እጀ ረጅሟ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት እየፈጸመች ያለችውን ሉአላዊነትን የሚዳፈር ተግባር ሳስበው ያ ግንኙነት ምን ነክቶት ነው ስል ራሴን እጠይቃለሁ። ሁኔታው ግንኙነቱን ‹‹ምንትስ በላው እንዴ›› በል በልም ይለኛል። እውነቴን ነው የምለው። ወይስ ያ ሁሉ ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከመሪዎቿ ጋር ነበር ስልም አስባለሁ።
የኢትዮጵያና አሜሪካ የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት የተጀመረው እ.አ.አ በ1903 ነው፤ ከአንድ ምአተ አመት በላይ ሆኖታል ማለት ነው። ግንኙነቱ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ብቻ አይደለም፤ ጠንካራም ነው።
አሜሪካ ኢትዮጵያን ስትራቴጂክ አጋር አርጋት ነው የቆየችው። ኢትዮጵያ መሰረቱን በሶማሊያ ያረገው የአልሸባብ ጉዳይ የራሷ ጉዳይ ቢሆንም፣ አሸባሪነትን መዋጋት ጥምረትን ይጠይቃልና በዚህ ላይ ከአሜሪካ ጋር በቅርበት ሰርታለች። በዚህም ለውጥ ማምጣት ተችሏል። አልሸባብ በምስራቅ አፍሪካ እንዳሻው ከመሆን የታቀበውም በእዚህ የጋራ ርብርብ መሆኑን አሜሪካም አትስተውም።
የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነቱም ጠንካራ የሚባል ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በዚህችው ሀገር ይኖራሉ። ከሀገራቸው ውጪ በሁለተኛ ደረጃ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሚኖሩት የት ነው ሲባልም በአሜሪካ ነው መልሱ።
በንግድ ግንኙነትም በኩልም ጥሩ ግንኙነት ያላቸው ሀገሮች ናቸው። አሜሪካ ከቀረጥ ነጻ ምርቶቻቸውን ወደ ሀገርዋ በአጎዋ በኩሉ እንዲያስገቡ ከፈቀደችላቸው የአፍሪካ ሀገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ኢትዮጵያ እአአ በ2017 ወደ ውጪ ለላከቻቸው ምርቶች ከቻይናና ሶማሊያ ቀጥሎ አሜሪካ ሶስተኛዋ መዳረሻ ሀገር ናት። በዚህም በዚሁ አመት ወደ አሜሪካ ከተላኩ ምርቶች 227 ነጥብ 3 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር አግኝታለች።
ይህ ግንኙነት ግን አሁን ንፋስ ገብቶበታል። ኧረ ከንፋስም በላይ ነው፣ አውሎ ንፋስ ሊባልም ይችላል። ምክንያቱ ደግሞ ግልጽና ግልጽ ነው። አሜሪካ በሀገር ክህደት ወንጀል እና በአሸባሪነት ለተፈረጀው አሸባሪው ህወሓት እያደረገች ያለችው ድጋፍ ግንኙነቱን ከንፋስም በላይ ነፋስ እንዲገባው አርጎታል። አሜሪካ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲሁም ቁልፍ አጋሬ የምትላትን የግብጽን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላት ፍላጎትም ሌሎች ግንኙነቱን በእጅጉ ንፋስ እንዲገባው ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው ።
በግብጽ ጥያቄ አሜሪካ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚካሄደው ድርድር ከታዛቢነት አልፋ ካላደራደርኩ ማለቷ ይታወሳል። ለግብጽ ያላትን ቅርበት በሚገባ የምታውቀው ኢትዮጵያ ይህማ እንዴት ታስቦ ብትላት ኢትዮጵያን የምትጎዳባቸውን መንገዶች ሁሉ እየፈለገች ነው።
አሜሪካ ጨርቋን የጣለችው ይሄኔም ይመስለኛል። ሽምግልና ማደራደር ንጽህናን ይጠይቃል፤ አሜሪካ ለዚያ ድርድር አደራዳሪነት አይደለም ታዛቢነትም ብቁ አይደለችም። አሜሪካ ዞር ይልባት የጀመረው ያኔ ይመስለኛል። ከአጋሮቿ ከአውሮፓ መንግስታት የኢትዮጵያ ጠላቶች ከሆኑ ጎረቤት ሀገሮች ጋር የማትሸርበው ሴራ የለም።
የሚያዋጣው ኢትዮጵያ ውስጥ ተላላኪ መንግስት መመስረት መሆኑን በማሰብም ይህን ለማስፈጸም ያንንም ያንንም ድንጋይ ስትፈነቅል ቆየች። ለእዚህ ደግሞ አሸባሪውን ትህነግ ከእነ ቆሻሻው ተቀብላ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን እያንገፈገፋቸው እንዲቀበሉት እያሴረች ትገኛለች። ወርዳ ወርዳ ከአሸባሪ ጋር ተቀመጠች። አሸባሪው ህወሓት ከመቃብር አፋፋ ተነስቶ እየተንፈራገጠ ያለው አሜሪካና አጋሮቿ ምእራባውያን እፍ ባሉለት ትንፋሽ መሆኑ ይታወቃል።
