ወርቅ በዕሳት እንደሚፈተነው ሁሉ የሰው ልጅ በመከራ ይፈተናል። አገርም ሊያፈርሷት በሚሞክሩ ሃይሎች ትፈተናለች። ሰው ሰው ነኝ ብሎ ካላመነ እና ፈተናውን ለማለፍ ካልታገለ ይወድቃል፤ ወርቅም ወርቅነቱን በእሳት ተፈትኖ ባለመቅለጥ ካላስመሰከረ ድንጋይ ነው ተብሎ ይጣላል። አገርም እንደዚያው ነው። አገር ነን ብለው ስለአገራቸው የሚቆሙላት ካልበዙ ትፈርሳለች። ኢትዮጵያ አገር ነኝ ብላ በማመኗ እና ልጆቿም አገር መሆኗን በማረጋገጣቸው እስከ ዛሬ አልፈረሰችም። ሆኖም ግን ሌሎች አገር ነን ብለው ያላመኑ እና ዜጎቻቸውም ስለአገርነታቸው ያላረጋገጡላቸው አገሮች ፈርሰው አይተናል። ለእዚህ በማሳያነት እነሶቬት ህብረት፣ አፍጋኒስታን፣ ሊቢያን ፣ ሶሪያን እና ሌሎችም አሁን ላይ የፈራረሱ እና እየፈረሱ ያሉ አገራትን መጥቀስ ይቻላል።
በተለያዩ ጊዜያት ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ባትፈራርስም አደጋዎች እንዳጋጠሟት የሚዘነጋ አይደለም። ምክንያቱም አገሪቱን ችግር ውስጥ በማስገባት እንድትፈራርስ የሚጥሩ ኃይሎች ጥቂት አይደሉም።ይህን የመፈራረስ አደጋ እና ችግር ማለፍ የሚቻለው ህዝብ በአንድነትና በትብብር መንፈስ መቆም ሲችል ብቻ ነው። ህዝብ እንደ ብረት ጠንክሮና እንደ አንድ ማሰቡ የመጣውን ሁሉ እንደ አመጣጡ ለመመከት መዘጋጀቱ የግድ ነው።
እራሱ በለኮሰው እሳት እየተለበለበ ያለው የህውሓት አሸባሪ ቡድን በአሁኑ ወቅት በተለይም ከየጦር ግንባሩ የሚመጡ መረጃዎች የሚያረጋግጡት ከህጻናት እስከ አዛውንት አባትና እናቶች፣ ከመነኩሴ እስከ ሼህ በግዳጅ ቢያሰልፍም ዳግም ሊያንሰራራ በማይችልበት ደረጃ እየፈራረሰ እና እየተፈረካከሰ የሚገኝ መሆኑን ነው። ይህም ቢሆን ግን የአሸባሪው የህወሓት ቡድን አሁን ላይ ከፍተኛ የሆነ የሞት ሽረት ትግል ላይ ነው ።ለእዚህ የሞት ሽረት ትግሉ ማሳመሪያው ደግሞ ማጣፈጫው ንጹኃንን እያስፈጀ በለመደው መንገድ ድራማ እየሰራ መንግሥት እና ህዝብን አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ ግርግር መፍጠሩን ተያይዞታል።እርሱ ወደሚናፍቀውና ወደኖረበት የብዝባዛ አገዛዙ ለመመለስ ከፍተኛ ስራን እየሰራ መሆኑን ልብ ይሏል። በዚህም የጥቅም አጋሮቹ ምዕራባውያንም የእሱን እኩይ ተግባር ብሎም ወንጀል አይተው እንዳላዩ ሰምተውም እንዳልሰሙ ከማለፋቸውም በላይ ንጹኃንን ልታደግ፤ ተኩስ አቁሜ ህዝቡን ከርሃብ፣ከችግር፣ ከስደት ላድን ባለው የፌዴራል መንግሥት ላይ ጫናዎችን በማሳደር ላይ ናቸው።
ምዕራባውያኑና አንዳንድ ተቋሞቻቸው ምንም እንኳን በስውር የሳተላይት መረጃ ከመስጠት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን ቢያደርጉም የህወሓት ሃይል በአስደንጋጭ ሁኔታ ለወሬ ነጋሪ እንኳን እንዳይተርፍ ሆኖ አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ ይገኛል ። ጁንታው” የአይጥን ያህል ቁመና ይዞ እንደዝሆን ቢንጠራራም “ ቅሉ አሁን ላይ ግን የሚተርፈው ነገር የሚኖር አይመስልም።
ነገር ግን እነዚህ ጥቅመኛ ጀሌዎቹ በተለይም ባለፉት ጊዜያት የእነሱን ሀሳብ አላስፈጽም ባሉ እንደ የመን እና ሶሪያ ያሉ መሪዎችን በመስደብ እና በማሰደብ፤ የሃሰት ወሬ በማስወራት እና በህዝቦቻቸው እንዲጠሉ በመሥራት አገራቱን አፈራርሰዋቸው ህዝቡን ለችግርና ለስደት ዳርገዋል። አሁን ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሳይታክቱ እየሰሩ ነው።ለዚህ አካሄዳቸው ይጠቅማቸው ዘንድ የውሸት ታሪክ አዘጋጅተው በሌላ ዙር፣ በሌላ መንገድ ለማንበርከክ እየመከሩ ናቸው።
ለእዚህ እኩይ ተግባራቸው ደግሞ አሁን ላይ በሱዳን በኩል የመተላለፊያ ኮሪደር እንዲከፈት ማድረግ፤ አልያም የሚመጣውን ብርቱ ማዕቀብ መቀበል ለኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ምርጫ አቅርበዋል። እንግዲህ ይህ ሁሉ የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን አንገት መቀንጠሺያ ካራ መሆኑ ነው።ለኢትዮጵያ አንገት መቀንጠሺያ የተዘጋጀውን ካራ ስለቱ ሁለት ፊት ይሆን ዘንድ ደግሞ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። “ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሀል “ እንደሚባለው ለውሸት ፕሮፖጋንዳቸው ማድመቂያ ከሚያደርጉት ዝግጅት መካከል የጀኖሳይድ ድራማ በተከዜ ወንዝ ላይ መስራት አንዱ ሆኗል።
ለዚህም እንዲጠቅማቸውም ከየአውደ ውጊያ የተሰበሰቡትን አስክሬኖች ስክሪፕት ተጽፎላቸው ትወናው ከሚደረግበት ተከዜ ወንዝ እየተወሰዱ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ድራማ ደግሞ በቀጥታ የሚተላለፈው የጥቅም አጋሮች በነበሩትና በሆኑ የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙሃኖች ነው።እነዚህ ከሙያ ስነ ምግባር እንዲሁም ከሰብዓዊነት ውጪ የሆኑ ሆድ አደር ሚዲያዎችም ይህንን ድራማ የገጻቸው ፊት፣ የዜናቸው መግቢያ እንዲያደርጉት የቤት ስራ ተሰጥቷቸው እሱን ለማሳካት ከወዲሁ ጩኸቱን እያቀለጡት ነው።
ምዕራባውያኑ በሁለቱም በኩል ስለት ያለው ካራ ይዘው እንደሚመጡ ቀድመው እያሳወቁ ነው። በግልጽ እንደተናገሩትም ዓላማቸው የትኛውንም በር ማስከፈት፣ ቀጥሎም መንግሥትን ከህወሓት ጋር ድርድር እንዲቀመጥ ማድረግ ነው። እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ደግም በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ትልቅ አደጋ ያላቸው ናቸው።
በቅርቡ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን “ የምዕራባውያኑ ጥያቄ ተንኮል ያለው ወጥመድ ነው። ከዚያም ያለፈ ነው። ሀገር የሚያፈርስ መርዝ የተለወሰበት ጥያቄ ነው” ብለው ነበር።
እንግዲህ አሁን ላይ ምርጫው በኢትዮጵያ ህዝብና በመንግሥት እጅ ውስጥ ይገኛል። ስለነገው ትውልድ፣ ስለመጪው የኢትዮጵያ ህልውና፣ ክብርና አንድነቷን የተረጋገጠች ሀገር የምንሻ ከሆነ ባለሁለት ስለቱን ካራ ወደ ጎን ገፍተን በቆራጥነት ኢትዮጵያን ማዳን አለብን። ከዚህ ውጪ ያለው ምርጫ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ከዓለም ካርታ ላይ እንድትፋቅ ለተዶለተው ሴራ እጅ ሰጥቶ፣ ሀገር አልባ ሆኖ በመቅረት እድሜ ዘመንን በባርነት አንገትን ሰብሮ፣ ከሰው በታች ሆኖ መኖር ብቻ ነው።
በእርግጥ ሁለቱም ምርጫዎች ዋጋ ያስከፍላሉ። አንደኛው ጊዜያዊ የሆነ፣ ሆዳችንን አስረን፣ ቀበቷችንን ጠበቅ ካደረግን የምንሻገረው ሲሆን፤ ሁለተኛው ግን ዘላለማዊ ጠባሳን የሚጥል እና አገር አልባ የሚያደርገን፣ ልጆቻችን ሀገራችን ብለው የሚኖሩባት ምድር የሚያሳጣቸው፣ በጥቅሉ ኢትዮጵያን የሚያፈራርስ ነው። ምርጫው አሁንም በእጃችን ነው።
ኢትዮጵያዊያን ልክ እንደ አንዳንድ ብርቱ አገራት ህዝቦች ከብረት ለበስ ታንክ ፊት ተኝተን፣ ድንጋይ ፈልጠን ጥረን ግረን የአገራችንን ኢኮኖሚ እንታደጋለን። እጅ ለእጅ ተያይዘን ችግርንም ረሀብን ችለን ሀገርን ከመፈራረስ በመጠበቅ አገራችንን ከምዕራባውያን ሴራ እንታደጋለን፤ ወይስ እንደ ሶሪያ፣ የመን፣ ኢራቅና ሊቢያ ህዝቦች፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የመንደር ሸማቂዎችን አምነን አገራችንን እናፈርሳለን? መልሱ ያለው ከኛው ጋር ነው። ሀገራችንን ከነሙሉ ክብሯ ጠብቀን የጠላቶቻችንን ህልም አቀጭጨን ኢትዮጵያን ማስቀጠል ከኛ ከልጆቿ የሚጠበቅ ግዴታ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድም ያሉት ይህንኑ ነው “የውጭ ሃይሎች እንድትረዱት የምንፈልገው በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ከመጣችሁ አንገቴ ይቀላል እንጂ አይደረግም ! ደሃ ነን፤ ከድህነት ፈጥነን ለመውጣት ሰላም፣ ትብብር፣ ድጋፍ ያስፈልገናል። ፈጥነን ከድህነት ለመውጣት ግን ክብራችንን መሸጥ አይጠበቅብንም” ብለዋል። ሰላም!
በእምነት
አዲስ ዘመን ነሐሴ 4/2013