርጉም ያለው ራስን የመሆን የታሪክ ምዕራፍ ባለቤት ሊያደርጋቸው አልቻለም።
ከዛ ይልቅ የአህጉሪቱ ህዝቦች ባልፈለጓቸው የተንሰላሰሉ የእርስበርስ ግጭት ውስጥ ለመግባት ተገደዋል። በብዙ ድካምና ትግል የሚገነቧቸው የኢኮኖሚ አቅሞችም የህዝባቸውን ሕይወት ከመለወጥ ይልቅ ለጦርነቶች ፍጆታ የሚውሉበት ሁኔታ ጎልቶ ታይቷል። በላባቸው ያገኙት ሃብት ተመልሶ ሕይወታቸውን የሚቀጥፍና ተስፋቸውን የሚያመክን ሆኗል።
በብዙ የደከሙበት ሀብታቸው ለጦር መሳሪያ አምራቾችና ደላሎች ሲሳይ ከመሆን ባለፈ የሕዝባቸውን ህይወት ሲለውጥ አልታየም። እያንዳንዷ የመለወጥ ተስፋቸውም በብዙ ዓለም አቀፍ ሴራዎች ወደሚጨበጥ ተስፋ ሊቀየር አልቻለም። ከዚህ ይልቅ ከአንድ የግጭት ምዕራፍ ውደ ሌላ ምዕራፍ በሚደረግ ጉዞ መኳተን ዕጣቸው ሆኗል።
የሀገራችንም አሁነኛ እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ሕዝባችን ለዘመናት ከተጣበቀው ድህነትና ከዚህ ከሚመነጨው ጉስቁልና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ከፍሎ ለመሻገር በተነቃቃ ማንነትና እልህ ውስጥ ይገኛል። ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብም ይህንን እውነታ ለመገንዘብ የሚቸግረው አይደለም ።
ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ይህንን መነቃቃትና የመሻገር እልህ ፍሬ እንዲያፈራና እኛ ኢትዮጵያውያን መሆን የፈለግነውን እንድንሆን ከመርዳት ይልቅ ከመጣንበት የጥላ ሕይወት እንዳንወጣ በግልጽም ይሁን በስውር እየተገዳደረን ይገኛል። ይህ የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ያልተገባ አካሄድ አዲስ ባይሆንም፣ ሊፈጥር የሚችለው ሀገራዊ መንገጫገጭ ግን በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።
በተለይም አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ በመግባት እየሄዱበት ያለው ያልተገባ መንገድ ሰብአዊነትን፣ ዓለምአቀፍ ህጎችንና መርሆዎችን የሚጣረስ ፤ ጉልበትንና የኢኮኖሚ ኃያልነትን መሰረት ባደረገ ጫና ላይ የተመሰረተ መሆኑ ዓለም ከትናንት ስህተቱ ለማመር ፈቃደኝነት ማጣቱን የሚያመላክት ነው።
ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ሀገርን እንደ ሀገር እስከ ማፍረስ የሚያደርስ በማን አለብኝነትና በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አመለካከት በቀደሙት ዓመታት ዓለምን የቱን ያህል ከፍ ያለ ዋጋ እንዳስከፈለ ባለንበት ዘመን በ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዝ ምታ የ ድንጋይ ክምር የሆኑ ሀገ ራትን ማየት ብቻ በ ቂ ነው ።
ይህ በማን አለብኝነትና በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አስተሳሰብና ከዚህ የሚመነጨው ክፋት በዓለማችን የተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ የቱን ያህል ንጹሀንን ዋጋ እያስከፈለ እንደሆነም ለመረዳት በፍርሽራሽ ከተሞች እና በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ሀገራቸውንና ተስፋቸውን ተነጥቀው ሕይወታቸውን ለማቆየት የተገደዱ ንጹሀንን ማሰብ በቂና ከበቂ በላይ ነው።
በአጠቃላይ ጉልበትንና የኢኮኖሚ አቅምን በመጠቀም ሀገራት እና ህዝቦቻቸው እጣ ፈንታቸውን በራሳቸው እንዳይወስኑ ፤ በቀደመው ጥላ ሕይወታቸው እንዲቀጥሉ የሚደረገው ጫና ከቀደመው የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ የተቀዳ ሰብዓዊነት የጎደለው፤ በሚቻል ቋንቋ ሁሉ ሊወገዝ የሚገባ ዘመኑን የማይመጥን አስተሳሰብ ነው!
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013