ይህ ሁሉ ድርጊትዋ በአንድ ሀገር ሉአላዊ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው። ኢትዮጵያውያን ግን በኢትዮጵያ ጉዳይ ተካይ ነቃይ መሆን አትችይም አሏት። በዚህች ሀገር ተላላኪ መንግስት እንደማይኖር በግልጽ ነገሯት። ሊያስገነዝባት የሚችለውን አንድነታቸውን አሳይዋት፤ እያሳይዋትም ይገኛሉ።
ኢትዮጵያውያን ወዳጅነቷን ባይክዱትም ወዳጅ ሆኖ የሚወጋን የሚጎዳን ግን አይቀበሉም። ዜጎችን ለሶስት አስርት አመታት ሲጨፈጭፍና ሲያስጨፈጭፍ፣ የሀገሪቱን ሀብት ሲዘርፍ ፣ ኢትዮጵያዊነትን ሲጠየፍ የኖረንና እየኖረ ከሚገኝ አሸባሪ ቡድን ጋር የሚተባበር የትኛውም ወገን ለኢትዮጵያ ሊጠቀም አይችልም። አሜሪካ ይህን የኢትዮጵያውያንን አቋም በሚገባ ተረድታ አሁንም ጊዜው አለና የያዘችውን አቋም መልሳ ልታየው ይገባል።
የሀያላኑ ቁንጮ የዘመኑ ሴረኞች መሪ የሆነችው አሜሪካ በኢትዮጵያ ምድር ላይ እኔ ካልፈቀድኩ ማንም በስልጣን ውሎ ሊያድር አይችልም የሚል መልእክት የሚያስተላለፍ ተግባር እየፈጸመች ነው። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንን ያወቀች ፈፅሞ አይመስልም። በእርግጥም ስውር ደባዋም ሆነ አፍጣ አግጥጣ የመጣችበት መንገድ መስዋዕትነት ቢያስጠይቅ እንጂ ኢትዮጵያን ሊያፈርስና ሊየስቆም ፈፅሞ አይችልም።
አፍሪካ ላይ የሚነሱ የእርስ በርስ ጦርነቶችና ግጭቶች ደጋሽ አሜሪካን ጨምሮ ምእራባዊያን ሀገሮች ናቸው፤ የሚፈቱትም በእነሱ ፍላጎት ነው። ሀያላኑ በተለይ አሜሪካ አፍሪካ ላይ ለእስዋ ታዛዥና የፈለገችውን ተግብር ባለች ጊዜ የሚተገብር መንግስት ካልሆነ የጠነከረ በራሱ የቆመ መሪ ማየት አትፈልግም። እኛም ላይ እየሆነ ያለው ይሄው ነው። ይህቺው ጭንብለ በጎ ተግባረ ክፉ የሆነች አገር በሴራዋ በዓለም ህዝብ ላይ ሰቆቃን አውርዳለች። አፍጋኒስታንን ያለከልካይ አፈራርሳለች፣ሊቢያ ያለተቃውሞ ንዳለች ፤ኢራቅን በሽብርተኝነት ስም አንትባለች።
እነ አሜሪካ ከ20 ዓመታት በላይ እንደ ዝናም ከሰማይ ቦምብ ከምድር ዕሳት እያፈራረቁ የዘሩባቸው እነዚህ አገራት በብዙ መልኩ ፈራርሰዋል። ከህዝባቸው አልፈው ሌላን ይረዱ የነበሩት መንግስታት ዛሬ በተሰራባቸው ደባ እንደ እድል የተረፉ ዜጎቻቸውን መመገብ ተስኗቸው፤ሰላማቸውን መመለስ አቅቷቸው ተብረክርከዋል። ዓለም እነዚህ አገራትን የበደሉ መንግስታትን አልጠየቀም፤ምድር እነዚህ አገራት ላይ የተፈጸመውን ግፍ በስርዓት ለዓለም አልተነፈሰችም። አዎን እነዚህ በወንጀል የተጨማለቁ ናቸው እንግዲህ ኢትዮጵያን የሚኮንኑት።
አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ ምእራባውያን መንግስታት አሁንም የኢትዮጵያን ህዝብ ጠንቅቀው አያውቁትም። ሊረሱት የማይገባውን የአድዋን ታሪክ ረስተውታል። አልሰማ ብለው ከመጡ እናስታውሳቸዋለን። በውስጥ ጉዳያችን ላይ ማንም በምንም መልኩ ጣልቃ እንዲገባ የማንፈቅድ በሉዓላዊነታችን ለመጣ ሁሉ ሉዓላዊነታችንን የሚያስጠብቅ እርምጃ የምንወስድ የጀግኖች ልጅ ልጆች መሆናችንን የተገነዘቡ አይመስሉም።
ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ዋነኛ አጋር መሆንዋን የእኛ ያልናቸው ሲነግሩን ከርመዋል፤ከዚያም ማዶ ለእናንተ ከእኛ ወዲያ ማን ወዳጅ አላችሁ ተብለናል። ያኔ በጉያችን የነበረው ሉዓላዊነታችንን አሳልፎ ለእነሱ የሰጠው፣ ለእነሱ ጥቅም አገርና ጥቅምን ያበረከተ ነበርና ነው። ዛሬ ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ፍላጎት የሚበጃቸውን ተከትለው በማንነትና በህልውናቸው ላይ የተጋረጠ የውስጥ ጠላት በማንበርከክ ላይ ይገኛሉ። ኢትዮጵያውያን የውስጥ ጠላትዋን እንደግፋለን የምትሉ የውጪዎቹ ጠላቶቻችን በውስጥ በጉዳያችን ጣልቃ መግባታችሁን አቁሙ እያሉ ናቸው።
አዎ ሁሌም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት ነው። ሙከራ ካልሆነ በቀር በእውናዊ ቁመናው ኢትዮጵያን ለማሸነፍ የሚሞክር ምድራዊ ሀይል ፈፅሞ ሊኖር አይችልም። ይህች አገር በልጆችዋ ያልተቆጠበ ጀግንነት እስከ ዛሬ እንደ ቆየችው ሁሉ ተለውጣና ሀያል ሆና ነገም ትቀጥላለች። አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9/2013