በ2010 ዓ.ም ቤተሰቦቻቸው ያልታወቁ 3ሺ890 ሰዎችን ቀብራለች
አዲስ አበባ፡- አዲስ አበባ ለመቃብር ሥፍራዎች የሚውል ሁለት ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬት በላይ ብትከልልም ዘመናዊ አሠራር ባለመከተሏ በቂ አለመሆኑን የአዲስ አበባ የተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ገለፀ። በአግባቡ የለሙ የመካነ መቃብር ስፍራዎች ሠርግ እና ልደት እየተደገሰባቸው መጠነኛ ገቢም እያስገቡ መሆኑንም ተገልጿል።
የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አደባባይ ሰንደቅ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ መንግስት በሚያስተዳድራቸው 15 ስፍራዎች ሁለት ሚሊዮን 40ሺ623 ካሬ ሜትር መሬት ለመቃብር የተከለለ ሲሆን፤ በተጨማሪ በቤተ እምነቶች የተያዙ ከ80 በላይ ሰፋፊ የመቃብር ሥፍራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ ከሚሰጠው አገልግሎት አኳያ በቂ አለመሆኑን አብራርተው ይህን ለማስተካከል ኤጀንሲው፣ ቤተ እምነቶች እና ማህበረሰቡ በጋራ ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። አቶ አደባባይ እንዳሉት፤ ቀጨኔ መድሃኒያለም፣ ጳውሎስ ወጴጥሮስ፣ ሳሎጎራ፣ ጉራራ፣ መካኒሳ፣ ዮሴፍ፣ ባለወልድ፣ ጀሞ፣ ፍሊጶስ፣ ሸጎሌ፣ ኮተቤ ገብርኤል፣ የኮልፌ ሙስሊም መቃብር፣ አዲስ አንድ እና አዲስ ሁለት የተሰኙ 15 የመካነ መቃብር ስፍራዎች በመንግስት የሚተዳደሩ ሲሆን፤ ከአገልግሎትና ከህብረተሰቡ ፍላጎት አኳያ በቂ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ 80 የመካነ መቃብር ሥፍራዎች በቤተ እምነቶች የሚተዳደሩ ቢሆንም፤ በከተማዋ ያሉት ዘላቂ ማረፊያዎች አያያዝና አጠቃቀም ዘመናዊ አለመሆኑን አብራርተዋል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት ከመካነ መቃብር ስፍራዎቹ አጠቃቀምና አያያዝ በቂ ባይሆንም፤ የተወሰኑት በመልካም ይዞታ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ጥቂት የመካነ መቃብር ሥፍራዎች በጥሩ ሁኔታ ስለተያዙ ሠርግና ልደት ይደገስባቸዋል ብለዋል።
መቃብር ስፍራዎችን ከአስፈሪነት ድባብ ወጥቶ ማራኪ መዝናኛ እንዲሆኑ በሰፊው እየተሰራ ነው። ሆኖም ነዋሪዎች በዚህ አካባቢ ሄዶ የመዝናናት ባህል ያልዳበረ በመሆኑ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በቀጣይ የዘላቂ ማረፊያ ሥፍራዎች ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚዘወተሩበት፣ ለማንበቢያ ምቹ የሆኑ ቤተመጽሀፍት የሚገነቡበትና የጎብኚዎች ፍሰት የሚበዛበት ሥፍራ ለማድረግም እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። በኤጀንሲው የካፒታል ፕሮጀክ ቶች ክትትል ባለሙያ አቶ ዮሐንስ ንጉሴ በበኩላቸው፤ መንግስት በሚያስተዳድ ራቸው የዘላቂ ማረፊያዎች ብቻ በ2010 በጀት ዓመት 8ሺ374 ሰዎች የተቀበሩ ሲሆን፤ 3ሺ890 ሰዎች አሊያም ቤተሰቦ ቻቸው ያልታወቁ ናቸው።
በ2011 ግማሽ በጀት ዓመት ውስጥ ደግሞ 4ሺ792 ሰዎች ተቀብረዋል። ከነዚህ ውስጥ 2ሺ091 ሰዎች ቤተሰብ ያልተገኘላቸው ናቸው። ይህ አሀዝ የ80 ቤተ እምነቶች መረጃን የማይጨምር ሲሆን፤ ቁጥሩ ከዚህ በእጅጉ የላቀ እንደሚሆን ገልፀዋል። አቶ ዮሐንስ እንዳሉት፤ የመካነ መቃብር ሥፍራዎች በተቻለ መጠን ገቢ እያስገኙ ቢሆንም በቂ አይደለም፡ ፡ ለአብነትም በ2010 በጀት ዓመት ከእነዚህ ሥፍራዎች 195ሺ ብር መገኘቱን ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ የተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ በአዋጅ ቁጥር 62/2010 የውበት፣ መናፈሻና ዘላቂ ማረፊያ ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ በሚል የሥም፣ ተግባርና ኃላፊነት ማሻሻል ማድረጉ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር