
የብዙ ባህልና ወግ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ የተለያዩ ስነ-ቃሎች ይነገርባታል። ህዝቡ ስነ- ቃልን ለተለያየ አላማ ይጠቀምበታል። ለምሳሌ ያህል ለደስታ ፣ ለሀዘን ፣ ለጦርነት ፣ ለፍቅር ፣ ለጥላቻ ፣ ለእምነት መግለጫ፣ በየዘመኑ የሚሾሙ ባለስልጣናትን አገዛዝ ለመግለጽና ለመገሰጽ ይጠቀሙበታል። በግብርና ወቅት የሚነገሩ በርካታ ስነ ቃሎችን እናገኛለን።
“ሰሚ ያጡ ድምጾች” የሚለው የፈቃደ አዘዘ መጽሀፍም ይህንኑ ያስረዳል። ከስነ-ጽሁፍ ዓይነቶች ስነ-ቃል ወይም ግጥም ሃሳብን በአጭሩና ባማረ መልኩ ለመግለጽ ምቹ በመሆኑ በሁሉም ሰው ይታመናል። ሁሉም እንደ ሀገሩ ቋንቋና ባህል፣ ግጥምን በተለየ መልኩ ቢጠቅምበትም ስነ-ቃል በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለየት ያለ ቦታና አገልግሎት አለው።
ከስነቃሎቻችን መካከል ፉከራ ቀረርቶና ሽለላ ከጀግኖች አባት እናቶቻችን የወረስናቸው ናቸው። በቃል ያለ ይረሳል በጽሁፍ ያለ ይወረሳል እንደሚለው የተረሱ ስነቃሎች ቢኖሩም ዛሬም ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ስነቃሎች አሉን።
ለቀደምት ጀግኖች፣ የጦር ውሎዎች የተደረደሩ ስንኞችንም እናገኛለን። ስንኞቹን ኢትዮጵያውያን በተለይ በጦርነት ወቅት በግጥም በዜማ በሽለላና ፉከራ ወኔን ለማነሳሳት ሲገለገሉባቸው ኖረዋል። ሀገራችን የተለያዩ ጦርነቶች የተደረጉባት እንደመሆኗም የጦርነቱን ጀግኖች ለማወደስ ፣ የጠላትን አቅም ለማኮሰስ ስንኞችን ይቋጥራሉ፤ በዚህም ይፎክራሉ፤ ይሸልላሉ። በተለይ የድል ቀናትን ስናስብ እና እንዲህ አንደ አሁኑ ያለ ጦርነት ሲገጥም ያለፉትን የጦርነት ውሎዎች ማሰብ ያስፈልጋል። በነዚያ የጦርነት ውሎዎች በበርካታ ግጥሞች፣ ሽለላዎችና ፉከራዎች ዜጎችን ለጦርነቱ ዝግጁ ለማድረግ ተሰርቷል። ጀግንነት ቅብብሎሽ መሆኑም በስንኞች ተቀምጧል።
ኢትዮጵያዊ ግፍና ጥቃት ያንገበግበዋል፤ ወገኑ ሲበደል ሲመለከት ትእግስቱ ያልቅና ጠላትን ለመበቀል እጁ ይፈጥናል። ጀግንነት ሲወርድ ሲዋረድ የተላለፈ ቅርሳችን ነው። ሀገራችን በፈጣሪዋ ተመክታ ያለች ናት። የሦስቱ አብርሃማዊ እምነቶች ብቸኛ ሀገር ማለትም፤ አይሁድ የኖረባት ክርስትና በቅድሚያ የተሰበከባት እስልምና መጀመሪያ የተጠለለባት ሃገር በመሆኗ አማኞች ይመኩባታል።
በክንዷም ተፈርታና ተከብራ የምትኖር የጎበዞች ሃገር ነች። ኢትዮጵያ የጀግኖች አምባ ናት። ዜጎች ይህን ሲያስቡ “ጀግንነት ቅርሳችንና ቁርሳችን” ሲሉ ይገልጻሉ። ይህንንም በስነቃሎቻቸው ያሰፍሩታል። ወላጆችም ልጆቻቸው ጎበዝ ሀገር ወዳድ ሆነው እንዲያድጉላቸው በብርቱ ይጥራሉ፤ የቤተሰብም ዝና ተጠብቆ እንዲኖር ሲታገሉ ማየት አዲስ ነገር አይደለም።
የብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ስብስብ ሥራዎች ሽለላ ወይም ቀረርቶን ሲያብራራ ኢትዮጵያውያን የጀብዱ ሥራን ለመቅረፅ ልጆቻቸውን ቀረርቶ እያሰሙ ያሳድጓቸዋል። ቀረርቶ ወይም ሽለላ የጦርነት ዘፈን ነው፤ ወይም ወታደር በጌታው ፊት በሰልፍ መካከል እና በጨዋታ ላይ የወንዶችን ወኔ ለማነቃቃት በዜማ የሚያሰማው ቃል ነው ይላሉ። በዶናልድ ሌቪን ትልቋ ኢትዮጵያ መጻፍ ፉከራና ሽለላ በኦሮምኛ ፉከራና ግርገራ እንደሚባሉና ዝማሬዎቹ ፈሪውን ለማሳፈር ጎበዙን ለማደፋፈር ያግዛሉ ።
ሽለላው ሽለላው ምንድነው ሽለላው
በአዲሱ ጎራዴ ደሙን ካላመሰው
ወንድ ልጅ ተወልዶ ካልሆነ እንዳባቱ
ስጡት ሐመልማሎ ይፍተል እንደናቱ የሚሉት ከብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀል ስብስብ ሥራዎች የተወሰዱ ስንኞች የሚያመለክቱትም ጀግንነት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የኢትዮጵያውያን መገለጫ መሆኑንና ሁሉም ወደፊት እንዲገፋ የሚያበረታቱ ናቸው።
ተክለጻዲቅ መኩሪያ አፄ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ አንድነት በሚል በጻፉት መጻሀፍ ኢትዮጵያውያን በጦር ሜዳ ውሏቸው ሩቅ አሳቢ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ስንኞችን እናገኛለን። ለሀገራቸው ሲሉ ባህር ማዶም ይዘምታል ብለው ገጥመውላቸው ነበር።
የታጠቅ ፈረሶች እንዴት ያሽካካሉ
ባህር ማዶ ጨፌ መልቀም ያስባሉ
አበሻ በመላው ምን ያጉተመትማል
በመርከብ ተሻግሮ ገና ባህር ይዘምታል
መኳንንቱም ከግብር በኋላ በንጉሣቸው ፊት ፡-
ዘራፍ ዘራፍ ያንተ አሽከር የነፍሰ ቢሱ
በደም ይዋኛል ከአውራሪሱ ብለው በመፎከር ለመታገል ወሰን ለማስከበር ዋጋ ይሰጡ ነበር።
ቀረርቶ እና ፉከራ አይለያይም፤ ቀረርቶ ይቀድማል ፉከራ ወይም ድንፋታ ይከተላል። ሽለላ ጠብ ማጫሪያ የነገር ማስነሻ ይመስላል። ሸላዮች ጀግኖችን በማመስገን በመንቀፍና በመገሰፅ ወጣቶችን አነቃቅተው ለመንፈስ ብርታትን ካስገኙም በኋላ እንኳን የወንዶችን የሴቶችንም ቢሆን የቆራጥነት ወኔያቸውን ይቀሰቅሱታል። ለምሳሌ በሚል የጠቀስዋቸውን እንመልከት
1. ወኔ ለመቀስቀስ
ንዳው ላሙን፣ ንዳው ላሙን፣ አቧራው ይነሳ፤
ይመጣ የለም ወይ ኮርማው እያገሳ።
ካባቴ ባድማ ፍግ አታፍሱበት፣
ነዲዱ ቢጠፋ ረመጡ አለበት።
እነዚያ ወረዱ እንውረድባቸው፣
አንበሳም አይደሉ እንደኛ ሰው ናቸው።
በዛ ምጡ፣ በዛ ምጡ፤
ወይ እኛ አልወለድን፣ ወይ እነሱ አልመጡ።
2. በጦርነት ጊዜ ስለማደፋፈር
በለው በለው ሲል ነው የጋሜ ኩራቱ፣
ሴትም ትዋጋለች ከረጋ መሬቱ።
ሂድ ሲሉት ካልሄደ፣ ና ሲሉት ካልመጣ፤
ስደደው ጎበዙን እጁን ይዞት ይምጣ።
3. ፈሪን ስለመገሰፅ
የለመደው መሸሽ የለመደው፤
በመጫኛም ቢያስሩት ሄደ እየጎመደው።
ቱሪ ናፋ፣ ቱሪ ናፋ፣
በጦር ሜዳ አትገኝ ከቀለቡ አትጠፋ።
አበዛኸኝ፣ ተወኝ ኣበዛኸኝ፤
አንተም አልተጠቀምክ፣ እኔንም ጎዳኸኝ።
አጼ ቴዎድሮስ ጀግንነትን ያገኙት ከአጎታቸው ደጃች ክንፉ ነው ይባላል። ክንፉ ከቋራ እስከ ደንቢያ ከጭልጋ እስከ መተማ ይገዙ እንደነበር ሰነዶች ያስረዳሉ። በዘመናቸው ከቱርክ ጋር በተደጋጋሚ የሚዋጉ፤ ለጠላት አልበገር ባይ ገዳይ ጀግና ስለነበሩ
የክንፉ ጎራዴ ጥቁር የነበረ
እየቀላ ሄደ ቱርክ እየመሰለ ተብሎ ተገጥሞላቸዋል።
ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም
ጀግናን ከደረቱ አበባን ከአናቱ የሚሉት ምሳሌያዊ አባባሎችም ወኔ የሚሰጡ ናቸው።
በኢትዮጵያ ምድር ጣሊያንን ደግፎ ኢትዮጵያን ሰይፎ ለተሰለፈ ባንዳና ከሀዲን ጉያ ይዞ እድገትና እንቅስቃሴ አዳጋች መሆኑም በስነቃል እንዲህ ተገልጾ ነበር።
ጠላትማ ጠላት ምንጊዜም ጠላት ነው፣
አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው።
አገር ተሰቃየች…ጣሯ ብቻ በዛ..
ግማሹ እየሸጣት…ግማሹ እየገዛ…!
የሰው ዘር መገኛ … ብለው ሲጎበኙን…
በብሄር ተጠምደን … ተከፋፍለን አዩን::
ማን እንደዘረፈኝ … ልቤ እያስተዋለ
የለመደው አፌ … ”የመንግስት ያለህ!” አለ::
የኢትዮጵያ ህዝብ ለጦርነት እንግዳ አይደለም። ዘር ማንዘር እየለዩ መጓዙ መዘዙ ብዙ ነው። እነ አዶልፍ ሂትለር አርያን ሬስ (ምርጥ ዘር ) በሚል እሳቤ ብዙ አይሁዶችን ጨፈጨፉ፤ በወቅቱ እንግሊዝና ፈረንሳይ አሜሪካም ጭምር እንደ አፋርና ማይካድራው ጭፍጨፋ ዐይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆኑ። ዞሮ ዞሮ ግን ወላፈኑ እነርሱም ጋር ደረሰና የዓለም ጦርነት ተቀሰቀሰ። የሚያወጣን በሰከነ መንገድ መደራደር መነጋገር ነው። ሁሉም እንደ ኢትዮጵያዊ ቆም ሰከን ብሎ ያስበው። ካልሆነ ደግሞ በመረጠው መንገድ እንዳመጣጡ መመለስ።
ይቤ ከደጃች ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 9/2013